Print this page
Saturday, 08 May 2021 13:06

የኮሮና ሟቾች ቁጥር ከሚነገረው ከእጥፍ በላይ ይበልጣል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      በሳምንቱ በአለም ግማሽ ያህሉ ተጠቂና ሩብ ያህሉ ሞት የተመዘገበው በህንድ ነው

             በመላው አለም በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር መንግስታት ካመኑትና የተለያዩ የመረጃ ተቋማት ይፋ ካደረጉት ከእጥፍ በላይ እንደሚበልጥና ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር ከ6.9 ሚሊዮን በላይ እንደሚበልጥ በጥናት መረጋገጡ ተዘግቧል፡፡
ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲንና ዎርልዶሜትር ድረገጽን ጨምሮ የኮሮና መረጃዎችን የሚያቀርቡ ማዕከላት እስከ ትናንት በስቲያ በመላው አለም በኮሮና ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር 3.26 ያህል እንደሆነ ቢናገሩም፣ ኢንስቲቲዩት ፎር ሄልዝ ሜትሪክስ ኤንድ ኢቫሉዌሽን የተባለው ተቋም ግን የሟቾች ቁጥር ከዚህ ከእጥፍ በላይ እንደሚበልጥና 6.9 ሚሊዮን እንደሚደርስ በጥናት ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡
የኮሮና ሟቾች ቁጥር አነስተኛ ተደርጎ ሪፖርት ከሚደረግባቸው ምክንያቶች አንዱ ብዙ አገራት በሆስፒታል ብቻ እንጂ በየቤቱ የሚሞቱ ሰዎችን አለመቁጠራቸው እንደሚገኝበት የጠቆመው ጥናቱ፣ በአለማችን የኮቪድ 19 ሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ተቀንሶ ሪፖርት የተደረገባት ቀዳሚዋ አገር አሜሪካ መሆኗንና በህንድና በሜክሲኮም ቁጥሩ ከተነገረው በሶስት እጥፍ ያህል የሚበልጥ መሆኑን አመልክቷል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና በህንድ ባለፈው ረቡዕ ከፍተኛው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችና ሟቾች ቁጥር መመዝገቡን የዘገበው አልጀዚራ፣ በእለቱ ከ412 ሺህ በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውንና 3 ሺህ 980 ሰዎች መሞታቸውን ገልጧል፡፡
በባለፈው ሳምንት በመላው አለም በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁት ሰዎች መካከል 46 በመቶ ያህሉ፣ ለሞት ከተዳረጉት መካከል ደግሞ ሩብ ያህሉ በህንድ እንደሚገኙ የአለም የጤና ድርጅት ከሰሞኑ ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፣ በአገሪቱ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከትናንት በስቲያ ከ21 ሚሊዮን ማለፉንና የሟቾች ቁጥርም ከ230 ሺህ በላይ መድረሱንም ዘገባው አክሎ አስረድቷል፡፡
የኬንያ የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ከቀናት በፊት በተደረገ ምርመራ አምስት ሰዎች በህንድ የታየው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ እንደተገኘባቸው ማረጋገጡን ቢቢሲ የዘገበ ሲሆን፣ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች በምዕራባዊ ኬንያ በሚገኝ የማዳበሪያ ፋብሪካ ሰራተኞች መሆናቸውንና ኬንያ በህንድ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የተገኘባት ሁለተኛዋ አፍሪካዊት አገር መሆኗንና ከዚህ ቀደም በኡጋንዳ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውንም አስታውሷል፡፡


Read 3433 times
Administrator

Latest from Administrator