Saturday, 08 May 2021 13:15

የኢዜማ የአዲስ አበባ እቅድ - በ138 አንቀጾች፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

     አዲስ አበባን በሚመለከት፣ ኢዜማ ያዘጋጀው የምርጫ መወዳደሪያ ሰነድ፣ ምን ምን እንደያዘ ለመቃኘት እንሞክር። በቅድሚያ፣ ብዙ ሰዎችን ከሚያሳስብ ጉዳይ እንጀምር - ከመኖሪያ ቤት እጦት።
በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ዙሪያ፣ “መመሪያዎችንና ደንቦችን በማሻሻል፣ ቀልጣፋና ከሙስና የፀዳ” አገልግሎት እንደሚሰጥ ኢዜማ ይገልፃል - በአንቀፅ 61። የግንባታ ፈቃድና የመሬት አጠቃቀም ስርዓትን እንደሚያሻሽል፣ “የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን” እንደሚሰጥም ይናገራል። “በቀላል ወጪ የከተማዋን የመኖሪያ ቤት ልማት... እናስፋፋለን” ይላል - አንቀፁ።
በእርግጥም፣ አላስፈላጊ፣ አደናቃፊና ብልሹ የቁጥጥር ህጎችን ወይም መመሪያዎችን ለማስተካከል ማሰብ፣ ጥሩ ነው። የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለል ይረዳ ይሆናል። አሳዛኙ ነገር ምንድነው?
በ62ኛው አንቀጽ፣ ነገሩን ያፈርሰዋል። አላስፈላጊና አደናቃፊ መመሪዎችን ገና ሳያቃልል፣ ተጨማሪ መመሪያዎችን ለመፍጠር ያስባል። ኢዜማ እንዲህ ይላል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ “የሕፃናት መዋያ፣ መፃሕፍት ቤቶች፣ የልጆች እና የአረጋውያን ስፖርት ማዘውተሪያዎች የሚያካትቱ እንዲሆኑ ይገደዳሉ” ይላል - አንቀፅ 62።
አነስተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች፣ በአምስት ዓመት ውስጥ፣ የ200 ሺ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንደሚካሄድም ያወሳል - በአንቀፅ 63።
እዚህ ላይ የሚነሳ የመጀመሪያው ጥያቄ አለ። በአነስተኛ ገቢ ለሚቸገሩ ነዋሪዎች፣ “የህፃናት መዋያ የሌለው ቤት” መገንባት አይቻልም? ቤተ-መፃህፍትም የግድ ነው? በዚያ ላይ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ከሌለው፣ የግንባታ ፈቃድ አያገኝም? ለልጆችና ለአዛውንት፣ “ጂም” የግድ ነው?
ኧረ ይሄን ይሄን እንተወው፣ ግድ የለም። ማለቴ... አቅም ያለው ሰው፣ የመዋኛ ገንዳም ሆነ የጎልፍ መጫወቻ ይስራ። “ይመቸው” እንዲሉ። ግን ሁሉም ሰው፣ እንደዚያ አይነት አቅም የለውም። ታዲያ፣ እንደ አቅሙ ትንሽነት፣ ከጉስቁልና ትንሽ ሻል ያለ መኖሪያ ቤት የመስራት እድል ቢያገኝ ምናለበት? አብዛኛው ሰው´ኮ፣ መኝታ ቤት፣ መታጠቢያ እና ምግብ ማብሰያ በሌላት አንዲት ክፍል ነው የሚኖረው። አላስፈላጊና አደናቃፊ ቁጥጥሮችን መቀነስ እንጂ መጨመር፣ ለማንም አይበጅም።
ይልቅ፣ የኢዜማ ሰነድ፣ ሌላ ጥሩ ሃሳብ ይዟል። በአንቀፅ 64 ላይ፣ የቀበሌ ቤቶችን በሽያጭ ለነዋሪዎች የማስተላለፍ ሃሳብ እንዳለው ይጠቅሳል። ጥሩ ነው። በትክክልና በስርዓት ተግባዊ ቢሆን፣ ውሎ አድሮ ብዙ ችግሮችን ለማቃለል ይረዳ ይሆናል። የመሬት ውዝግብንና ችግርን ለመፍታት ሊያግዝ ይችላል።
የመኖሪያ ቤትና የመሬት ጉዳይን ከሚመለከቱ አንቀፆች በኋላ፣ የትራንስፖርት ጉዳይ ይመጣል - (ከ75ኛ እስከ 85ኛ አንቀፅ)።
የትራንስፖርት ወረፋ፣ “መላ ያጣ” ችግር!
እውነት ለመናገር፣ ከአዲስ አበባ ዋና ዋና ችግሮች መካከል፣ ከኢንዱስትሪና ከስራ እድል እጥረት፣ እንዲሁም ከመኖሪያ ቤትና ከሰላም እጦት ቀጥሎ፣ የትራንስፖርት ችግር ትልቅ ፈተና ነው።
የመንገድ ግንባታን ማበራከት፣ የመንገድ አጠቃቀምን ማሻሻል፣ የሚኒባስ ታክሲዎችን ስራ አለማደናቀፍ፣ በቀዳሚነት ሊጠቀሱ የሚችሉ መፍትሔዎች ናቸው።
ነገር ግን፣ ዛሬ፣ ዛሬ ሚኒባስ ታክሲዎችን “መጥመድ” የተለመደ ሆኗል። ገዢው ብልፅግና ፓርቲ፣ አውቶብስ፣ አውቶብስ ይላል። ኢዜማ ፓርቲም፣ አውቶብስ ባይ ነው።
እሺ፣ አውቶብስ ጥሩ ነው። ግን፣ በየመንገዱ ተመልከቱ። የከተማዋ ነዋሪ፣ በትራንስፖርት ወረፋ፣ ፀሃይና ዝናብ ይፈራረቁበታል። ምናለፋችሁ! ብዙ ተጨማሪ ሚኒባስ ታክሲዎች ያስፈልጋሉ። ፓርቲዎቹስ ምን ይላሉ? አውቶቡስ፣... እና ብስክሌት፣...
ለምንድነው እንደዚህ የሚሉት? ያው፣ እንደዘመኑ ፈሊጥ፣ የነዳጅ ጭስን ለመቀነስ... “የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ”፣ “የሰሜን ዋልታ በረዶ እንዳይቀጥል ለመከላከል”፣... ከሚሉ ወገኛ አባባሎች ውጭ ሌላ ምክንያት አይኖራቸውም። እውነታው ምንድነው? ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ መንግስታዊ አስተዳደር፣ የፌደራልም ሆነ የከተማ፣ የብልፅግናም ሆነ የኢዜማ አስተዳደር፣ ዋና ስራው ኢትዮጵያ ላይ ያተኮረ እንጂ፣ የሰሜን ዋልታ በረዶን የሚመለከት አይደለም።
ለነገሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ መኪኖች ሁሉ ቢቆሙ፣... “ካርቦንዳይ ኦክሳይድ አትተንፍሱ” ተብለን ብንታፈን እንኳ፣ ለሺ አመታት አገሪቱ ሰው አልባ ብትሆን እንኳ፣ ጥፋት እንጂ ፋይዳ የለውም። በአንድ አመት ከቻይና የሚወጣው ጭስ፣ ከኢትዮጵያ የምዕተ ዓመታት ጭስ ይበልጣል። እና ምን ቤት ነን፣ ስለ ጭስ እና ስለ ሰሜን ዋልታ በረዶ፣ የሃገር ሃብትን የምናባክነው? የምሰቃየው? “ሲሉ ሰምታ” ካልተባለ በቀር።
“የፀሐይ ሃይል”፣ “የነፋስ ሃይል”፣ እየተባለ ብዙ ገንዘብ የሚባክነውም፣ በሌላ ምክንያት አይደለም - “የካርቦን ልቀት ለመቀነስ” በሚለው ቀሽም ፈሊጥ ሳቢያ ነው። ገዢው ብልፅግና ፓርቲ፣ እንዲህ አይነት የቀድሞ ብክነቶችን መግታት አለበት። ኢዜማም እንዲሁ።
ይሁን እንጂ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ የፀሃይ ሃይል ኤሌክትሪክ በየቤታቸው እንዲያስገቡ የብድር ዋስትና እሰጣለሁ ይላል - ኢዜማ። አሁን ይሄ ምን ይባላል? ይልቅ፣ የኤሌክትሪክ መስመሮችንና ማከፋፈያዎችን በአግባቡ ለማስተካከልና ለማሟላት፣ መላ መፈለግና መሞከር ነው የሚያዋጣው።
በዚያ ላይ፣ ከመደበኛው የኤሌክትሪክ መስመር ተጨማሪ፣ “የፀሐይ ሃይል ኤሌክትሪክ አምሮኛል” የሚል ሰው ካለ፣ አቅም ቢኖረው ነው። ካዋጣው፣ በራሱ ወጪ ሞክሮ ይየው። ድጎማን ምን አመጣው? ለድሀ፣ ለችግረኛ በሚል ስያሜ የተፈጠሩ ድጎማዎች ሳያንሱ፣ ለሌላውም ድጎማ? ለዚውም ለ50 ሺ ቤተሰብ! እንደዚያ ይላል አንቀፅ 131። ግድ የለም፣ ይሄ ይሄ ይቅር። ዋና ዋና ነገሮች ላይ ማተኮር ይሻላል።
በእርግጥም፣ በኢዜማ ሰነድ ውስጥ፣ ቅድሚ አግኝተው፣ ከአንቀፅ 1 እስከ 30 ድረስ የተዘረዘሩት ጉዳዮች፣ በአብዛኛው፣ ዋና ዋና ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ናቸው። ህግን ከማስከበርና ሰላምን ከመጠበቅ፣ ዜጎችን ከእንግልትና ከበደል የሚያድን የመንግስት አስተዳደርን የሚመለከቱ አንቀፆች መሆናቸው መልካም ነው።
ቢሆንም፣ እንደተለመደው፣ እዚህም እዚያም፣ ስለ ድጎማና ስለ ድጋፍ፣ እየደጋገመ ማውራቱ አልቀረም። ለጎዳና ተዳዳሪ፣ ለስራ አጥ፣ ለችግረኛ፣... የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚሰጥ ይጠቅሳል - 103ኛ አንቀፅ። በገንዘብ፣ በስልጠና፣ በትምህርት፣ በስነ-አእምሮ ህክምናም እደግፋለሁ እያለ እስከ 104ኛ አንቀፅ ይቀጥላል። ግን ድጎማ ብቻ አይደለም። አንድ ምሳሌ በመጥቀስ እንጨዋወት።
“ጠንካራ ህግ” ወይስ “ጠንከር ያለ ህግ”
“ሰርተው መለወጥ የሚችሉትን የማህበረሰብ ክፍሎች፣ በስንፍና ልመና ላይ እንዲሰማሩ ላለመበራታታት፣ ጠንከር ያለ ህግ ወጥቶ በሥራ ላይ ይውላል...”
ይሄ፣ በኢዜማ ሰነድ ውስጥ 105ኛ ግብ ተብሎ ቀርቧል። እሺ። ግን፣ ምን ለማለት ፈልጎ ነው ብላችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ።
“መስራት የሚችሉ ሰዎች፣ እንዳይለምኑ የሚከለክል ጠንካራ ህግ አወጣለሁ”.... እንደማለት ይመስላል።
በዚህ አተረጓጎም የማይስማሙና፣ “እንደዚያ ማለት አይደለም” ብለው የሚከራከሩ ይኖራሉ። በፓርቲው ሰነድ ላይ የተፃፈው፣ “ጠንካራ ህግ” እንደሚወጣ የሚገልፅ አይደለም። “ጠንከር ያለ ህግ” እንደሚወጣ የሚገልፅ ነው ሊሉ ይችላሉ። ደግሞም፣ 105ኛውን ግብ ወይም አንቀፅ፣ በደንብ ስንመለከተው፣ እውነት አላቸው።
“ደልደል ያለ”፣ “ደልዳላ”፣ “የተደላደለ”፣ “የደላው”፣ “ድሎት”፣... እነዚህን ሁሉ የኑሮ ደረጃዎች፣ ልዩነት እንዳላቸው አይካድም።
ልክ እንደዚያው፣ “ጠንከር ያለ ህግ” ማለት፣ “ጠንካራ ህግ” ከማለት ይለያል።
ለማንኛውም፣ ህግ የሚወጣው፣ “በስንፍና ልመና ላይ እንዲሰማሩ ላለመበረታታት” እንጂ፣ “ልመናን ለመከልከል” አይደለም የሚልም ይኖራል - አንቀፁን ያነበበ አስተዋይ ሰው። እውነት ነው።
በዚያ ላይ፣ አንቀፁ፣ “ህግ አወጣለሁ” አይልም። “ህግ ወጥቶ በስራ ላይ ይውላል” ይላል እንጂ። ይሄም፣ እውነት ነው። አሳጥረን ትርጉሙን ለመጨበጥ እንጂ፣ በረዥሙ የተፃፈውንማ ማን ይከዳል? በእርግጥ፣ የሚክድ ይኖራል። ዛሬ ዛሬ፣ እውነትንና ሃሰትን መለየት አስቸጋሪ ሆኗልኮ። የሆነ ሆኖ፣ ወደቀጣዩ አንቀፅ ወይም ወደቀጣዩ ግብ እንሻገር።
106ኛው አንቀፅ እንዲህ ይላል። “በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል”.... በማለት ይጀምርና ይቀጥላል። ምን ለማለት ፈልጎ ነው? “የከተማዋ ነዋሪዎች ኑሮ ለማሻሻል....” ለማለት ይመስላል።
107ኛው አንቀፅ፤ “አዲስ አበባ፣ ለአካል ጉዳተኞች እና፣ ጧሪ እና ቀባሪ ለሌላቸው አረጋውያን የምትመች ከተማ እንድትሆን”፣... በማለት እቅዱን ያቀርባል። ዓረፍተ ነገሩ፣ ገና መጀመሩ ነው። ሩብ ያህል የማይሞላውን ነው የጠቀስኩላችሁ። ትርጉሙስ? “አዲስ አበባ፣ ለሁሉም ነዋሪዎች፣ ለአካል ጉዳተኞች’ም’፣ ለአረጋውያን’ም’ የምትመች ከተማ” በሚል ሃሳብ ካልተረዳነው፣ አባበሉ “ኮሚክ” ይሆናል።
108ኛ ደግሞ እንዲህ ይላል።
“የወጣትና ጎልማሳ ሴቶችን ሕይወት ለማሻሻል ለሚደረገው ዘመቻ፣ የተለየ ድጋፍ እናደርጋለን”...
እንግዲህ፣ ከታሪክ አንብባችሁ ከሆነ፣ “ወጣቶች”፣ “ሴቶች”... በሚሉ ስያሜዎች፣ ባለፉት 45 ዓመታት፣ ብዙ ዘመቻዎች ተካሂደዋል። ስለ የትኛው ዘመቻ እንደሚናገር፣ አንቀፁ በግልፅ አይጠይቅስም። እንደ አዲስ፣ በፓርቲው የተጀመረ ወይም የሚጀመር ዘመቻ ሊሆን ይችላል። ፍንጭ ልስጣችሁ። እስከዛሬ፣ “ጎልማሳ ሴቶች” የተሰኘ የፖለቲካ አባባል አልነበረም። አዲስ ነገር ነው።
እንዲህ እንዲህ እያለ፣ እስከ 110ኛ አንቀፅ ይዘልቅና፣ ወደ ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ይሻገራል።
“ከተማችንን የጥበብ ማዕከል ማድረግ” በሚለው ተከታይ ርዕስ ስር፣ የኢዜማ ሰነድ፣ ምን ይዟል?
“ወደ አስራ አንድ የሚሆኑ አንቀፆችን ይዘረዝራል”። ... ይሄ፣ በበርካታ የዘመኑ ጋዜጠኞች ዘንድ እጅግ የተለመደ አባባል ነው። ጋዜጠኞችንም መተቸት ያስፈልጋል። ይህን የተንዛዛ አባባል ሲያሻሽሉት፣ “ወደ አስራ አንድ የሚደርሱ አንቀፆችን ይዘረዝራል” ብለው ይዘግባሉ። እቅጩን፣ “አስራ አንድ አንቀፆችን” ብለው ከተናገሩ፣ ውበቱ የሚቀንስባቸው ሳይመስላቸው አይቀርም።
ወደ ፓርቲው ግቦች እንመለስ። እንግዲህ፣ “ከተማችንን የጥበብ ማዕከል ማድረግ” በሚል ርዕስ ስር የቀረቡት ግቦች ወይም አንቀፆች፣ በእርግጥ በቀጥታ ከጥበብ ጋር የሚገናኙ ናቸው ለማለት ይከብዳል።
“በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊነት ያላቸውና ለቱሪስት መስብህ ሊሆኑ የሚችሉ ህንፃዎች፣ አካባቢዎችና ሌሎችም ቅርሶች በሙሉ በማስዋብ....” ብሎ የሚጀምረው 111ኛ አንቀፅ፣ ለአዲስ ግንባታ ሲባል እንዳይፈርሱ እከለክላለሁ ይላል።
ዋና ዋና አደባባዮችንና መናሃሪያዎችን አሻሽላለሁ፤ አዳዲስም እገነባለሁ በማለትም ቃል ይገባል - በቀጣዮቹ ሁለት አንቀፆች። ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት፣ በሰላም እንዲከበሩና የቱሪስት መስብህ እንዲሆኑ ድጋፍ እሰጣለሁ ይላሉ - ሌሎች ሁለት አንቀፆች።
ለፈርቀዳጅ ግለሰቦች ሃውልት ለማቆምና፣ መንገዶችን በመታሰቢያነት ለመሰየም እንዳቀደም ይገልፃል። ...”ይህን ስራ፣ በጥናት ላይ በተመሰረተ መልኩ የሚያከናውን እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በአባልነት የሚያካትት፣ ራሱን የቻለ ኮሚቴም አናቋቁማለን” ይላል - ይሄው 116ኛ አንቀፅ።
“ጥናት ላይ ተመስርቶ ይህን የሚሰራ ኮሚቴ አቋቁማለሁ” እንደማለት ነው - አጠር ሲደረግ። ያው፣ አባላትን ያላካተተና ራሱን የማይችል ኮሚቴ አይኖርም በሚል ተስፋ ማለቴ ነው። በእርግጥ፣ “ራሱን የቻለ” የተባለው፣ “independent” ለማለት ይመስላል።
ቀሪዎቹ አራት አንቀፆች፣ “አለማቀፋዊ” ነገሮችን የሚጠቁሙ ናቸው። ግንቦት 17 ቀን፣ በየአመቱ “የአፍሪካ ቀን” ተብሎ፣ በስፓርትና በኪነጥበባት ደምቆ እንዲከበር አደርጋለሁ ይላል - 119ኛ አንቀፅ። ትዝብት ላይ የሚጥሉ አንቀፆች የሚመጡት ከዚህ በኋላ ነው።
ብልፅግና ፓርቲና ኢዜማ መንገድ በመዝጋት ሊፎካከሩ?
ከ122ኛው እስከ 138ኛ የተዘረዙት አንቀፆች፣ “ፅዳትና ውበት የተላበሰች፣ አረንጓዴ ከተማ” በሚል ርዕስ ስር የቀረቡ ናቸው።
“አዲስ አበባ ከተማ፣ ለአረንጓዴ ልማት ሽግግር”፣... ብሎ ተነስቶ፣ ስለ ችግኝ ተከላ ይናገራል። መልካም። ከዚያ በኋላ፣ የፕላስቲክ ምርቶችን እንደገና ስለመጠቀም ወደ ማውራት ይዞራል።
ይሄ፣ እንዴት ለጽዳት ይጠቅማል? የውሃ መያዣ ፕላስቲኮችን እንደሆነ፣ ከየአካባቢው እየተለቀሙ እየተሰበሰቡ፣ ለፋብሪካ ምርት እየዋሉ ነው - የፓርቲ ወይም የመንግስት ትዕዛዝ ወይም ጥሪ አያስፈልግም። 123ኛው አንቀፅ ግን፣ በረዥሙ ያትተዋል። የጥራት ደረጃ እንደሚያወጣለትም ይገልጻል። ከዚያስ?
“የከተማዋን ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ አሰባሰብና አወጋገድ ስርዓት ለማስተካከል”፣... በሚል በቁም ነገር የሚጀምር 124ኛ አንቀፅ፣ ምን ብሎ ይጨርሳል?
“ቆሻሻን ከምንጩ መቀነስ የሚቻልበትን፣ መጠነ ሰፊ ጥናት በማድረግ፣ በስራ ላይ እናውላለን”።
ቆሻሻን ከምንጩ መቀነስ? “ለዚህም፤ መጠነ ሰፊ ጥናት”?... ኧረ። ቁም ነገር እናውራ።
“ነዋሪው ሕዝብ፣ ከአደጋ ስጋት ነፃ ሆኖ፣ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴውን እንዲከናውን፣ እንዲሁም ጤናማ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህሉ እንዲደርግ፣ በከተማዋ ዋና ዋና አካባቢዎች፣ ከተሸከርካሪዎች ነፃ የሆኑ የእግረኛና ብስክሌት መንገዶችን እናዘጋጃለን” ይላል 125ኛ አንቀፅ። እንዴት?
ያው፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴርና የጤና ሚኒስቴር፣ የብልፅግና ፓርቲ ባለስልጣናት፣ በየፊናቸው፣ የከተማዋን መንገዶች፣ “ከመኪና ነፃ” ለማድረግ ሲሽቀዳደሙ ነው የከረሙት። ...በኢዜማ የምርጫ ሰነድ ውስጥ ሰፈረው የዚህኛው አንቀፅ ልዩነት፣ “በከተማዋ ዋና ዋና አካባቢዎች” የሚል አባባል መጨመሩ ይመስላል።
እንግዲህ፣ የአስፋት መንገዶችን እየዘጋ እንዲያውከን፣ የትኛውን ፓርቲ እንምረጥ?
ድሮ ድሮ፣ አስፋልት መንገዶችን የመዝጋት ዛቻ፣ የአመጽ ዛቻ ነበር። ዛሬ፣ የፓርቲዎች መፎካከሪያ ሆኗል። ብልፅግና ፓርቲም፣ ኢዜማ ፓርቲም፣... አስፋልት መንገዶችን ከመኪኖች ነጻ እናወጣለን ይላሉ። በዚህ በዚህ አይተናነሱም። ወደ ጀመርነው ርዕስ ስንመለስ፣ የኢዜማው ሰነድ ቀጠል አድርጎ፤ “በመንገዶች ዳር እና ዳር፣ ተንጠልጣይ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሳጥኖች በበቂ መጠን እንዲዘጋጁ እናደርጋለን” ይላል። ልብ በሉ። “ተንጠልጣይ” ናቸው ሳጥኖቹ።
ግን ቢያንስ ቢያንስ፣ ቁም ነገር አላቸው። አንደኛ ነገር፣ ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በቀጥታ ይገናኛሉ። “ጽዳትና ውበት የተላበሰች አረንጓዴ ከተማ” የሚል ነው ርዕሱ። በዚያ ላይ፣ “ቆሻሻን ከምንጩ ለመቀነስ”፣ “መጠነ ሰፊ ጥናት ከማካሄድ” ይልቅ፣ ለፅዳት የሚያገለግሉ ሳጥኖችን ማዘጋጀት ይሻላል - የሚንጠለጠሉም ሆኑ የሚተከሉ።

Read 3318 times