Print this page
Saturday, 08 May 2021 13:36

‘ማርኬቲንግ ስትራቴጂ’ እና ‘ግፍ’... አይደበላለቅ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

     እንኳን ለዳግማይ ትንሳኤ አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“ስንት አልከኝ?”
“ሰባት ሺህ...”
“ሰባት ሺህ ለበግ?!”
“እንደውም የጠዋት ገበያ ነው ብዬ አስተያየት አድርጌ ነው”
ምን ይደረግ! እንዲሁ እንደ ቆዳ ስንለፋ እንኑር እንጂ! ምን መሰላችሁ የበሬውን ዋጋ በግ ወሰደው፣ የመኪናውን ዋጋ በሬ ወሰደው፣ የጂ ፕላስ ፎሩን ዋጋ መኪና ወሰደው!
ለነገሩ ምን መሰላችሁ...በአንድ በኩል እሰየው ነው፡፡ ልክ ነዋ...ነጋ ጠባ “እንደው እንደምንም ብለህ አንዲት ኩርኩር ነገር እንኳን መያዝ አቅቶህ ነው!” የሚል ኪሳችንንና የዶላር ምንዛሪ ተመንን ያላገናዘበ ጭቅጭቅ ይቀርልናል፡፡ እናላችሁ አሁን ኩር፣ ኩር የሚለው ባለ ሦስት እግር ወይም ባለ አራት እግር ተሽከርካሪ ሳይሆን የእኛ ሆድ ነው ለማለት ያህል ነው፡፡
ስሙኝማ...መቼም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሰበብ አስባቡ፣ ሰብሰብ የምንልባቸው ሰበቦች እየተመናመኑ፣ እየቀነሱ ነው የሄዱት፡፡ ከእቁብ አቅም እንኳን የ‘ክላስ’ ነገር ልትሆን ምንም አልቀራት! መቼም የሌለ ነገር አይቆጠብ! የምር ግን...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... እቁብን የመሰለ ለስንቱ ሰው ‘ቀን ያወጣ’ ነገር አለ እንዴ!
“ስማ፣ እንዳትረሳ ሚያዝያ ላይ ነው ሰርጉን የምደግሰው”
“ምን! ድግስ! አንተ ሰውዬ ያምሀል እንዴ! ቦንዳ አልጋህን መለወጥ ያልቻልክ ከየት አምጥተህ ነው የምትደግሰው!”
“እቁብ ገብቻለሁ”
አያችሁልኝ አይደል! እቁብ፣ አይደለም... “ሶፋ እለውጣለሁ...” “ሀምሳ ኢንች ፍላትስክሪን እገዛለሁ...” ማለት....ለሰርግ ድግስ እቅድ ለማውጣት የልብ ልብ የምትሰጥ ነበረች፡፡
ወይ ደግሞ...
“ስማ እሷ ሴትዮ ያንን ጃን ሜዳ የሚያክል ክትፎ ቤት የከፈተችው፣ ያን ሁሉ ገንዘብ ከየት አምጥታው ነው?”
“ሞቅ ያለ እቁብ ደርሷት ነው አሉ!”
እናላችሁ... እቁብን የመሰለ የክፉ ቀን ማምለጫ ብቻ ሳይሆን፣ የነገ እቅድ ማውጫ እየተመናመነች ነች ነው የሚባለው፡፡ ምናልባትም ጥናት ቢካሄድ ከየትኛውም አካባቢ በበለጠ በእቁብ የትጥለቀለቀች ሳትሆን የማትቀረው መርካቶ እንኳን “እቁብ ድሮ ቀረ!” ሊባልባት ምንም አልቀራትም ይሉናል ውስጥ አዋቂ ቤተኞች፡፡
እናማ... እንዲሁ በየግላችን የሚያቅተንን በጋራ ሰብሰብ ብለን በበዓል ሰሞን የበይ ተመልካች እንዳንሆን ስትከላከልልን የነበረችው ‘ቅርጫ’ እንኳን ይኸው እሷም “ከእለታት አንድ ቀን... ነገር ልትሆን ጫፍ ላይ ነች፡፡ የምር አሳዛኝ ነው፡፡ እንደ አቅማችን ለወራት የደረቀ አንጀታችንን ለስለስ እንድናደርግ ስታደርገን የቆየችው ‘ቅርጫ’ም፤ የጠቅላላ እውቀት ጥያቄዎች ‘ማቴሪያል’ ልትሆን ነው ማለት ነው!
“እሺ ከተለያዩ ሙያዎች የመጣችሁ ተወዳዳሪዎች፤ የሚቀጥለውን ጥያቄ ለሚመልስ የአስር ሺህ ብር ሽልማት አለው። ቅርጫ ማለት ምን ማለት ነው?”
“ይቅርታ፣ ጥያቄው ይደገምልን”
“ቅርጫ ማለት ምን ማለት ነው?”
“እ..እ ቀራጭ...የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾችን የሚቀርጽ ባለሙያ...”
“አልተመለሰም፣ ሌላ ተወዳዳሪ...”
“እ..እ...የሚከፈል የቀረጥ አይነት...ማለት ኬላ ላይ...”
“አልተመለሰም፡፡ ጥያቄውን የመለሰ ተወዳደሪ ስለሌለ የአስር ሺህ ብር ሽልማቱን ማንም አያገኝም፡፡ ወደ ሚቀጥለው ጥያቄ...”
"ቆይ እንጂ! ቅርጫ ምን ማለት እንደሆነ አንተ ንገረና... መልሱን ጽፈህ ይዘኸው የለም እንዴ!" ጽፎ ይዞታል፡፡ ግን ተወዳዳሪዎች “ቀራጭ፣” “ቀረጥ...” ያሉት ነገር ጥርጣሬ አሳድሮበታል፡፡ ልክ ነዋ...መልሱን ያገኘበትን መጽሐፍ የጻፉት ሰዎች፣ ለራሳቸው ‘የቡድን ፍላጎታቸው’ እንዲጠቅም አድርገው አንጋደውት እንደሆነስ! (እመኑኝ... እርስ በእርስ መጠራጠራችን የደረሰበት ደረጃ የሆነ ዓለም አቀፍ ጥናት የሚጠይቅ ሊሆን ምንም አልቀረው!) እናማ... መልሱን የያዘው ጠያቂ ራሱ ጠይቆ፣ ራሱ ግራ የሚጋባበት ዘመን ላይ ነን ለማለት ነው፡፡
ስሙኝማ...ማንም ይሁን ማን ለፋሲካ ተሠራልን አይደል! ልክ ነዋ… እንደ ወዲያኛው ዘመን “አሻጥረኛ ነጋዴ...” እየተባለ በማርሽ ሙዚቃ መግለጫ የሚሰጥበት ዘመን ስላለፈ ነው እንጂ ከሶስትና ከአራት ወራት በፊት በውድ በሦስት ሺህ ብር የተገዛች በግ አሁን ስድስት ሺህ አምስት መቶና ሰባት ሺህ! ይሄ ‘ማርኬቲንግ ስትራቴጂ፣’ ‘ነጻ ገበያ፣’ ቅብጥርስዮ ሳይሆን በምስኪኑ ሸማች ላይ የተፈጸመ ግፍ ነው፡፡ እንደውም ጭካኔ ነው! ከወርና ከሁለት ወር በፊት ሦስት መቶና በጣም ሲወደድ  ሦስት መቶ ሀምሳ የነበረ አንድ ኪሎ ቅቤ፣ አምስት መቶ ሰባ አምስትና ስድስት መቶ ብር! ይሄ የለየት ግፍ ነው፡፡  ይቺን ቀን እንኳን አእምሩዋችን በነገር ሳይወዛገብ፣ በጭንቀት እረፍት ሳያጣ እንዳይውል! ይሄን ያህል ምን አደረግናችሁ!
ይቺን ስሙኝማ... አንዳንድ ዓመል አይለቅም አይደል፣ ሰውየው ይሄ አባወራ በሌለበት በሰው መስኮት የመዝለል አመሉ አልለቅ ብሎት ጓደኛ እየመከረው ነው...
“ስማ ትናንት ትመጣለህ ብዬ ጠብቄህ ምነው ቀረህ?”
“ምን እባከህ፣ አላደረሰኝም፡፡ እሷ ቤት ነበርኩ...”
“እሷ ቤት ማለት...”
“ያቺ... ያቺ ላይ ሰፈር ያለችው...”
“አንተ ሰውዬ ከሰው ሚስት ጋር መማገጥህን አልተውም ማለትህ ነው! ምናለ ለራስህ ለባለቤትህና ለልጆችህ ብትጨነቅ! በአንተ ጦስ እነሱ መከራ ማየት አለባቸው እንዴ!”
“ምን ላድርግ ብለህ ነው፣ እየሞከርኩ ነው...”
“ብቻ የተጋለጥክ ቀን አንተን አያድርገኝ!”
“ትናንት ገና ከቤቷ ሳልወጣ ባልየው ከች አይል መሰለህ!”
“ምን! ዘሎ ጎሮሮዬን አነቀኝ በለኝ!”
“ምን ያንቀኛል… ጠደፍ አልኩና የተበላሸ ነገር ለመጠገን ተጠርቼ የመጣሁ አናጢ ነኝ አልኩት”
“አጅሬ ለዚህ፣ ለዚህ ማን ደርሶብህ...”
“ምን ዋጋ አለው…ለካስ እሱ እራሱ አናጢ ነው!”
እናማ... ምንም ነገር ላይ አይታወቅብንም እየተባሉ የተሠሩ፣ እየተሠሩ ያሉና ሊሠሩ የታሰቡ ነገሮች ሁሉ በአንድ ያልታሰበ ቀን ውሽማም፣ ባልም ሁለቱም አናጢ ሲሆኑ መጋለጣቸው የጊዜ ጉዳይ ነው ለማለት ነው። ‘እጅ ከፍንጅ’ የሚሉት ነገር አለ አይደል! (እንትና... ይቺን አንብበህ “ይህ አባባልህ በፋሲካው ገበያም ለነበረው ሁኔታ ሊሠራ ይችላል የምትለኝ ከሆነ መረጃና ማስረጃህን ወዲህ በል!)
ሰውየው “ያንን ወስላታ ምግብ አዘጋጁልኝ፣” አሉ እንደተባለው ነው፡፡ እናላችሁ... በዘመኑ አማርኛ  በ‘ወስላታነት’ የተፈረጀው ምን ቢሆን ጥሩ ነው... ፍርፍር። ምን መሰላችሁ... ፍርፍር፤ እርፍናው ህብረ ምግባዊ መሆኑ ነው፡፡ ልክ ነዋ...ይብላኝ እንጂ ለድስትና ለመጥበሻ... አለ አይደል... ምን የሚቀር ነገር አለና ነው፡፡ እንጀራው በሉት፣ በአንድ ወቅት ‘እንጀራ’ የነበረው በሉት፣ ዳቦ በሉት፣ ምንነቱ  ያልተጣራ የምግብ አይነት በሉት፣ የተረፈች ስጋና የከረመች የምስር የጋራ ግንባር በሉት...ምን አለፋችሁ ፍርፍርን የመሰለ ሁሉን አካታች ምግብ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ወስላታ ያሏት ሰው ይህን ነገር እንኳን በፌስቡክ ዘመን አላሉት!
እናማ... የቅቤ፣ የበሬ፣ የበግ፣ የፍየል፣ የዶሮ (ጨረስኩ አይደል!) ነጋዴዎች ልብ በሉ.... የጠፋው ቢጠፋ የምንሸሽበት ‘ወስላታ’ ምግብ አናጣም፡፡ ይብላኝንል ለሥጋ...ረጅም እድሜ ለፍርፍር!
እንደገና... መልካም ዳግማይ ትንሳኤ ይሁንላችሁማ!
ደህን ሰንብቱልኝማ!


Read 1444 times