Monday, 10 May 2021 00:00

አምባሳደር ታደለች ኃይለሚካኤል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የመጀመሪያዋ የሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር

             "--ይህች አገር ከረሃብ፣ ከጦርነትና ከግጭት ጋር አብሮ የሚነሳ ስሟን አድሳ መልካም ገፅታ መጎናጸፍ  እንደምትችል አምናለሁ። የዕድሜ ባለፀጋ ጥንታዊት አገር ናት። የትልቅ ባህል ባለቤት ናት፤ አሁን ደግሞ ፈጣን ግስጋሴዋ ጉልበት እያገኘ ነው። የኔ ምኞት፤ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የብልጽግናና የዕድገት አገር እንድትሆን ነው።--"

            ለሰብአዊ መብትና ለፍትህ ያለኝ ስሜት፣ ከህልውናዬ ጋር የተሳሰረና በጥልቅ መሰረት ላይ የተገነባ ነው። አብሮኝ የተወለደ የተፈጥሮዬ አካል ሆኖ ይሰማኛል። በደርግ ወታደራዊ የአገዛዝ ዘመን፣ በእስር ቤት ያሳለፍኳቸው 12 ዓመታትና 8 ወራት፣ ስለ ሰው ልጅ ማንነት ክፉና ደጉን አስተምረውኛል። ለጊዜው ባይታየንም እንኳ፣ እያንዳንዱ ሰው፣ የየራሱ ልዩ በጎ ማንነት አለው። እድል ካገኘም፣ በጎ ማንነቱ በእውን በአደባባይ ይገለጣል። በእነዚያ የእስርና የሰቆቃ ዓመታት፣ ቅስሜ ሳይሰበርና ጤናዬ ሳይቃወስ፣ ከልጆቼና ከቤተሰቤ ጋር  ለመገናኘት መቻሌ ለእኔ የህይወት ዘመን ስኬት ነው፡፡ ዳግም ነፍስ  የመዝራት ያህል እንደገና  ተነስቼ፣ አዲስ  በተቋቋመው መንግሥት፣ የመጀመሪያዋ የሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን፣ የአገሬ ሴቶችና ሕፃናት መብታቸው እንዲከበር መሥራቴም ሌላው የሕይወት ዘመኔ ስኬት ነው።
በአዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ ነው የተወለድኩት። ወላጆቼ አቶ ኃይለሚካኤልና ወ/ሮ በርአልጋ የተደላደለ ኑሮ ስለነበራቸው፣ ጥሩ ትምህርት ቤት የመግባት እድል ነበረኝና ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ስዊዘርላንድ ሄጄ፣ ከፍሪቦርግ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በጋዜጠኝነት ዲፕሎማ አግኝቻለሁ። ራሱን በራሱ እያስተማረ በእውቀት ለማበልፀግ የቻለው አባቴ፣ ከዘመኑ ቀድሞ የተራመደ ስልጡን ሰው ነበር። ለትምህርት ከፍተኛ ክብር የሚሰጥ ከመሆኑም የተነሳ፣ ብዙ ልጆችን በትምህርት እየደገፈ አሳድጓል። በተለይ ደግሞ በሴቶች ትምህርት ላይ ድርድር አያውቅም ነበር። ሴት ልጆቹን ሰብስቦ፣ የቤት አያያዝና የምግብ ዝግጅት ለመለማመድ ሳይሆን፣ ለትምህርታችን ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን ሲመክረን፣ “የባሎቻችሁ የቤት አገልጋይ  መሆን የለባችሁም።” ይለን ነበር። “ጥሩ ትምህርት እንድታገኙ ማድረግ የኛ የወላጆች ኃላፊነት ነው፤ የትዳር አጋራችሁን የምትመርጡት ግን እናንተ ራሳችሁ ናችሁ” ይለናል።
እናቴ በልጅነት እድሜ ብቻ ሳይሆን፣ እስር ቤት በነበርኩበትና ቤተሰባችን ላይ መከራ በተደራረበበት በዚያ ክፉ ዘመን ጭምር፣ በጎውን መንገድ ያሳየችኝ አስተማሪዬና አርአያዬ ናት። በደስታና  በሃዘን፣ በተድላና በመከራ ወቅቶች ሁሉ፣ የቤተሰባችን ምሰሶ ነበረች። በታሰርኩ ጊዜ፣ ሴት ልጆቼን ቅንጣት ሳታጎድልባቸው ፍቅር እየመገበች አሳድጋልኛለች። የሰዎችን ሃቅ መንካት የማትወድ፣ ጠንካራ የፍትህ ሰው የነበረችው እናቴ፤ የጥላቻ መንፈስ ስለማይነካካት “ሰው ላይ ለመፍረድ አትቸኩሉ” እያለች ሁሌም ትገስፀን ነበር። ከእስር ወጥቼ፣ እኒያ ህዝቡን እያሰሩ ሲቀጠቅጡና ሲያሰቃዩ የነበሩ የደርግ መሪዎች ለፍርድ በቀረቡ ጊዜ፣ በጥላቻ ስሜት እንዳልዘፈቅ እናቴ የመከረችኝ አይረሳኝም።  “መፍረድ ያንቺ ፋንታ አይደለም። እነዚህ ሰዎች በፈጣሪ እጅ ውስጥ ናቸው። የሚመጣባቸውን ነገር እንዲቀበሉ ተያቸው። በቴሌቪዥን ባየሻቸው ቁጥር በጥላቻ መብሰልሰልና መንገብገብ ከጀመርሽ ግን፣ ጉዳቱ አንቺው ላይ ነው፤ ያንቺም ሆነ የልጆችሽ በጎ መንፈስና ኃይል ሙጥጥ ብሎ ይጠፋል።” ትለኝ ነበር።
ንጉሡን ከስልጣን ለማስወገድ በተካሄደው አብዮት ሳቢያ፣ ቤተሰባችን ሃብትና ንብረቱን ቢያጣም፤ እንደ አብዛኛው የዚያ ዘመን ወጣት አብዮቱን ደግፌያለሁ። አውሮፓ ስዊዘርላንድ ውስጥ እየተማርኩ፣ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር እንዲሁም በማህበሩ የሴቶች ክንፍ ውስጥ እየተሳተፍኩ፣ ´ታገይ´ የተሰኘውን የሴቶች መጽሔት አዘጋጅ ነበር። ከባለቤቴ ከብርሃነ መስቀል ረዳ ጋር የተዋወቅሁትና የተጋባነው፣ እዚያው ስዊዘርላንድ ሳለን ነበር። ብርሃነ መስቀል፣ ስመጥር የተማሪዎች ንቅናቄ መሪ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) መሥራች እንደሆነ ይታወቃል። በጥንታዊው የፊውዳል አገዛዝ ሳቢያ፣ ፋታ የለሽ ድህነት ውስጥ መፈናፈኛ አጥተው የኖሩ ዜጎች፣ ያንን አገዛዝ ለማስወገድ ያነገቡት “መሬት ላራሹ” የተሰኘው የዘመኑ መፈክር፣ በብርሃነ መስቀል የተቀመረ ነበር።
በ1969 (70) ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የተመለስኩት፣ አገሬን ለማየትና የድህረ ምረቃ የማስተርስ ዲግሪ ጥናቴን ለማካሄድ ብቻ አልነበረም። የወለድኳትን ልጃችንን ለባለቤቴና ለቤተሰቤ ለማሳየት ስለጓጓሁም ጭምር ነበር። እንዲያም ሆኖ ፣ በዚህ የቀውስ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ መምጣቴ የዋህነት ነበር። ተመልሼ ወደ አውሮፓ አልሄድኩም። አገሪቱ፣ በተለይ ደርግን ለሚቃወሙ ሰዎች እጅግ አደገኛ እንደሆነች ብገነዘብም፣ ወላጆቼን እየደገፍኩ ከልጆቼና ከባለቤቴ ጋር እዚሁ ለመቆየት ወስኜ ሥራ ጀመርኩ።
አውሮፓ ወይም አሜሪካ ተምረው የመጡ ወጣቶች፣ ለአብዮቱ ጠላት ናቸው ተብለው በአይነ  ቁራኛ በሚታዩበት በዚያ ዘመን፣ ከደርግ ጥርስ ውስጥ ላለመግባት ከቦታ ቦታ እየተሸሸግሁ፣ ሁለተኛዋን ልጄን ወለድኩ። ነገር ግን በአዲስ አበባ ተደብቄ መቀጠል አልቻልኩም። አፈናው ስለበረታ፣ በርካታ የተቃዋሚ ወገን አባላት በሕይወት ለመሰንበት ሲሉ በህቡዕ ለመንቀሳቀስ ተገደው ነበርና እኔም ከእስር ለማምለጥ ሁለቱን ልጆቼን እናቴ ዘንድ ትቼ፣ ከአዲስ አበባ ወደ ገጠር ሸሸሁ። በገጠር አካባቢ ተሰማርቶ ከነበረው ኢህአፓ የእርምት ንቅናቄ ጋር ስቀላቀል፣  የውጭ ቋንቋዎች ስለምችል፣ የንቅናቄው የመረጃ አገልግሎት ክፍልን እንድመራ ተመድብኩ። ብዙም አልቆየሁም። የእርምት ንቅናቄውን በመወከል በውጭ አገራት እንድሰራ ስለተወሰነና እርጉዝም ስለነበርኩ፣ ከአገር ለመውጣት ለጉዞ ተዘጋጀሁ። ከጉዞው በፊት ግን፣ ከከተማ ወጥተው ባለቤቴ ወደሚገኝበት ካምፕ ለመምጣት የሚፈልጉ በርካታ ወጣቶች ችግር ስላጋጠማቸው መርዳት ነበረብኝ። ወጣቶቹን መንገድ እየመራሁ ሳለ፣ ወሎ ውስጥ በደርግ ተይዤ ማዕከላዊ እስር ቤት ገባሁ።
እንደ ብዙዎቹ እስረኞች፣ ለበርካታ ወራት ለብቻዬ ተቆልፎብኝ ፣ ሊሰሙት የሚከብድ መከራ ደረሰብኝ። ከብዙ የምርመራ ስቃይ በኋላ፣ “ትረሸን” ብለው ሊገድሉኝ ሲወስኑ ደግሞ፣ ከሞት ጋር ተፋጠጥኩ። በዚች ቅፅበት፣ እርጉዝ መሆኔን ስላወቁ ከሞት ተረፍኩ። የእስር ጊዜዬ ግን ገና መጀመሩ ነበር። የእስር ቤት ውሎና አዳር፣ የራሴ የምትይውን ነገር ሁሉ ይቀማሻል። ሰው የመሆን ክብርን አሳጥቶና የሰብአዊነት መንፈስ አሟጥጦ፣ ያሰቃያል። እንዲያውም ሆኖ፣ እኔና መሰሎቼ የእስር ቤት ኑሯችን ጨርሶ በድን እንዳይሆን ለማድረግ መፍጨርጨራችን አልቀረም። ወጣቶችን ለሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ለማዘጋጀት እናስተምር ነበር። እስር ቤት ውስጥ የወለድኳትን ሶስተኛ ልጄን ያሳደግኋት እዚያው ነው። የእስር ቤት ኑሮ ትዕግስትን፣ ማዳመጥንና ከሌሎች መማርን አስለምዶናል። የሁሉም ሰው መብት መከበር አለበት የሚለው እምነቴ፣ ደረጃ በደረጃ ጥልቀት እያገኘና እየፀና የመጣውም በዚሁጊዜ ነው። በእስር ያሳለፍኳቸው ዓመታት፣ የጥንካሬዬ መሰረት ሆነ። ያንን የእስር ዘመን ተቋቁሜ ካለፍኩ በኋላ፣ የትኛውንም ፈተና መቋቋም እንደምችል አውቃለሁና ላመንኩበት ነገር ሁሉ በግልጽ የመናገር ድፍረት ተጎናጽፌያለሁ።
የደርግ አገዛዝ በ1983 ዓ.ም ተሸንፎ ከእስር እንደተለቀቅሁ፣ በሽግግር መንግሥቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ውስጥ፣ የስነ ፆታ ጉዳዮች ዋና ተጠሪ እንድሆን ጥያቄ ቀረበልኝ። ይህንን ኃላፊነት የሚመጥን በቂ የስራ ልምድ እንደሚጎድለኝ ባልክድም፣ በሴቶች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የቻልኩትን ሁሉ ለመስራት፣ አቅምና ፍላጎት እንዳለኝ እርግጠኛ ነበርኩ። ጥያቄውን ከመቀበሌና ኃላፊነት ከመረከቤ በፊት ግን፣ በሴቶች መብትና ተሳትፎ ላይ  ተጨባጭ ውጤት የሚያመጣ እውነተኛ ነገር እንድሠራ፣ መንግስት ፈቃደኛ መሆኑን ማረጋገጥ ነበረብኝ። በደርግ ዘመን፣ የሴቶች ንቅናቄ በስፋት ሲካሄድ እንደነበር ይታወቃል። ያንን መልሼ መድገም አልፈለግሁም። የሽግግር መንግሥቴ መሪዎች፣ ለሴቶች መብትና ተሳትፎ ፅኑ አቋም እንዳላቸው ስገነዘብ፣ የቀረበልኝን የኃላፊነት ቦታ ተቀብዬ፣ በሙያ ዘመኔ በእጅጉ የወደደኩትና የረካሁበትን ስራ ጀመርኩ። በእርግጥ ሥራው በተቃውሞ የተከበበ ፈታኝ ሥራ ነበር። በሴቶች መብትና ተሳትፎ ላይ የሚነሳው ተቃውሞ፣ በአገሪቱ ባህል ውስጥ ለዘመናት ስር ሰድዶ የዘለቀ ስለሆነ፣ በቀላሉ የሚገላገሉት አይደለም። ይሄም ሆኖ ግን ችግሩን ለመቅረፍ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅብናል። “ሴቶችን አሳንሶ ከሚያይ ኋላቀር ልማዳዊ አስተሳሰብ ባሻገር መጓዝ አለብን፤ ደግሞም መጓዝ እንችላለን” የሚል ወኔ፣ ተስፋና እምነት ይዤ ነው የገባሁበት። ከብዙ አጋሮቼ ጎን ተሰልፌም፣ በሙሉ ልብና ብርታት ታግያለሁ።
ከባልደረቦቼ ጋር በመላ አገሪቱ በሰፊው በማማከርና የረዥም  ጊዜ ራዕይ በመሰነቅ፣ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው የሆነውን የሴቶች ፖሊሲ  አዘጋጅተን በ1985 ዓ.ም እንዲጸድቅ ለማድረግ ችለናል። “ሩቅ አሳቢ፣ ቅርብ አዳሪ” ላለመሆንም፣ ፖሊሲውን በተግባር ለመተርጎም ተቋማዊ ስርዓቶችን ነድፈን የአሰራር ሂደቶችን ለመዘርጋትና ሙያተኞችን ለማሟላት በቅተናል። ይህም ብቻ አይደለም። ሕገ-መንግስቱን በማርቀቅ ሂደት ውስጥ የሴቶችን መብት የሚያስከብር ሕግ እንዲወጣ ለማስቻል ሽንጣችንን ገትረን ተሟግተናል። በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ማናቸውም  የአድልዎ አይነቶችን ለማስወገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈረመው ስምምነት በአገሪቱ ሕገ-መንግስት ውስጥ እንዲካተት የሴቶች ጉዳይ ቢሮ በፊታውራሪነት ታግሏል። የሴቶችን መብት  የሚመለከቱ ህጎች በተለይም የቤተሰብ ሕግ፣ ዋነኛ መሠረታቸው የአገሪቱ ሕገ-መንግስት እንደሆነ ግልጽ ነው። ለዚህም ነው የሴቶችና ህፃናት መብት በህገ-መንግስቱ ሁነኛ ዋስትና ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ የጣርነው። በህገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ውስጥም፣ ሶስት ወንበር ለሴቶች እንዲመደብ ማድረጋችን፣ ትልቅ ትርጉም ነበረው። ሴቶችን በሰፊው ለማሳተፍ ባዘጋጀነው የምክክር መድረክ፣ የኢህአዴግ ሴቶች ማኅበርና የሶማሌ ሴቶች ማህበር ተወካዮች፣ ሁለቱን ወንበሮች እንዲይዙ ተመረጡ። ሶስተኛው ወንበር የተሰጠው፣ ሰርተው ለማይደክሙት ባለሙያ ለወ/ሮ አፀደወይን ተክሌ ነበር። እንዲህ ሳንታክት በመስራታችን፤ ለሴቶች መብት ጠንካራ ዋስትና የሰጠውን አንቀፅ 36፣ በሕገ-መንግስቱ ውስጥ እንዲካተት ለማድረግ ችለናል። የሕገ-መንግስቱ መነሻ ረቂቅ፣ እንደ ነባሩ ሕግ ሴቶችን አሳንሶ በመመልከት፣ ያለ ሞግዚት የራሳቸውን ህይወት በራሳቸው ውሳኔ የመምራት መብት እንዳይኖራቸው የሚገድብ ነበር። ዝም አላልንም። ድምፃችን ጎልቶ እንዲደመጥ ከዳር ዳር የአገሪቱን ሴቶች ቀሰቀሰን። በአገሪቱ ምክር  ቤት ፊት ቀርቤ ንግግር አሰማሁ። በመጨረሻም ከመንግስት አመራር ድጋፍ  አግኝተን፣ ለሴቶች መብት ጠንካራ ዋስትና በእጃችን ለማስገባት በቃን።
ሕገ-መንግስቱ ፀደቀ ብለን፣ አርፈን አልተቀመጥንም። ህዝቡን  በአጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ በየትምህርት ቤቱ ያሉ ታዳጊ ወጣቶችን፣ ስለ ሴቶች መብት ለማስተማር ለተከታታይ ዓመታት በትጋት ሰርተናል። የመማሪያ መጻህፍትና በራሪ ወረቀቶችን በብዛት ከማሳተማችንም በተጨማሪ ሳናሰልስ ባደረግነው ጥረት፣ የሴቶች መብት ፅንሰ ሀሳብ በትምህርት ስርዓቱ  ውስጥ እንዲካተት አድርገናል። የሴችን ተሳትፎ በተግባር ለማጠናከር፣ የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት አዲስ አሰራር ለመፍጠር የሚያስችል መመሪያ አዘጋጅተናል። ከአጋሮቻችን ጋር በመተባበር፣ ለድሃ ሴቶች የኢኮኖሚ እድል የሚፈጥርና የሙያ ስልጠና የሚሰጥ የሴቶች ልማት ፈንድ እውን እንዲሆንና በየአካባቢው እንዲተገበር አድርገናል።
በስርዓተ ጾታ ጉዳዮች ዙሪያ፣ ለሴቶች መብትና ጥቅም መስራት ቀላል አይደለም፣ ትግል ነው። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ፣ በስርዓተ ጾታ ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ የስራ ባልደረቦቼ፣ እለት ተእለት ፈተናዎች ይጋረጡባቸው ነበር። ፈተናው የሚመጣው ታዲያ፣ ከወንዶችም ከሴቶችም ነው። ሳንታክት ስለ ሴቶች መብት መሟገታችንንና፣ በመንግስት ፖሊሲዎች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ እንዲካተት ያለ እረፍት መከራከራችንን አልወደዱልንም። ሳይታክቱ ይቃወሙናል ብለን ዝም ማለት አንችልም። ስለ ሴቶች መብትና ተሳትፎ መከራከር ሥራዬ ነው፣ ለባልደረቦቼም ሥራቸው ነው። ያኔም ሆነ አሁን በጣም አስፈላጊና በሙሉ ልብ የምናምንበትም ሥራችን ነው። ለምዕተ ዓመታት ስር የሰደደውን ኋላቀር አስተሳሰብ ለመቀየር የምንችለው፣ ከአቋማችን ፍንክች ሳንል ለሴቶች መብትና ተሳትፎ በመሟገትና ሳናሰልስ በማስተማር ብቻ ነው። ባከናወናቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ፣ የስነ-ጾታ ጉዳይን ብሔራዊ አጀንዳ ለማድረግ መቻላችን ከልብ ያኮራኛል።
በምዕራብ አፍሪካ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ አገራት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኜ ተመድቤ፣ ወደ ኮትዲቯር በመሄድ አገሬን ማገልገሌም ያኮራኛል። በሁለተኛው ዙርም፣ በፈረንሳይ፣ በሞሮኮ፣ በስፔንና በዩኔስኮ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ሰርቻለሁ። የንግድ ትስስር እድሎችን እንዲሁም የኢትዮጵያን ባህላዊ ሃብቶችና ተፈጥሯዊ ውብ ፀጋዎችን ለውጭው ዓለም በማስተዋወቅ አገሬን ማገልገሌም፣ ለኔ አስደሳች ነበር። የኢትዮጵያ ሚሌኒየም በዓለም አቀፍ መድረክ እውቅና ተሰጥቶት እንዲከበር ለማድረግና ዩኔስኮን ለማሳመን ያደረግነው ጥረት ትዝ ይለኛል። ጥረቱን መምራቴና  ለስኬት ማብቃቴ አስፈንድቆኛል። ዩኔስኮ በፓሪስና በኢትዮጵያ ውስጥ ባሰናዳናቸው አውደ ርዕዮችና የበዓል ዝግጅቶች የአገራችንን ሚሌኒየም አክብሯል።
ይህች አገር ከረሃብ፣ ከጦርነትና ከግጭት ጋር አብሮ የሚነሳ ስሟን አድሳ መልካም ገፅታ መጎናጸፍ  እንደምትችል አምናለሁ። የዕድሜ ባለፀጋ ጥንታዊት አገር ናት። የትልቅ ባህል ባለቤት ናት፤ አሁን ደግሞ ፈጣን ግስጋሴዋ ጉልበት እያገኘ ነው። የኔ ምኞት፤ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የብልጽግናና የዕድገት አገር እንድትሆን ነው። ፍትህ የሰፈነባትና ሙሉ ለሙሉ የሚተገበርባት፣ ልጆቻችንም ሆኑ ወላጆቻችን የማይሸሿትና ጥለዋት የማይሰደዱባት አገር እንድትሆን እፈልጋለሁ። በደስታና በሰላም ሁላችንም አብረን የምንኖርባት ውብ አገር ትሆናለች።
ታሪኬን ለሚያነቡ ልጃገረዶች፣ አንድ ነገር ልነግራቸው እፈልጋለሁ። የእያንዳንዳችሁን ሕይወት የሚያሻሽል ወደር የለሽ መሳሪያ ቢኖር ትምህርት ነው። በትምህርት ማመን አለባችሁ። በየትም ቦታና ሁኔታ፣ ከወላጆችም ሆነ ከቤተሰብ ጋር፣ ከትዳርም ሆነ ከፍቅር አጋር ጋር፣ ከልጆችም ሆነ ከማህበረሰቡ አባላት ጋር የሚገጥማችሁን ችግር መቋቋምና ማሸነፍ የምትችሉት በትምህርት ብቻ ነው። “ከራሴ ህይወት የተማርኩት ቁም ነገር፣ ወደ ማላውቀው ቦታ በመሸሽ ኑሮዬ ሊሻሻል ይችላል ብሎ ማሰብ፣ ከንቱ መሆኑን ነው። ችግሮችን ተጋፍጣችሁ ማሸነፍ ይኖርባችኋል። አጥብቄ የምመክራችሁ፡- ለሙያችሁና ለሥራችሁ ከልብ የምታስቡና በፅናት የምትቆሙ እንድትሆኑ ነው። አሁን በደረሳችሁበት ደረጃና እስካሁን ባገኛችሁት ውጤት ብቻ እረክታችሁ አትቀመጡ። እምቅ አቅማችሁ ትልቅ እንደሆነ ተገንዝባችሁ፣ ወደ ላቀ ደረጃ ተራመዱ።
("ተምሳሌት - ዕጹብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች" መጽሐፍ የተወሰደ፤ 2007 ዓ.ም)


Read 830 times