Tuesday, 11 May 2021 00:00

ከአጣዬ ጥቃት የተረፉት እናት ምን ይላሉ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

    “የወደመብኝ ንብረት እስከ 40 ሚ.ብር ይገመታል”

             ወይዘሮ ዘነቡ አዘነ ይባላሉ። የኤፍራታ ግድም ወረዳ የአጣዬ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ተወልደው ያደጉት ደግሞ በቀድሞው ገምዛ ወረዳ ማጀቴ ከተማ ነው። ወይዘሮዋ የ5 ልጆች እናት ሲሆኑ ልጆቻቸውን ያለ አባት ለማሳደግ ብዙ ወርደውና ወጥተው ለወግ ለማዕረግ አብቅተዋል። በተዋጣለት የንግድ ስራቸውና እንቅስቃሴያቸው በተደጋጋሚ “የልማት አርበኛ” እየተባሉ ሲመሰገኑና ሲሸለሙ የቆዩ ቢሆንም፤ በአጣዬ በተደጋጋሚ በደረሰው ጥቃት ንብረታቸው ሲወድም መልሰው  ሲያቆሙና ሲታገሉ መክረማቸውን በእንባ ታጅበው ይናገራሉ።  ሰሞኑን በአጣዬ በተከሰተው እልቂትና ጥፋትም የሁለት ልጆቻቸውና የራሳቸው መኖሪያ ቤትም ሆነ የንግድ ስራቸው ወድሞ ነፍሳቸውን ለማትረፍ ሲሉ ከአካባቢው ሸሽተው ወደ ሌላ ስፍራ መሄዳቸውን ይገልፃሉ፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከወይዘሮ ዘነቡ አዘነ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

              እንኳን በህይወት ለመትረፍ በቁ…
አዎ በእግዚአብሔር ቸርነት ተርፌያለሁ። ዋናው እርሱ ነው፤ ከህይወታችን በቀር እድሜ ልክ የለፋንበት ሀብትና ንብረት አመድ ሆኗል። ይህንንም ለመናገር የበቃሁት ከእነልጆቼ በመትረፌ ነውና እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ።
እስኪ የደረሰዎትን ችግር ከመጀመሪያው ጀምሮ በዝርዝር ይንገሩኝ?
የተከሰተው ችግር አንድ ጊዜ ብቻ የተፈጠረ አይደለም፤ ከ2011 መጋቢት 28 እና 29 ቀን ጀምሮ በተከታታይ የደረሰብንን ጭምር ነው የምነግርሽ። ከላይ በጠቀስኩልሽ አመትና ቀናት ከእነልጆቼ የጥቃት ሰለባ የሆንኩት ቁጥር አንዷ እኔ ነኝ። ጥቃቱን ለመጥቀስ የልጄ የብስራት ከፍያለሁ ሱቁና ንብረቱ ተዘርፎና በመኪና ተጭኖ የተወሰደ ሲሆን የተረፈውም የእሳት ሲሳይ ሆኗል። የእኔም  “ዘነቡ ሆቴል” የተባለው ድርጅቴ 42 አልጋ ከእነፍራሹ 150 ሳጥን ለሰላሳ፣ 300 ሳጥን ጊዮርጊስ ቢራ፣ 100 ሳጥን ሜታ ቢራ፣ 150 ሳጥን ዋልያ ቢራ፣ 120 ሳጥን ሚሪንዳ፣ 35 ሳጥን አምቦ ውሃ፣ 110 ሳጥን ሶፊ ማልትና ቤት ውስጥ ያለው ቴሌቪዥን እንዲሁም ሌላው ሌላው ሁሉ ነው በሙሉ  የወደመው።
22 ሰራተኛ ቀጥሮ የሚያስተዳድር ሆቴል ነበር። በዛን ወቅት ሆቴሉ በ24 ጥይት ተደብድቦ ኦና ቀረ። ከመንግስትም ሆነ ከየትኛውም አካል ካሳም ማፅናኛም ሳናገኝ፣ ክርስቲያን ተስፋ አይቆርጥም መቼም እንደ ገና ከየትም ከየትም ብለን መልሰን አቋቁመን፣ ከኖርንበት የት እንሄዳለን ብለን መስራት ጀመርን፤ ችግሩ አይደገምም ያለፈው አልፏል ብለን ነበር ወደ ስራ የገባነው። አሁን ደግሞ የትልቁ ልጄ ሱፐር ማርኬት፣ የትንሿ ልጄ የኤደን ጥላዬ በመጀመሪያው ዙር ጥቃት ድራፍት ቤቷ፣ የባለቤቷ ወርቅ ቤት ነበር፤ ድራፍት ቤቱ እንዳለ ተዘርፋል፡፡ 120 ወንበር ሶስት 3 ፍሪጅ፣ 3 ጀኔሬተር፣ 2 ትልልቅ ቴሌቪዥን ዘርፈው መኖሪያ ቤቷን ሳይቀር አራቁተውና የቤቱን መስታወት ሰባብረው ሁሉንም አውድመው ሄዱ። የባለቤቷ ወርቅ ቤትም እንዲሁ ከመዘረፍና ከመውደም አልተረፈም - 1 ሺህ 500 ግራም ወርቅ፣ 1ሺህ ግራም የውጭ ብር ተዘረፈ፡፡ ይሄ  በ2011 ዓ.ም በደረሰው ጥቃት የደረሰብንን ነው።
እንደውም አንድ የረሳሁት ነገር በዛን ጊዜ አንዲት የእህቴ ልጅ ቤቴ ውስጥ በጥይት ተመትታ ነበር። ያን ጊዜ እሷን አፋፍሰን አዲስ አበባ አቤት ሆስፒታል አምጥተን ብናሳክማትም፣ አሁንም ወደ ጤናዋ አልተመለሰችም። እኛ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለመንግስት እሪ ኡኡ እንላለን። ደህንነታችን ያሰጋናል እንላለን፣ ሰሚ አላገኘንም። ሆኖም ተስፋ ሳንቆርጥ እንደገና አንሰራርተን ቅድም እንደነገርኩሽ ወደ ስራ ተመለስን። በ2012 መስከረም 24 ቀን ደግሞ እንደዚሁ በድንገት ተኩስ ተጀመረ። ለሁለተኛ ጊዜ እንዲሁ ንብረታቸን ወድሞ የሰው ህይወት ጠፍቶ ነገሩ አለፈ። ከእነልጆቼ በተደጋጋሚ የደረሰብኝን በደልና ጥቃት የቱን ነግሬሽ የቱን ልተወው። ለቅሶ...
እስኪ በቅረርቡ በተነሳው ግጭት የደረሰብዎትን ይንገሩኝ?
በመጋቢት 10፣ 11፣ 12 ቀን 2013 ዓ.ም እንደዚሁ  ሳናስበው ድንገት ተኩስ ተከፈተ። መኖሪያ ቤቴም ሆቴሌም ወደመ። ቤቱ ባለ አንድ ፎቅ ነው። ፎቁ ላይ 20 አልጋ፣ መሬት ላይ 32 አልጋ ነበረው። አንዲት ሰባራ ስንጥር ንብረት ሳላወጣ አመድ ሆኖ ቀረ። እንግዲህ ቤቱ ውስጥ ያለው የሆቴሉን ንብረት አስቢው፡- ወንበር፣ ፍሪጅ፣ ጀነሬተር ቢራው፣ ለስላሳው ስንቱ ነገር መሰለሽ.... አንድም የተረፈ ነገር የለም። በበፊቱ ጥቃት ከ500 ግራም በላይ የኔ የወርቅ ጌጣጌጥ ተዘርፎብኝ ነበር። አሁን ደግሞ 180 ወንበር- የመናፈሻው ሳይቀር መኖሪያ ቤቴ ሁሉ ወደመ።
ቤትዎና ድርጅትዎ በምን ያህል ካ.ሜ ቦታ ላይ ያረፈ ነበር?
በ1ሺህ 200 ካ.ሜ ላይ ያረፈ ነው፡፡ ምን ዋጋ አለው… ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል ለ35 ዓመት የለፋሁበት ሀብት ንብረቴ የእሳት ሲሳይ ሆነ። ከኔ መንከራተትና መሰደድ በላይ 22 ቤተሰብ የሚተዳደርበት ከእኔ ጋር የሚሰሩ ሰራተኞችን ውለዱ እያልኩ እያስወለድኩ እያሳደግኩ የማስተምርበት፣ ብዙ ችግረኞችን የምረዳበት ድርጅቴ ወድሞ እነሱንም በተንኳቸው። አሁን እንዴት ሆነው ይሆን የት ደርሰው ምን እየላሱ እየቀመሱ ይሆን? እያልኩ ሌት ከቀን አለቅሳለሁ፡፡ እኔኮ የሚገርመኝ የሰው ልጅ ብዙ መከራና ስቃይ ያሳልፋል፤ ነገር ግን በእኛ በአጣዬ ላይ ምን በረዶ ምን ውርጅብኝ እንደመጣብን  ሊገባኝ አልቻለም፡፡ በአንድ ላይ ተካፍለን በልተን ተሳስበን ስንኖር አማራ ነሽ፣ ትግሬ ነህ ኦሮሞ ነህ፣ አፋር ነሽ፣ ሱማሌ ተባብለን አናውቅም። አሁን እንዲህ የተጨካከንበትን ምስጢር ባወጣ ባወርደው ሊፈታልኝ  አልቻለም፡፡ እኔ አጣዬ ላይ ልጅ ድሬያለሁ፤ በሰርጉ ላይ ሁሉም ተገኝቶ ተደስተን ነው ሰርጉ ያለፈው፡፡ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ የሚባል ነገር ጠርተን አንስተን አናውቅም፡፡ ተዋደን ተከባብረን ተጋግዘን አምሮብን ነበር የምንኖረው፡፡ ታዲያ አሁን  የመጣብን ታሪክ ምንድን ነው? የሚያስረዳኝ ማነው?... (ለቅሶ)
ጥቃቱ በተፈፀመ ጊዜ ብዙ ሰው ሞቷል፤ የቆሰለውም ሰው ብዙ ነው፡፡ እርስዎ ከእነልጆችዎ እንዴት አመለጡ?
እኔ በአጋጣሚ ማጀቴ ወደ ተባለው  የትውልድ ቦታዬ ሄጄ ነበር፤ እዛም  ድርጅት አለን፡፡ እናም ይሔ ነገር  ሐሙስ ቀን ተነስቶ አርብ ወደ አጣዬ ልመለስ ስል “ኧረ ችግር ተፈጥሯል” ስባል በዛው ቀረሁ፡፡ ልጄ ኤደን ደግሞ ልጇን አሞባት አዲስ አበባ መጥታ ነበር፡፡ ትልቁ ልጄ ደግሞ “መክሊት ግሪን ኤሪያ” የሚባል ሆቴል 02 ቀበሌ ከፍቷል  ለዚያ ሆቴል አሳ ከሀዋሳ የሚያመጡለትን  ሰዎች ለመቀበል አዲስ አበባ ነበር፡፡ ተመልከቺ የእግዚአብሔርን ሥራ!! እሱ በኪነ-ጥበቡ አመቻችቶ ምክንያት ፈጥሮ ከዚያ ከተማ አስወጥቶ አተረፈን እንጂ እዛ ብንሆን አንተርፍም ነበር፡፡ ማጀቴ የሄድኩት በዋናነት ለቅሶ ለመድረስ ነበር፡፡ ለለቅሶ አሸርጬ በወጣሁበት ልብስ ነው የቀረሁት። ቤቴ ውስጥ የነበረኝ የወርቅ ጌጣጌጥ…. ኧረ ስንቱ! ፈቃድ አውጥቼ ያወጣሁት ሽጉጥ እራሱ ይውሰዱት ያቃጥሉት የማውቀው ነገር የለም። በአጠቃላይ የዘረፉትን ጭነው ወስደው ሌላውን አቃጥለው አመድ አድርገውት ነው የሄዱት።
ጥቃቱ ሲፈፀም በአካባቢው ፖሊስ ልዩ ሃይልና መከላከያ አልነበረም?
ነበሩ! እኛ የመጀመሪያው ተኩስና ግድያ ጋብ ሲል የተረፈንን ንብረት ለመጫን ወስነን ነበር። እንዴት ዕቃ ትጭናላችሁ? “እኛ” አለን ቤቱን አድሰን አስተካክለን መልሳችሁ ወደ ቀድሞ ህይወታችሁና ስራችሁ ትመለሳላችሁ አሉን “እናንተ የቀራችሁን ጭናችሁ ከወጣችሁ አካባቢው ባዶ ሊሆን ነው። እኛም እናንተን ብለን ነው እዚህ ያለነው” ሲሉን እንደገና እቃ መጫኑን ትተን ባዶ እጃችንን ሄድን። ይህ በተባለ በሳምንቱ ነው አጣዬ ሙሉ ለሙሉ የነደደችውና የወደመችው። በዚህ ቃጠሎ ማንም መመስከር ይችላል፣ እንደኔ የተጎዳ የለም። አንዲት ክፍል የተረፈኝ የለም። ለ35 ዓመት ለፍቼ ልጆቼን ያለአባት ባሳደግኩበት ከተማ ንብረቴ፣ ሀብቴ ወድሞ ያለ አንዲት ነጠላ በመውጣቴ በጣም አዝናለሁ።
እኛ ለስራ ማጀቴ በመጣንበት ጊዜ በባለ አራት ወለሉ የእርስዎ ፔንሲዮን ነበር ያረፍነው፡፡ ያኛውስ ህንፃዎ ተርፏል?
እዛ አካባቢ ችግር አለ፤ ግን ከተማ አልተነካም። የአካባቢው ህዝብ ብዙ ትንኮሳ ቢደርስበትም ታግሶ ከተማውን እየጠበቀ ነው። አሁንም ቢሆን ቆላው ላይ ድንኳን ጥለው ወደ ከተማው ዘልቆ ጥቃት እንዳይፈፀም ተገትረው ውለው ተገትረው ያድራሉ። በእውነት ነው የምልሽ ህዝቡ በጣም ነው የሚያሳዝነው። እርግጥ መጋቢት 11 እና 12 ቀን ማጀቴ ላይ ብዙ ሰዎች ሞተዋል።
በተለይ በ12 ቅዳሜ ቀን ነጋዴዎችም ገበሬዎችም፣ የ12 ዓመት ልጅ ሳይቀር ሞቷል። ቆስለው ህክምና ላይ  ያሉም አሉ። ቆላ አካባቢ ያለው ሙዝ፣ ማንጎ ፓፓዬ፣ ሽንኩርት ሲዘረፍ ቆይቷል የማጀቴ ህዝብ ንብረት። ንብረቱ ይወሰድ ግን ከተማ እንዳይፈርስ በሚል ነቅተው በድንኳን ሆነው እየጠበቁ ነው። አካባቢው የስጋት ቀጠና በመሆኑና እንደ አጣዬ ማጀቴም  እንዳይፈርስ ህዝቡ በሰቀቀን ላይ ነው። የሚገርምሽ የፋሲካ በዓልን በድንኳን እንጂ ቤታቸው አልፈሰኩም። እዛው ድንኳን ውስጥ ናቸው።  እምነታቸውንም በማክበር ታቦት ይዘው እየወረዱ እየጸለዩ  ወዲህ እየጠበቁ የስጋትና የሰቆቃ ኑሮ ነው የሚመሩት። በዚህ ምክንያት ማጀቴ ከተማ ላይ የገባ ጥቃትና የፈረሰ ወይም የተቃጠለ ነገር እስካሁን የለም።
የአጣዬ እጣ ፈንታ ምንድን ነው ይላሉ? ለእናንተስ ከመንግስት እስካሁን የተደረገላችሁ ድጋፍ አለ?
እኔ የአጣዬ እጣ ፋንታ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አልችልም። እርዳታን በተመለከተ እኔ እስካሁን በተደጋጋሚ በንብረቴ ላይ ጥቃትና ውድመት ሲደርስብኝ ዞር ብሎ ያየኝ የለም። መንግስት በ2011 ዓ.ም በደረሰው ጥቃት፣ ለጥቃቱ ሰለባዎች እርዳታ ያደረገ ይመስለኛል።
እኔ ያን ጊዜም ሆነ አሁን ከእነልጆቼ ይሄ ሁሉ ሲደርስብኝ 1 ብር ከመንግስትም ሆነ ከሌላ አካል አይቼ አላውቅም። አሁንም ከየቦታው በበጎ አድራጎት በኩል እየተሰበሰበ ነው ይባላል፤ እኔ የማውቀው ነገር የለም።
በአሁኑ የወደመብዎት ንብረት በጠቅላላ ወደ ገንዘብ ቢቀየር ምን ያህል ብር ይሆናል ብለው ይገምታሉ?
የእኔ ሆቴሉ ከእነ 52 አልጋው፣ በውስጡ ያለው ንብረት፣ መኖሪያ ቤቴ ከእነ ንብረቱ አመድ ነው የሆነው፤  ከ35-40 ሚሊዮን ብር ይገመታል፤ ያውም ከዚያ በላይ ሊሆን እንደሚችል ነው የማስበው። ምክንያቱም ሆቴሉ ብቻ 52 ክፍል ነው ያለው፤ ፍራሹን አልጋውን አስቢው፣ መኖሪያ ቤቴም ትልቅ ቤት ነው፣ የሰራተኞቼን የመኖሪያ ክፍል አስቢው... እኔ እውቀቱ ስለሌለኝ በግምት ነው የምነግርሽ እንጂ ከዚያም በላይ ነው።
የልጆችዎስ?
የልጄ ብስራት ከፍያለው ሆቴል፣ እንደገና የባለቤቱ የብሩክ ላቀው ድርጅቶች ለብቻው ነው። የብሩክ ላቀው የ80 ዓመት አዛውንት እናቷ መጦሪያ የነበሩ ስድስት ሱቆች ከእነ ንብረታቸው፣ የትንሿ ልጄ የኤደን ጥላዬ ሱቅ፣ ድራፍት ቤት፣ መኖሪያ ቤት በሙሉ ነው የወደመው። የልጆቿን ልብስ እንኳን ይዛ አልወጣችም። የባለቤቷ የአቶ ቢኒያም ገብረ ማሪያም ወርቅ ቤት፤ እንደነገርኩሽ 1 ሺ 500 ግራም ወርቅ በላይ፣ የውጭ ብር  ከሺህ ግራም በላይ ተዘርፏል። እንደውም ቢኒያም ይህንን ንብረት አወጣለሁ ብሎ ሲታገል ህይወቱ በመከራ ነው የተረፈው።  እነዚህም ልጆች በአገራቸው እናድጋለን እንለወጣለን ብለው ሲታትሩ ሁለት ልጆቻቸውን አሳድገው ለወግ ለማዕረግ ለማብቃት ሲፍጨረጨሩ በነበረበት ወቅት ነው ይሄ ሁሉ ውድመት መጥቶ ባዶ እጃቸውን የቀሩት። የኔና የልጆቼ ብቻ አይደለም፤ የጎረቤቶቼ የአቶ ማስረሽና የወ/ሮ ባዩሽ አበበ ንብረት በሙሉ ወድሟል። ህይወቱን ያጣም ባለሆቴል አለ። ብቻ የደረሰብን በደል የወረደብን በረዶ ቀላል አይደለም።
እርስዎ በአጣዬም ሆነ በማጀቴ “የልማት አርበኛ” ተብለው ሲሸለሙ የነበሩ፣ ለብዙዎች የስራ እድል የፈጠሩ ጀግና ባለሀብት እንደሆኑ ሰምቻለሁ። አሁን ንብረትዎም ሀብትዎም ወድሟል። ከዚህ በኋላስ ምን ያስባሉ?
እኔ በፊትም ሆነ አሁንም እንኳን ልጆቼን ቤተሰቤን ቀርቶ የተቸገረን ሌላውንም ቢሆን መርዳትና ማገዝ የሚያስደስተኝ ሰው ነበርኩኝ። ማጀቴ ያለውን ባለ 4 ወለል ፎቅ ስመለከት፣ አሁን በኔ በሴቷ አቅም ነው ይሄ ሁሉ የተሰራው እያልኩ ይገርመኛል። ግን ያ ሁሉ ከንቱ ነው፤ ዓለም ከንቱ ናት። ዓለም ማለት እንደ ኦሞ ናት፤ ውሃ ውስጥ እንደተጨመረ ኦሞ በአንዴ የምትሟሟ። እኔ´ኮ ልንገርሽ “እኔ ቤት ውስጥ የሚሰሩትን እኔ እናታችሁ አስካለሁ ውለዱ” እያልኩ እዛው እኔው ጋ ያረግዛሉ፣ ይወልዳሉ አስተምራለሁ። በዲግሪ ተመርቀው ወደየራሳቸው ስራ የሄዱ ብዙ ናቸው። አሁን  እንኳን በዚህ  አደጋ ጊዜ የእነዚሁ እኔ ጋ የሚሰሩት ሰዎች የ4 እና የ8 ዓመት ህፃናት ልጆች አብረው ከቤቱ ጋር ሊቃጠሉብኝ፣ በስንት አሳርና ተዓምር ነው የወጡልኝ። ጉልበት ያላቸው እንደየ ጉልበታቸው ወጥተው አመለጡ፤ እነዚህ ህፃናት ቀርተው በስንት ኡኡታ ወጡልኝ። ተመልከቺ እዛው ቢሞቱ የዘላለም ፀፀት ነበር የሚሆኑብኝ። ብቻ እስኪ ተይኝ... ስንቱን ቁስሌን ልንገርሽ የኔ ልጅ። ዓለም እንደዚህ ናት፤ ከቤቴ ወጣሁ ሳልመለስ ቀረሁ። ተመልሼ የሀብት ንብረቴን አመድ ማየት ፈልጌ ነበር አልቻልኩም ፈራሁ። አመዱን እንኳን ለማየት ፈራሁ (ለቅሶ....) ስማችን እየተጠራ “ዘነቡ አዘነ... ማስረሻ” እየተባለ ሊገሉን ነበር። ጎረቤቴ አቶ ማስረሽም ከልጅነት እስከ እውቀት ያፈራው ንብረት ወድሞ ዘበኛው ተገድሎበታል። እኛ ስራ በሰራን፣ የስራ እድል በፈጠርን፤ ለመንግስት የሚጠበቅብንን ግብር በከፈልን ምን አጠፋን? ምን በደል ሰራን እስኪ የኢትዮጵያ ህዝብ ወገናችን ይፍረደን፣ መንግስት ይመልከተን፣ ፍርድ እየጠበቅን ነው..... (ከፍተኛ ለቅሶ...) እኔ የማጀቴውን ፎቅ የሰራሁት ድሮ ገምዛ ወረዳ የነበረው በድንገት በደረሰብን የጎርፍ አደጋ ወደ አንጾኪያ መኮይ ተዛውሮ አልተመለሰም። እናም እንዲመለስ ጥረት ሲደረግ፣ አይ ማጀቴ በመሰረተ ልማት ወደኋላ የቀረች ከተማ ስለሆነች ለወረዳነት አትመጥንም ሲባል እኛ ተወላጆቿ አልምተን ወረዳውን እናስመልሳለን በሚል የበኩሌን ለማድረግ ነው የሰራሁት፤ በእግዚአብሔር ቸርነት እሱ ተርፏል። ከዚያ ይልቅ የኔ ቦታ የኔ መኖሪያ ሁሉ ነገሬ ያለው አጣዬ ነው። አጣዬ ላይ እኮ ከፌስታል ወደ ሻንጣ፣ ከሻንጣ ወደ ቁምሳጥን፣ ያደግኩበት፣ አምስት ልጆቼን ያለ አባት ያሳደግኩበት የዳርኩበት የኳልኩበትና ወግ ማዕረግ ያየሁበት ቦታ ነው። ይህ ብዙ ዓለም ያየሁበት ከተማ እንዲህ  አመድ ሆኖ ሳይ ያመኛል - ይቆጨኛል። ቅድም አንቺ እንዳልሽው እንኳን እኔ ከእነቤተሰቤ ሳልሞት ተረፍኩ።
ወ/ሮ ዘነቡ፤ በመጨረሻ ምን ማለት ይፈልጋሉ?
እኔ እንግዲህ መንግስት የእስካሁን መከራችንን አይቶ በቃ ብሎን ጉዳታችንን፣ ስብራታችንን ቁስላችንን አይቶና ርህራሄ አድርጎልን መልሶ ቢያቋቁመን ነው የምመኘው። የአጣዬ፣ የካራ ቆሬና የማጀቴ ህዝብ ጩኸትና ተማፅኖ ይኸው ነው። ምክንያቱም ከራሱ አልፎ ለብዙዎች የስራ ዕድል የፈጠረው፣ ነገ እለወጣሁ ብሎ እድሜ ልኩን ሲለፋና ንብረት ሲያፈራ የነበረው፣ ልጅ ወልዶና አስተምሮ አገር ተረካቢ ትውልድ ሲያዘጋጅ የነበረው ጀግናው፣ አምራቹ፣ ነጋዴው የአጣዬ፣ የካራቆሬና የማጀቴ ህዝብ ዛሬ ባዶ እጁን ቀርቶ፣ ሀብት ንብረቱን በእሳት፤ ቤተሰቡን በጥይት ተነጥቆ የተረፈው ህይወቱን ይዞ በደብረ ሲና፣ በመንዝ፣ በደብረ ብርሃን በአዲስ አበባ ተበታትኖ፣ የሰው እጅ እያየና እርዳታ እየጠበቀ በሚያሳዝን ሁኔታ ነው ያለው። እኔም አዲስ አበባ ዘመድ ጋር ተጠግቼ ነው ከእነልጆቼ ያለሁት። ይህ ሁሉ ህዝብ መልሶ  ካልተቋቋመ  ምን ሊሆን እንደሚችል አይገባኝም፤ እናም መንግስት ይድረስልን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደን ነው የምለው።


Read 1732 times