Monday, 10 May 2021 00:00

መምረጥ መብት ወይስ ግዴታ?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የመምረጥ መብት እ.ኤ.አ በ1948 በወጣው ሁሉን አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) (አንቀጽ 21)፣ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን (ICCPR) (አንቀጽ 25) እና በሌሎች ድንጋጌዎች ላይ መሰረታዊ ከሆኑ ዴሞክራሳዊ መብቶች አንዱ እንደሆነ በግልጽ ሰፍሯል፡፡ በአንድ በኩል እነዚህን ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው መሆኑ፣ በሌላ በኩል በሃገሪቷ ህገ-መንግስት አንቀፅ 9/4/ ስር “ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው አለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ የህግ አካል ናቸው” ተብሎ መደንገጉን ስናሰላ ሃገሪቷ የመምረጥ መብትን መሰረታዊ የሆነ ዴሞክራሳዊ መብት አድርጋ እንደተቀበለች እንረዳለን፡፡ በተጨማሪም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት እና በአዋጅ 1162/11፤ ማንኛውም ምርጫ ሁሉን አቀፍ፣ ቀጥተኛ፣ በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ መራጩ ፈቃዱን በነፃነት የሚገልፅበትና ያለምንም ልዩነት በሚደረግ ሕዝባዊ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡  አንድ ሰው ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ ሆኖ፣ ዕድሜው 18 እና ከዚያ በላይ ከሆነ እንዲሁም በምርጫ ክልሉ ቢያንስ 6 ወር ከኖረ የመምረጥ መብት ይኖረዋል፡፡ ይህን መብት እንዳይጠቀም የሚያደርገው የአእምሮ ሕመም ካለበትና የመምረጥ መብቱ በሕግ የታገደ ከሆነ ብቻ ነው፡፡
ከላይ የተመለከትነውን የመምረጥ መብት ኢትዮጵያውያን ቢያንስ በአሃዝ ደረጃ አምስት ጊዜ ተጠቅመውበታል ሊባል ይችላል፤ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ደግሞ በግንቦት መገባደጃ ላይ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ምርጫ ላይ እድሜያቸው ለመምረጥ ደርሶ በምርጫው መሳተፉ የሚችሉ ዜጎች ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ መሆናቸውን ምርጫ ቦርድ በተለያየ ጊዜ የለቀቃቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ሆኖም በምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ካርድ በተጠበቀው መልኩ በመራጮች እየተወሰደ አለመሆኑን ቦርዱ በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ ይህ ለምን ሆነ ለሚለው ጥያቄ የራሱ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም፤ ሀገሪቷ ያለችበት የፀጥታ ችግር፣ የዜጎች በፖለቲከኞች ተስፋ መቁረጥ፣ መራጮች የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ የተደረገው ቅስቀሳ በቂ አለመሆን፣ የዕጩዎች መታሰርና የመሳሰሉትን በምክንያትነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህ ሁኔታ  ታዲያ አንድ ጥያቄ እንዳነሳ አድርጎኛል፤ ይህም ‘አንድ ሰው በሕግ የተሰጠውን የመምረጥ መብት በግዴታ እንዲጠቀም ማድረግ ይገባል ወይስ ውሳኔው ለግለሰቡ መተው አለበት? የሚል።
ከላይ ያነሳሁትን ጥያቄ በተመለከተ ሁለት ዓይነት እሳቤዎች አሉ፡፡ አንደኛው ‘የመምረጥ መብትን መጠቀም በራሱ መብት ሳይሆን የዜግነት ግዴታ ነው’ የሚል ሲሆን ሌላኛው ‘መምረጥ መብት እንጂ ግዴታ አይደለም’ የሚል ነው፡፡ በእነዚህ እሳቤዎች  ላይ ከሚነሱ መከራከሪያዎች መካከል የተወሰኑትን በመቀጠል የምንመለከት ይሆናል፡፡
የመጀመሪያው እሳቤ መምረጥ ግዴታ መሆን አለበት (Compulsory voting) የሚል ነው፡፡ የዚህ እሳቤ መርህ አንድ ዜጋ የምርጫ ካርድ መውሰድ እንዲሁም በምርጫ ቀን ድምጹን ላሻው ተመራጭ መስጠት ሕጋዊ ግዴታው ሊሆን ይገባል የሚል ነው፡፡ ይህ እሳቤ መልኩ መታየት ጀመረ የሚባለው በጥንታዊቷ ግሪክ ቢሆንም፣ በተለይ በመካከለኛው ዘመን በፈረንሳይና በስዊዘርላንድ ይበልጥ እያደገ እንደመጣ የተለያዩ ድርሳኖች ያሳያሉ። በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጠናቀቂያና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ደግሞ እሳቤው ያደገበት ወቅት ነበር፡፡ እንደ ሃገር መምረጥን ግዴታ በማድረግ አዋጅ ያወጣች ቀዳሚዋ ሃገር ቤልጅየም ናት፤ እ.ኤ.አ በ1983፡፡ ከዛን በኋላ በተለይ ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት መገባዳጃ በኋላ አርጀንቲና፣ ኒዘርላንድ፣ አውስትራሊያ፣ ግሪክና ኦስትሪያ የመምረጥ መብትን ግዴታ በማድረግ የምርጫ ሥርዓታቸው አንድ አካል በማድረግ ስማቸው ይነሳል፡፡
መምረጥ ግዴታ መሆን አለበት ብለው የሚሟገቱ አካላት ለክርክራቸው መሰረት አድርገው ከሚያቀርቡት መከራከሪያዎች መካከል ዋነኞቹን ለማሳያነት ያህል  እጅግ አጠር ባለ መልኩ ላስቀምጥ፡-
1፡- በተለይ ከ19ኛው ክ/ዘመን በኋላ  በምርጫ ላይ የሚሳተፉ ዜጎች በቁጥር እያነሱ መጥተዋል፡፡ በተለይ በምርጫ ላይ ለመሳተፍ እድሜያቸው የደረሱ ወጣቶች ይህን መብታቸውን የመጠቀም ጉዳይ እጅግ አስጊ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ለዴሞክራሲ ትልቁ ፈተና ነው፡፡ በምርጫ ወቅት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መራጮች ብቻ ተሳታፊ ከሆኑ ዜጎች አባል በሆኑበት ማኅበረሰብ ላይ የሚኖራቸው ድርሻ አነስተኛ ይሆናል፤ የዚህ ውጤት በበኩሉ በተለያየ መልኩ አድልዎች እንዲፈጠሩ እድል ይፈጥራል፡፡ በሌላ አባባል፣ ተመራጮቹ በምርጫ ላይ የተሳተፉ አባላትን ፍላጎት ብቻ በሟማላት ላይ ስለሚያተኩሩ ዜጎች የሚገባቸውን ጥቅም ሊያገኙ የሚችሉበት በር መጥበቡ አይቀርም፡፡ ለዚህ ችግር ጥሩ መፍትሄ የሚሆነው ታዲያ ዜጎች በምርጫ ላይ በግዴታ እንዲሳተፉ ማድረግ ነው፡፡
2፡- መምረጥን ግዴታ ማድረግ በሕግ መምረጥ የሚችሉ ዜጎች በሙሉ ያለ ምንም መገለል በምርጫ ሂደቱ ላይ እንዲሳተፉ እድሉን ይሰጣል፡፡ ይህም ማለት መምረጥ የዜግነት ግዴታ ከሆነ በፖለቲካ ምህዳሩ ላይ ያለውን ኢ-እኩልነት ማደብዘዝ ይቻላል፡፡ የተማረ ካልተማረ፣ ሀብታምና ደሃ፣ ወጣት አሊያ በእድሜ የገፋ ሳይል በሕግ መምረጥ የሚችል ዜጋ በሙሉ በፖለቲካ ዑደቱ ላይ ተሳታፊ ያደርገዋል፡፡
3፡- አንድ የፖለቲካ ሥርዓት ሕጋዊ መሰረት እንዲኖረው የምስረታ ሂደቱ ሕጋዊ መልክ ሊኖረው ይገባል፡፡ በተለይ የውክልና ዲሞክራሲ ተግባራዊ በሚደረግባቸው ሀገራት የምርጫ ሥርዓቱ የሚካሄድበት ዑደት ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባበት ዋነኛው ምክንያት፣ ህዝቡን ወክለው በስልጣን ቦታ ላይ የሚቀመጡ ግለሰቦች ሕጋዊነት ምንጭ ምርጫ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም በምርጫ ሂደቱ ላይ የሚሳተፉ ዜጎች በቁጥር በበረከቱ ቁጥር መንግስት የሚሆነው ተመራጭ ፓርቲ አሊያም ግለሰብ ሕጋዊነት በዛው መጠን ይጠነክራል፡፡
4፡- መምረጥን ግዴታ በማድረግ ዜጎች ስለ ፖለቲካ የሚኖራቸው እውቀትና መረዳትን የጎለበተ ማድረግ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ፖለቲካዊ ውይይቶችና ክርክሮች ይበልጥ እንዲከናወኑ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፡፡
5:- መምረጥ ግዴታ ከሆነ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በተመራጭነት የሚቀርቡ ግለሰቦች አሊያም ፓርቲዎች ከተመረጥን እንተገብረዋለን የሚሉት ፖሊሲ በአንድ ጉዳይ ላይ ያተኮረ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ ይህም ማለት መምረጥ መብት በሆነባቸው ሀገራት በምርጫ ሂደቱ ላይ የሚሳተፉ ዜጎች ከተለያዩ መመዘኛዎች አንፃር የትኞቹ እንደሆኑ በእርግጠኝነት በቀረበ መልኩ ሊገመት የሚችል በመሆኑ ተመራጪዎቹ በቅስቀሳ ወቅት ትኩረት የሚያደርጉት የመምረጥ መብታቸውን ይጠቀማሉ ብለው የሚያስቡት የማኅበረሰብ ክፍል የሚፈልገው ርዕሰ ጉዳይ ብቻ ይሆናል፡፡
6፡- በአሁኑ ወቅት በፖለቲካ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ያለውን ‘ፖፕላሪዝም’ (popularism) ለመግታት ትልቅ መሳሪያ ሆኖ ሊያገልግል ይችላል፡፡ ምክንያቱም የመራጪዎቹ ቁጥር በበዛ ቁጥር የተለያዩ እሳቤዎች የመንጸበረቅ እድል በዛው ልክ ሰፊ ይሆናል፡፡
ከላይ በምሳሌነት ካነሳነቸው በተጨማሪ መምረጥን ግዴታ ማድረግ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ እንደሚያዘነብል በመቀበል አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂየም፣ ቦሊቭያ፣ ብራዚል፣ ቺሊ፣ ሲንጋፖር፣ ቱርክ በምርጫ ስርዓታቸው ላይ አካተውታል። ታዲያ መምረጥን ግዴታ ያደረጉ ሀገራት ግዴታቸውን ባልተወጡ ዜጎቻቸው ላይ የተለያዩ አይነት ቅጣቶች ጥለው የምናገኝ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል  ፔሩ መምረጥ ያለበት ዜጋዋ ምርጫ ከተከናወነ በኋላ ለወራት ያህል መምረጡን የሚጠቁም ካርድ ካልያዘ፣ በተለይ በመንግስት ተቋማት አገልግሎት እንዳያገኝ የሚያደርግ ሕግ አላት፡፡ በቦሎቪያ ያልመረጠ ዜጋ የባንክ አገልግሎት አያገኝም፡፡ ወደ አውሮፓ ስናሻገር በቤልጂየም የመንግስት ስራን ለማግኘት በምርጫ ላይ መሳተፍ  የግድ ነው፡፡ ሌሎችም በተለያዩ መልኩ የመምረጥ ግዴታቸውን ባልተወጡ ዜጎች ላይ እስከ እስር የሚያደርስ ቅጣት ጥለው ይገኛሉ፡፡
መምረጥ መብት እንጂ ግዴታ  በፍፁም ሊሆን አይገባም የሚሉ ተከራካሪዎች በበኩላቸው ከሚያነሷቸው መከራከሪያዎች የተወሰኑትን በቀጣይ የምንመለስበት ይሆናል፡፡

Read 2685 times