Saturday, 01 September 2012 10:12

የድህረ-መለስ አስተዳደር ፖለቲካዊ ትንተና

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት የቀሩት የ2004 ዓ.ም በአስከፊነቱ ራሱን በታሪክ መዝገብ ውስጥ ለማስመዝገብ በቅቷል፡፡ ዘንድሮ አመት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተመልሶ ባልመጣ ከሚባሉት አስከፊ፣ አስቸጋሪና ፈታኝ አመታት አንዱ ነው፡፡ አመቱ ልክ እንደ ልክፍተኛና እኩይ ምቀኛ፣ ክፉአይኑን የጣለው በሀገሪቱ ምርጥ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ይህ አመት ሞት የተሰኘውን ጨካኝ ጋሻ ጃግሬውን አስከትሎ፣ ቀደም ብሎ ታዋቂውን የስነጽሑፍ ሰው ስብሐት ለአብ ገብረእግዚአብሔርን በመውሰድ አሀዱ ያለውን ክፉ ጀብዱውን ደራሲና ተርጓሚ ማሞ ውድነህን በማስከተል ክልኤቱ ካለ በኋላ ዝነኛውን የስነጥበብ ሰው ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን በመንጠቅ ሰለስቱ ብሏል፡፡ በዚህ በበቃው እያልን ብንመኝም ቅሉ አጅሬ ሞት ሌላ ምኞት ነበረውና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መሪና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመኖቿ መንፈሳዊ አባት የነበሩትን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያን በመንጠቅ በከፍተኛ ሀዘን አንገታችንን አስደፋን፡፡

አሁንም ግን በቃችሁ አላለንም፡፡ ሀዘኑ በቅጡ ሳይወጣልንና ገና እንባችን ከጉንጫችን ላይ እንኳ ሳይደርቅ ክፉው ሞት ይግረማችሁ ብሎ ያልታሰቡትንና ያልተገመቱትን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የመሰለ መሪ ዘርፎ አንጀታችንን በእጥፉ ቆረጠው፡፡ ኢትዮጵያን ከዳር ዳር የሀዘን ማቅ አለበሳት፡፡ መላ ኢትዮጵያውያንንም ከህፃን እስከ አዋቂ፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ደረት እያስደቃ በእንባ አራጫቸው፡፡

አሁን ጊዜው በእርግጥም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን መልካም ቀን አይደለም፡፡ የወደቀባቸው መከራ ከባድና የሚያስጨንቅ ነው፡፡ እናም የ2004 ዓ.ም ቀናቶች እስከወዲያኛው እስኪያልቁ ድረስ ዳግመኛ መልሶ አያምጥብን ያሰኛል፡፡

ኢትዮጵያውያን “ዞሮ ዞሮ ከቤት፣ ኖሮ ኖሮ ከመሬት” የሚል የተለመደ አባባል አላቸው፡፡ ነገሩ ሞት ለማንም የማይቀር የተፈጥሮ ህግ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ እርግጥ ነው ሞት ተለይቶ የታወቀ መልክና ቁመና የለውም፡፡ ነገር ግን ከሞትም ሞት አለ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ለኢትዮጵያና በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከሞትም የበለጠ ሞት ነው፡፡

የተለያዩ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የየራሳቸውን አተያይ መሰረት በማድረግ በተለያየ ሁኔታ ገልፀዋቸዋል፡፡ እኔም ከራሴ አተያይ ብቻ በመነሳት የምገልፃቸው ከዚህ እንደሚከተለው አድርጌ ነው፡፡

አይሁዶች “ጫማውን አድርገህ አንድ ማይል እንኳ ሳትጓዝ ሰውየውን አትገምት ወይም በሰውየው ላይ አትፍረድ” የሚል አሪፍ አባባል አላቸው፡፡ ለእኔ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በችሎታቸው፣ በእውቀታቸውና በስራቸው የወዳጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን የእርሳቸውን ጫማ አድርገው አንድ ማይል እንኳ ሳይጓዙ የገመቷቸውንና የፈረዱባቸውን ሰዎች ልብና ቀል መማረክ የቻሉ፣ ለአይነት በኢትዮጵያ የተፈጠሩ መሪ ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፤ በሀገራቸው ውስጥ ለሚሊዮኖች የብሩህ ዘመን የተስፋ ብርሃን ያበሩና እንደ ሰው የመቆጠርን ልዩ ፀጋ መልሰው ያጐናፀፉ ልበ ብርሃን መሪ ነበሩ፡፡ በውጭ ሀገር ደግሞ የኢትዮጵያን የተሰበረ ስም ያደሱ፤ የተናቀውን ክብሯንም ከፍ አድርገው ደረታችንን ያስነፉ መሪ ነበሩ፡፡

በዚህም የተነሳ በውጪ የሚኖሩ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን (መድረሻቸውን ሳያውቁ ወደ ማዕበሉ የሚቀዝፉትን ነውረኛ የዲያስፖራ ፖለቲከኞችን ሳይጨምር) በኩራት ልባቸው እንዲሞላና አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ ያደረጉ አኩሪ መሪ ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፤ ኢትዮጵያ በፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ውስጥ ለአለም ጥቁርና ግፉአን ህዝቦች አንፀባራቂ የነፃነት ኮከብና የትግል አርአያ እንደነበረችው ሁሉ፣ በፀረ ድህነትና ራስን የመቻል ትግል ውስጥ ደግሞ የእድገትና የብልጽግና አርአያ ሆና በብዙዎች ዘንድ እንድትታይ ያስቻሉ አሪፍ መሪ ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፤ ኢትዮጵያ ሰላም ላጡ ህዝቦች የቁርጥ ቀን የሰላም ዋስትናቸው እንድትሆንና ዘመን የማይሽረው ባለ ውለታና ባለ ታላቅ ክብር ሀገር እንድትሆን አድርገዋል፡፡ በተለያዩ አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተወካይ እንድትሆን ያደረጉ፣ አፍሪካን በመወከልም ዋስ ጠበቃ በመሆን ከረጅም አመታት ወዲህ ታይቶ ባልታወቀ ሁኔታ ኢትዮጵያ ስሟ የላቀና የተከበረ እንዲሆን ያስቻሉ፣ የበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ህዝቦች አፍ አውጥተው በግልጽ “የእኛ መሪ በሆኑልን” ብለው የተመኟቸው ድንቅና ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለእኔ እንዲህ አይነት መሪ ነበሩ፡፡ እኒህ ለአይነት ብቻ የተፈጠሩ ድንቅ መሪ፤ ዛሬ በህይወት አብረውን አይገኙም፡፡ እኒህን መሪ ባሰብኳቸው ቁጥር ልዩ ስሜት የሚፈጥሩብኝ በርካታ የግል ትዝታዎች ስላሉኝ በህልፈታቸው የተሠማኝን ሀዘን ዝቅ ብዬ እጅ በመንሳት እሰናበታቸዋለሁ፡፡

እኒህ ታላቅና ባለታሪክ መሪ በክብር ተሸኝተው ካረፉ በኋላ ቀጣዩ ስራ አንድ ነው፡፡ ሀዘኑን ዋጥ አድርጐ በመያዝ አንጀትን ጠበቅ አድርጐ ወደ ስራ መሠማራት ብቻ፡፡

ከእንግዲህ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ቀጣዩ ዘመን የድህረ መለስ ዘመን ነው፡፡ ይህን አዲስ ዘመን የተረከበው ኢህአዴግም የመጀመሪያ ስራውና ዋና ጉዳዩ የስልጣን ርክክቡን በተመለከተ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መታመም ወሬ ከተወራበት ጊዜ ጀምሮ በየግላቸው የተሰማቸውን ስጋትና መላምቶች በከፍተኛ ሁኔታ ሲገልፁ ከርመዋል፡፡

በተለይ የውጭ ሀገር የፖለቲካ ተንታኞችና የዲያስፖራ ፖለቲከኞች፤ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ሞት ተከትሎ በሀገሪቱ አለመረጋጋትና ሁከት ሊፈጠር እንደሚችል በአብዛኛው አሉታዊ የሆነ ትንታኔአቸውን በላይ በላዩ ሲያቀርቡ ባጅተዋል፡፡ እነዚህ ተንታኞች፤ ለአሉታዊ መላምታቸው እንደ ዋነኛ መሟገቻ አድርገው ያቀረቡት በአብዛኛው ኢህአዴግን በመሠረቱት አራት ተጣማሪ ድርጅቶች መካከል ስር የሰደደ አለመግባባትና የስልጣን ሽኩቻ ስላለ ይሄው ጉዳይ አብጦ ይፈነዳል የሚል ነበር፡፡ ለዲያስፖራ ፖለቲከኞች ግን የመላምታቸው መነሻ ድርጅቱን ኢህአዴግንና መሪውን መለስ ዜናዊን አንድ አድርጐ በማየት መሪው መለስ ከሞቱ፣ ኢህአዴግም አብሮ ይሞታል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ስልጣኑን ለመያዝ የሚደረግ ደም አፋሳሽ ሁከትና ግጭት ይነሳል የሚለው ነው፡፡

የጉዳዩ ግንባር ቀደም ባለቤት የሆነው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ግን ለእነዚህ መላምቶችና “የፖለቲካ ትንታኔዎች” የሰጠው መልስ አጭርና ቀላል ነው፡፡ “መሠረተ ቢስ ሟርት ነው” የሚል፡፡ ጉዳዩን በበለጠ እንዲያብራሩ የተጠየቁት የመንግስት ባለስልጣንም፤ የስልጣን ርክክቡ ጉዳይ በድርጅቱ ውስጥ ቀደም ብሎ እልባት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን፣ ህጋዊ ሂደቱ በፓርላማ እስኪከናወን ድረስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜአዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሀገሪቱን እየመሩ እንደሚገኙ፣ የድርጅቱ የወቅቱ ዋነኛ ጉዳይም ሟቹን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በክብር ማሳረፍ እንጂ የፓርላማው ጉዳይ ከቀብሩ በኋላ ካሉት ቀኖች በአንዱ ሊፈፀም የሚችል ምንም አይነት አጣዳፊነት የሌለው ጉዳም መሆኑን ነው፡፡

ድርጅቱ ኢህአዴግ በተግባር እያደረገው ያለውም ይህንኑ ነው፡፡

ይህ የኢህአዴግ ድርጊት ከላይ ለተጠቀሰው መላምትና የፖለቲካ ትንታኔ በማያዳግም መልኩ በተግባር የተሠጠ መልስ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የጤና እክል አጋጥሟቸው ከህዝባቸው አይን ከራቁበት ቀን ጀምሮ በኢህአዴግ ውስጥ ይደርሳል የተባለው የስልጣን ሽኩቻና እሱን ተከትሎ ይነሳል ተብሎ በበርካቶች ዘንድ የተገመተውና የተተነበየው ደም አፋሳሽ ግጭትና ሁከት ኢህአዴግ እንዳለው “ከባዶና መሠረተ ቢስ ሟርትነት” ሊዘል አልቻለም፡፡ እንደተባለውም ህጋዊ ስነስርአቱ ከቀብሩ በኋላ ለፓርላማው ቀርቦ እስኪከናወን ድረስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሀገሪቱን በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህ ፖለቲካዊ ሂደት አሁን ባለበት ደረጃም እራሱ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የራሱን አዎንታዊ አሻራ ማሳረፍ የቻለና ልዩ ምዕራፍ መክፈት የቻለ ጉልህ ሂደት ነው፡፡ ለምን ቢባል ሂደት በዘመናዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለአንዳች የፖለቲካ እገጭ እጓና ደም መፋሰስ በሰላማዊ መንገድ የስልጣን ሸግግር የተካሄደበት ፈር ቀዳጅ ሂደት በመሆኑ ነው፡፡

ይህን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተከትሎ የሚቀርበው መሠረታዊ ጥያቄ ደግሞ እንዲህ  የአዲሱ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ቁጥር አንድና አጣዳፊው ስራ ምንድን ነው? የሚል ይሆናል፡፡

ለዚህ መሠረታዊ ጥያቄ የሚቀርበው መልስ ደግሞ ሌላ ሳይሆን መለስ ከማረፋቸው በፊት የነበረውን ሁኔታ ማስቀጠልና ቁጥጥሩን ማረጋገጥ “Business continuity and control” ነው፡፡ ይህ የቅድሚያ እርምጃ በኢትዮጵያና በኢህአዴግ ብቻ የሚደረግ ሳይሆን ያለ ፖሊሲ ለውጥ አመራሮቻቸውን በሚቀይሩ በስልጣን ላይ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ የሚከወን ፖለቲካዊ እርምጃ ነው፡፡

ከላይ ቀደም ተብሎ እንደተጠቀሰው ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከዚህ አለም በሞት መለየት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል ብለው በርካቶች ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የዲያስፓራ ፖለቲከኞችና እነርሱንም ተከትለው እንደ International Crisis Group ያሉ ተቋማት የሽግግር መንግስት እንዲመሠረት በከፍተኛ ሁኔታ ወትውተዋል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህ ሁለት ሀሳቦች ከባዶ የግል ስሜትና ውትወታ በስተቀር በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ጨርሶ ያልተመሠረቱ፤ የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ለአመል ታህል እንኳ ከግንዛቤ ውስጥ ያላካተቱ ቀሽም ግምቶች ናቸው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሞት መለየት ለሃያ አንድ አመታት ሲመሩት በነበረው ድርጅታቸው በኢህአዴግ ውስጥ የፈጠረው ክፍተት የአንድ መሪ እንጂ የፖሊሲ አይደለም፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው ኢህአዴግ፤ መለስ ዜናዊ የሌሉበት ኢህአዴግ እንጂ የመለስን ሞት ተከትሎ የፖሊሲ ለውጥ ያደረገ ኢህአዴግ አይደለም፡፡ የመለስን ሞት ተከትሎ ህዝቡ ለኢህአዴግ ያቀረበው ጥያቄና ከፍተኛ አመራሮቹ በተደጋጋሚ ያረጋገጡት ጉዳይም መለስ ያስጀመሩት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ከመቸውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ እንዲቀጥሉ ብቻ ነው፡፡

ይህ ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳየው እውነታ አንድ ነው፡፡ በአጭርም ሆነ በመካከለኛ ጊዜ በአዲሱ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ አስተዳደር የሚደረግ የውስጥም ሆነ የውጭ የፖሊሲ ለውጥ አይኖርም፡፡ በሀገር ውስጥ የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎች በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ መሠረት መከናወናቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በውጭም በኩል ሀገሪቱ የገነባችውን አለማቀፋዊ ተሰሚነትና የክብር ቦታ ለማስጠበቅ ከአለም አቀፍ አጋሮቿ ጋር ያላትን የጠበቀ ወዳጅነትና እያደገ የመጣውን የልማት እርዳታ ላለማጣት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተጀመሩና ሲካሄዱ የነበሩ የዲፕሎማሲ፣ የሰላም ማስጠበቅና የሽምግልና እንቅስቃሴዎች ሳይቋረጡ መቀጠላቸውም ብዙ ማሰብና መመራመር የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡

የውጭ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ መቀጠል አለመቀጠሉን አፍን ሞልቶ መናገር የማይቻለው አንድ ጉዳይ ቢኖር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አፍሪካን በመወከል ያደርጉት የነበረው የአካባቢ ጥበቃ አለም አቀፍ ድርድሮች ናቸው፡፡ ይህ ጉዳይ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የግል እውቀትና በአለም አቀፍ መድረክ ላይ የመደራደር ብቃትን መሠረት አድርጐ ሲካሄድ የነበረ በመሆኑ እርሳቸው ትተውት የሄዱትን ክፍተት እከሌ ሊሞላው ይችላል ብሎ ለመናገር በእርግጥም አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡

እንግዲህ የአዲሱ አስተዳደር የቅድሚያ ትኩረት ምን እንደሆነና አዳዲስ የፖሊሲ ለውጥ እንደማያደርግ ከተረዳን፣ ትኩረታችንን በአዲሱ የድህረ መለስ አስተዳደር ላይ እናድርግና ከዚህ የሚከተለውን ጥያቄ እናቅርብ፡፡ ለመሆኑ አዲሱ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ማን ናቸው;

ስለ አዲሱ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ስናነሳ ፈጽሞ ልንዘነጋ የማንችለው በሀገሪቱ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰላማዊ ሁኔታ የመሪነት ስልጣን የጨበጡ መሪ መሆናቸውን ነው፡፡ አቶ ሀይለማርያም የፕሮቴስታንት ክርስቲያን እምነት ተከታይ የሆኑና ከደቡብ ክልል የተገኙ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አቶ ሃይለማርያም በኢህአዴግ ታሪክ ውስጥ በትጥቅ ትግሉ ውስጥ ያልተካፈሉ የመጀመሪያው የኢህአዴግ መሪ የሆኑ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡

ስለ ሰውየው ሃይለማርያም ደሳለኝ ካነሳን አይቀር ወጋችን የሚጀምረው በ1957 ዓ.ም ሀምሌ 12 ቀን ከተወለዱበት የደቡብ ክልል የወላይታ ዞን ነው፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአካባቢያቸው ባሉ ትምህርት ቤቶች ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ፋካልቲ በሲቪል ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ፊንላንድ ውስጥ በሚገኘው የቴምፕር የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሳኒቴሽን ምህንድስና በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ ተመርቀዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው እንደወጡ የመንግስት ስራን አንድ ብለው የጀመሩት አሁን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሆነው ቀደም ብሎ ግን የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እየተባለ ይጠራ በነበረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ መምህርና የተቋሙ ዲን በመሆን ነበር፡፡ በዚህ ተቋም ውስጥ ያገለግሉ በነበረበት ወቅትም በመምህርነትና በተቋሙ መሪነት ያላቸውን ከፍተኛ ችሎታ ማስመስከር እንደቻሉ ተደጋግሞ ይነገርላቸዋል፡፡

ስለፖለቲከኛው ሀይለማርያም ደሳለኝ እንናገር ከተባለም ታሪካቸው የሚጀምረው ኢህአዴግን ከመሠረቱት አራት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ከሆነውና የደቡብ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደህዴን) ከተሰኘው የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ይህን ድርጅት ከቀድሞው ሊቀመንበር ከአቶ አባተ ኪሾ በመረከብ እስካሁን ድረስ እየመሩት ይገኛሉ፡፡

በፖለቲካው መድረክ የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጫንቃ ከባድና ወሳኝ ሃላፊነቶችንመ መሸከም የጀመረው በፓርቲ መሠሪነት ብቻ አልነበረም፡፡ እናሳ? ከዚህ የቀጠለው የፖለቲካ ህይወታቸው ምን ይመስላል? ለመሆኑ በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እግር ልክ መሆን ይችላሉን? የወደፊት ተግዳሮቶቻቸውስ ምን አይነት ይሆኑ; የሳምንት ሰው ይበለን፡፡

 

 

Read 3965 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 10:20