Saturday, 15 May 2021 14:27

በአጣዬና አካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች የቤት መስሪያ ቁሳቁሶች ማሰባሰብ ተጀመረ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   ግብአት ማሰባሰቡ እስከ ግንቦት 30 ይቀጥላል ተብሏል
                 
              የሸዋ ልማትና ሰላም ማህበር (ሸዋ ሰማ) ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ በአጣዬና በአካባቢው በደረሰ ጥቃት ቤት ንብረታቸውን አጥተው በየአካባቢው ለተበታተኑ ዜጎች የቤት መስሪያ የሚሆን የግንባታ ግብአቶችን ማሰባሰብ መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ማህበሩ ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ በጣይቱ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው በጥቃቱ ከአጣዬ፣ ከሸዋ ሮቢት፣ ከካራ ቆሬና ከሌሎች አካባቢዎች በጦርነት ተፈናቅለው ያለ ቤት ንብረት ለቀሩ ከ200 ሺህ በላይ ወገኖች ለቤት መስሪያ የሚውል ቆርቆሮ፣አሸዋ፣ ሲሚንቶ ምስማርና ሌሎችንም የግንባታ እቃዎች ከግንቦት 2 ጀምሮ በጣይቱ ሆቴል ግቢ ማሰባሰብ መጀመሩን  የማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው ተናግረዋል፡፡ ማህበሩ የጉዳቱ ሰላባ የሆኑት ወገኖችን በአስቸኳይ ለመደገፍ ባደረገው ጥሪ፤ ከሀገር ውስጥና ከውጭ  ከ1.5 ሚ ብር በላይ ገቢ መሰባሰቡን የገለፁት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤  ከዚህ ገቢ ውስጥ 750 ሺ ብር ወጪ በማድረግ የእለት ደራሽ የሆኑ ምግብ ነክ፡- ማለትም (ዱቄት፣መኮረኒ፣ፓስታና ሌሎች) ቁሳቁሶችን  በመግዛት በመሃል ሜዳ፣ፈረድውሃ፣በርግቢ፡- በካራቆሬ፣ ቆሬሜዳ፣በካራለጎማና አጣዬ አካባቢዎች እንደ ተጎጂዎቹ ብዛትና አይነት ማከፋፈሉን  አስታውቋል። ቀሪው ከ750 ሺህ ብር በላይ ደግሞ የሚችለውን ያህል የግንባታ እቃ ተገዝቶ፣ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ስራ ይውላል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው፤ እስካሁንም በዓይነት የመጡ አልባሳት መኮረኒ፣ዱቄትና ሌሎች 1 ሚ 422 ሺህ 87 ብር የሚገመቱ የአይነት ልገሳዎች ለተጎጂዎች ማድረሱን ገልፀዋል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ዕለትም 3 መኪኖች የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ለተረጂዎች ለማድረስ ከጣይቱ ሆቴል መንቀሳቀሳቸውን ተናግረዋል፡፡
የማህበሩ የበላይ ጠባቂና ምክትል የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ  አቶ ተሾመ አየለ (ባላገሩ) በበኩላቸው፤ “ደራሽ ለአጣዬ” በሚል መርሀ ለአንድ ሳምንት የዘለቀ የሀብት ማሰባሰብ ዘመቻ ማድረጋቸውን በራሳቸው፣ በባልደረባቸው ገነቱ ደገፋና በጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ግሩም ስም የሚንቀሳቀስ አካውንት በንግድ ባንክ፣ በአቢሲኒያና አባይ ባንክ ከፍተው እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህ በአንድ ሳምንት 5 ሚ 150 ሺህ ብር ማሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡ ይህም ገንዘብ በአግባቡ ለተረጂዎች ስለመድረሱ የሚያመለክት የባንክ ስቴትመንት በዕለቱ አቅርበው፤ ከግንቦት 2 ቀን ጀምሮ ይህ አካውንት እንደማይሰራና ገንዘብ በማህበሩ አካውንት ብቻ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
እስከ ግንቦት 30 የሚዘልቅ የግንባታ ግብአቶችን ማሰባሰብ ዘመቻ የጀመረው የሸዋ ሰላምና ልማት  ማህበር ከግንባታ ቁሳቁሱ በተጨማሪ በገንዘብ መደገፍ ለሚፈልጉ ዲያስፖራ ወገኖች ማህበሩ እውቅና በሰጣቸው አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ አቶ አብርሀም ታመነና አቶ ሀብታሙ ታፈሰ በተባሉት 3 ግለሰቦች ሥም “go fund me” አካውንት መከፈቱም ተገልጿል።

Read 976 times