Saturday, 15 May 2021 14:33

ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሰብልን ከወፎች የሚከላከል አዲስ ቴክኖሎጂ መጠቀም ጀመረ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

  ሰብልን ከወፎች የሚከላከሉ የሰለጠኑ ጭልፊቶችንም አስመጥቷል
                        
          ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሰብልን ከወፎች ለመከላከል የሚያስችልና በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው የተባለውን አዲስ ቴክኖሎጂ፤ መጠቀም መጀመሩን ይፋ አደረገ። ቴክኖሎጂው ድሮን (ሰው ሰራሽ በራሪ ወፍ) እና ሰብልን ከወፎች በመከላከል ተግባር ላይ የሰለጠኑ ጭልፊቶችን የሚያካትት ነው።
ቢጂአይ ኢትዮጵያ ዝዋይ በሚገኘው የወይን እርሻው ላይ ተግባራዊ  ማድረግ የጀመረው ይኸው ቴክኖሎጂ ቀደም ሲል በባህላዊ መንገድ ጅራፍ በማስጮህ፣ ጭስ በማጨስና ወንጭፍ በመጠቀም የወይን እርሻውን ከወፎች ለመጠበቅ ያደርግ የነበረውን አስቸጋሪ ትግል የሚያስቀር ነው ተብሏል። ቴክኖሎጂው ከፈረንሳይ አገር የመጣ ሲሆን ሰው ሰራሽ በራሪ ወፍ /ድሮኖቹን/ የሚያበሩ ባለሙያዎችም አብረው መምጣታቸውንና የሚተኳቸው ኢትዮጵያዊ ባለሙያዎችንም በማሰልጠን ላይ እንደሚገኙ የቢጂአይ ኢትዮጵያ የኮሚኒኬሽንና ሲኤስአር ማናጀር አቶ ገብረ ስላሴ ስፍር ገልፀዋል።
ወፎች በተፈጥሯቸው ነገሮችን ቶሎ የመላመድ ባህርይ እንዳላቸው የገለጹት አቶ ገብረሥላሴ፤ ይህንን ችግር ለማስወገድም ወፎችን ከሰብል ላይ በማባረር የሰለጠኑ አራት ተፈጥሯዊ የወፍ ዝርያዎችን አስመጥቶ ዝዋይ በሚገኘው የወይን እርሻው ላይ መጠቀም መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሰሞኑን ዝዋይ የሚገኘውን የካስቴል ወይን እርሻውንና አዲሱን ቴክኖሎጂ ለጋዜጠኞች ባስጎበኘበት ወቅት የድርጅቱ የዝዋይ ቅርንጫፍ ስራ አስኪጅ አቶ ጫላ ዲሮ እንደተናገሩት፤ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ከቢራ ፋብሪካዎቹ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በዓለም የወይን ምርት እንድትታወቅ ያደረጋትን ካስቴል ወይን ፋብሪካ አቋቁሞ፣ ዘመናዊ የወይን አጠማመቅ ዘዴን በመጠቀ፣ ከ12 ዓይነት በላይ የወይን ምርቶችን እያመረተ ይገኛል። ከእነዚህ የወይን ምርቶቹ መካከል ሶስቱ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የዓለም የወይን ፌስቲቫል ላይ 3 የወርቅ ሜዳሊያዎችን  አግኝቷል።  ይህን የወይን ምርት ጥራት ጠብቆ ለማቆየትና የጥራት ደረጃቸው ከፍ ያሉ ምርቶችን በማምረት ወደ ውጪ ለመላክ በወይን እርሻው ላይ የሚታዩት የምርት ጥራቱን የሚቀንሱትን ወፎችን የአካባቢውን ተፈጥሯዊ ሁኔታ በማይለውጥ መንገድ ለመከላከል የሚያስችል ቴክሎጂን መጠቀም መጀመራቸውን ተናግረዋል።
የኮሙኒኬሽንና ሲኤስአር ማናጀሩ አቶ ገብረሥላሴ በበኩላቸው በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው የተባለው ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ፤ የወይን እርሻውን ከወፎች በመከላከሉ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል። ድርጅቱ በዝዋይ ላለው የወይን እርሻ በቂ የሆኑ ሰው ሰራሽ ወፎችን (ድሮኖችን) እና ወፎችን በማባረር የሰለጠኑ ጭልፊቶችን ከፈረንሳይ አገር በከፍተኛ ዋጋ አስመጥቶ ስራ መጀመሩንም ሃላፊው ጠቁመዋል።
ከአዲስ አበባ በ163 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ዝዋይ ከተማ ውስጥ በ2007 ዓ.ም የተመሰረተው ካስቴል የወይን ፋብሪካ፤ ከ12 ዓይነት በላይ የተለያየ ጣዕም ያላቸውን የወይን ምርቶቹ እያመረተ ለገበያ ያቀርባል።

Read 11550 times