Print this page
Saturday, 15 May 2021 14:55

የኦሮሚያ ክልል የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ሪፖርት አጣጣለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

  የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የሚፈፀመውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ ያወጣው ሪፖርት ወቅቱን ያልጠበቀና በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው ሲል የኦሮሚያ ክልለ አጣጣለ፡፡ ኮሚሽኑ ያወጣው መረጃ የዘገየና እርምት የተወሰደበት ነው ብሏል፡፡
ኮሚሽኑ ሰሞኑን ያወጣውንና በኦሮሚያ ክልል አሳሳቢ የሆነ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መፈጸሙን የሚያመለተውን ሪፖርቱን የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ግዛቸው ጋቢሳ ጊዜውን ያላገናዘበ ተጨባጭነት የሌለውና ወራት ባስቆጠረ ጉዳይ ላይ የተጠናከረ ሪፖርት በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡
ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የተወሰዱ እርምጃዎች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ግዛቸው፤ እነዚህን ስህተቶች ለማረምና ክፍተቶችን ለመዝጋት መሞከሩንና በተወሰኑ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ይህን ሪፖርት በዚህ ሊያወጣ የቻለበት ምክንያት ግልፅ አይደለም ብለዋል- ሃላፊው።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሰሞኑ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ በክልሉ እየተፈፀመ ያለው የሰብአዊ  መብት ጥሰት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ኮሚሽኑ በክልሉ 21 ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ምርመራ አድርጌ አገኘሁት በማለት ይፋ ያደረገው ሪፖርቱ በክልሉ ከህግ አግባብ ውጪ የሚታሰሩና የሚገደሉ ሰዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውንና ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመባቸው እንደሆነ በምርመራ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡ ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች እያከናወኑ ያሉት ተግባር  ከህግ ውጭ ነው ያለው የኮሚሽኑ ሪፖርት የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም እንዲታቀቡ አሳስቧል፡፡
በክልሉ የፍርድ ቤቶች ትዕዛዛትን አለማክበር እንደቀጠለ መሆኑን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በክልሉ በዞንና በወረዳ ደረጃ የተቋቋሙ የፀጥታ ም/ቤቶች ከሰዎች መታሰርና ከእስር መለቀቅ ጋር በተያያዘ የሚያከናውኑትን ተግባር እንዲያቆሙና የስራ ስምሪት የሚሰጧቸው የፀጥታ ኃይሎች ተገቢው ቁጥጥር እንዲደረግባቸው አሳስቧል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የኮሚሽኑ ሪፖርቱ ከአንድ ወገን በተገኘ መረጃ ላይ መሰረት ያደረገ በመሆኑ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም ማለቱን አስመልክቶ ኮሚሽኑ በሰጠው ማብራሪያ መረጃዎቹ ከእስረኞቹና ከቤተሰቦቻቸው ከተሰበሰቡት በተጨማሪ በአካላዊ ምልከታ ጭምር የተጠናቀሩ መሆናቸውን ገልጿል።

Read 11297 times