Saturday, 15 May 2021 15:01

ኤች አይ ቪ እና እርግዝና

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)


             ኤች አይ ቪ በደማቸው ወስጥ ያላባቸው  ሴቶች ማርገዝ በሚፈልጉበት ጊዜ ኤች አይ ቪ እና እርግዝናን በተመለከተ መሰረታዊ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። በእርግዝና ወቅት የተቀናጀ የፀረ ኤች አይ ቪ ሕክምናን መጠቀሙ የኤች አይ ቪ ስርጭት መጠን በግምት ከ 20%-30 % ሲሆን ይህን በከፍተኛ መጥን ይቅንሰዋል፡፡ ይህ ማብራሪያ የዶ/ር ያየህይራድ አየለ ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ነው። በዚህ እትም የምናስነብባችሁን ስለ ኤችአይቪ እና እርግዝና የሚመለከተውን መረጃ የሰጡን ዶ/ር ያየህይራድ አየለ ናቸው፡፡
የኤችአይቪ እና የእርግዝና አጠቃላይ እይታ፤
የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ወስጥ ያላባቸው ሴቶች በእርግዝና ወቅት፣ በምጥ እና በወሊድ ወቅት እንዲሁም በተወሰነ ደረጃ በጡት ማጥባት  ወቅት ወደሚወለዱት ልጅ ቫይረሱ ሊተላለፍ ይችላል። ነገር ግን በእርግዝና እና በምጥ ወቅት  እናቶች የኤች አይ ቪ መድኃ ኒቶችን የሚጠቀሙ ከሆነ ኤች አይ ቪን ወደ ሕፃኑ የማስተላለፍ አደጋን በእጅጉ ሊቀንሰው ይችላል ፡፡
ከእርግዝና በፊት እንክብካቤ፤
ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ወስጥ ያላባቸው ሴቶች ለማርገዝ ከመሞከራቸው በፊት የጽ ንስና ማህጸን ሐኪም ማነጋገር አለባቸው። አንዳንድ መድሃኒቶች በእርግዝና ወቅት ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ ቢባልም አብዛኞቹ ግን ችግር ላያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከእርግዝና በፊት ስለሚወስዱዋቸው መድሀኒቶች እና ስለቀጣዩ ሁኔታ ከሕክምና ባለሙያ ምክር ማግኘት ግድ ይላቸዋል፡፡
አንዲት እናት ኤችአይቪ ቫይረስ በደምዋ ውስጥ መኖሩ በአወላለድ ላይ የተዛቡ ነገሮችን ያስከትላል ወይንስ አያስከትልም የሚለውን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ በኤችአይቪ ቫይረስ ምክንያት ያለጊዜው መወለድ ፣ ዝቅተኛ ክብደት እና ሕይወት የሌለው ጨቅላ ሊወለድ ይችላል የሚል ግምት ለመስጠት የሚያስችሉ ምንም የጥናት ውጤት የለም፡፡ በሌላ በኩል ግን የተወሰኑ የኤች.አይ.ቪ መድኃኒቶች በእርግዝና እና በምጥ ጊዜ ሲወሰዱ ህፃኑ በኤች አይ ቪ የመያዝ እድሉን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስለት በሳይንሱ የተረጋገጠ ነው፡፡
ኤችአይቪ በደምዋ ውስጥ ያለች እናት ወሊድ፤
ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ላለባቸው ሴቶች ልጅን ለመውለድ (ማለትም፣ በምጥ ወይም በቀዶ ጥገና በሚወልዱበት ጊዜ) በእርግዝናቸው ወቅት ባላቸው የኤች አይ ቪ ቫይረስ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነው ፡፡ በአጠቃላይ ኤች አይ ቪ የማስተላለፍ እድሉ አነስተኛ ከሆነ (የኤች አይቪ ቫይረስ ጭነት ዝቅተኛ በሚሆንበት ጊዜ) ለእናት እና ለህፃን ደህንነት ሲባል በምጥ መውለድ ይመረጣል፡፡ በደማቸው ውስጥ ከፍተኛ የቫይረስ መጠን ላላቸው ሴቶች ወይም በበሽታው ለተጠቁ ደሞ በቀዶ ሕክምና ልጃቸውን ቢወልዱ (cesarean section) ይመከራል፡፡
በባለሙያዎች ውሳኔ መሰረት ተመራጭ በሆነው መንገድ ከወለዱ በኋላ በእርግዝና ወቅት የኤች አይ ቪ መድኃኒቶችን ሲወስዱ የነበሩ ሴቶች የኤች አይ ቪ መድኃኒቶችን መቀጠሉ በጤናቸው ላይ ስላለው ጥቅም ከዶክተራቸው ጋር መወያየት ይኖርባቸዋል። ከኤች አይ ቪ ጋር የተዛመደ የህክምና እንክብካቤን፣ የስነልቦናና ማህበራዊ ድጋፎችን (ከወሊድ በኋላ ለሚፈ ጠረው የድብርት ምርመራ እና የመድኃኒት ተገዢነት ድጋፍን ጨምሮ) ቀጣይ እንክብካቤ እና የድጋፍ አገልግሎቶች እናትየው የራሷንና የቤተሰብዋን ፍላጎት እንድታሟላ ሊረዳት ይችላል፡፡
ኤችአይቪ እና ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ፤
በኤች አይ ቪ ለተያዘች ሴት የእርግዝና መከላከያ ምርጫ ብዙውን ጊዜ የተወሳሰበ ስለሆነ የሚከተሉትን ጉዳዮች መመልከት ያስፈልጋል ይላሉ ዶ/ር ያየህይራድ፡፡
1) የእርግዝና መከላከያዎቹ እርግዝናን ለመከላከል ውጤታማነታቸውን፤
2) ሌሎች በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች (STIs) የመተላለፍ አደጋ፤
3) በተወሰኑ የፀረ ኤች.አይ.ቪ እና በሆርሞኖች፡ የወሊድ መከላከያ መካከል   የመድኃኒት መስተጋብር መኖሩን (drug- drug interaction)
በኤች አይ ቪ የተያዘችው እናት በጣም አነስተኛ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ጭነት (vral load) በሚኖርበት ጊዜም ቢሆን ኤች አይ ቪ ሊተላለፍ እንደሚችል ሴቶች እንዲያውቁ ሊመከሩ ይገባል። በኤች.አይ.ቪ እና በሌሎች የአባለዘር በሽታዎች የመያዝ አደጋ የተነሳ እንደ ኮንዶም ያሉ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች መፍትሔ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይመከራል፡፡ ሌሎች ምክን ያቶችን ለምሳሌ አንዲት ሴት የኤችአይቪ ሁኔታዋን መግለጽ መቻሏ ፣ በቤት ውስጥ ብጥብ ጥን መፍራት( domestic violence)  እና ሌሎች የጤና ሁኔታዎችን ጨምሮ በሴቶች የእር ግዝና መከላከያ ምርጫ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ነገሮችን መከላከል ያስፈልጋል፡፡
ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ (PMTCT)
የኤችአይቪ ቫይረስን ከእናት ወደ ልጅ ማስተላለፍን ለመከላከል የሚደረግ እንክብካቤ አጠቃላይ ሁኔታ የሚከተለውን ይመስላል፡፡ የፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድሃኒት ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለመከላከል (PMTCT) የሚያስችሉ የስትራቴጂ ዋና መሠረት ነው ፡፡ ሆኖም  የተሟላ የ ኤችኤቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ (PMTCT) የሚያደርጉ አገልግ ሎቶች የፀረ-ኤችአይቪ ቫይረስ መድሃኒት ከመውሰድ ባለፈ ተጨማሪ እርምጃዎችን ያካትታል፡፡
በእርግዝና ወቅት መጀመሪያ በኤች አይ ቪ የተያዙ ሴቶችን ለመለየት የቅድመ ወሊድ ክትትል ላይ መደበኛ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ ማድረግ፡፡
የኤች.አይ.ቪ ምርመራ በሚደረግበት ጊዜ ውጤታማ የሆነ ዕድሜ ልክ የፀረ-ኤች.አይ.ቪ ሕክምና (ART) መጀመር፡፡
በእርግዝና ወቅት የእርግዝና ክሊኒክ  (PMTCT) ቫይረሱ  ከእናት ወደ ልጅ እንዳይ ተላለፍ የሚደረግ ክትትል ላይ የመድሃኒት ጎንዮሽ ጉዳት  ክትትል እና መደበኛ የእርግዝና እንክብካቤ፡፡
በጤና ተቋም መውለድ፤
የሕፃናት የኤችአይቪ ቫይረስ መከላከያ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ነጥቦች ናቸው፡፡
ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ካለባቸው ሴቶች የተወለዱ ሕጻናት አመጋገብ፡፡
ለሕፃናት አመጋገብ የሚሰጡ ምክሮች የተለያዩ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል በእናት ጡት ወተት የኤችአይቪን ስርጭት አደጋ እና በሌላ በኩል ደግሞ ጤናማ ባልሆኑ የአመጋገብ ልምዶች የተመጣጠነ ምግብ እና የከባድ ኢንፌክሽኖችን አደጋ በአትኩሮት መመልከት ይገባል፡፡ ለአጠቃቀም እንዲመች ከዚህ በታች ያለውን የአመጋገብ ስልት መመልከት ጠቃሚ መሆኑን ዶ/ር ያየህይራድ ገልጸዋል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጡት ማጥባትን በማስተዋወቅ እና ተላላፊዎችን ለመከላከል የፀረ ኤች.አይ.ቪ ጣልቃ-ገብነትን በማቅረብ ወይም ጡት ማጥባትን በማስቀረት ጤናማ የአመጋገብ አማራጭ መንገዶችን እንዲያገኙ ይመክራል ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ከእናትየው የፀረ-ቫይረስ ሕክምና እና የሕፃናት መከላከያ ዘዴ ጋር ተዳምሮ የመጀመሪያ ስድስት ወራት  ጡት ማጥባትን ይመክራል ፣ ይህም ከእናትየው የኤች አይ ቪ ስርጭት ወደ ልጁ እንዳይተላለፍ ለመቀነስ እንደሚረዳና እንዲሁም ጡት ማጥባት ለህጻኑ ጤንነት የሚያስገኘው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻል፡፡
ከላይ ከተገለጹት እውነታዎች በተጨማሪ በእርግዝና እና በድህረ ወሊድ ጊዜ ከፍተኛ ባዮሎጂያዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳ ሮቶች ህክምናን በመከታተል ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ፡፡ ሌሎች ግለሰባዊ ምክንያቶች፣ ለምሳሌ ስለኤችአይቪ ወይንም ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ ስለመተላለፉ ያላቸውን ግንዛቤ ለማስፋት ድጋፍ ማጣት፣ እና መገለልን መፍራት እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ መሰናክሎች እናቶች ሊገጥሙአቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ እናቶች ከእርግዝናቸው በፊት ስለኤችአይቪ ቫይረስ በቂ እውቀት እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ሲሉ ዶ/ር ያየህይራድ አየለ ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካ ኮሌጅ ማብራረያቸውን ቋጭተዋል፡፡

Read 12686 times