Saturday, 15 May 2021 14:59

“አንተ ከነብሩ ጋር ነህ ወይስ ከእኔ ጋር?”

Written by 
Rate this item
(10 votes)

   ከእለታት አንድ ቀን፣ አንድ አዳኝ ነብር። የሚያድነው ወደ ጫካ ሄዶ ነው።
ነብር ፍለጋ ወደ ደኑ ሊገባ ሲል አንድ መንገደኛ ያገኘዋል። መንገደኛው፤ “ወገኔ ወደምን እየገባህ ነው?” ይለዋል።
“ነብር ላድን” ይላል አዳኙ
“ነብር ከሳትከው አደገኛ መሆኑን ታውቃለህ?”
አዳኙ፡-  “ብስተው ወዲያውኑ አቀባብልና ደግሜ እተኩሳለሁ” አለው።
መንገደኛው፡- “ዳግም ብትስተውስ?”
አዳኙ፡- “እንዲወረወር እድል ሳልሰጠው ሶስተኛውን እለቅበታለሁ፤ ያኔ ትክክለኛ መልሱን ያገኛል።”    
መንገደኛው፡- “እንዳጋጣሚ ሆኖ  አሁንም ብትስተውስ?”
አዳኙ፡- “ሰውዬ አንተ ከነብሩ ጋር ነህ ወይስ ከኔ ጋር? ኋላ ጉድ እንዳትሆን ነግሬሃለሁ” አለው ይባላል።
*   *   *
ወዳጅና ጠላታችንን ሳንለይ ጉዞ መጀመር የዋህነት ነው። ምክንያቱም አላማችንም ሆነ ኢላማችን በቅርቡ ከዚሁ ጋር የተሰላሰለ ስለሆነ ነው። ፖለቲካችንና ኢኮኖሚያችን እጅና ጓንት ሆነው ካልተጓዙ ጉዳያችን ሁሉ የእምቧይ ካብ ነው የሚሆነው።
ዓመቱና ዓመቱ የተዋቀረ
ዘመኑ ከዘመን እየተባረረ
ይኸው ጅምሩ አልቆ ማለቂያው ጀመረ።
ይህ ከተባለ እጅግ እረጅም ጊዜ አልፏል። ይህንን እውነታ እንለውጠው ዘንድ መላ መምታት ግድ ይለናል። አዳዲስ መጻህፍትን  ስንመርቅ ድሮ መዝገበ ቃላት ላይ የተጻፈውን  ልብ እንበል። እነሆ፡-
ይቺን ጨቅላ መፅሐፍ የምታነቡ ሁሉ
 አደራ ስለ እኔ ማርያም ማርያም በሉ።
 ከሆዴ  የትምህርት ሽል
ያለችግር እንድወልድ እንድገላገል
ከያ ስድስቱ  ወንዶች ፊደላት
አርግዣለሁና መዝገበ ቃላት
ለትምክህት አይደለም ይሄን መናገሬ
ለማስቀናት እንጂ ሰነፉን ገበሬ
ሃዋርያው ሲናገር ወደ ምዕመናኑ
ለምትበልጥ ጸጋ ይላል ጽኑ ቃሉ
የእለቱ መልዕክታችን ይህና ይሄ ብቻ ነው!!

Read 12680 times