Saturday, 15 May 2021 15:04

ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(2 votes)

  ሕዝብን ማን ይሰራዋል? ሀገርን የሚያክል ግዙፍ ጥያቄ… መልሱ ግን በአንዲት ቃል የሚገለጽ ቀላል! ሕዝብን ማን ይሰራዋል? ጋዜጦች! እንዴት ካልኽ ተከተለኝ… ቶማስ ጀፈርሰን አሜሪካዊያን founding fathers እያሉ ከሚያንቆለጳጵሷቸው ታላላቆች አንዱ ነው፡፡ ፈላስፋ፣ አርክቴክት፣ የህግ ባለሙያ፣ ዲፕሎማት ወዘተ ወዘተ ከስሙ ፊት ለቁልምጫ የሚደረደሩ የማዕረግ ስሞቹ ናቸው፡፡ ለአሜሪካ እንደ ሀገር በዴሞክራሲ መንገድ ጸንቶ መቆም ካስማ እንደሆነ የሚነገርለት Declaration of indipendenceን የጻፈው እሱ ነው፡፡ በኋላም ሦስተኛው የአሜሪካ ፕሬዚደንት በመሆን ሐገሪቱን መርቷል፡፡
ይህ ሰው ለሌላኛው አሜሪካዊ የአካባቢ ገዥ ኤድዋርድ ካሪንግተን በጥር 16፣ 1787 እ.ኤ.አ ከፓሪስ በጻፈለት ደብዳቤ እንዲህ አለ፡- ‹‹The basis of our governments being the opinion of the people, the very first object should be to keep that right; and where it left to me to decide whether we should have a government without news papers, or news papers without a government, I should not hesitate for a moment to prefer the latter…››  ሌላም ልጨምርልህ። አሜሪካዊው የተውኔት ጸሐፊ አርተር ሚለር፤ ጥሩ ጋዜጣ ማለት ይላል… ‹‹A good news paper is a nation talking to itself.›› ሌላኛው የኖቤል ሽልማት አሸናፊ አሜሪካዊ ደራሲ ሪቻርድ ክሉገር እንዲህ ይላል፡- ‹‹የማይረባ እንኳን ቢሆን አንድ ጋዜጣ በሞተ ቁጥር ሀገር ወደ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የበለጠ ትቀርባለች፡፡››
ባለኝ ግርድፍ መረጃ፤ ከግንቦት ሃያ 1983 ዓ.ም ወዲህ ባለፉት 30 ዓመታት፣ ከ700 በላይ ጋዜጦችና መጽሔቶች በኢትዮጵያ አድማስ ስር እየታዩ ጠፍተዋል፡፡ ብዙዎቹ በመንግስት መራር የብረት መዳፍ ጭቆና፣ ሌሎች ጥቂቶች ደግሞ በራሳቸው ሀሳብ አጠርነት እንደ ጥቅምት አደይ ልብ ሳይባሉ፣ አንድ በአንድ እየረገፉ አልቀው፣ አሁን በገበያው ውስጥ ያሉት 20 እንኳን አይሞሉም፡፡ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በሌሎችም ቋንቋዎች የሚታተሙትን ጨምሮ ማለቴ ነው…
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የደፈጣ ተዋጊ ወይም የወንጀል ቡድን ዓይነት ባህሪ የሚያሳዩ ያልተረጋጉ ናቸው፡፡ አሰራራቸው ቡድናዊ ነው፡፡ ካላመንከኝ ሂድና ሞክራቸው፡፡ አምደኞቹ የዛሬ አስራ ሁለት ዓመት የምታውቃቸው ናቸው፡፡ ግን በንባባቸው፣ በሕይወትና በፖለቲካው አረዳዳቸው  መቆርዝቆ እንጂ ዕድገት አታይባቸውም፡፡ አንተ በየፌስቡኩ አንበልብለኸው የቸከህን አሉቧልታ፣ በቀለም ሸላልመው በወረቀት ያቀብሉሀል። ከገጽ እስከ ገጽ፣ እጅ እጅ የሚል ፖለቲካ ብቻ… በጣም ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኞቹ ጥበብ፣ ሙዚቃ፣ ስዕል፣ ዳንስ፣ ሒስ (critic) ብሎ ነገር ቢጠበስ አይሸታቸውም፡፡      
52 ሚሊዮን ሕዝብ ብቻ ወዳላት ጎረቤት ኬንያ ሂድ… The daily Nation የተሰኘው ዕለታዊ ጋዜጣዋ ብቻ በየቀኑ በአማካይ 170,000 ቅጅዎችን ይቸበችባል፡፡ በቀን በአማካይ እስከ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በተለያየ መንገድ ያነቡታል፡፡ የእኛን ሀገር የፖለቲካ ውሎ ጨምሮ ጥበቡ፣ ፖለቲካው፣ ፍልስፍናው ሁሉም በዓይነት ይዘገብልሃል፡፡ ወደ አሜሪካ ዝለቅ፣ ምናምን tribune፣ ምናምን times፣ ምናምን chronicle፣ ምናምን post፣ ምናምን monitor… የሚባሉ ለቁጥር የሚታክቱ ዕለታዊና ሳምንታዊ ጋዜጦች የንባብ ጠረጴዛህን ያጨናንቃሉ፡፡ የእኛውንማ የምታውቀው ስለሆነ አልመለስበትም፡፡
ጋዜጦች ግን የህዝብ ልሳን ናቸው፡፡ የህዝብን አስተያየት የመለወጥ፣ የመጠምዘዝ የማቃናት ከፍተኛ አቅም አላቸው፡፡ ህዝብ እንደ ደነበረ ደራሽ ጎርፍ ነው፡፡ በመራኸው በቀደድክለት ሁሉ ይሰግርልሃል፡፡ ህዝብ እንደ መንግስት ሁሉ ይሳሳታል፡፡ እንዲያውም ልክ ሆኖ አያውቅም ልልህ እችላለሁ፡፡ ጠንካራ ጋዜጦች ያሉት ህዝብ ግን ጎርፍ ሳይሆን የረጋ ውኃ ነው፡፡ ጥልቀት አለው፡፡ የሚጠብቁት የማይከደኑ ዓይኖች፣ የመንግስትን ስህተቶች በድፍረት የሚነቅሱ ጋዜጦች ስላሉት፣ እንደ ሰደድ እሳት አይግለበለብም፡፡ በአጭሩ ለምን አልነግርህም፣ ሀገርህ የእጅ መሀረብን ያህል አንሳ ተጨምቃ የምትቀርብበት ነገር ምንድን ነው ብትለኝ ጋዜጣ እልሃለሁ፡፡ ጋዜጣህን አሳየኝና ስለ ህዝብህ፣ ስለ ሀገርህን ማን ምንነት እነግርሃለሁ!   
ጋዜጦች ለእኔ እንደ ዕለት ማስታወሻም (diary) ናቸው፡፡  እ.ኤ.አ ከ1900 እስከ 1983 ዓ.ም የኖረው እስፓኝ ሜክሲኳዊው የፊልም ባለሙያ ሉዊስ ቡኔል፤ ጋዜጣን በተመለከተ አንዲት ልብ የምትነካ አባባል አለችው፡፡ #ከሞትኩ በኋላ በየአስር ዓመቱ ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ከመቃብር እየተነሳሁ ጥቂት ጋዜጦችን ብቻ ገዝቼ መመለስ ብችል ደስ ይለኛል፡፡; የምትል፡፡ እውነቱን ነው። ስደትን አምርሬ የምጠላው እኔ፤ The Atlantic የተሰኘውን መጽሔቷን በየወቅቱ ለማንበብ ብቻ አሜሪካ ድረስ በእግሬ እንኳን ብሄድ ቅር አይለኝም፡፡  
ጋዜጦች በተወሰነ የሚታወቅ ዕለት፣ ጊዜ ጠብቆ ብቅ እንደሚል የልብ ወዳጅ ተናፋቂ ናቸው፡፡ ጋዜጦች የትውልዶች የቃል ኪዳን ሰነዶች፤ ራስን፣ ሐገርን፣ ትውልድን የመመልከቻ መነጽሮችም ናቸው፤ የዘመን የትውልድ መልኮች፣ የልብ ጓደኞች፣ መተከዣዎች፣ መነሳሺያዎች (muse)፣ ምናብን የሚያናጥቡ የሚያስደነብሩ የጠዋት ፀሐይ፣ ጣፋጭ ማኪያቶ ዓይነት ስስ ለስላሶች፣ አጫዋቾች...
ምናልባት ከዚያም በላይ!
… ጋዜጦች!


Read 3850 times