Print this page
Saturday, 15 May 2021 15:16

እስራኤልና ፍልስጤም ወደ ከፋ ጦርነት እንዳይገቡ ተሰግቷል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  በፍልስጤማውያን እና በእስራኤል ፖሊስ መካከል ባለፈው አርብ በአል አስቃ መስጊድ በተፈጠረ ብጥብጥ ዳግም ያገረሸውና ካለፉት ሰባት አመታት ወዲህ በሁለቱ አገራት መካከል የተከሰተ ከፍተኛው ግጭት እንደሆነ የሚነገርለት የሰሞኑ ግጭት በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ መቀጠሉ የተነገረ ሲሆን፣ ግጭቱ ወደከፋ ጦርነት እንዳያመራ መሰጋቱን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
በምስራቅ እየሩሳሌም ከሚገኘው የሼክ ጃራ የተባለ አካባቢ የሰፈሩ ፍልስጤማውያን ቤተሰቦች ከቦታቸው ይፈናቀላሉ መባሉን ተከትሎ  የተቀሰቀሰው የፍልስጤማውያን ተቃውሞ፣ ለቀናት ተባብሶ መቀጠሉንና የእስራኤልና ፍልስጤም ታጣቂዎች በሮኬት ጥቃትና በአየር ድብደባ ሳምንቱን ማገባደዳቸውን የዘገበው ሮይተርስ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና አውሮፓ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መሪዎች ግጭቱ ወደ ከፋ ጦርነት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አመልክቷል፡፡
ካለፈው ሰኞ አንስቶ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአየር ጥቃቶችን መፈጸሟንና የፍልስጤም ታጣቂዎች በበኩላቸው፤ ከ 1 ሺህ 50 በላይ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፋቸውን የዘገበው አልጀዚራ፣ በግጭቱ 17 ህጻናትን ጨምሮ ከ83 በላይ ፍልስጤማውያንና 6 እስራኤላውያን ለሞት መዳረጋቸው መነገሩንም አክሎ ገልጧል፡፡
ግጭቱ መባባሱንና ውጥረት መንገሱን ተከትሎ፣ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ፤ በሁለቱ ሃይሎች መካከል የተካረረው ውጥረት በአፋጣኝ እንዲረግብና ጥቃቶች እንዲቆሙ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው፤ በግጭቱ የሚገደሉ ንጹሃን ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ እንደሚያሳስባቸው ጠቁመው፤ሁለቱ ሃይሎች ግጭቱን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ አስተላልፈዋል ፡፡
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው፤ ውጥረቱ መባባሱ እንደሚያሳስባቸው ገልጸው፣ እስራኤልና ፍልስጤማውያን ንጹሃንን ተጎጂ ከሚያደርጉ ድርጊቶቻቸው እንዲታቀቡ ያሳሰቡ ሲሆን የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚሼልም፤ ሁለቱ ሃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ ጠይቀዋል፡፡
ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው ከገለጹና ለሁለቱ ሃይሎች የሰላም ጥሪ ካስተላለፉ የአለማችን አገራት መካከልም ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ቻይና፣ ፓኪስታን የሚገኙበት ሲሆን፣ እስራኤል በጋዛ ጥቃት መፈጸሟን ማቆም ይገባታል ካሉት መካከልም ግብጽና ሩስያ ይገኙበታል፡፡
ባለፈው አርብ ፍልስጤማውያን ተቃዋሚዎች በእስራኤል ፖሊስ ላይ ድንጋይ መወርወራቸውን ተከትሎ ፖሊስ ተቃዋሚዎችን ለመበተን ባደረገው ጥረት ከ200 በላይ ፍልስጤማዊያንና 17 ያህል የእስራኤል ፖሊሶች መጎዳታቸውን ያስታወሰው አልጀዚራ፣ ቅዳሜና እሁድ  ግጭቱ ከእየሩሳሌም በተጨማሪ ሃፋና ራማላህን ጨምሮ ወደተለያዩ ከተሞች መስፋፋቱንና ባለፈው ሰኞ ዕለት ሃማስ ወደ እየሩሳሌም ሮኬቶችን መተኮሱና እስራኤል በአጸፋው በጋዛ ሰርጥ የአየር ጥቃቶችን መሰንዘሯ ጉዳዩን እንዳካረረው ዘግቧል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ከመዲናዋ ቴልአቪቭ አቅራቢያ በምትገኘው ሎድ ከተማ ከፍተኛ አመጽ መቀስቀሱንና ጉዳት መድረሱን ተከትሎ የእስራኤል መንግስት በከተማዋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀ ሲሆን፣ በዕለቱ ክልስ አይሁዶችና አረቦች ተቀላቅለው በሚኖሩበት የእስራኤል አካባቢ በተፈጠረ ሁከት ምክንያት 36 የፖሊስ መኮንኖች መጎዳታቸውንና ይህንም ተከትሎም 374 ሰዎች መታሰራቸውን የእስራኤል ፖሊስ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
እስራኤል ባለፈው ረቡዕ በፈጸመችው የአየር ድብደባ የሃማስ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦችን መግደሏንና በጋዛ የሚገኝ ግዙፍ ህንጻን ማውደሟን፤ ሃማስ በበኩሉ፤ ከ130 በላይ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል በማስወንጨፍ የአጸፋ እርምጃ መውሰዱን የዘገበው ቢቢሲ፣ ግጭቱ በእስራኤል ውስጥ በአይሁዶችና በእስራኤል አረቦች መካከልም የጎዳና ላይ ሁከት እንዲፈጠር ሰበብ መሆኑን አክሎ ገልጧል፡፡
ሶስቱ የአሜሪካ ግዙፍ አየር መንገዶች አሜሪካን ኤርላይንስ፣ ዩናይትድ ኤርላይንስና ዴልታ ኤርላይንስ ግጭቱ መባባሱን ተከትሎ ወደ እስራኤል የሚያደርጉትን በረራ ሙሉ ለሙሉ ማቋረጣቸውን ከትናንት በስቲያ ማስታወቃቸውም ተዘግቧል፡፡


Read 4413 times
Administrator

Latest from Administrator