Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 10:13

“ዕንባ ዐባይ ከሆነ፣ እሱንም እንገድብ ብዙ አሳብ አለብን፣ የሩቅና የቅርብ!”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አንድ ንጉሥ ሶስቱን ጥበበኛ አማካሪዎቻቸውን ጠርተው፤

የመጀመሪያውን፤ “በጣም በትንሽ ብር ይሄን ቤት የሚሞላ ነገር ገዝተህ ና” ብለው ጠየቁት፡፡

ሁለተኛውን አስቀርበው፤

“ሰውን እንዳይረሳ የሚያደርገው ምን እንደሆነ መርምረህ ንገረኝ” አሉት፡፡

በመጨረሻም ሶስተኛውን ጠርተው፤

“መጽሐፍ ገልጠህ፣ አዋቂ ጠይቀህም ሆነ፣ ከምትወዳቸው ሰዎች ጋር ተማክረህ፤ አንድን ህዝብ ታላቅ የሚያደርገው ምን እንደሆነ እንድትነግረኝ” አሉት፡፡

ሦስቱም በየአቅጣጫው ሄዱ፡፡

በነጋታው መልሳቸውን ይዘው መጡ፡፡

ጥበበኞቹ አስተዋዮች፤ አርቆ አሳቢዎችና ተመራማሪዎች ስለሆኑ መልሱን በአጥጋቢ ሁኔታ መለሱ፡፡ በሸንጐም የተሰበሰበው ህዝብ ጭብጨባ ለገሳቸው፡፡

መልሳቸውም፤

የመጀመሪያው - ቤቱን የሚሞላ ነገር ሻማ (ብርሃን) ነው፤ አለ

ሁለተኛው - ሰውን እንዳይረሳ የሚያደርገው ሥራው ነው፡፡

ሦስተኛው - አንድን ህዝብ ታላቅ የሚያደርገው ክፉ ሆነ ደግ መሪውንና ታላላቅ ሰዎቹን የማክበር ባህል ያለው እንደሆነ ነው፡፡ ብርሃን፣ ሥራና ባህል ሦስቱ መልሶች ሆኑ ማለት ነው! ንጉሡ መልሳቸውን አድንቀው የመጨረሻ ጥያቄ ጠየቁ፤

“ከመለሳችሁት ሁሉ እጅግ ትልቅ ግምት የሚሰጠው የቱ ይመስላችኋል?” ሲሉ ጠየቁ፡፡

ሦስቱም በጉዳዩ ላይ ከተወያዩ በኋላ፤

“ንጉሥ ሆይ! ከሁሉም የሚበልጠው መሪዎቹን የማክበር ባህል ያለው ህዝብ ነው” ሲሉ መለሱላቸው፡፡

***

ብርሃን የሚያይ ህዝብ የታደለ ነው!

ሥራ የገባው ህዝብ የታደለ ነው!

መሪውን የማክበር ባህል ያለው ህዝብ የታደለ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ልዩነት ይኑረው፣ ምንም ዓይነት ግጭት ይፍጠር፣ ምንም ዓይነት ምሬትና ብሶት ይኑርበት ታላላቅ መሪዎቹንና ሰዎቹን የሚያከብር ህዝብ ታላቅ ህዝብ ነው፡፡ ታላቅ ህዝብ ያቀፈው ባህል ቢጋርዱት የማይጋረድ፣ ላጥፋህ ቢሉት የማይጠፋ ብርሃን ነው፡፡ የፖለቲካን ኬላ ሰብሮ ተፈጥሮንና ህይወትን ያያል፤ ያሳያልም፡፡ ስለ ሰው ልጅ ያለውን ሰብዓዊ ርህራሄ ያገዝፋል፡፡

የያዝናቸው ወራት የሀዘን ወራት ናቸው፡፡ ታላላቅ ሰዎችን አጥተንባቸዋል፡፡ ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር (የካቲት 2004)፣  ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ (ሚያዚያ 2004) ደራሲ ማሞ ውድነህ  (መጋቢት 2004)፣ አቡነ ጳውሎስ (ነሐሴ 2004) እና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (ነሐሴ 2004) በተከታታይ ያጣናቸው ታላላቅ ሰዎች ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሐዘኑን ያቅልልሰት፡፡ መጪውን ጊዜ የሰላምና የጽናት ያድርግለት፡፡ ከተጠቀሱት ታላላቅ ሰዎች የአቶ መለስ እጦት ትልቁን ሚዛን ይደፋል፡፡

አቶ መለስን እንደሰው፣ እንደ ምሁሲ እና እንደ አገር መሪ አይቶ ክፉ ደጉን አመዛዝኖ ህዝብ ሐዘኑን የገለፀበት ሁኔታ እጅግ አስገራሚ አንድምታ እንዳለው ማስተዋል አያዳግትም፡፡ ጨዋ ህዝብ መሆኑንም በግልጽ አስመስክሯል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ሥራን፣ ታታሪነትን፣ የረዥም ጊዜ የትግል ህይወትንና ፅናትን በውስጣቸው ለማየት አያስቸግርም፡፡ ልብ ያለው የሚማርበት፣ ዐይን ያለው የሚያየው በጐ ሥራ አላቸው፡፡ (To err is human and to forgive is devine (መሳሳት የሰው ልጅ ይቅር ማለት የመለኮት፣ እንደሚባለው ስህተት የለባቸውም ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል) ቁም ነገሩ በሰውነታቸው ማክበር የአንድ ህዝብ ታላቅ ባህላዊ እሴት መሆኑ ላይ ነው፡፡

የመሪውን አስከሬን ለመቀበል በሀዘንና በክብር የወጣውን ህዝብ ሁኔታ ላየ፤ አንድም አሳማኝ የህዝብ ኃይል ምን ያህል ማረጋገጫ መሆኑን ለማንም ትምህርት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ታዋቂነትንና ተቀባይነት ማግኘትን የማድነቅ ባህልም የዛኑ ያህል ታላቅ ዕሴት ነው፡፡ ለአብነት ያህል፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንትነት፣ የዓለም ሎሬትነት፣ የታላላቅ የዓለም ኮንፈረንሶች ተሳታፊነትና መሪነት… የሀገር ምስል ማድመቂያ፤ ሀገር የሚያስጠሩ የክብር ቀለሞች ናቸው፡፡ በማንኛውም መስክ ኢትዮጵያን በዓለም የሚያሳውቁ ሰዎቻችንን እናክብር! እናድንቅ! ይሄን ባህል እናስፋፋ!

“ተፋልሞ ተፋልሞ፣ ሮጦ ያመለጠ

ሌላ ቀን ሊፋለም፣ መንገዱን ገለጠ፡፡” ይላሉ እንግሊዞች፤ ብልህነት የትግል አካል መሆኑን ለማስረዳት ማጥቃት ብቻ ሳይሆን መከላከል፣ መከላከልም ብቻ ሳይሆን ማፈግፈግ፤ ለሌላ ትግል መዘጋጀት መሆኑን ነው እሚነግረን፡፡ ይህን የሚያውቅ መሪ መኖሩ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ይህን የተረዳ ህዝብ መኖሩ ፀጋ ነው፡፡

ሞት ለሁሉም ነው፡፡ ህይወት ግን የታገለ የሚኖርባት ናት!

የጣሊያን ፀሐፊዎች፤ “ምን ጊዜም ከዤዙ ጨዋታ በኋላ ንጉሡም ወታደሮቹም አንድ ሣጥን ውስጥ ነው የሚገቡት” ይላሉ፡፡ ሞት የማይቀር ተፈጥሮአዊ ክስተት ነው - ከራስጌም ከግርጌም ሊያገኘን ይችላል፡፡ ሞትን የማሸነፊያ አያሌ መንገዶች አሉ፡፡

ቻርለስ ማኬይ እንዲህ ይለናል

“ሞት የሚሉት ነገር የለም፤ ተፈጥሮ ሞትን የት ያቃል

ከያንዳንዷ አሳዛኝ ቅጽበት፣ አንዳንድ ህይወት ይወለዳል!”

ህይወትን መውለድ ማለት መኖርን በወትሮ ወጉ መኖር፣ እንዲቀጥል ማድረግ፤ አስፈላጊ ሲሆን መለወጥና ማሳደግ ነው!

ዓመቱ የሐዘን ዳመና ያጠላበት መሆኑን ልብ ካልን ዘንድ፤

“ሐዘን አብርድ” እንደሚባለው፤ ሰብዓዊ ሐዘንን በመቀነስ፣ የአዘቦት ህይወታችን የጐደለውን በወጉ አሟልተን በዝግጁ ጥንቃቄ መቀጠል ግድ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ አክብረን፤ ከአክብሮት ባህሉ ተምረን፤ የተሻለ አመራርና የተሻለ አስተዳደር ፈጥረን መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡

“ዕንባ፤ ዐባይ ከሆነ፤ እሱንም እንገድብ

ብዙ አሳብ አለብን፤ የሩቅና የቅርብ!”

የሚለው ግጥም ነገን ይጠቀልለዋል!!

 

 

 

Read 3500 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 10:32