Print this page
Tuesday, 18 May 2021 00:00

ከሞግዚትነት እስከ ቢዝነስ ኢንቨስትመንት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  • ሴት ልጅ ዓላማ ሲኖራትና ተስፋ ስትሰንቅ ትበረታለች
      • ዳያስፖራው የአገሩን ፍቅር በደስታና በተድላ አይለውጥም
      • ኢትዮጵያ እንደ ጨለመባት አትቀርም፤ ይነጋላታል


          ተወልደው ያደጉት በደቡብ ክልል፣ አለታ ወንዶ በተባለች ትንሽ የወረዳ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ ቀዬአቸው ተምረው፣ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ወደ ይርጋአለም መሄዳቸውን  ይናገራሉ። ከዚያም ትዳር ለመመስረት ወደ ደሴ መሄዳቸውንና ከደሴ ተመልሰው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ ኮሌጅ ገብተው፣ በአካውንቲንግ ዲፕሎማቸውን ያገኙ ሲሆን፤ በትምህርት ሚኒስቴር ተቀጥረው ሰርተዋል፡፡ ከዚያም ወደ እስራኤል የመጓዝ ዕድል የገጠማቸው ሲሆን ጉዳያቸውን ሲጨርሱ ወደ አገር ቤት ከመመለስ ይልቅ የስደት ኑሮን መርጠዋል፡፡ በእስራኤል ብቻ ሳይሆን በካናዳም ተሰደው ኖረዋል - የዛሬዋ እንግዳችን ወ/ሮ ሮማን አዛለ።
ለመሆኑ ወ/ሮ ሮማን ልጆቻቸውን ለባለቤታቸው ጥለው በስደት መኖርን እንዴት መረጡ?  በስደት አገርስ ምን ገጠማቸው? የፈረንጅ ህጻናትና አዛውንት ሞግዚት ሆነው ሲያገለግሉ የኖሩት ወ/ሮ ሮማን፤ በምን ተዓምር ወደ ኢንቨስትመንት ገቡ? ሁሉንም ይነግሩናል፡፡ መከራውንም ስኬቱንም፡፡ ልፋቱንም ሽልማቱንም፡፡ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት  ዮሴፍ ጋር እንዲህ አውግተዋል፡፡


             መቼ ነበር ወደ እስራኤል ያቀኑት? ለምንና እንዴት?
ወደ እስራኤል የሄድኩት በ1987 ዓ.ም፣ ለጉብኝት ነበር፡፡ ሆኖም ጉብኝቴን እንደጨረስኩ አልተመለስኩም።
ለምን አልተመለሱም?
እዚያው ለመስራትና ለመሻሻል በማሰብ ነው የቀረሁት፡፡ ለሰባት አመት ያህል በእስራኤል ኖሬአለሁ።
በእስራኤል ቆይታዎ ኑሮን ለማሸነፍ ብዙ ውጣ ውረድ ማሳለፍዎን ሰምቻለሁ። እስኪ ያጫውቱኝ...?
የውጪ አገር ኑሮ ከባድ ነው። እስራኤል አገር የህፃናትና አዛውንት ሞግዚት ሆኜ ብዙ ፈተና አይቻለሁ። የህፃናትና አዛውንት ሞግዚትነቴ ሳያንስ፣ የፅዳት ስራም ይደረብብኝ ነበር። ብዙ ድካም፣ ብዙ ውጣ ውረድ ነበረው። እኔ ከዚህ ስሄድ አዲስ እንደመሆኔ፣ የባህል የቋንቋና መሰል ችግሮችም ተጋፍጫለሁ፡፡ እነሱ እብራይስጥ ነው የሚናገሩት። እኔ ደግሞ እንግሊዝኛ ነው የምችለው። ባህሉም ህዝቡም የተለየ ነው። በዚያ ላይ አራት ትንንሽ ልጆቼን ጥዬ ስለሄድኩኝ ናፍቆት ያንገላታኛል፡፡ ፈተናው ተደራርቦብኝ ነበር። ቶሎ ብዬ እብራይስጥ ቋንቋ  መልመዴ ግን ጠቅሞኛል፡፡ ፈተናዎችን ተቋቁሜ ለሰባት ዓመት ከሰራሁ በኋላ ከእስራኤል ወደ ካናዳ አቀናሁ።
የተሻለ ስራ ተገኝቶ ነው ወይስ በሌላ ምክንያት?
በዚያው በህፃናት ሞግዚትነት ነው ወደ ካናዳ የሄድኩት፤በ2000 ዓ.ም። በግሌ ከኤጄንሲዎች ጋር ተነጋግሬ ነው ሥራውን ያገኘሁት። በካናዳም ለአራት ዓመታት ያህል በሞግዚትነት ሰርቻለሁ። ከዚያ በኋላ ግን እስከ መቼ ነው በዚህ ሁኔታ የምቀጥለው? የራሴን ስራስ መቼ ነው የምጀምረው? በማለት ማሰብ ጀመርኩኝ። በመቀጠልም ለምን የሀበሻ ምግብ ቤት አልጀምርም? ብዬ ከራሴ ጋር ተነጋገርኩ።
እንዴት የሀበሻ ምግብ ቤት ለመክፈት አሰቡ? በዚያ ላይ በውጭ አገር ሬስቶራንት ለመክፈት ብዙ ወጪ ይጠይቃል ----
በእውነቱ ይሄ ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ የሚገርምሽ እዚህ ኢትዮጵያ እያለሁ የምግብ ስራ ላይ እምብዛም ነበርኩኝ። ነገር ግን በውጭ መኖር ከጀመርኩ በኋላ አንዳንድ ቦታ ሄጄ ነጮች ለእኛ ምግብ ያላቸውን ፍቅር ስመለከት፣ ሀበሾቹም በፍቅርና በስስት ሲመገቡት ሳይ ነው፣ ፍላጎት ያደረብኝ። ይህን ያህል ተፈላጊ ከሆነማ እኔ ጥሩ አድርጌ ብሰራው፣ ውጤታማ ልሆን እችላለሁ ብዬ አሰብኩ። ከዚያም ያለኝን  አቅም ሁሉ አስተባብሬ፣ “ዘንባባ” የተሰኘ ሬስቶራንት ከፈትኩኝ። ይህን ሬስቶራንት ከከፈትኩ በኋላ ደንበኞች አላጣሁም፤ እግዚአብሔር ይመስገን። ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ የውጪ ዜጎች እኔ ሬስቶራንት ውስጥ በፍቅር መመገብ ጀመሩ። ባልታሰበ ፍጥነትና ሁኔታ እያደገና እየሰፋ መጣ። ለ12 ዓመታት ከሰራሁ በኋላ፣ እዛው ካናዳ አልበርታ ውስጥ ሁለተኛ ቅርንጫፍ ከፈትኩኝ። በመቀጠልም፣ ሶስተኛውን ሬስቶራንት ለመክፈት ቻልኩኝ። በልፋትና በትጋት ጫናውን ሁሉ ተቋቁሜ በመስራቴ ህይወቴ ተቀየረ።
አንድ ነገር ልንገርሽ፤ ሰው ውጪ ሀገር ቢኖርም ትንሽ ኪሱ ሞላ ሲል አገሩን ያስባል፤ ምን ላድርግ ይላል። ምክንያቱም በሰው ሀገር ምንም ሀብት ብታካብቺና ቢደላሽ፣ ደስታሽ ሙሉ አይሆንም። እኔም ወደ ሀገሬ ማሰብ ጀመርኩኝ፤ ምክንያቱም ልጆቼም አድገዋልና። እስራኤል እያለሁ ገንዘብ እየላኩ፣ ምንም ነገር ሳይጎልባቸው እንዲያድጉና እንዲማሩ የተቻለኝን አድርጌአለሁ፡፡ ወደ ካናዳ ከመሄዴ በፊትም ወደ ኢትዮጵያ ለእረፍት መጥቼ አይቻቸው ነበር። ካናዳ እግሬን ከተከልኩ በኋላ፣ ልጆቼን ወስጄ አስተማርኳቸው፡፡ የመጀመሪያ ልጄ ዮዲት መሰለ፣ ሁለተኛ ልጄ ካሌብ መሰለ፣ ሶስተኛው ልጄ ሳዲር መሰለ፣ አራተኛዋና የመጨረሻዋ ልጄ ደግሞ ስቴላ መሰለ ይባላሉ።
ወደ እስራኤል ስሄድ ለአባታቸው ጥያቸው ነበር የሄድኩት። ከዚያም ሁኔታዎች ሲመቻቹ ነው ወደ ካናዳ የወሰድኳቸው። አሁን ትምህርታቸውን ጨርሰው፣ ሁሉም ስራ ይዘው፣ ራሳቸውን ችለዋል። እግዚአብሔር መርቆ ልጅ ሲሰጥሽ፣ በምንም ሁኔታ ላይ ብትሆኚ ኑሮሽን ያቀልልሻል። ልጆቼ በጣም ጥሩና የተባረኩ ናቸው። እውነት ለመናገር፣ እኔ ወደ እስራኤል ስሄድ፣ አባታቸው በጥሩ ሁኔታ በስነ-ምግባር አንጾ ነው ያሳደጋቸው፤ የተባረከ ሰው ነው። ከዚህ ስወስዳቸው አድገውም ስለነበር ጫናው ቀንሶልኛል። በአግባቡ ትምህርታቸውን ተምረው፣ ስራም ይዘው ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰውልኛል፤ በዚህ በጣም ደስተኛም እድለኛም ነኝ እላለሁ።
ቅድም እንደጀመሩልኝ፣ "ሁሉም ነገር ያለ አገር ትርጉም የለውም" እርስዎም ስለ አገርዎ ማሰብ ጀመሩ ... ከዚያስ ምን ላይ ደረሱ?
ሀገሬን ካሰብኩ በኋላ አሁን እኔና አንቺ ቁጭ ብለን የምንነጋገርበትን፣ ባለ ስድስት ወለል ህንፃ ለመገንባት ዕቅድ ነድፌ መንቀሳቀስ ጀመርኩ። ይህ ህንፃ ከተጀመረ ከ6 ዓመት በላይ ሆኖታል። የኔ ሀሳብ፤ ይህንን ህንፃ ቶሎ ገንብቼ፤ ወደ ሀገሬ ተጠቃልዬ መግባት ነበር። ነገር ግን በዚህ ህንፃ ምክንያት ያልደረሰብኝ በደልና እንግልት የለም፡፡ በመጨረሻም ተስፋ ቆርጬ፣ ግንባታውን አቁሜ ወደ ካናዳ ተመልሼ ነበር።
እስቲ የደረሰበዎትን በደልና እንግልት በዝርዝር ይንገሩኝ?
ምን መሰለሽ... ህንፃው የተጀመረው ዶ/ር ዐቢይ ከመምጣታቸው በፊት በኢህአዴግ መንግስት ነበር፡፡ ለሁለት ወር ወይም ለአንድ ወር ተኩል አቅጄ እየመጣሁ ነበር። እዚህ በምመጣበት ጊዜ የኔ ጉዳዮች ባሉባቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች በኩል ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩ። በቀጠሮ ማመላለስ፣ በቀላሉ የሚፈታውን ነገር ማወሳሰብ፣ ስራዎቼን ማበላሸት... ብቻ ምኑን ልንገርሽ... አቅጄ የመጣሁትን ስራ አንድም ነገር ሳላሳካ የመጣሁበት ቀን ያልቅና ወደ ካናዳ እመለሳለሁ። ምክንያቱም እዛም እንደነገርኩሽ ንግድ አለኝ። እዚህ ቆይቼም ሳይሳካ፣ እዛም ስራዬ ተበላሽቶ፣ እንዴት ይሆናል አልኩኝና፣ ይሄንን  እርግፍ አድርጌ ትቼው፣ ወደ ካናዳው ሥራዬ ተጠቃልዬ ገባሁ።
ህንፃውን አቁመው ጥለውት ሄዱ--?
መሰረቱ በደንብ ወጥቶ ብሎኬት መደርደር እንደተጀመረ ነበር፤ይሄ ችግር የገጠመኝ።  ችግሩ አሁን ሲወራ ቀላል ይመስላል፤ በጣም በጣም ፈታኝ ነበር። አሁን ስላለፈ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ማለት ጥቅም የለውም፤ ግን በአንድ ሰዓት ውስጥ ሊያልቅ የሚችል ነገር ለአንድ ሳምንት ይቀጥሩሻል፤ በሳምንቱ ስትሄጂ ሌላ ሰንካላ ምክንያት ይፈጥሩና ያንገላቱሻል። ሌላው መስሪያ ቤት ስትሄጂም ተመሳሳይ ችግር ነው የሚገጥምሽ፤ መንታ እስኪመስሉሽ ድረስ እዛም ተስፋ እቆራጭ ነገር ይገጥምሻል። እቃ  ከውጪ ገዝተሸ ለማስገባት ፈቃድ ለመጠየቅ... ሁሉም ቦታ ነገሩ የተቆላለፈና የተወሳሰበ ነው። በኋላ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጌ ትቼው፣ ወደ ካናዳ ተመልሼ፣ ሬስቶራንቶቼን ተረጋግቼ መምራት ጀመርኩኝ።
ከዚያስ እንዴትና መቼ ተመልሰው አጠናቀቁት?
እንግዲህ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ፣ እኛን መጥተው ወደ አገራችሁ ግቡ፤ ብዙ የሚስተካከሉ ነገሮች አሉ፤ አገራችሁ ትፈልጋችኋለች አሉን። እኔም በእርሳቸው ጥሪ መሰረት እስኪ ልሞክረው ብዬ መጣሁ። እውነትም ነገሮች በተወሰነ መልኩ ተቀይረው አገኘኋቸው። ነገሩ ተስፋ ሰጪ ሲሆን፤ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል እዚሁ ቁጭ ብዬ፣ ይሄን የምታዩትን ውብ  ህንፃ አጠናቅቄ ባለፈው ጥር ወር ተመርቋል። ቆንጆ የእንግዳ ማረፊያ ነው፤ ስትጎበኚው የወደድሽው ይመስለኛል።
እውነት ነው... በጣም በሚያምር ሁኔታ ነው የተሰራው፤ ነገር ግን ስሙ ለመያዝ ትንሽ ይቸግራል። “ሮዮካሳስ” ምን ማለት ነው?
“ሮዮካሳስ” ምህፃረ ቃል ነው፤ በእኔ እና በአራቱ ልጆቼ ስም የመጀመሪያ ፊደላት ስብስብ የተሰየመ ነው። ሮማን፣ ዮዲት፣ ካሌብ፣ ሳዶርና ስቴላ፤ “ሮዮካሳስ”፡፡
በስደት ላይ ሳሉ የልጆችዎ ናፍቆት፣ የቋንቋ ችግር፣ የህፃናትና አሮጊቶች ሞግዚት መሆን ወዘተ--- አላማረረዎትም?
ጥሩ! ልንገርሽ፡፡ ሴት ልጅ አላማ ሲኖራት፣ ተስፋ ስትሰንቅ ጠንካራ ናት። ግብ ሲኖራት፣ ትዕግስተኛ ናት። እኔ አገሬ እያለሁ ስራም ትዳርም ነበረኝ፤ ምንም የጎደለብኝ ነገር አልነበረም። እስራኤል ሄጄ ስቀር ዓላማ ነበረኝ። ሰርቼ ልጆቼን የተሻለ ቦታ ለማስተማር፣ ህልሜን ሰንቄ ነው የቀረሁት።  ስለዚህ ድካሙ   ውጣ ውረዱ፣ የአዛውንቶቹ አንሽኝ፣ ጣይኝ ወዘተ---ትዝ አይለኝም።  ልጆቼን የተሻለ አገር ወስጄ ማስተማር፣ የራሴን ህይወት መቀየር፣ ለሰዎች የስራ እድል መፍጠርና ሌሎች ብዙ ህልሞች... ይህን ለማሳካት መጠንከርና መታገስ ነበረብኝ።  አሁን ልጆቼን  ወስጄ አስተምሬ፣ ራሳቸውን ችለው  የወለዱም አሉ፤ አያት  እስከ መሆን ደርሻለሁ። ከተቀጣሪነት ወጥቼ፣ የራሴን ቢዝነስ ከፍቼ፣ ከራሴ አልፌ በሶስቱ የካናዳዎቹ ሬስቶራንቼም ሆነ በአዲስ አበባው ገስት ሀውስ ለሰዎች የስራ እድል ፈጥሬአለሁ። ወደፊትም ብዙ እቅድና ዓላማ አለኝ። ይህን የህይወት ተሞክሮዬን፣ የአገሬ ታዳጊ ወጣቶች እንዲማሩበት እፈልጋሁ።
በስራ ትጋትዎና ታማኝነትዎ ከአሰሪዎችዎ ሽልማት መሸለምዎን ሰምቻለሁ። እስቲ ትንሽ ስለሱ ይንገሩኝ?
ሽልማት ያበረከቱልኝ ካናዳ የነበሩት አሰሪዎቼ ናቸው። እንደነገርኩሽ ካናዳም፣ በህፃናት ሞግዚትነት ነው፤ ለ4 ዓመታት የሰራሁት። ከእስራኤል በስራ ፍቃድ፣ በሞግዚትነት ነው ካናዳ የገባሁት። እስራኤል አገር ለሚያሰሩኝ አይሁዶች፣ ልጆቼን የተሻለ አገር መውሰድ እንደምፈልግና፣ ወደ ካናዳ ለመሄድ ከኤጀንሲዎች ጋር መነጋገር መጀመሬን ስነግራቸው፣ ራሳቸው አይሁዶቹ ናቸው ካናዳ ያሉትን አሰሪዎቼን ያነጋገሩልኝ። ለ4 ዓመታት  ልጆች  በጥሩ ሁኔታ ካሳደግኩኝ በኋላ ወረቀቴንም አገኘሁ። ሬስቶራንቴንም ከፈትኩ። እነዚህ አሰሪዎቼ በጣም ስለተደነቁብኝና ስለተደመሙብኝ፣ መኪና ገዝተው ሸለሙኝ። እኔም በጣም ደስ አለኝ፡፡  
እርስዎ በሚኖሩበት ካናዳ ያለው ዳያስፖራ፣ ለሀገሩ ያለው ስሜት ምን ይመስላል?
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በውጭ ሲኖር፣ የሀገር  ፍቅር የሌለው የለም። ሁሉም አገሩን ይወዳል። ሰው በውጪ ሲኖር የሚበላው፣ የሚኖርበት አያጣም። ጥሩ ይለብሳል፣ ቤትና መኪናም ይኖረዋል። ሁሉ ነገር የተሟላለት ነው፤ የሚጎድለን ነገር ቢኖር ቤተሰብና የሀገር ፍቅር ነው። እንደምታውቂው ደግሞ የሀገራችን ችግር አለ። የሀገር ችግር ደግሞ ጣት ተበላሽ ተብሎ ተቆርጦ እንደማይጣለው ሁሉ ሀገር ስትቸገር ገሸሽ ማለት አይቻልም። ሀገርን እስከ ችግሯ እስከነ መከራዋ ነው መቀበል ያለብን። እኛ ያደግንበት ትዝታኮ ተፍቆ የማይጣል፤ ከባድ ነገር ነው። ስለዚህ እኔም ሆንኩ ሌላው ኢትዮጵያዊ፣ የሀገሩን ፍቅር በደስታና በተድላ የሚለውጥ አይደለም። ለዚህ እኮ´ነው ኪሳችን ትንሽ ዳጎስ  ሲል ምንም ቢሆን አገራችን ላይ ኢንቨስት የምናደርገው። እዚሁ አገራችን  ላይ መጥተን፣ ከተቸገረው ጋር መቸገር፤ ከተደሰተው ጋር  መደሰት፣ ከታመመው ጋር መታመም... እንፈልጋለን። እግዚአብሔር ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን እንጂ ይሄ የምለውን ነገር ሁሉ አገሬ ላይ ማድረግ እፈልጋለሁ። እግዚአብሔር ይርዳን እንጂ ሌላውም ይሄንን ይመኛል። ምክንያቱም ሀገርን የመሰለ ነገር የለም፤ አይኖርምም፡፡ እዚህ ምድር ላይ ሺህ ዘመን አንኖርም። እድሜ ልካችንን በአላርም ተኝተን፣ በአላርም እየተነሳን ምግብ ሳይጠፋ በራበን ሰዓት እንኳ አንበላም፤ ምክንያቱም አብዛኛው በሰዓት የሚሰራና የሚሯሯጥ ነው። እንደዚህ ካልተሆነ መኖር አይቻልም። ይሄ ሁሉ ስቃይ ማብቃትና አንድ ቦታ ላይ መቆም አለበት፡፡ ውጪ የተወሰነውን እድሜ  በስራ ስንኖር  የሚገኝ ነገር አለ፡፡ ያንን ይዘን አገራችን በመግባት የእረፍትና የጥሞና ጊዜ ማሳለፍ አለብን እኔ ይሄንን ለሁሉም እመኛለሁ፡፡
ብዙዎች ከዚህ ወደ ካናዳ እንዲሄዱና ራሳቸውን እንዲችሉ በማገዝ ይታወቃሉ። እውነት ነው?
እንግዲህ በኢትዮጵያውያን ዘንድ መደጋገፍ መተዛዘን ያለ ነገር ነው። ሬስቶራንት ስትከፍቺ የኢትዮጵያ ሬስቶራንት እንደመሆኑ፣ የምትቀጥሪው ኢትዮጵያውያንን ነው፡፡ እኔን እያዩ ብዙዎቹ ይበረታታሉ፣ እኔም አበረታታቸዋለሁ። ይሄ ግዴታዬ ነው፡፡ እንደውም ግዴታዬ እንደመሆኑ ይህን አደረግኩ፤ ያንን ፈፀምኩ ብሎ መናገሩ አስፈላጊ አይመስለኝም። ነገር ግን ለሰው ያስተምራል ያበረታታል ካልሽ፣ አንዱን ብቻ ልንገርሽ፡፡ ለምሳሌ እኔን ለረጅም ጊዜ በኪችን ውስጥ ስትረዳኝ የነበረች፣ ፅጌረዳ በየነ የተባለች ሴት አለች። በጣም ታታሪና ቀና ልብ ያላት ናት፡፡ እንደኔ የልጆች እናት ናት፡፡ ከእኔ ጋር እየተጋገዝን እየተመካከርን ለአምስት ዓመታት ያህል አብራኝ ሰርታለች፡፡ የእኔን ሞራልና ትጋት በማየትና በመበረታታት፣ ልምድም በመቅሰም የራሷን ሬስቶራንት ከፍታ፣ በጥሩ ሁኔታ እየሰራች ነው፡፡ ልጆቿንም ለቁም ነገር አድርሳለች በዚህ በጣም ደስ ይለኛል። የህይወት ልምድና ተሞክሮዬን፣ በሴትነቴ ያሳለፍኩትን  ከፍታና ዝቅታ፣ የዓላማ ፅናቴን ሁሉ ስነግራቸው ይበረታታሉ፡፡ ብዙዎች በዚህ መንገድ ስኬታማ ሆነዋል፡፡
አሁን አገራችን በውስጥም በውጪም ክፉኛ እየተፈተነች ያለችበት ጊዜ ነው፡፡ እርስዎ ስለ ሃገርዎ ምን ተስፋ ያደርጋሉ?
የደፈረሰ ነገር ሳይጠራ አያልፍም። ማንኛውም ነገር ሲደፈርስ የጥራት ምልክት ነው ብዬ ነው  የማምነው፡፡ እኔ በአገሬ ላይ ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡ ከጨለማ በኋላ ትልቅ ንጋት አለ፡፡ ተፈጥሮንም ብናይ፤ ይጨልማል ይነጋል፡፡ ፀሐይ ማታ ትጠልቃለች፣ ጠዋት ትዋጣለች፤ የኢትዮጵያም ጉዳይ እንደዚሁ ነው፡፡
እኔ በእርግጥ ፖለቲከኛ አይደለሁም፤ በስራና በፀሎት የማምን ሰው ነኝ። እግዚአብሔር ፍቅሩን፣ ሰላሙን፣መቻቻሉን እንዲሰጠን እፀልያለሁ። ከዚህ በተረፈ ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት፣ የቃል ኪዳን ሀገር ስለሆነች እንደጨለመባት የምትቀር አገር አይደለችም፤ አትሆንምም፤ ችግሮቿና ተግዳሮቶቿ እንዳይቀጥሉና ወደ ቀደመው ሰላምና መረጋጋት እንድትመለስ፣ እኛ ልጆቿ ተስፋዎቿ ነን፤ በየተሰማራንበት ስራና ሀላፊነት ላይ በትጋትና በታማኝነት መስራት አለብን እላለሁ፡፡ እኔ የበኩሌን እያደረግኩ ነው።


Read 4340 times