Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 10:29

“ያለፈ ጥረታችንን፣ ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ፤ ከሞከርነው ነገር ይልቅ፣ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ” ፀ.ገ.መ (የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ)

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በርካታ ባለሟሎች፣ ወታደሮችና አማካሪዎች የነበሯቸው አንድ ተዋጊና ጀግና ንጉሥ በ18ኛው ክፍል ዘመን ይኖሩ ነበር ይባላል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ታላቅ ውጊያ ተዋግተው ሲመለሱ፤ መኳንንቶቹና ወታደሮቹ ሹመት ካልተሰጠን ብለው አስቸገሯቸው፡፡

ንጉሡም እንሾም ያሉትን ሁሉ ሰበሰቡና፤

“በሉ እንግዲህ እያንዳንዳችሁ በምን ምክንያት  ሹመት እንደምትጠይቁ አስረዱኝ?” አሉና ጠየቁ፡፡

ኮነሬሉ ተነስተው፤

“እኔ በእኛ ጦር ውስጥ ከ20 ዓመት በላይ ያገለገልኩ ስለሆነ ሹመት ይገባኛል” አሉ፡፡

ፊታውራሪው ተነሱና፤

“እኔም ለ18 ዓመት በአዝማችነት ሳዋጋ ነበር፡፡ ስለዚህ ሹመት ተገቢዬ ነው!” አሉ፡፡

ነጋድራሱ ብድግ ብለው

“ብዙ ጦርነት ሄድን ብዙ ውጣ ውረድ አየን፡፡ ሹመታችን ግን አንዲት ሣንቲም ከፍ አላለም፡፡” አሉና ተቀመጡ፡፡

ዋግ - ሹሙ ተነስተው፤

“ንጉሥ ሆይ ሹመትን የበላ ጅብ አልጮህ ካለኮ ሰነበተ፡፡ ብዙ አገለገልን፡፡ ግን እዚያው ባለንበት ቆመናል!”

ቀኛዝማች ተነስተው፤

“ንጉሥ ሆይ! ከርሶ ጋር ሳንለይ ዳገት ወጥተን ቁልቁለት ወርደን መከራ አይተን፣ ጠላትን አባረን፤ ከፊሉን ማርከን አገራችንን እዚህ አድርሰናል፡፡ በጀብዷችን ልንካስ፣ ልንሾም ልንሸለም ይገባል!” አሉና በኩራት ተቀመጡ፡፡

በዚህ ዓይነት ባለሟሎቹ ሁሉ የአገልግሎት ዘመናቸውን እየጠቀሱ ልንሾም ይገባል አሉና ጠየቁ!

ንጉሡም፤

“ባለሟሎቼ፤ መኳንንቶቼ፣ ወታደሮቼ!

ለረዥም ዘመናት ከእኔ ጋር ሆናችሁ አገልግሎት እንደሰጣችኝ ጠቅሳችሁልኛል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፤ ሹመት የሚሰጠው በአገልግሎት ዘመን ርዝመት ከሆነ መሾም ያለበት 42 ዓመት ሙሉ ከእኔ ጋር ጦር ሜዳ ለጦር ሜዳ ሲንከራተት የነበረው ፈረሴ ነው!” አሉ፡፡

ባለሟሉ ሁሉ ኩም አለ፡፡

ንጉሡ ቀጠሉና፤

“ለመሆኑ እስቲ ስለ እኔ ንገሩኝ?” ሲሉ ጠየቁ፡፡ መኳንንቶቹ ተፈራሩና “ሁላችንም ከምንናገር፤ አንድ ተወካይ መርጠን እኛን መስሎ፣ እኛን አክሎ ይናገርልን” አሉና ፈቃድ ጠየቁ፡፡

ተፈቀደላቸው፡፡ ተመካከሩና ጨረሱ!

ተወካይ ተመረጡና ሊናገሩ ተነሱ

“ንጉሥ ሆይ! በመሠረቱ የእርሶን ሥራ ዘርዝረን አንጨርሰውም!! ጀግና የጦር መሪ ነዎት፤ አስተዋይ አስተዳዳሪ ነዎት፡፡ የጉግሥ ጨዋታ አዋቂና አሸናፊ ነዎት፡፡ ጦር ወርዋሪና አዳኝ ነዎት፡፡ የአገር ቀያሽ የአገር መሀንዲስ ነዎት፡፡ ጦር ወርዋሪና አዳኝ ነዎት፡፡

የዕውቀትና የትምህርት ሰው ነዎት፡፡ ያልከፈቱት ተቋም፤ ያላስፋፉት ኢንዱስትሪ የለም፡፡ የረገጡት መሬት ይለመልማል፡፡ ያረሱት እርሻ ባንዴ ያዘምራል…” ብለው ተጨብጭቦላቸው ተቀመጡ፡፡

ይሄኔ ንጉሡ ድምፃቸውን አጠሩና፤

“ወዳጆቼ

የተናገራችሁትን ሰማሁ፡፡ ግን እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ ይሄን ሁሉ ሥራ የሠራሁት እኔ ከሆንኩ፤ እናንተ ምን ስትሠሩ ከረማችሁ?!” ብለው ወደመጡበት እንዲሄዱ አደረጉ፡፡

***

አገር ከሚያወሩ አፎች ይልቅ የሚሠሩ እጆችን ትሻለች፡፡ አገር የምታድገው በደቦ ነው፡፡ በወል ሡታፌ ነው፡፡ ሀገራችን ብሔራዊ ሀዘኗን ስትጨርስ ወደፊት ለመጓዝ እያንዳንዱ የግሉን ሀላፊነት በነጠላ፣ የሕብረቱን ኃላፊነት በጋራ ለመወጣት የመንፈስም፣ የአካልም ጥንካሬና ጽናት ትፈልጋለች፡፡ ነገን አስተማማኝ የሚያደርገው ከአፋም ይልቅ ልባም፣ ከስሜታዊ ይልቅ ረግቶ አረጋጊ፣ እንደወይራ አልታጠፍም ከሚል ይልቅ ተግባብቶ አላስፈላጊውን አስወግዶ፣ ተገቢውን አክሎ ተጓዥ፤ አስተዋይ አመራር ነው፡፡ ስለሉዓላዊነት መከበር ስናወሳ፣ ስለመልካም አስተዳደር ስናወራ፣ ስለ ዲሞክራሲ ስንናገርና ስለፍትሐዊ ሥርዓት ስናወጋ ሰላምንና መረጋጋትን፤ እንዲሁም ብስለትንና አርቆ አስተዋይነትን ዋቤ አድርገን መሆን አለበት፡፡

የጐደለንን ለመሙላት ከአንድ ራስ ሁለት ራስ ብለን፣ መክረን ተመካክረን መሆን አለበት፡፡ ይሄን ደምረን ይሄን እናተርፋለን በሚል የአፍንጫ ሥር ቀመር (Shop – keeper’s analysis እንደሚሉት ፈረንጆቹ) መሄድ ሁሌ አያዋጣም፡፡ የበሰለና ሥር - የሰደደ ትንተና፣ ከወገናዊነትና ከሽኩቻ የፀዳ አስተሳሰብ እንደሚያስፈልግ ማሰብ ይገባል፡፡ ሌሎችን የማሳተፍን ባህል በቅጡ መለማመድ ለአዲስ ራዕይ በር ይከፍታል፡፡ ከእርግቧ ጐጆ ውጪ (Beyond the pigeon – hole) ለማሰብ ዝግጁ መሆን አለብን፡፡ የጥፋታችን ስብስብ፣ ታሪክ ከሚሆን ይልቅ፣ የማይሞት መልካም ሥራ ማቆየትን እናምልክ፡፡ ከሟርት እንውጣ!

ተስፋ እንጂ ሞት አገር አያኖርም!

“እናም ታሪክ የሚሠራው፣

እራሳችን ውስጥ ባለው፣

በእኛው እኩይ - ተግባር ነው

ለመልካምነት ግና፣ ጊዜ - እሚባል ፅንፍም የለው!”

(“History is made by the criminal in us

Goodness is timeless.”)

ይለናል ኦደን፡፡

መልካም የሠራ ዘለዓለማዊ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው!

ዛሬ ሀገራችን መሪዋን አጥታ ያለችበት ሐዘናዊ ንፍቀ ክበብ ውስጥ ናት፡፡ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ትፈልጋለች፡፡ ጽናትን ትጠይቃለች፡፡

ከሁሉም በላይ ግን ያልተሠሩትን ነገሮች መሥራት፣ ያላየናቸውን ሠናይ ተግባራት መተግበር፣ ዓለማቀፋዊ ስሟ እንዳይደበዝዝ በምን እንተካው ማለት ዋና ነገር ነው፡፡ መሪው እጽፋቸዋለሁ ብለው ሳይጽፏቸው የቀሩትን በከፊልም ቢሆን የተገኙትን ማሰባሰብ ሌላው መዘክር ሊሆን ይችላል፡፡ ያልጨበጥናቸውንና ያላገኘናቸውን እሴቶች ለመጐናፀፍ በቁጭት ከገጣሚው ጋር፤ “ያለፈ ጥረታችንን፤ ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ

ከሞከርነው ነገር ይልቅ፣ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ!” ማለት ይገባናል!

 

 

Read 3563 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 10:32