Saturday, 15 May 2021 00:00

የቢሊየነሮቹ ጥንዶች ድንገተኛ ፍቺ!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  - የ140 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ለሁለት ይካፈላሉ
         - የፍቺው መንስኤ አልታወቀም

               ቢሊየነሮቹ ቢል ጌትስና ሜሊንዳ ጌትስ ባለፈው ሳምንት ፍቺ (ሜይ 3) ለመፈፀም መወሰናቸውን ይፋ ሲያደርጉ ብዙዎች ተደናግጠዋል። ለ27 ዓመታት የዘለቀው ትዳራቸው  ሰላማዊና የተረጋጋ እንደነበር ይነገራል። በቢዝነስ ስራቸውና በበጎ አድራጎት እንቅስቃሴያቸው  ስኬትና ዕውቅና ተቀዳጁት ጥንዶቹ ሦስት ልጆችንም አፍርተው ለቁም ነገር አብቅተዋል- አሁን የኮሌጅ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው። ጥንዶቹ የ45 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያፈሩ ሲሆን በስማቸው የሚንቀሳቀስ የ50 ቢሊዮን ዶላር ፋውንዴሽን መስርተዋል- የዛሬ 20 ዓመት። ይሄ ሁሉ ግን ትዳራቸውን ከፍቺ አልዳነም። ፍቺውን ተከትሎም የ140 ቢ.ዶላር ሃብት ክፍፍል እንደሚፈጸም ታውቋል። ፍቺው “የቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽንን” የወደፊት ዕጣ ፈንታን ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባው ተነግሯል።
ቢል ጌትስና ሚሊንዳ ጌትስ የተዋወቁት እዚያው ማይክሮሶፍት ውስጥ ነው። የማይክሮሶፍት መስራቹ ቢል ጌትስ፤ ያኔ የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ የነበረ ሲሆን ሚሊንዳ ደግሞ የመልቲ ሚዲያ ምርቶች ማርኬቲንግ ማናጀር ነበረች። እ.ኤ.አ በ1987 የፍቅር ግንኙነት የጀመሩት ጥንዶቹ፤ በ1994 ዓ.ም በሃዋይ ደሴት ላይ ጋብቻውን ፈፅመዋል። በሲያትል የዋሽንግቶን ሃይቅ ዳርቻ ላይ የተንጣለለ ቪላ ውስጥ የሚኖሩት። በእርግጥ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ሌሎች መኖሪያ ቪላዎች እንዳላቸውም ይታወቃል።
እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም የተመሰረተው “ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን”፤  በአፍሪካና ሌሎች ታዳጊ አገራት የማህበረሰብ ጤና፣ የአየር ንብረት ለውጥና በትምህርት ላይ አተኩሮ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው። ባለፉት 20 ዓመታት ባደረገው እንቅስቃሴም የብዙዎችን ህይወት በመለወጥ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን በዓለም ግዙፉ የግል የበጎ አድራጎት ድርጅት ለመሆን በቅቷል።
ሜሊንዳ ጌትስ “ፓይቮታል ቬንቸርስ” የተሰኘ የኢንቨስትመንት ተቋም በ2015 በግሏ የመሰረተች ሲሆን ተቋሙ በአሜሪካ የሚገኙት ሴቶችና ቤተሰቦችን ለመደገፍ እንዲሁም ማህበራዊ ግስጋሴን ለማምጣት አልሞ የሚሰራ ነው ተብሏል።
ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ጥንዶቹ ፍቺ ለመፈጸም መወሰናቸውን ባለፈው ሜይ 3 ይፋ ሲያደርጉ፤ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት አጭር መግለጫ፤ “በቀጣዩ የህይወታችን ምእራፍ ጥንዶች ሆነን አብረን መቀጠል እንችላለን ብለን አናምንም” ብለዋል። ሜሊንዳ ጌትስ በበኩሏ፤ “ይሄ ትዳር ሊጠገን በማይችል ሁኔታ ፈርሷል” ብላች- በፍቺ ማመልከቻዋ ላይ።
“ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል” እንደዘገበው፤ የቢሊየነሮቹ ትዳር ድንገት አይደለም ለፍቺ የበቃው። ሚሊንዳ ጌትስ  ከ2019 ጀምሮ ፍቺ ለመፈጸም የተለያዩ ጠበቃዎችን ስታማክር ቆይታለች። ለዚህ ውሳኔዋ ያበቃት ደግሞ ቢል ጌትስ፣ በወሲብ ንግድ ተከሶ ከተፈረደበት ጄፍሪ ኢፒስቲን ጋር ግንኙነት እንዳለው ከተገለፀ በኋላ ነው ብሏል- ጋዜጣው።  ኒውዮርክ ታይምስ በኦክቶበር 2019 ባቀረበው ዘገባ፤ ቢል ጌትስ ከ2011 ጀምሮ ከኢፕስቲን ጋር ለበርካታ ጊዜያት መገናኘቱን ጠቁሟል። ቢል ጌትስ በበኩሉ፤ ከኢፕስቲን ጋር ምንም ዓይነት የቢዝነስም ሆነ የወዳጅነት  ግንኙነት እንደሌለው አስተባብሏል- በወቅቱ።
ጥንዶቹ ፍቺያቸውን ይፋ ባደረጉበት ዕለት፣ ቢል ጌትስ ከ1.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የአክስዮን ድርሻ ለባለቤቱ ማዛወሩን ዘገባዎች ያመለክታሉ። የሃብት ክፍፍሉ አካል ይመስላል።
ቢሊየነሮቹ ጥንዶች የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ባሉት ጊዜያት  በሥራ ተጠምደው ነው የከረሙት። ፋውንዴሽኑ ኮቪድ -19ን ለመከላከል የሚደረገውን ዓለማቀፍ ጥረት ለመደገፍ 1.75 ቢሊዮን ዶላር የለገሰ ሲሆን በኮቪድ-19 ክትባቶች ጥናትና ምርምር ላ አስተዋፅኦ ማድረጉ ተዘግቧል።
እንግዲህ የሁለቱ ታዋቂ የዓላማችን ቢሊየነሮች ፍቺ አይቀሬ ከሆነ ዘንዳ ቀሪው በከፍተኛ የህግ ባለሙያዎች የታገዘ የሃብት ክፍፍል ይሆናል። ጥንዶቹ ሃብታቸውን እኩል የሚካፈሉ ከሆነም ሚሊንዳ ጌትስ በዓለማችን ሁለተኛዋ የሴት ቢሊየነር እንደምትሆን ዘገባዎች ይጠቁማሉ። በክፍፍሉ የ70 ቢ.ዶላር ገደማ ሃብት ይደርሳታል። በዚህ መሃል የሚነሳው ጥያቄ ታዲያ የቢልና ሜሊንዳ ሶስት ልጆችስ ምን ያህል ገንዘብ በውርስ ያገኛሉ የሚለው ነው።
በነገራችን ላይ ሶስቱም ልጆቻቸው ነፍስ ያወቁ የኮሌጅ ተማሪዎች ናቸው። እነሱም የ25 ዓመቷ ጄኒፈር ካታሪን ጌትስ፣ የ21 ዓመቱ ሮሪ ጆን ጌትስ እና የ19 ዓመቷ ፎቢ አዴሌ ጌትስ በመባል ይታወቃሉ።
በአሁኑ ወቅት የዓላማችን አራተኛው ቢሊየነር እንደሆነ የሚታወቀው ቢል ጌትስ በተደጋጋሚ በሰጠው መግለጫ፤ አብላጫውን የሃብቱን ድርሻ የሚሰጡት ለቤተሰቡ ፋውንዴሽን መሆኑን አስታውቋል። ልጆቻቸው  ከሃብቱ የሚደርሳቸው 10 ቢሊዮን ዶላር ብቻ  ነው ተብሏል።
እ.ኤ.አ በ2017 ቢል ጌትስ ለልጆቹ ለምን ከፍተኛ ገንዘብ በውርስ እንደማይሰጥ አስረድቷል። “ለልጆች ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብቱን ማውረስ ውለታ አይደለም። የራሳቸውን የህይወት መንገድ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት ያበላሻል።” በማለት።
የቢሊየነሮቹ የሃብት ዝርዝር
-  ዋሺንግተን ሃይቅ ደርቻ የሚገኝ የተንጣለለ
   የመኖሪያ ቪላ-65 ሚ.ዶላር
- በፍሎሪዳ፤ ዌሊንግተን የሚገኝ መኖሪያ ቤት-
   55 ሚ.ዶላር
- በካሊፎርኒያ፤ ኢንዲያን ዌልስ የሚገኝ መኖሪያ
   ቤት-1 ሚ.ዶላር
- በማዕከላዊ አሜሪካ ቤሊዜ የሚገኝ የግል
  ደሴት- 25 ሚ.ዶላር
- ቅንጡ የስፖርት መኪናዎች ስብስብ
   - 650 ሺ   ዶላር
- የስነ-ጥበብ ስብስብ (የሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ
   ስራዎችን ጨምሮ)- 130 ሚ.ዶላር
- ካስኬድ ኢንቨስትመንት (ኩባንያ) -29.9
   ቢ.ዶላር
- ዲሬ ኤንድ ካምፓኒ (አክስዮን)- 11.9 ቢ.ዶላር
- የካናዳ ብሔራዊ የባቡር መስመር (አክስዮን)-
   11 ቢ.ዶላር
- ዲያጎ (አክስዮን)- 1.6 ቢ.ዶላር
- ማይክሮሶፍት (አክስዮን) - 26.1 ቢ.ዶላር
የዓለማችን ሁለቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ቢሊየነሮች ፍቺ  የዓለማቀፍ ሚዲያዎች ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ነው የሰነበተው። በተለይ ደግሞ ጥንዶቹ ፍቺውን ይፋ ከማድረግ ባለፈ ምክንያታቸውን ለመግለፅ አለመፍቀዳቸው ሁሉም የየራሱን ግምትና መላ ምት እንዲሰጥ አስገድዶታል። የጥንዶቹ ትዳር ለሶስት አስርት ዓመታት ገደማ መዝለቁና የሁለቱም ባለትዳሮች ዕድሜ ከ50 ዓመት ያለፈ መሆኑ ለብዙዎች ፍቺውን እንቆቅልሽ አድርጎባቸዋል። የማይክሮሶፍት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ ለበርካታ ዓመታት ኩባንያውን የመራው ቢልጌትስ፤ በ2009 ዓ.ም ከዋና ሥራ አስፈፃሚነቱ የለቀቀ ሲሆን ዓምና ደግሞ ከቦርድ ሊቀ መንበርነቱ በፈቃዱ አስረክቧል። ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ በአሁኑ ሰዓት ፋውንዴሽንን በሊቀ መንበርነት እያስተዳደሩት ይገኛሉ። የጡረታ ዘመን ሥራቸው ያደረጉትም ይመስላል።
ጥንዶቹ በአሁኑ ሰዓት ይህ የቤተሰቡ ፋውንዴሽን ከፍቺው በኋላ ይቀጥላል ወይ የሚለው ጉዳይ ለብዙዎች ጥርጣሬ  የፈጠረ ቢሆንም ጥንዶቹ ግን ፋውንዴሽኑን በተመለከተ ምንም የሚለወጥ ነገር እንደማይኖር ነው የገለፁት። ግን ግን ጥንዶቹን ለፍቺ ያበቃቸው ምክንያት ምን ይሆን?  በመሃላቸው ገብቶ ሰይጣን ቢገባ ነው? (የፈረንጅ ትዳር ውስጥ ሰይጣን አይገባም እንዴ?!)


Read 863 times