Saturday, 15 May 2021 00:00

የራስን እያጣጣሉ...‘መሰልጠን!’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

 እንኳን ለኢድ አልፈጥር አደረሳችሁ!
 ኢድ ሙባረክ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በቅርቡ ነው፡፡ እሱዬው የሆነች ቆንጅዬ ጫማ አድርጓል፡፡ እናላችሁ... አንድ ‘ዘመናዊነትን’ አስገድዶ የእሱ አገልጋይ ለማድረግ መከራውን እያየ ያለ የሚመስል ወዳጅ አለው፡፡ ሲገናኙም ገና ጫማውን እንዳየ በቃ፣ ይቁለጨለጫል፡፡
“አንተ እንዴት አይነት ምርጥ ጫማ ነው ያደረግኸው!”
“ወደድከው?;
“ወደድከው ብቻ! ኬት ነው የተላከልህ?
“ማለት..?;.
“ማለትማ የት ያሉት ዘመዶችህ ናቸው የላኩልህ? ይሄ ወይ የጣልያን፣ ወይ የስፔይን ጫማ መሆን አለበት;
“እዚሁ ነው የገዛሁት”
“እንዲህ አይነት ጫማ ኢምፖርት ያደርጋሉ ማለት ነው!”
“አልተረዳኸኝም፣ ይሄ የሀገር ውስጥ ጫማ ነው፡፡ እዚሁ በእኛ ፋብሪካ የሚሠራ ነው”
ይኼኔ ምን ቢሆን ጥሩ ነው... የሆነ እንቆቆ ወይም ከእንቆቆም ባስ ያለ አምስት ሺህ ቮልት ያህል የኤሌትሪክ ሀይል የሚለቅብን ነገር ያጠጡት ይመስል ሁለመናው ይኮመታተራል፡፡
“እኔ እኮ የውጪ መስሎኝ ነው፡፡ ምን አለ በለኝ፣ ከአስራ አምስት ቀን በላይ ሳታደርገው ብጥስጥስ ነው የሚለው!”
አያችሁልኝማ! በዚህም ዘመን፣ ስንት የተሻሻሉ ነገሮች ባሉበት ጊዜ፣ ነገሮችን በመፈተሽ፣ በመጠየቅና እህ ብሎ በማዳመጥ መገንዘብ በሚቻልበት ዘመን የሀገር ውስጥ ጫማ ስለሆነ ብቻ... አለ አይደል... “ምን አለ በለኝ፣ ከአስራ አምስት ቀን በላይ ሳታደርገው ብጥስጥስ ነው የሚለው!” አይነት ንግግር አያሳፍርም! አሁንም ከድንበራችን ውጪ ያለው ምኑም፣ ምናምኑም አሪፍ፣ ከድንበራችን ወዲህ ያለው ምኑም ምናምኑም ቀሺም ብሎ ነገር፣ ከጊዜ ጋር ባለን ሩጫ፣ ምን ያህል ወደ ኋላ የመቅረታችን ምልክት ነው፡፡ (‘ሥነ ጽሁፍ’ ምናምን ሞካከረኝ እንዴ!
ስሙኝማ...ጣት መቀሳሰር ቀላል ስለሆነ አንጂ በዚህ የሀገር ውስጥ የሆነውን ነገር ሁሉ በማጣጣል ነገር ውስጥ አብዛኞቻችን ገና ያልለቀቀን፣ እርግማን ሊሆን ትንሽ የቀረው ባህሪይ አለብን፡፡ እርግጥ ነው፣ በ‘ቦተሊካው’ እልም ያልን የዓለም ቀሺሞች ነን፣ በፖለቲከኞችም አልሸሹም ዘወር አሉ አይነት ነው፡፡ በአክቲቪስትነት እልም ያልን የዓለም ቀሺሞች ነን፡፡ ምናልባት እነኚህን ነገሮች ከዕለታት አንድ ቀን አሪፍ እንሆንባቸው ይሆናል፡፡ ምልክቶቹን ገና እያየን ባይሆንም፣ መቼ እንደምናያቸው ባናውቅም፣ በዚህ ክፍለ ዘመን ለመታየታቸው እርግጠኞች ባንሆንም፡፡
ነገር ግን ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ይህን ነገር አልፎ፣ አልፎ ማንሳታችን አልቀረም፡፡ ግን እኮ በባዶ ሜዳ “የሀገር ውስጥ ምርት ካልሸመትክ እንቁላል ሻጭ ነህ...” አይነት ነገር ሳይሆን፣ ከቀድሞው በተለይ በጥራት በእጅጉ የተሻሻሉ ነገሮች እንዳሉ በማስረዳት ማሳወቅ ይቻላል፡፡
እናማ...ከዚህ ቀደምም እናነሳው የነበረ ነገር፣ አሁንም እንዳለ ነው ለማለት ያህል ነው፡፡ 
“ከአማርኛ ልብወለዶች የምትወደው መጽሐፍ የትኛው ነው?”
“አማርኛ ልብወለድ ነው ያልከኝ!”
“አዎ አማርኛ ልብወለድ፤ ምነው?”
“እዚሀ ሀገር ምን አማርኛ መጽሐፍ አለና ነው የማነበው!”
“ጥሩ፣ ግን እስካሁን ምን ያህል አንብበሀል?”
“እየነገርኩህ እኮ ነው፡፡ አማርኛ አላነበብኩም፣ እያነበብኩ አይደለም፣ ወደፊትም እስከ መጨረሻው አላነብም፡፡”
“ከአንጀትህ ነው! አንድም መጽሐፍ አንብበህ አታውቅም?”
“እንኳን ሙሉ መጽሐፍ አንድም ገጽ አንብቤ አላውቅም፡፡”
“ታዲያ አንድም ገጽ አንብበህ ሳታውቅ፣ እንዴት ብለህ ነው፣ ‘ምን አማርኛ መጸሐፍ አለና ነው’ የምትለው!”
እዚህ ላይ አይደል ጥያቄው! ስሙኝማ... በዚህ ወቅት ስንት ነገር በሚታወቅበት ዘመን፣ አንዲት ገጽ እንኳን የእኛ የሚባል መጽሐፍ ሳናነብ፣ መጽሐፉ በእኛ ሰው ስለተጻፈ  ብቻ #ቀሺም; ነው ማለት በራሱ ቀሺም አይሆንም! የምር ግን...ምኑንም ጠልቀን ሳናውቀው፣ ይሄ የሀገር ውስጥ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ እኛ ነካ ያደረግናትን ነገር ሁሉ፣ ማጣጣል ላይለቀን ነው! እናማ... በታሪክ ስንትና ስንት ብዕራቸው የተባ ዜጎች ያልነበሩን ይመስል፣ አሁንም ስንትና ስንት የሚጥሩ ወጣትና አንጋፎች ባሉበት ዘመን፣ አንዲትም ገጽ ሳያነቡ “ምን አማርኛ መጽሐፍ አለና ነው!” ብሎ ነገር በቃ...ከዘመናዊ እንቁላል ሻጭነት ለይተን አናየውም! ቂ...ቂ...ቂ...
ስሙኝማ.. እንግዲህ ጨዋታም አይደል...መቼም ማንበብ አሪፍ ልምድ ነው፡፡ እንደው...አለ አይደል... “አጉል ቻርለስ ዲክንስ፣ ሼክስፒር ቅብጥርስዮ አትሁንብን፣” አትበሉኝና ንባብን የመሰለ ሁልጊዜ አትራፊ ልምድ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ አሁን እዚሀ ሀገር እንዳለንበት ለመግለጽ እንኳን አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ፣ አእምሯችንን ሺህ ቦታዎች ሊሰነጣጥቁ የሚሻሙ ነገሮች በበዙበት፣ ማንበብ አሪፍ የቻይና ግምብ ነው፡፡ አለ አይደል...ብንሳሳት እንኳን አውቀን መሳሳቱ ይሻላል፡፡  (እፎይ፣ ‘በቅስቀሳው’ የድርሻዬን ተወጣሁ አይደል!)
እናላችሁ... ስለ ንባብ ስናወራ ምን ይገርመኛል መሰላችሁ... ለምንድነው የሌለንን ልምድ በግድ ያለን የምናስመስለው! የሰማይ ስባሪ የሚያካክሉ ዓለም አቀፍ ስሞች እየጠቀሱ... “የእሱን ሥራዎች ሁሉንም ማለት ይቻላል አንብቤለታለሁ...” ማለት ምን ያስፈልጋል! ማለቴ ጠበቅ አድርጎ የሚጠይቅ ሲመጣ እኮ መፋጠጥ ይሆናል፡፡
ታዲያላችሁ... አንድ ጊዜ ዩቫል ሀሪሪ ከተባለው ጸሀፊ ሥራዎች በተለይ ‘ሳፒያንስ’ የተባለው ታትሞ በወጣ ጊዜ ሽያጩ፣ መጽሐፍ አካባቢ ያለውን ነገር እናውቃለን የሚሉ ሰዎችን ሳይቀር ‘ጉድ’ አሰኝቶ ነበር። በዛ ሰሞን ድንገት እዚሀ ሀገር የመጣ ሰው ቢያየን፣ “የዚህ ሀገር ሰዎች እንዲህ የጠለቁ የእንግሊዝኛ መጽሐፍትን ማንበባቸውን አላውቅም ነበር፣” ምናምን ባለ ነበር፡፡ ያው እስካሁን አፋችንን ሞልተን “አነበብኩት እኮ!” የምንል ድምጻችን ይህን ያህል ባይሰማም። እናማ... የዳንኤል ስቲልን መጽሐፍ “ትንሽ እንግሊዝኛው ከበደኝ፣” የምንል ሰዎች፣ “በዚህ ክረምት አትላስ ሽረግድን ነው የማነበው፣” ስንል ትንሽ...አለ አይደል...ባቡሩ ሀዲዱን ይለቃል፡፡ አንባቢ ለመሆን የ‘ፈረንጅ አፍ’ መጽሐፍ ማንበብ ግዴታ አይደለም ለማለት ነው፡፡ “ምን የአማርኛ መጽሐፍ አለና ነው!” ከማለት በፊት እስቲ ከኋለኞቹ ዘመናትም፣ ከዚህ ዘመንም አለፍ፣ አለፍ እያሉ ማንበቡ አያከስርም፡፡ አውቀን መተቸቱ ይሻላል ለማለት ያህል ነው፡፡  
“ፊልም ትወዳለህ?”
“እንደ ፊልም የምወደው ነገር የለም”
“እስቲ ስለ አማርኛ ፊልሞቻችን የሚሰማህን ንገረኝ”
“የአማርኛ ፊልሞች ነው ያልከኝ!”
“አዎ...”
“ምን የአማርኛ ፊልም አለና ነው! አይደለም የአማርኛ ፊልሞች ልመለከት፣ የአማርኛ ፊልም በሚያሳዩ ሲኒማ ቤቶች በራፍም አላልፍም፡፡”
“ካየሃቸው እስቲ አንዱን ጥቀስልኝ”
“ነገርኩህ እኮ! በሲኒማ ቤቶቹ በራፍም አላልፍም እልኩህ እኮ!”
አዎ፣ ብዙዎቻችን እንዲህ ነን፡፡ ፊልም የሚመስለን ስቲፍን ሴጋል፣ በባዶ እጁ የአንድ ሙሉ ከተማ ህዝብ ሲረፈርፍና እሱ ጭረት ሳይነካው ሲወጣ፣ የሆነ የፈረንጅ ጀግና ምናምን አሥራ ሁለት በሚጎርስ ሽጉጥ አንድ ጊዜም መልሶ ጥይት ሳያጎርስ፣ ሀያ ሦስት ጊዜ ተኩሶ፣ ሠላሳ ሰባት ሰው ሲረፈርፍ...በቃ እንደዚህ ነው፡፡
“ስማ የእንትናን የሙዚቃ ክሊፕ አየኸው?”
“ማን አልከኝ?
“እንትና...”
“እ...ሶሪ ግን ምንድነው የሚጫወተው? ጃዝ ነው ሮክ ነው?...”  (አይ፣ እንግዲህ!)
“እንትናን እኮ ነው የምልህ! በቀደም አዲስ አልበም አውጥቶ ቲቪ ላይ እንኳን ክሊፑን አላየኸውም?”
“ስለ ሀገር ውስጥ ሙዚቃ ነው እንዴ የምታወራልኝ! ምን ሙዚቃ አለና ነው!”
እመኑኝ፣ በእንደዚህ አይነት የራስን ነገር ሁሉ በማጣጣል ‘የሰለጠንን’ እና ዘጠነኛው ደመና ላይ የተሰየምን የሚመስለን፣ ገና ከጉድጓድ አንኳን ብቅ ያላልን መአት ነን፡፡
ልቦናውን ይስጠንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1604 times