Saturday, 15 May 2021 00:00

"የሁለቱ መደመሮች" መጽሐፍት ዳሰሳ

Written by  አንዳርጋቸው ጽጌ
Rate this item
(0 votes)

 (ክፍል - 6)
በኢትዮጵያ የተደረጉት የትኛዎቹም የግዛት ማስፋፋት ወረራዎች አውሮፓውያኖቹ ደርሰውበት በነበረው የማህበረስብ የእድገት ደረጃ በደረሱ የአካባቢው ሃይሎች ተከናውኖ ቢሆን ኖሮ ወረራውን ተከትሎ ይመጣ ይችል በነበረው ፈጣን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ለውጥ ዛሬ አብዛኛዎቹ ወይም ሁሉም ቋንቋዎችና ባህሎች ጠፍተው ኢትዮጵያ የአንድ ወጥ ቋንቋና ባህል ሃገር ትሆን ነበር። በፈረንሳይ፣ በጣሊያን በጀርመንና በሌሎች የአውሮፓ ሃገሮች የሆነው ይህ ነው። በኢትዮጵያ ግን አልሆነም።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እንደሌሎች የመካከለኛውና የአፍሪቃ ሃገሮች በቅኝ ባላመገዛቷ ከቅኝ ገዥዎች የተረከበችው ማንነትንም ባህልን የሚቦረቡር በፍጥነት የመዘመን ፍላጎት የሚያደናቅፉ  የመንፈስና የሞራል ስንቅ የተራበች ሃገር አይደለችም።
ይህም ሆኖ በዘመናዊነት እንደገነኑት ምእራባውያንና ምስራቃውያን ሃገሮች ተዘጋጀቶ የተቀመጠ፣ አንድ ቋንቋ ከሚናገር፣ አንድ ባህል እና እመነት ከሚጋራ ማህበረሰብ በቀላሉ ሊቀዳ የሚችል አንድ ወጥ የማንነት እሴት የላትም። በዚህ መንገድ የሚቀዳ እሴት የላትም ማለት አለማዊ ልዩ ተፈጥሯዋን የሚያንጸባርቅ የራሷ የሆነ እሴት የላትም ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ የብዙ ባህል ቋንቋ እምነት ያሏቸው ማህበረሰቦች ሃገር መሆኗ አንድ ወጥ ሃገራዊ እሴታችን፣ አንድ ወጥ ብሄር እንዳለባቸው ማሀበረሰቦች ያለ ምንም ድካም ለሁሉም ፍንትው ብሎ ይታያል ማለት አይደለም።
እንግዲህ ከዚህ በላይ እንዳቀረብኩት ለፈጣን የዘመናዊ እድገት ሃገሮችን እንዲነሱ የሚኮረኩረው የአንድ ሃገር ህዝብ ባህሉን፣ ቋንቋውን፣ ትውፊቱን፣ እምነቱን  በጥቅሉ ማንነቱን ከሌሎች ሃይሎች ወረራና ጭፍለቃ ለመከላከል ነው ብያለሁ።  ይህ ሃቅ የበርካታ የዘመኑ ሃገሮች የመዘመን ግፊት ምክንያት እንደሆነ በተጨባጭ መረጋገጡ ላይ ጥያቄ የማናነሳ ከሆነ ቀጥሎ የሚነሳው ጥያቄ የሚከተለው ይሆናል።
በፍጥነት የመዘመን ፍላጎትና ውስጣዊ ግፊት የሚመጣው ታሪክን፣ ባህልን፣ ቋንቋን፣ ተውፊትን፣ እምነትንና ማንነትን ለመከላከል ሲባል ከሆነ የብዝሃን ሃገር የሆነችው ኢትዮጵያ ይህ የመዘመን የእሽቅድድም ግፊት ከየት ልታመጣው ነው የሚል ነው። የበለጠ ግልጽ ለማድረግ፣ አንድ ህዝብ በፍጥነት ለማደግ የሚተጋው ማንነቱን፣ ምንነቱን ባህሉን ቋንቋን ከሌሎች ወራሪዎች ለመከላከል ካለው ትልቅ የክብርና የኩራት ፍላጎት ጋር በተያያዘ ነው ካልን፣ ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው የብዝሃን ሃገር የሆነችው ኢትዮጵያ የትኛውን ማንነት፣ የትኛውን ባህል፣ ቋናቋ፣ የትኛውን ክብርና ኩራት ለመከላከል ነው ህዝብ በህብረት በአንድነት ተባብሮ ዶ/ር አብይ እንደሚለው ተደምሮ ለዘመናዊነት ለብልጽገና ለሰለጠነ አስተዳደር የሚተጋው?
ባለፉት ጥቂት መስመሮች እንዳቀረብኩት የዘመናዊ ማህበረሰብ ግንባታ ፍላጎት የሚመመነጨው ቀጥተኛ ከሆነ ወይም ካልሆነ የባህል የማንነት ወረራና መጨፈለቅ ራስን ለመከላከል ከሆነ ቀጥሎ ደግሞ የሚነሳው ጥያቄ በኢትዮጵያ ወስጥ የሚገኙ የተለያዩ በባህል በቋንቋ በትውፊት ልዩነቶች ላይ የተመሰረቱ ማህበረሰቦች የየራሳቸውን ማንነት፣ ባህልና ቋንቋ ትውፊትና እምነት በተናጠል ይዘው እሱን ለመከላከል ሲሉ ወደ ዘመናዊና ፈጣን እድገት መግባት ይችላሉ ወይ የሚለው ነው? ካልሆነስ እንዴት በጋራ ሆነው በፈጥነት ለዘመናዊ እድገት መነሳት ይችላሉ?
በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ እንደሃገር ማዘመን ካልተቻለ እንዴት ሆኖ ነው ሁሉም ባህልና ቋናቋ ተላባሾች በተናጠል እራሳቸውን ማዘመን የሚችሉት? በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ማህበረስቦች ራሳቸውን ወደ ተፋጠነ ዘመናዊ እድገት ለመምራት በቅድሚያ ራሳቸውን፣ አካባቢያቸው ከሚገኙ ሌሎች ቋንቋዎች ባህሎች ተላባሾች ለይተው የኔ የሚሉትን የተለየ ማንነት የያዘ ግዛት ሊያስፈልጋቸው ነው?  
በዚህ መንገድ ሄደው የተሳካላቸው ከ19መቶ ክፈለ ዘመን መባቻ ላይ ራሳቸውን ሃገር ማድረግ የቻሉ የአውሮፓ ሃገሮች ብቻ ናቸው። ያ ዘመን አልፏል። ባለንበት ዘመን ይህ አካሄድ በኢትዮጵያ ውስጥ መሳካት ይችለል ወይ?
የሃገሪቱ አፈጣጠር፣ የብዝሃነቷ ግዙፍነት፣ ህዝቡ በባህል፣ በእምነት፣ በደም፣ ከምስራቅ እስከ ምእራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ የተጋመደበት ሁኔታ፣ በባህል በእምነት የኔ ናቸው የሚላቸው እሴቶችና ቅርሶች በመላው ሃገሪቱ በተበተኑበት ሁኔታ፣ እነዚህን ቅርሶችና የሀገሪቱን የግዛት አንድነት ከወራሪዎች ለመከላከል ሁሉም ከየቀየው እየተመመ ከቀየው ውጭ ከተለያዩ የወጭ ወራሪዎች ጋር በተደረጉ ውጊያዎች ደሙን እያፈሰሰ የተከላከለበት ሁኔታ፣ ይህን በተለያዩ ማንነቶች ላይ  የተመሰረቱ የነፃ ግዛት ግንባታ ይፈቀዳል ወይ?
ከሰማኒያ በላይ የባህልና የቋንቋ አሃዶች አሉንና ከኢትዮጵያ ሰማንያ አገር ወጥቶ ሰማንያውም በከፍተኛ ፍጥነት የዘመነው አለም ላይ ለመድረስ የሚያስችል አቅምና እሴት ይኖራቸዋል ወይ? በየትኛውም አመክንዮ ይህ መንገድ ሙት መንገድ ለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ብዙ ደጋፊ ሊኖረው የማይችለው ለዚህ ነው።
ታዲያ ሌላው አማራጭ ምን ሊሆን ነው? ኢትዮጵያ የአንድ ባህል ቋንቋ፣ እምነት፣ ትውፊት ተላባሽ ህዝብ ሃገር ካልሆነች፣ ሃያላን እና አስፈሪ የሆኑ ነጮችና ቢጫዎች የሚያሳድሩባትን ጫና ወደፊትም ሊያስከትሉባት የሚችሉትን  አደጋዎች ለመከላከል ለፈጣን እድገት በመኮርኮሪያነት የምትጠቀምበት፣ ማንነት፣ ትውፊት፣ ታሪክ፣ ባህል እምነት ምን ሊሆን ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ የማያወላዳ ነው። “የብዝሃን ማንንነት ላይ የተመሰረተ” የሚል ከመሆን ውጭ ሌላ መሆን አይችለም።
ይህ ውስብስብ የሆነ የሚመስል  የብዝሃን ማንነት ራሱ ኢትዮጵያዊ ማንነት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ይህን ማንነት መሰባሰቢያ አድርጎ የሃገሪቱ ህዝብ በአንድነት መቆም ይችላል። ያለውን ጉልበት፣ አቅም፣ ሃብት፣ አሰባስቦ ሃገሪቱ እንደሃገር፣ ህዝቧ ከነብዝሃነቱ ወደፊት በዘመናዊ ስልጣኔ እንዲገሰግስ የሚያደርግ የመንፈስና የሞራል ስንቅ ከኢትዮጵያዊ ማንነት ውስጥ ማግኘት ይችላል። ብዙዎች እንደሚሰጉት ይህ ስራ ከባድ ስራ አይደለም። ለዚህ ስራ መሰረት የሚሆነው መደላድል ለዘመናት በጋር ሲገነባ ስለነበር እንደሌሎች አፍሪካ ሃገሮች ከዜሮ አንነሳም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አስፈሪ ቡርቦራ ቢካሄበትም ጠቅሎ አልወደመም። እኛ ማድረግ የሚገባን እንደ አውሮፓውያኖች ዳዋ እንዲለብስ አቧራ እንዲሸፍናቸው የተደረጉትን የቅርብና የሩቅ የጋራ ታሪኮቻችንን ዳዋና አቧራቸውን ገፈን የዘመናዊ እድገት ፍላጎታችን መኮርኮሪያ ማድረግ ብቻ ነው።  
በሌሎች የተለያዩ ማንነቶች ባሉባቸው አፍሪካ ሃገሮች እንዲህ አይነቱን ሃገራዊ ፍልስፍና እንገንባ ቢባል ሊያስቸግር ይችላል። ምክንያቱም ነጮች በጉልበት ማሰባሰቢያ ካደረጉት የቅኛ ተገዥነት ሙጫ ውጭ የየአንዳንዱን አፍሪካ ሃገር የተለያዩ ማህበረሰቦችን አንድ አድርጎ የሚያስተሳስራቸው የጋራ ታሪክ የላቸውምና። ብዙዎቹ ሃገሮች የጋራ መሰባሰቢያ የሚሆኑ ነገሮች ለማግኘት አበሳቸውን እያዩ ነው።  ለዚህ ነው የአፍሪቃ ምሁራን የናጀሪያ፣ የጋና፣ የደቡብ አፍሪቃና ውዘተ ፍልስፍና ሳይሆን እነዚህን ሃገሮች የሚሻገር  ሰው ሰራሽ የቅኝ ገዥዎችን ድንበር የሚንድ የአፍሪቃን ህዝብ አንደ አንድ ሰው ሊያስተሳስር የሚችል ፍልስፍና ያስፈልገናል ያሉት።
የአፍሪካ መዘመኛ የሚሆን ፍልስፍና ያላት ሃገር፤
ከሌሎች አፍሪካ ሃገሮች በተለየ ሁኔታ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ማህበረሰቦች ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነትና ትውፊት መትረፍ የቻለው፣ ሁሉም በጋራ ይህን የያንዳንዳቸውን ማንነት ሊያጠፋ ባህር አቋርጦ የመጣን ጠላትን በጋር በመመከታቸውና በጋራ ድል በማድረጋቸው መሆኑን ያውቁታል።
በጋራ ተከላክለን ያተረፍነው ብዝሃነታችን ነው ስንል ትንሽ ከሚመስል ነገር ይጀመራል። ከቋንቋ ከባህል በታች ከሚወርድ ነገር። ኢትዮጵያ ሁሉም አይነት የመልክ፣ የቀለም አይነቶች ያሏት ሃገር ናት። አዎ ሁላችንም ጥቁር ነን። ይህን አላጣሁትም። በራሳችን አይን ግን ነጭነት የሌለብን፣ በጥቁርነት ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የቀለም ዝርያዎች ያቀፈ ዥንጉርጉር ህዝብ ነን።
የዛሬ ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግሬነት፣ ሶማሌነት፣ ጉራጌነትና ወዘተ የተረፈው አድዋ ምድር ላይ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ጉራጌው፣ ትግሬውና ወዘተ ደሙን በጋራ አፍሶ አጥንቱን ከስክሶ ነው። የእምነት የቋንቋና የባህል ልዩነታችን የድክመታችን ምንጭ ሆኖ፣ አድዋ ላይ በጋራ ተሰባስበን ጣሊያንን ማሸነፍ ባንችል ኖሮ፣ ዛሬ ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግራዋይነት፣ ሲዳማነት ወዘተ የሚባል ነገር አይኖርም ነበር።
ክርስትና፣ እስልምና፣ ዋቄ ፈታ፣ አክሱም ጽዮን፣ ላሊበላ፣ አልነጃሺ፣ እሬቻ፣ ጨምበላላ፣ ገዳ፣ ቡሄ፣ አሽንዳ፣ አተቴ፣ ሌሎችም በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ወስጥ የሚገኙ ድንቅ የእምነትና የባህል እሴቶችቻን አይኖሩም ነበር። የሺ ዘመናት እድሜ ያላቸው የተዋህዶ ክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት መትረፍ የቻሉት፣ ክርስቲያኑ ከሙስሊሙ ጎን፣ ሙስሊሙ ከክርስቲያኑ ጎን አድዋ ላይ ወድቆ ነው። እሬቻ የተረፈው፣ እሬቻ ዛሬ በአል ሆኖ የሚከበረው፣ ኦሮሞና አማራ አንድ ላይ ከሌሎች የሃገሪቱ ህዝቦች ጋር በጋራ ጣሊያንን ስለሰበሩት ብቻ ነው። የዘመኑ የኦሮሞ የዋህ ልሂቅ  እንደሚለው፣ ኦሮሞው አማራውን ወይም አማራው ኦሮሞውን ሰብሮት ቢሆን ኖሮ እንኳን እሬቻ ሁላችንም አንኖርም ነበር። አማራና ትግሬ ብቻቸውን አድዋ ላይ ገጥመው በጣሊያን ተሸንፈው ቢሆን ኖሮ፣ ኦሮሞነት አይኖርም ነበር።
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በመቶ ሚሊዮኖች ተከታዮች ያሏቸው፣ ታሪክ የራሱን የዘመናት አሻራ ያሳረፋባቸው፣ ከማንነታችን ጋር የተጋመዱ የክርስትና እና የእስልምና ልዩ እምነቶች አሉን። አድዋ ላይ ተሸንፈን ቢሆን ኖሮ እምነቶቻችንም፣ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ወይም እስልምና ወይም ዋቄ ፈታ ወይም ሌላም ሃገራዊ እምነት መሆኑ ቀርቶ ጣሊያኖች የሚጭኑብን፣ የጣሊያኖች እምነት ብቻ  ይሆን ነበር። ከዛም በታች ተዋርደን ሁሉም ቀርቶ “ደግሞ ለባሪያ የምን  እምነት” ተብለን እንደ ውሻ ከቤተ እምነት ደጃፍ ላይ እንዳንደርስ እንደረግ ነበር።  
የብዝሃነታችን ሚስጥር አንድነታችን ለመሆኑ ትንሽ ሰፋ አድርጎ ማሳየቱ ወደፊት ለማቀርበው የመደመር እይታ ጠቃሚ ስለሆነ ልቀጥል።  
ስማችን ኦኬሎና አርዬት፣ ለሜሳና ጫልቱ፣ ሃጎስና ሃዳስ፣ ሃሰንና ዘይነብ፣ ሃይለ ሚካኤልና ወለተማሪያ፣ አንበርብርና ተዋበች፣ ዘበርጋና ኬርየዢ፣ ኤራቶና መፋያት፣ በርገኖና ጫኪሴ፣ ገቲሶና ሚሸሜ፣ ግሽና እና አቸም፣ ወዘተ የሚል ሆኖ የምናገኘው አያቶቻችን በጋራ ብዝሃነታችንን ሲከላከሉ ደማቸውን በማፍሰሳቸውና አጥንታቸውን በመከስከሳቸው ነው።
ቅደመ አያቶቻችን በጋራ ጣሊያንን መመከት ተስኗቸው ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ ሁሉም የዚህ ሃገር ወንድና ሴት በሙሉ ሰብአዊ ክብራችንን ገፎ በባርነት ሊገዛን ባህር አቋርጦ መጥቶ በነበረው በጣሊያን የባሪያ ገዥ ስም ነበር የምንጠራው። ወንዱን ከዚህ መልስ “ማሪዎ” ተብለሃል፣ ሴቷን ደግሞ ከዚህ መለስ “ማርገሪታ” ተብለሻል እየተባለ የጅምላ ስም ይታደለን ነበር። ለባርነት በተዳረጉ ሌሎች ሃገሮች ይህ የስም አሰጣጥ ተግባራዊ መደረጉን አንርሳ!
ልብሳችን፣ ምግባችን፣ ሙዚቃችን፣ ጭፈራችን፣ ቋንቋችንና ትውፊታችን እንደ ብዝሃነታችን የተዋበና ያማረ ሆኖ መትረፍ የቻለው፣ በጋራ አድዋ ላይ የወደቁ የቅደመ አያቶቻችን የመስዋእትነት ልጆች ስለሆንን ብቻ ነው። አድዋ ላይ ተሸንፈን ቢሆን  አለባበሳችንም አመጋገባችንም አንድ ወጥ የጣሊያን አለባበስና አመጋገብ፣ መልካችንም የጣሊያን ዲቃላ፣ ነጫጭባ፣ ሙላቶ ይሆን ነበር።
አድዋ ላይ ተዋርደን ቢሆን ኖሮ ሁላችንም የምንናገረውም ቋንቋ ጣሊያንኛ ይሆን ነበር። ወይም ከጣሊያን ጋር ተስማማተው ኢትዮጵያ ላይ የሰፈሩ አውሮፓውያን ጌቶቻችን ቋንቋ ይሆን ነበር።
ዛሬ የልዩነትና የግጭት ምክንያት አድርገን የምናቀርበው የዘውግ ማንነት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የዘር ልዩነት ወድሞ፣ ተጨፍልቆ እንደ ሰው በኩራት ሳይሆን፣ ጣሊያን በፋብሪካው ከሚያመርተው ርካሽ የፋብሪካ እቃ ወይም በገመድ ጣሊያኖች አስረው በየፓርኩ ከሚጎትቷቸው ውሾች የተለየ ማንነት የማይኖረን፣ ከቢጫው ዘር በታች የተመደብን፣ የመጨረሻው የተዋረድን የአለም ፍጥረቶች ሆነን እናርፈው ነበር። ያም እድለኞች ከሆንን እንጂ፣ እንዲህ አይነቱ እድል ላይገጥመን ይችል ነበር።
ኢትዮጵያ በብዝሃነት ያሸበረቀችው፣ የኢትዮጵያ ልጆች በቅኝ ከተገዙ የአለም ህዝቦች የተለየን ሆነን የተረፍነው፣ ነጭ ከኛ የተለየና የተሻለ ፍጡር ነው ብለን የማናምነው፣ በአለም አደባባይ አንገታችንን ቀና አድርገን መራመድ የቻልነው፤ የእምነት፣ የባህል፣ የቋንቋና ሌሎችም ብዝሃነታችንን የሚያንጸባርቁ እሴቶቻችን ማትረፍ የቻልነው፣ በጋራ የቆሙ በጋራ የወደቁ ቅድመ አያቶቻችን ልጆች ስለሆንን ነው።
በ19ኛው ምእተ አመት መጨረሻ፣ ነጮች ለጥቁር ዘር የደገሱት ድግስ ምን እንደሆነ በደንብ ለሚረዳ፣ የእኛ ቅደመ አያቶች አድዋ ላይ ተሸንፈው ቢሆን ኖሮ፣ አገራችንን ባህር አቋርጦ ለመጣ ጠላት ማስረከብ ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው በዚች ምድር ላይ መኖራችንም አጠራጣሪ ይሆን ነበር።
የነጮች ህልም በተፈጥሮ ሃብት፣ በመልካም አየር ጠባይና በመሬት ስፋት የታደለችውን አፍሪካ ከውስጧ ነባሩን የጥቁር ዘር  አጥፈተው፣ እንደ አውስትራሊያና እንደ ሰሜን አሜሪካ የነጮች መፈንጫ ለማድረግ ነበር። አላማቸው ለአውሮፓ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ሃብት ከአፍሪካ መውሰድ አልነበረም። የቅኝ ግዛት አላማቸው ጥሬ እቃ ፍለጋ መሆኑ ቀርቶ ሰው ማስፈሪያ ፍለጋ ሆኖ ነበር።
እኛ ኢትዮጵያውያን በአድዋ ድል ስንኮራ የሚያይ የጥቁር ዘር በሙሉ #እኛም  የተረፍነው በእናንተ ቅድመ አያቶች መስዋእትነት ነው። ክብር ለአድዋ ሰማእታት” የሚለን ለዚህ ነው።
አድዋ ላይ ቀደምቶቻችን ጣሊያንን ድል በመንሳት ያተረፉት ከብዝሃነታችን ጋር የተያያዙ የየአካባቢያችንን ትውፊቶች፣ የታሪክ ቅርሶችና ቋንቋዎች ብቻ አይደለም። እነዚህ የየአካባቢውን እምነቶች፣ ትውፊቶች፣ የታሪክ ቅርሶች፣ የሁሉም የሃገሪቱ ህዝብ ሃብቶች እንዲሆኑ በማድረግ ጭምር ነው።
ለወላይታው ወጣት የአክሱም ሃውልት ትርጉም የሚሰጠው ያለ እሱ ቅድመ አያቶች የአድዋ ምድር መስዋእትነት አክሱም የጣሊያን እንጂ የትግሬ ሃገር አለመሆኗን፣ ሃውልቱም የኢምፔሪያል ጣሊያን የድል አድራጊነት ምልክት እንጂ የአንድ አፍሪካዊ ህዝብ የታላቅ ስልጣኔ ማስታወሻ እንደማይሆን ስለሚታወቅ ነው። ሌሎችም ከደቡብ እስከ ሰሜን፣ ከምእራብ እስከ ምስራቅ ያሉ የታሪክ ቅርሶች በሙሉ የአካባቢው ሳይሆኑ የመላው የሃገሪቱ ዜጎች መኩሪያና መመኪያ ቅርሶች ተደርገው የሚታዩት በዚህ ሎጂክ ነው። ያለ ሁሉም መስዋእትነት አንዳቸውም አይተርፉምና ነበርና ነው።
አድዋ፤ ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎችን ብቻ አይደለም ያተረፈው። የትግርኛ የአማርኛ፣ የግእዝ ቋንቋዎች የሚጻፍባቸውን ብቸኛውን የጥቁር ህዝብ የሳባ ፊደልንም ጭምር ነው ያተረፈው። ያለ ኦሮሞ፣ ያለ ከምባታ፣ ያለ ጉራጌ፣ ያለ አፋርና ሌሎችም ህዝቦች ደም አማርኛ ብቻ ሳይሆን ቋንቋው የሚጻፍበትም ፊደል አይተርፍም ነበር። ለዚህ ነው “አንድ ኦሮሞ ይህን ብቸኛ የጥቁር ዘር የሳባ ፊደል የኔም ፊደል ነው። ለትግሬና ለአማራ ብቻ የሰጠው ማነው” ማለት የሚችለው። አፋሩም፤ ወላይታውም፣ ከንባታውም፣ ሱማሌውም፣ ሃድያውም፣ ሲዳማውም ይህን የማለት ሙሉ መብት አለው። ጋምቤላውና ቤንሻንጉሉ ሌሎችም በርካታ የደቡብ ብሔረሰቦች የኔ ነው ብለው እየተጠቀሙበት ነው። የጥቁር ዘር ብቸኛው ፊደል ነው። ሁሉም ኢትዮጵያውያን ደማቸውን ገብረው ያተረፉት ፊደል ነው። የትኛውንም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝን ቋንቋ፣ ባህል፣ትውፊትና ሌላውንም የታሪክ ቅርስ፣ በየትኛውም የሃገሪቱ ግዛት ውስጥ የሚኖር ዜጋ የኔ ጭምር ነው የማለት የሞራል ልእልና ያለው ለዚህ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው ማንኛውም ዜጋ፣ በየትኛውም የሃገሪቱ ክልል በነጻነት እንዳሻው የመኖር፣ ሁሉም ክልል ውስጥ የሚገኝ የከተማና የገጠር መሬት፣ በከርሰ ምድርና ከከርሰ ምድር በላይ የሚገኝ ሃብት የኔ ነው የማለት ሙሉ መብቱን የተጎናጸፈው የዚችን ሃገር መሬትና ሃብት የውጭ ወራሪዎች መሬትና ሃብት እንዳይሆን በጋራ ቅድመ አያቶቹ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ከየቀያቸው እየወጡ በጋራ ደማቸውን አፍሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው የተከላከሉት በመሆኑ ነው። ማንኛውም ብሔር ወይም ብሔረሰብ ዛሬ የሚኖርበትን ክልል ለብቻው ከውጭ ወራሪ ተከላክሎ ባላዳነበት ሁኔታ፣ “ይህ ክልል የኔ ብቻ ነው” አትድረሱብኝ የሚል ንግግር ምንም አይነት የታሪክም ሆነ የሞራል ቅቡልነት ሊኖረው አይችልም።  
ደግሞ ደጋግሞ በታሪክ እንደታየው፣ የታሪክ ጸሃፊዎችም እንደሚያስገነዝቡን፣ ሀገራትን ሃገር ከሚያደርጋቸው ትልቁና ጠንካራ ኩነት ዋናው የአንድ ሃገር ህዝቦች ራሳቸውን ከወራሪ ጠላት በመከላከል በጋራ የከፈሉት መስዋእትነትና በጋራ የሚቀዳጁት ድል ነው። አድዋ የዘመናዊት ኢትዮጵያ የሃገር መሰረት የሆነውም፣ ከመሆንም ውጭ አማራጭ እንዳይኖረን ያደረገው፣ በዚህ ታሪካዊ ትርጉሙ የተነሳ ነው።
ሌላው ከአድዋ ድል ጋር ተያይዥነት ያለው፣ የዛ ድል ምልክት ወይም ምስል ሆኖ በመላው የጥቁር ዘርና በአለም ህዝብ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ነው።
በአድዋ ምድር ላይ የተሰለፉት ከመላው ሃገሪቱ የተሰባሰቡ ጀግኖች የኢትዮጵያዊነታቸው መለያ አድርገው ያውለበለቡት የኢትዮጵያን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለውን ሰንደቅ አላማ ነው። ይህ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የብዙ መቶዎች አመታት እድሜ እንዳለው ይታወቃል። የሩቁን ዘመን ታሪክ እንተወው። ምክንያቱም በዛ ዘመን የኢትዮጵያ አካል አልነበርንምና የዛ ዘመን የሰንደቅ አላማ ታሪክ አይመለከተንም የሚሉ አሉና።
ዛሬ ኢትዮጵያ ብለን በምንጠራት ሃገር ውስጥ ለረጅም ዘመን የሚታወቀው ሰንደቅ አላማ ይኼው የዛሬው ሰንደቅ አላማ ብቻ እስከሆነና ሌላ ተግደርዳሪ ሰንደቅ አላማ እስካልነበረ ድረስ በየትኛውም ወቅት የሃገሪቱ ህዝብ አካል የሆነ ህዝብ፣ ይህን ሰንደቅ አላማ የራሱ አድርጎ ሊቀበለው የሚያስችለው ከሚገባው በላይ በቂ ምክንያት አለው። እንደሌላው ነገራችን የሰንደቅ አላማውም ታሪክ የተወሰነው አድዋ ላይ ነው። ስለሆነ ከአድዋ እጀምራለሁ።
ጣሊያን ድል አድራጊ እንደሚሆን ተማምኖ በአውደ ውጊያው ወቅት የሃገሩ መለያ የሆነውን  አረንጓዴ፣ ነጭና ቀይ ባንዲራውን በኩራት አውለበለበ። ኢትዮጵያውያንም የሃገራቸው መለያ የሆነውን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ  ሰንደቅ  አላማቸውን በኩራት አውለበለቡ። ኢትዮጵያውያን ድል ሲያደርጉ፣ የጣሊያን ባንዲራ በአድዋ ምድር ላይ እንደ አልባሌ ነገር ወደቀ። የሽንፈትና የውርደት ምልክት ሆነ። በአለም አደባባይ ከፍ ብሎ የተውለበለበው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ  ሆነ።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ  ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በዚህ ሰንደቅ አላማ  ስር የተሰለፈው ሁሉም ባለ እምነት፣ ሁሉም ባለ ቋንቋ፣ ሁሉም ባለ ባህል እንደሆነ ታሪክ ከትቦታል። ስለዚህም ነው ሰንደቅ አላማው ጥንታዊነቱ አብቅቶ በኢትዮጵያ ህዝቦች የደም ጠበል ተነክሮ የሁሉም ማህበረሰቦች ቋንቋዎች ባህልና እምነት ባለቤቶች ሰንደቅ አላማ የሆነው። ለዚህ ነው ይህን ሰንደቅ አላማ የትኛውም እምነት ተከታይ፣ የትኛውም ብሔር ወይም ብሔረሰብ የኔ ብቻ ነው ማለት የማይችለው። የኔ ብቻ ነው ለማለት ለብቻው ጣሊያንን መክቶ አላተረፈውምና ነው።
በአድዋ ምድር ከፍ ብሎ የተውለበለበውን ሰንደቅ አላማ ከውርደት ያዳኑት ሁሉም የሃገሪቱ ጀግኖች ልጆች ናቸው። ኦሮሞውም፣ አማራውም ትግራዋዩም፣ ጉራጌውም፣  ክርስቲያኑም ሙስሊሙም ናቸው። ለክርስትና እምነት መዳን በዚህ ሰንደቅ አላማ ስር ተሰልፎ የወደቀው ሙስሊም ከፈለገ ይህን ሰንደቅ አላማ በቤተ መስጊዱ ላይ ማውለብለብ መብቱ ነው። ይህ ባንዲራ ከኔ እምነት ጋር ብቻ የተሳሰረ ነው ለሚለው የትኛውም አካል “እኔ ከጎንህ ባልቆም አንተም፣ እምነትህም ሰንደቅህም አይኖሩም ነበር” የሚል በሃቅ ላይ የተመሰረተ መልስ በልበ-ሙሉነት መስጠት ይችላል።
በሌላ በኩልም ይህን ሰንደቅ አላማ የሁለንተናቸው መገለጫ አድርገው የሚያዩ ዜጎችም ይህን የማድረግ ሙሉ መብት አላቸው። ማድረጋቸው ሊገርመን አይገባም። የሚያስገርመው ባያደርጉ ነበር። ምክንያቱም ባህላቸው፣ እምነታቸው ወይም ቋንቋቸው ብቻ ሳይሆን ህልውናቸውም ሳይቀር መትረፍ የቻለው ይህን ሰንደቅ አላማ በሚያውለበልቡ የሃገሪቱ ልጆች መስዋእትነት ስለሆነ።  
ትልቁ ቁም ነገር የዚህ የሰንደቅ አላማ ባለቤት፣ አንድ አካል ብቻ መሆን የማይችል መሆኑ ነው። ይህን የማለት መብት ያለው ብቸኛ አካል፣ በዚህ ሃገር ላይ እንደሌለ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የኛ ብቻ ነው ለሚሉ አካላት መልሳችን፣ #ያውላችሁ እንዳሻችሁት አድርጉት; በማለት ቅድመ አያቶቻችን በደማቸው በአለም አደባባይ በኩራት እንዲውለበለብ ያደረጉትን ሰንደቅ አላማ ትተን፣ ሌላ  ሰንደቅ አላማ መፈለግ አይደለም። ይህን ማድረግ ለምን እንደማይገባን ተጨማሪ ምክንያት እነሆ፤
በአረንጓዴ ቀይና ቢጫው ሰንደቅ አላማ ስራ ቅድመ አያቶቻችን ተሰልፈው ያዳኑት ቋንቋችንንና ትውፊታችንን ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው በዚች ምድር የመኖራችንን እድል ነው ያተረፉት። ከራሳቸው አልፈው፣ ከእኛ አልፈው፣ የጥቁር ዘርን በሙሉ ነው፣ ከዘላለማዊ ጥፋት ያዳኑት።
አባቶቻችን አድዋ ላይ ተሸንፈው፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ወድቆ የጣሊያን ሰንደቅ አላማ ተውለብልቦ ቢሆን ኖሮ፣ እኛን ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም፣ የጥቁርን ዘር ከምድረ ገጽ የማጥፋቱ ሂደት ይጀመር የነበረው በሽንፈታችን ማግስት ይሆን ነበር።
አባቶቻችን ለነጻነቱ ያነሳሱት ጥቁርን ብቻ ሳይሆን የቢጫውንም ዘር እንደሆነ ከአድዋ ድል በኋላ እስያ ውስጥ የተቀጣጠለውን የነጻነት ትግል በዋቢነት በማጣቀስ የታሪክ ጸሃፊዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
የአድዋ ድል የአለምን የታሪክ አቅጣጫ የቀየረ ታላቅ አለማቀፋዊ ኩነት ነው የሚባለው ለዚህ ነው። በዚህ የተነሳ መላው የጥቁር ዘር ኢትዮጵያውያን በጋራ አድዋ ላይ ያውለበለቡትን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ አላማ  የጥቁርነቱና የነጻነቱ መለያ አድርጎ ወስዶታል። የጥቁር ዘር በሙሉ፣ “እነዚህ  አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት  የአንድነት፣ የቆራጥነት፣ የጀግንነትና የጽናት ምልክቶች ናቸው” አለ። “ከዚህ ሰንደቅ አላማ ጀርባ ያሉትን እሴቶች ከኢትዮጵያ ወስደን” አለ፤ አፍሪካ “የአፍሪካን የተሃድሶ ፍልስፍና፣ ስሙን ኢትዮጵያዊነት ብለን ጠርተን፣ አህጉራችንን ትልቅ አህጉር እናደርጋለን” ብሎ ፎከረ።
አሜሪካኖች የቀድሞዎቹን የአሜሪካ ምድር ኗሪዎች አጥፍተው በጉልበት በያዙት ምድር ላይ የተከሉትን ባንዲራ በባርነት ቀንበር ተገፎ አሜሪካ የሄደ አፍሪካዊ ሳይቀር ባገኘው አጋጣሚ በኩራት የሚያውለበልብበትን ሁኔታ እያየን ነው። እኛ ቅድመ አያቶቻችን በጋራ ነጭን በጀግንነት ያንበረከኩበትን፣ የነጻነትና የአልገዛም ባይ ምልክታችንን፣ በተለያዩ ሰበብ አስባቦች የኔ አይደለም ወደሚል ሄደናል። ይህን የሚያዩ አፍሪካውያን፣ የአፍሪካ ማፈሪያ፣ የአፍሪካ ማድያት እያሉ እንደሚጠሩን ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን?   
“የአፍሪካ ህልውና የአፍሪካ ስልጣኔ፣ የአፍሪካ ገናናነት አፍሪካዊ የፍልስፍና መሰረት ከሌለው እውን ሊሆን አይችልም። በነጮች ፍልስፍና አፍሪካን መገንባት አይቻልም።” ይህ የአፍሪካ ፍልስፍና፣ “ታሪክ አዋጭነቱን፣ ድል አድራጊነቱ በተግባር ያስመሰከረው ኢትዮጵያዊነት ነው” በማለት አፍሪካውያን ወደ እኛ ሲያማትሩ፣ እኛ ምን እያደረግን ነው?
አድዋ ሌላው የሰራው ነገር የኢትዮጵያን የሺዎች አመታት፣ የኋልኛዎቹ ቅድመ አድዋ ታሪካችንን የሁላችንም ማድረግ ነው። ኢትዮጵያ የ3000 ዘመን ታሪክ ያላት ጥንታዊት ሃገር የሚል ትርክት፣ አድዋ ላይ ተሸንፈን ቢሆን ኖሮ ያበቃለት ነበር። የ3000 አመት ታሪክ እኔን አይወክልም ለሚሉቱ ወገኖች፣ ያ ታሪክ የእነሱ እንዲሆን አድዋ ላይ ቅድመ አያቶቻቸው መስዋእትነት ከፍለው ያዳኑት ታሪክ መሆኑን መገንዘብ ብቻ ይበቃቸዋል። አድዋ የጥንቱን የሁላችንም እንዳደረገው ሁሉ ከአድዋ በኋላ የመጣውንም ዘመን የሁላችን እንዲሆን አድርጎታል። ከአድዋ በኋላ በተደረጉ በርካታ አውደ ውጊያዎች ኢትዮጵያውያን በጋራ መስዋእትነት እየከፈሉ ያቆዩዋት ሃገር ናት፤ ኢትዮጵያ።
መላው አፍሪካ ያልታደለው፣ በአለም ላይ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሃገሮችና ህዝቦች ያልታደሉትን እኛ ኢትዮጵያውያን በታሪክ አጋጣሚ ድንቅና  ልዩ ታሪክ ታድለናል። የውስጥ ችግራችን የፈለገውን ያህል ቁስል ይኑረው፣ በጋራ ራሳችንንና መላውን የጥቁር ዘር ለማትረፍ የከፈልነው መስዋእትነት የትኛውንም የውሰጥ ቁስል እንዲሽር የሚያደርግ ትልቅ ድልና ትልቅ የጋራ እሴት ነው።
የውስጥ ችግራችን የፈለገውን ያህል ቁስል ይኑረው፣ በጋራ በቋንቋ በእምነት፣ በባህል፣ በትውፊት፣ በታሪክ ያሸበረቀ ብዝሃነታችንን ለማትረፍ በጋራ የከፈልነው መስዋእትነትና የተቀዳጀነው ድል፣ የትኛውንም የውስጥ ቁስል እንዲሽር የሚያደርግ ትልቅ ድልና የጋራ እሴት ነው።
ፈጥነን ወደ ዘመናዊ እድገት እንድንሄድ የሚኮረኩረን፣ እኛም እንደ ጃፓኖች የራሳችን ማንነት ያለን የተለየን ህዝቦች ነን፤ በፍጥነት ለስልጣኔና ለእድገት ካልተጋን፣ ይህን ኩሩ ማንነትታችንን ከወራሪዎችና ከጨፍላቂዎች መከላከል አንችልም። ለእድገት የምንተጋው ብዙ ዳቦ የሚያመርት የዳቦ ፋብሪካ ለመገንባት አይደለም። ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ለመስራት፣ በዘመናዊ መጓጓዣ ለመጓጓዝ አይደለም። እነዚህ የዘመናዊነት ትሩፋቶች ናቸው።
በፍጥነት ለእድገትና ለብልጽግና የምንነሳው ማንነታችንን ለመከላከል ነው። በሳይንስና በቴክኖሎጂ እየተራቀቁ ያሉ፣ ከኛ እምነት ባህል ትውፊትና ማንነት ጋር የተለየ ማንነት ያላቸው ሁሌም በእኛ ኪሳራ የራሳቸውን ማንነት ማበልጸግ የሚፈልጉ ጉልበተኛ ሃገራትን ሴራ፣ ትንኮሳና ወረራ ለመመከት ነው። ከኛ አልፈን፣ መጪው ዘመን በጥቁር ዘር ላይ ይዞት የሚመጣውን አደጋ በጋራ ለመመከት፣ ለአፍሪካም የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሳይንስና የነጻነት ብርሃን ለመሆን ነው። ከዚህ በላይ በጋራ እንድንነሳ ሊያደርገን የሚችል ራእይ ሊኖረን አይችልም።
Read 765 times