Monday, 17 May 2021 16:28

እትት --- ብርድ

Written by  ሳሙኤል በለጠ (ባማ)
Rate this item
(5 votes)

ምን አሳዘናት?
በልቧ ትወድቃለች፤ መንገዱን ብዙ ሰው ይረማመድበታል። ልቧን ይረግጡታል። ብዙ ሃሳብ በውስጧ እየተመላለሰ ያስቃትታታል። “ጣል በእጅ እሰር በፍንጅ” ብላ ሃሳቧን እ’ንዳትጥለው። ሌላ አንዳች ነገር አዕምሮዋ ላይ እንዳታስር፣ ሃሳቧን መጣያ ጥቂት ስፍራ ታጣለች፤ ደግሞም ነገርዬው ቸል የማይባል እንዳልሆነ ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ በእርግጥ ቆንጆ ናት፤ ግን ሐዘኗ ያለበሳትን ትቢያ በጥብጣ ጠጥታዋለች፤ የሕያውያን ዐይኖች ወደ እሷ ይመለከቱ ነበር፤ አሁንም ያያሉ፤ ለጋ ከንፈር፣ ከባሻገር አሻቅበው፣ ግርዶሽ ሰርስረው፣ ውበትን የማየት ‘ሚችሉ ዐይኖች፤ የችግርን ዳገት ሳይታክቱ የሚወጡ፣ የማይንጠባጠቡ እግሮች አሏት፤ እኒህ ሁሉ ውበቶችና እውነቶች የሷ አልመስል አሏት፤ የሐሴቷ ክር ተበጠሰ፤ ውስጠ-ነፍሷ ጸጥ ብሏል። ሥጋዋ ጸጥ።
በፊትም ሳምራዊት ያለ እኔ አታወራም፤ እኔም ያለ ሳምራዊት ትንፍሽ አልልም፤ ደስ የምትል ሕይወት፡፡ አንድ ቀትር ድንገት ሐሳብ ውጦኝ ሳምራዊት ልቤ ጫፍ ላይ አንጸባረቀችብኝ፤ የእጅ ስልኬን አነሳሁና ደወልኩላት፤ ስልክ አታነሳም፤ አፍናኝ የነበረችው የደስታ ጢስ ብን-ብን ብላ ጠፋች፡፡
ወደ ዝምታዬ ተመለስኩ (ከሶስት ወር በፊት መሰለኝ)፡፡
ዝምታዬንና ቅሬታዬን ለመቀልበስ እየጣርኩ፤ ከተከራየሁበት ቤት ወዲያ የሚፈሰውን የውኃ ድምጽ ትንሽ ትንሽ እሰማለሁ፤ ፍራሼ ላይ ጋደም ብያለሁ፤ የትንፋሼ ጠልም (ልምላሜ) ደርቋል። በእግዜር እስትንፋስ የሞቀውን ገላዬን በሐዘን አቀዝቅዞታል። ቆይ እግዜር የሰራን ከእርጥብ ዕንባና ከእርጥብ አፈር ነው እ’ንዴ? ሲጋራና ክብሪት ከፍራሹ ፈቀቅ ብሎ ‘The Redemtion’ ከሚለው መጽሐፍ ሥር ተቀምጧል። ተንጠራርቼ አመጣሁት፤ በሚንቀጠቀጥ ጣቴ ክብሪቱን ለኩሼ፣ ከሲጋራው ጋ አገናኘሁት፤ ሲጋራውን ስስበው ትንሽ ሐሴት ነዘረኝ፤ አሁንም አሁንም ሳዬ ትመጣብኛለች፤ ሁለ-ጸዳሏ ከተመለከተኝ ከጽንፍ ጽንፍ በደስታ ናውዤ እመለሳለሁ፤ መቅደሴ ናት! መቅደሴ ለምኔ? ለነፍሴ! የሲጋራው ጢስ ዐይኔ ውስጥ ገባ፤ ዕንባዬ ተንጠለጠለ፤ ዐይኔን አሸሁት፤ ፍም መሰለ፤ በእርግጥ ገጣሚው እንዲህ ብሎ ነበር..
“ሲጋራ አጨሳለሁ፣ ላንቺ ስል ላንቺ ስል፣
በጭሶቹ መሃል፣ አገኝሽ ይመስል፤”
ለምን እንዲህ ግጥም ደረደረ? ገጸ-ምስሏ ርቆት ልቡ ስለተቆረጠ? ‘ገባኝ፤ አሁን ገና’ እንደዚህ ነው። ኅልፈተ-እሷን ተከትሎ ምስሏን ወይ ጠረኗን ከሁለመናው ቢያጣው ነው፣እንዲህ ያለው ብዬ ሳሰላስል፣ የስልኬ ‘ትክትክታ’ ተሰማኝ፡-
“ሄሎ ሳዬ”
“ደህና ነህ?”
“ደህና ነኝ መሰለኝ”
“ምነው?”
“ኧረ እሱስ ደህና ነኝ፤ እንዲያው--”
“ትመጣለህ? እቤት ና እስቲ--”
“እሺ  እመጣለሁ”
ሲጋራውን ደፈጠጥኩት፤ ወዲያው ተነስቼ ታጠብኩ፣ ብሩህ መንፈስ ጸለለብኝ፤ ከመቅጽበት ጥርሶቼ ሳቅ አዝለው ተብለጨለጩ፤ የጸጥታዬን መርከብ ከወደቡ አሳርፌ፣ ለራሴ ማንጎራጎር ጀመርኩ፤ የውሃው ጉዞ አሁንም ይሰማል፤ በፍጥነት ከቤቴ ወጣሁ፤ ቁልቁል የሚፈሰውን ውሃ አየሁት፤ ስሜቴን፣ መንፈሴን  ስቃየን በፍሰቱ ስለሚወስድልኝ መኖሩን እወደዋለሁ፤ እግዜር ደገኛ አምላክ ነው። ‘ጥፍር ይሰጥህና ቁስል ይሰጥሀል’ ያቺ ዘማዊት ዕንባ ስላላት አይደል፣ ከሐጢያቷ የዳነችው፤ ‘ዕንባ ይሰጠንና በዕንባችን ያደፈ ሐጥያታችን ይታጠባል!’
ሁሉን ነገር ተበስተ ኋላዬ ጥዬው ሄድኩኝ፤ መጠበቋን በመራብ ወደ ሳዬ እክለፈለፋለሁ፤ በእሷ ውስጥ ያለው የመጠበቅ ምስል ምን አይነት ይሆን? ብቻ መድረሴን ሳላስበው፣ ‘ሚከተለኝን ድቅድቅ ጨለማ ወደ ኋላ እረግጬው፣ የሳዬን ሳቅ ይሁን ተስፋ ተንጠልጥዬ ቤቷ ደረስኩ፡፡   
“መጣህ  ና ግባ”
“ግብት”
ውብ ዐይኖቿ ወደ ህያውነት ያዳልጣሉ፣ ጸዳሏ ከመለምለም ተቆጥቦ አያውቅም፤ ከአልጋው ላይ ፍራሽ አውርዳ መሬት አንጥፋዋለች፤ የ ረታ አዳምን ‘ከሰማይ የወረደ ፍርፍር’ የተሰኘ መጽሐፍ ለማንበብ ገልጣ ትታዋለች፡፡ "በእርግጥ የሱ መጽሐፎችን ገጹ መጀመሪያ ላይ እንጨርሰውና፣ ገጹ መጨረሻ ላይ እንጀምረዋለን፤ እንዲያ ነው የሚነበበው" ብዬ ለራሴ በለሆሳስ አልጎመጎምኩ፤ ወደ እግዜር ሕልውና ‘እምንፈስበት ወይን ይታየኛል።
“ናፍቄሃለሁ አይደል?”
“ምን ይሉታል እያወቁ ለማወቅ መንሰፍሰፍ?”
“እ?”
“ተይው በቃ፤ ይልቅ ነይ እቀፊኝ”
ተቃቀፍን፤ ተነፈሰችብኝ፤ ትንፋሿ ደሜን ቀጥ አደረገው፤ በናፍቆት ጨምቄ ሳምኳት፤ ተላቀቅን፤ ዝምታ ዳሰሰን፡፡
“እራት ላቅርብ ቆይ”
“እሺ:-”
እጆቼና እጆቿ ተላቀቁ፤ ትንሽ ራቅ ብላ ዐየት አደረገችኝ፤ በፈገግታዋ ልታጠምቀኝ ሳቅ እያለች ወደ እኔ ቀረበች፡፡
“እስቲ እንብላ”
“እሺ”
አጎረሰችኝ፤ ጣቷ ከንፈሬን ነካው፤ ከእሷነቷ ጥግ የተራከብኩ መሰለኝ፤ ሁለመናዬ ጋለ፤ የወይኑን ጭላጭ እጨልጠዋለሁ፤ ከዐይኗ ጋ ስጋጠም ከፍትወት እኩል ውስጤ በሃሴት ይደንሳል። የጥምና የርሃብ ሕልውና ታጠፈ።
ልብሴን አወላልቄ ፍራሹ ጠርዝ ላይ ወረወርኩት፤ ስስ ልብስ ለበስኩ፤ ሳዬ ጭልጭልጭልታዊ ብርሃን ሰውነቷን አጉላልቶት ግን፣ የጡቶቿ ጫፎች የሚዋጉ ብርሃናዊ ጦሮች መስለው፣ ደጋን ልቧ ላይ ተወጥረው ወደኔ አፍጠዋል። ቀረብ አለችኝ፤ በጡቶቿ፤ ው-ግ-ት-ግ-ት-ግ-ት፤ የከንፈሮቼን ጥጋጥጎች በከንፈሯ፤ በከንፈሬ ስ-ፍ-ት-ፍ-ት፤ ገላዬ ገላዋን፣ ጥ-ግ-ት፤ ላቤ ላቧን፣ ን-ክ-ት:-
“ት-ት-ወ-ጂ-ኛ-ለ-ሽ?”
“ህ-ህ-ህ አዎ ማርዬ”
ትንፋሿ ውስጥ የተከፈተ ሕልውና አለ፤ በስሜቷ ንቃቃት መኃል ስሜቴን አፈሰስኩት፤ ከሰመመናዊ ድካሜ ነቅቼ:-
"ደ-ስ አ-ለ-ሽ?”
“ለመሞት እስካለሁ ድረስ ደስተኛ ነኝ፤ በእርግጥ ቅድም ስቃዬ በስቃይ ሞቶ ነበር፤ አሁን ከዝንጋኤው ባነነ ‘ንጂ በቃ እንዲህ ነው። ሕይወት የድግግሞሽ አዙሪትን መዞር ነው። ጨለማ ብርሃንን፣ሳቅ ሳግን፣ ሐሴት ሐዘንን ይዞራል። ምንጊዜም ባንተ ደስተኛ ነኝ" በረጅሙ ተነፈሰች፡፡
(ጥዋት ሆነ፣ ማታም ሆነ፣ ከሶስት ወር ብኃላ)
አክለፍልፋ ጠራችኝ፤ እንደ ያኔው ልቧን ቁስል ተጭኖታል። ሕልም የሌለው መንገድ የምትጓዝ፣ ውሽንፍር ‘ሚቀጣት ትመስላለች፤ ደሟ ወደ ላይ ላይመለስ ይረጫል። ዐየት ስታደርገኝ ነፍሷ ከሥጋዋ ይመነጨቃል።
“ምነው ዓለሜ?” አልኩ፤እኔ
ዝም ብላ፣ ከራሷም ከእኔም፣ በራሷ ጥልቀት ጠለቀች፤
ጠፋች
ሄደች
(ዝምታውን ሰንጥቃ ነገሩን ከነገረችኝ በኋላ ብቻዋን ትቻት፣ ብቻዬን ትርክዛው ላይ ቁጭ ብዬ ማሰላሰል ጀመርኩ)
እንዴት ይህ ይህ ሆነ? ድንግልናዋ ሳይገረሰስ እንዴት ተፈጠረ? (የወር አበባዬ ቀረ ብላኛለች) እንዴት ተፈጥሮ ከተፈጥሮ ውጪ ሆና ታውቃለች?
ሰው እንዴት እንዲህ በመኖርና ባለመኖር፣ መሃላዊ ስንክሳር ይፈተናል? በድንግልና የተጸነሰ ሰው አለ፤ ምናልባት ክርስቶስ፤ እሱም መለኮት ነው። አጥንቴ ውስጥ ጠጣር ጭንቀት ጠጠረብኝ፤ ወንድ መሆን ቀፈፈኝ፤ስሜቴ ተልፈሰፈሰ፤ደግሞ ድሃ ነኝ፤ ልጄ ቢመጣ ምን አደርገዋለሁ? ምንም! ተመልሼ ወደ ቤት ገባሁ፡፡ ታነባለች፤ ስታነባ ልቤን  አባባችው፡፡
“እኔ ምለው ለምን ልጁን አ-ታ-ስ-ወ-ጪ-ው-ም?”
“ምን?”
የሃፍረት ናዳ ጨፈለቀኝ፤ ሃፍረቴ ዝምታ ወለደ፡፡
“ስ-ስ-ለ-ማ-ፈ-ቅ-ር-ሽ ነው ‘ኮ ነው”
“ውጣልኝ አንት ጨካኝ! ራስህን እንጂ ማንንም አፍቅረህ አታውቅም!” አለችኝ፤ ዝም ብዬ ወጣሁ፡፡
 ጺሜን እየነጨሁ ከቤት ጥዬ ወጣሁ። ምን ታደርግ ይሆን? “አንተ ከራስህ ውጪ ማንንም አፍቅረህ አታውቅም” የሚለው ንግግሯ፣ በሕሊናዬ ጆሮ ደጋግሞ ይሰማኛል:- ገብረ ክርስቶስ ደስታ ‘ሕይወት’ ብሎ የገጠመውን ግጥም በለሆሳስ ለራሴ አልኩት፡-
“ሕይወት ጨለማ ነው የምንጓዝበት
ደስታችን መብራት፤
መንገድ አሳይቶን ወዲያው የሚጠፋ
የመከራ ዝናብ ችግሩ ሲያካፋ”
ወዴት እንደምሄድ ግራ ገብቶኝ ተገትሬ ቆሚያለሁ፡፡


Read 1696 times