Saturday, 22 May 2021 11:58

የፖለቲካ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ እንዲመክሩ ጥሪ ቀረበ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

       • “ሚዲያን አስወጥታችሁ በር ዘግታቸሁ ምከሩ” ሰላም ሚኒስቴር

             የፖለቲካ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ በጋራ እንዲመክሩና አገሪቱ ካለችበት እጅግ ፈታኝ አጣብቂኝ ውስጥ ልትወጣ የምትችልበትን መንገድ በመፈለጉ ጉዳይ ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ፡፡ የመገናኛ ብዙኃንም በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ ተዓማኒነት ያለው መረጃ በማቅረብ ግጭቶችን ማርገብ እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባላስልጣን “መገናኛ ብዙሃን ለሰላም ለአብሮነትና ለአገር ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ከትናንት በስቲያ አዘጋጅቶት በነበረው ውይይት ላይ የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፍሪያት ካሚል እንደተናገሩት፤ አሁን አገራችን ያለችበት ወቅት እጅግ የበዛ ስክነትና ኃላፊነት ያለበትን ውሳኔ የሚጠይቅ ወቅት ነው ብለዋል፡፡ ይህንን ፈታኝ ጊዜ ለማለፍም የሃይማኖት አባቶች የፖለቲካ አመራሮችና የአገር ሽማግሌዎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ ሊማከሩ የሚገባበት ወሳኝ ወቅት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ “ከሁሉም ነገር በፊት አገርን ማዳን ይቀድማል፤ ለሌላው ጉዳይ ቀስ ብለን እንደርስበታለን በጋራ ሆናችሁ ሚዲያውን አስውጡና በር ዘግታችሁ ምከሩ፤ አሁን አገሪቱ የግለሰቦችን ሚና የምትፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነው የምትገኘውና አገራችንን ከመፍረስ እናድናት” ብለዋል- ወ/ሮ ሙፈሪያት። መገናኛ ብዙኃን ባለፉት ዓመታት ወጥ በሆነ ፖሊሲና ስትራቴጂ ባለመመራታቸው የሚገባ ቁመና ላይ አልተገኙም ያሉት ሚኒስትሯ፤ አሁን ግን መገናኛ ብዙኃኖቻችን ስለ አገራቸው ግድ ሊሰጣቸውና ሃላፊነት ሊሰማቸው የሚገባበት ወሳኝ ወቅት ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም፤ በሚዲያ አካላት ውስጥ የማይቋረጥ ውይይት እንደሚያስፈልግና አገርን ማዳን ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ሃሳባቸውን ከአጋሩ ታዋቂ ሰዎች መካከል መጋቢ ሀዲስ እሸቱ እንደተናገሩት፤ መንግስት በሚዲያዎች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር ማጥበቅ ይገባዋል፡፡ በብሔር የተደራጁ የመገናኛ ብዙኃን የሚያስተላልፉት መልዕክት ግጭት ቀስቃሽና አንዱን ብሔር ከሌላው የሚያጋጭ ሆኖ እያለ መንግስት በዝምታ ማለፉ አስገራሚ ነው ያሉት መጋቢ ሃዲስ እነዚህን ሚዲያዎች ማስታገስ የሚቻልበት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል፡፡
አገር ልትፈርስ እያጣጣረች ባለችበት ወቅት መስቀል አደባባይ ላይ አፍጥር ይደረግ አይደረግ ዓይነት ክርክር መነሳቱ እጅግ እንዳስገረማቸው የተናገሩት መጋቢ ሃዲስ እሸቱ፤ አገር ሰላም ሆና በእግሮቿ ስትቆም አብረን አፍጥረን አብረን ደመራ እንተክላለን፤ ለጊዜው ግን መጨነቅ ያለብን ስለ አገራችን ነው፤ እኛ እቃው እየተሰረቀ ካርቶኑ ላይ እየተደባደብን ነው፤ መጀመሪያ አገራችን እንደ አገር መቀጠል መቻሏን ማረጋገጥ አለብን ብለዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችም “እባካችሁ አስባችሁ ተናገሩ፤ ከተናገራችሁ በኋላ አታስቡ ሲሉም አክለዋል፡፡
አገር በማስቀጠሉ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባውና አገር አፍራሽ ከሆኑ መልዕክቶችና ጉዳዮች ህብረተሰቡን በመጠበቁ ረገድም ሁሉም የየድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም በዚሁ ውይይት ላይ ተገልጿል፡፡

Read 11491 times