Saturday, 22 May 2021 12:18

“መረጃው ግልጽ ነው…ትኩረት ለሚድዋይፎች”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

      ዓለም ከምንግዜውም በላይ አዋላጅ ነርሶችን አሁን ትፈልጋለች፡፡  
የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ለሁሉም ሚድዋይፎች እንኳን ለአለም አቀፍ የሚድዋይፍ ቀን አደረሳችሁ ይላል፡፡ የዓመቱ መሪ ቃል “መረጃው ግልጽ ነው፡ ትኩረት ለሚድዋይፎች” የሚል ነው፡፡ ማህበሩ እንደገለጸው በዓሉን ስናከብር ሚድዋይፎች በቅድመ ጽንስ፣ በእርግዝና፣ በምጥና በወሊድ እንዲሁም በድህረ ወሊድ ወቅት የእናትና ጨቅላ ህጻን ጤናማነትን ለማረጋገጥ፣ የማህፀንና ጽንስ የጤና ችግሮችን በመለየት፣ በመንከባከብና በማከም፣ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በመስጠት፣ የወጣቶችና አፍላ ወጣቶች የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት በመስጠት ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እውቅና በመስጠት ነው ብሎአል፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ከአዲስ አበባ ምእራፍ ቢሮ እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር 29 ኛውን አለም አቀፍ የሚድዋይፍ ቀን ሲያከብር ለባለሙያዎቹ ያወጣውን የእንኩዋን አደረሳችሁ መልእክት ይጋራል፡፡
ሚድዋይፍ በሚለው ሙያ የተሰማሩ አዋላጅ ነርሶች የእናቶችን ሞት በመቀነሱ ረገድ የሚያ ደርጉት አስተዋጽኦ ከዚህ በመለስ በማይባል ደረጃ የሚገመት ነው፡፡ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2000/ ወዲህ ቀደም ሲል የነበረው የእናቶች እና የህጻናት ሞት በግማሽ በመቀነሱ ከ100.000 በሕይወት ከሚ ወልዱ 412/እናቶች እና ከ1.000/ህጻናት 67 ያህል ዝቅ እንዲል የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም አሁንም ይህ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ለመቀነስ ጥረቱ ቀጥሎአል፡፡  
የእናቶች ሞት በአለም ላይ ቁጥሩ እጅግ ዝቅ እንዲል አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ባለሙያዎች መካከል ሚድዋይፎች ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡ አለም አቀፉ የሚድዋፎች ቀን እ.ኤ.አ 5th May 2021/ ሲከበር የዘንድሮው መሪ ቃል ‹‹መረጃው ግልጽ ነው…ትኩረት ለሚድዋይፎች›› የተባ ለበት ምክንያትም ከእናቶችና ህጻናት ሕይወትና ደህንነት ጋር በተያያዘ ውጤታማ ስራን እንዲሰሩ ለማስቻል በማሰብ ነው፡፡  
አለም አቀፍ የሚድዋይፎችን ቀን ምክንያት በማድረግ የወጡ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያ መለክቱት ከሆነ ሁሉም የእናቶች ሞት በሚያሰኝ ሁኔታ የሚከሰቱት በታዳጊ ሀገራት ነው፡፡ 94% የሚሆነው የእናቶች ሞት በዝቅተኛ እና በመካከለኛ ደረጃ ገቢ ባላቸው አገራት የሚያ ጋጥም ነው፡፡ በመልማት ላይ ባሉት ሀገራት የሚደርሰው የእናቶች ሞት ካደጉት ሀገራት በግምት ሰላሳ ሶስት ጊዜ በልጦ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ በ2017 በአለም አቀፍ ደረጃ ከደረሱት የእናቶች ሞት ውስጥ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ብቻ 2/3ኛው እንደደረሰ ይገመታል፡፡    
የእናቶች ሞት በአንድ ሀገርና ከሀገር ሀገር ይለያያል። በአንድ ሀገር በሀብትና ድህነት እንዲሁም በገጠርና በከተማ በሚኖሩ እናቶች እንደሚለያየው ሁሉ ከሀገር ሀገርም እንዲሁ በስልጣኔ እና በእድገት ደረጃ በሚኖረው አኑዋኑዋር የእናቶች ሞት መጠን ሊለያይ ይችላል፡፡
እናቶች በመውለድ ጊዜ የተለያዩ ችግሮች ሊገጥሙዋቸው ይችላሉ፡፡
በወሊድ ወቅት አስፈላጊውን የህክምና አገልግሎት ማግኘት አይችሉ ይሆናል፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ምክንያቶች በማስወገድ እና ሌሎችም ተያያዥ የሆኑ ምክንያቶችን ጥራት በተመላው መንገድ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ ከተቻለ የእናቶችን ሞት እና የሚደርስ ጉዳት ለመቀነስ ያስችላል፡፡  
በኢትዮጵያ (2016) DHS ቅኝት መሰረት በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር እ.ኤ.አ በ2000/ 5% የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2016/ 26% ደርሶአል፡፡ በተመሳሳይ ወቅት በቤት ውስጥ መውለድ በ2000/ ከነበረበት 95% በ2016 ወደ 7% ዝቅ ብሎአል፡፡ ሴቶች ገቢያቸው የተሻለ ከሆነ ወይንም በጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከሆነ በዝቅተኛ ደረጃ ከሚኖሩትና እጅግ አነስተኛ ገቢ ካላቸው እናቶች በ12/እጥፍ በሰለጠነ ባለሙያ እጅ ይወልዳሉ፡፡ ቢሆንም ግን አሁንም በየገጠሩ ያሉ የጤና ተቋማትና ኃላፊነቱን የወሰዱ ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ አገልግሎቱን መስጠት እንዲችሉ የማሻሻያ ድጋፎች እንዲደረጉላቸው ማስፈለጉን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ የዘንድሮው አለም አቀፍ ሚድዋይፎች ቀን መሪ ቃልም የሚያመላክተው ይህንን እውነታ ነው፡፡ የስነተዋልዶ፤ የእናቶች እና የጨቅላ ህጻናትን እንዲሁም ጾታዊ ደህን ነትን ለመጠበቅ ወይንም ለማሻሻል የሚድ ዋይፎችን አቅም ለማጎልበት የሚረዱ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል በማለት የሚከተሉት እውነታዎች በአለም ደረጃ ላሉ ህዝቦች እንዲሁም ለሚመለከታቸው አካላት እንዲዳረስ ለንባብ በቅቶአል፡፡  
በዚህ በአለም አቀፍ ሚድዋይፎች ቀን ሊገለጽ የሚገባው እውነታ ለሚድዋይፍ ወይንም ለአዋላጅ ነርሶች ትኩረት ማድረግ ወይንም ድጋፍ መስጠት ማለት ሕይወትን ለማዳን፤ የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል እና ለማጠናከር ይረዳል፡፡ በአለም ላይ 93% የሚሆኑት ሚድዋይፎች ሴቶች ሲሆኑ ከአጠቃላይ ከ70% በላይ የሚሆኑት የጤና ባለሙያዎችም ሴቶች ናቸው ሲል UNFPA ይገልጻል፡፡
ሚድዋይፍ ወይንም አዋላጅ ነርሶች ትኩረት ከተደረገላቸው በአለም ላይ በአመት 64% የጨቅላ ህጻናትን ሞት በመቀነስ በአመት 4.3 ሚሊዮን ህይወትን ለማዳን ይችላሉ፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ያለው የሚድዋይፍ ወይንም የአዋላጅ ነርሶች ቁጥር ማነስ ህይወት እያስከፈለ ነው፡፡ መረጃው ግልጽ ነው …ትኩረት ለሚድዋይፎች ማለት ሙሉ አቅማቸውን እንዳይጠቀሙ የሚያደርጋቸውን መሰናክል ሁሉ ለማስወገድ ይረዳል፡፡
ወላዶች በሚድዋይፍ ወይንም በአዋላጅ ነርሶች ወይንም በሰለጠነ ሰው እጅ መውለዳቸው በየአመቱ በ25% ከጨመረ የእናቶችን ሞት በ41% የጨቅላዎችን ሞት ደግሞ በ39% መቀነስ እና ሞተው የሚወለዱትን እ.ኤ.አ እስከ 2035/ በ26% ለመቀነስ ያስችላል፡፡ በዚህም በየአመቱ 2.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሞቶችን መቀነስ ያስችላል፡፡
በአለም የእናቶችን ህይወት ለማዳን፤ጤንነትን ለማሻሻል፤ አሰራርን ወይንም አቅምን ለማጠና ከር፤ ሚድዋይፎች በስነስርአቱ መማርና መሰልጠን አለባቸው፡፡
የዘንድሮው አለም አቀፍ የሚድዋይፎች ቀን በተለያዩ ሀገራት ትኩረት በተሰጠው መንገድ ተከብሮና ታስቦ የዋለ ሲሆን አንዳንድ ለንባብ የበቁ መጣጥፎችም ነገ ዛሬ ሳይባል ለለውጡ መነሳት አሁን ነው ይላሉ። ጎጂና ሁዋላ ቀር የሆኑ የስርአተ ጾታ ልምዶችን ለማስወገድ የአዋላጅ ነርሶች እገዝ ለእናቶች እና ለጨቅላ ህጻናት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህን ጠቀሜታ ዝቅ አድርጎ መመልከት በብዙዎች ዘንድ የሚታይ ነው፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ያለው የአመራር ደረጃ እንኩዋን  ሲፈተሸ ከ4/ የጤና አመራር ውስጥ አንድ ብቻ ሴት ትገኛለች። በስራው ዘርፍ ግን 80% ያህሉ የአለም አቀፍ ጤና አገልግሎት ሰራተኞች ሴት ነርሶች እና ሴት ሚድዋፎች ናቸው፡፡ ስለዚህ በአሰራር ደረጃ እኩልነትን ለማስፈንና ለተጠቃሚውም ማለትም ለእናቶችና ጨቅላ ህጻናቶ ቻቸው የጤና ደህንነት እና ህይወትን ለማትረፍ እንዲረዳ አዋላጅ ነርሶችም በአመራር ደረጃ ቢሳተፉ ጥሩ መሆኑን UNFPA ይገልጻል፡፡
UNFPA በተጨማሪም  ሚድዋይፎች ወይንም አዋላጅ ነርሶች አስቸጋሪ የሆነ የጾታ እና የስነተዋልዶ ጤና ችግሮችን ለመፍታት በየቀኑ ጠንካራ ስራ ይሰራሉ። ነገር ግን አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች የሚያሰሙዋቸው ድምጾች አይሰሙም፡፡
ከቀረቡት ሪፖርቶች ውስጥ መረዳት እንደሚቻለው 11/ የሚሆኑት አገራት በአመራር ደረጃ ምንም ሚድዋይፎች ወይንም አዋላጅ ነርሶች እንደሌሉዋቸው ያሳያል፡፡ በአውሮፓ ወደ 15% የሚሆኑት ሀገራት ብቻ ሚድዋ ይፎች በብሔራዊ ደረጃ በአመራር እንደሚሳተፉ ያሳያል፡፡ ሚድዋይፎች (አዋላጅ ነርሶች) ለእናቶችና ጨቅላዎቻቸው፤ ለህጻናት  እና ለህብረተሰቡ ሰብአዊ መብት መከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ ባለሙያዎች ናቸው ሲል UNFPA ያራራል፡፡ ስለዚህ ሚድዋይፎች ወይንም አዋላጅ ነርሶችን በሙያ ብቃታቸውን በማሳደግ ፤አቅማቸውን በማጎልበት እና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እነሱ አገልግሎት የሚሰጡዋቸው እናቶችና ህጻናትን ሕይወት ማትረፍ ይገባል ሲል መግለጫውን ይቋጫል፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ለሚድዋይፎች እንኩዋን ለ29ኛው አመታዊ በአል አደረሳችሁ ይላል፡፡

Read 11579 times