Saturday, 22 May 2021 12:26

ተጠያቂነትን የሚፈራ መሪ….

Written by 
Rate this item
(19 votes)

          ከመደናገር መነጋገር በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃች የዶ/ር ሳሙኤል ወልዴ ምጥን መፅሀፍ ውስጥ ለዛሬ ርዕስ አንቀፃችን የምትሆን ቁምነገረኛ አስተማሪ ፅሁፍ አግኝተን እንደሚከተለው አቀረብናት፡፡

    ተጠያቂነትን የሚፈራ መሪ….

ተጠያቂነት የሚፈራ መሪ፣የቤት ስራውን ሳይሰራ እንደሚቀመጥ ሰነፍ ተማሪ ነው። ከተጠያቂነት የሚሸሹ መሪዎች፤ ለዜጎቻቸው የስራ ሪፖርት ማሰማትም ሆነ ለውይይት መጋበዝ አይፈልጉም፡፡ጋዜጣዊ መግለጫን እንደ ጦር ይፈሩታል፡፡ ምክንያቱም ይነሳሉ ብለው ለሚጠረጥሯቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ አይኖራቸውም፡፡ ይህን ካደረጉም እነሱም በጥሩ ቀለም የሚስላቸውን ድርጊት እየቀነጫጨቡ፣ትንሹን እያባዙ በማቅረብ ሳይጠየቁ በራቸውን በፍጥነት ይዘጋሉ፡፡
ከተጠያቂነት የሚሸሹ መሪዎች በትናንትና ጥፋታቸው እየጸኑ የሚሄዱ እንጂ፣ከጥፋታቸው ተምረው የሚመለሱ አይደሉም፡፡ ከተጠያቂነት የሚሸሹ መሪዎች ሊጠይቃቸው የሚችለውን ግለሰብ ፊት የሚነሱ ብቻ ሳይሆኑ፣ የዛ ግለስብ ስምም ዝክርም እንዲወሳ የማይፈቅዱ ናቸው። ከተጠያቂነታቸው የሚሸሹ መሪዎች ተቃራኒ ወይም ተቃዋሚ ሀሳብን የሚያዳፍኑ ናቸው። የተዳፈነ እሳት ደግሞ ጊዜ ጠብቆ ምን ሊሆን እንደሚችል የሰው ልጅ የረጅም ጊዜ ታሪክ ደጋግሞ አስምሮበታል፡፡
ይህም ሲባል አሉታዊ ምላሽ ሁሉ ገንቢ ነው ማለት አይቻልም፡፡ አንዳንድ ግለሰቦችም ሆኑ የማህበረሰብ አባላት፣የሚደረገው መልካም ነገር የማይታያቸው፣ ሁልጊዜ ለስሞታና ለሀሜታ የሚፈጥኑ መሆናቸው አይቀርም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ወይም የማህበረሰቡ አባሎች የራሳቸው የተደበቀ የጨለማ ምክር ያላቸው፣ እነሱ ካልመሩና አንቱ ካልተባሉ በስተቀር የመኖር ትርጉም የሚጠፋባቸው፣ስነ- ልቦና ቀውስ የተጠናወታቸው ህመምተኞች ናቸው፡፡
ሌላውን ግለሰብ ወይንም የማህበረሰብ ክፍል ድካምና ጥረት ውድቅ ባደረጉ ቁጥር፣እነሱ ታላቅነትን የተላበሱ ስለሚመስላቸው አንደበታቸውን ለሰባሪ ቃል፣አይናቸውን ደግሞ ጥፋትን ብቻ ለመመልከት የተከፈቱ ናቸው፡፡ ሲናገሩ ገንቢ ሂስ ለማስተላለፍ ሳይሆን፣ሌላውን ዜጋ ወይንም በጊዜው በመሪነት ወንበር የተቀመጠውን ሰው፣ በአደባባይ የውስጥ ልብሱን ገልበውና አውልቀው በማዋረድ ራሳቸውን ለማስከበር የሚያሴሩ ሸረኞች ናቸው፡፡
እነዚህ ቅን የሆነን ጅማሬ ውሃ በማጠጣትና በመንከባከብ ወደ ፍሬ እንዲደርስ ከማገዝ ይልቅ ትንሿን እንቡጥ፣ ከስር በመንቀል ወዲያው እንድትወድም የሚችሉትን ሁሉ ከመጋረጃ ጀርባ ይሁን በአደባባይ የሚፈፅሙ፣ የህዝብ ሰላም፣ምቀኞች ናቸው፡፡ ሌላው ወገናቸው ሰርቶ ሲመሰገን ማየትና መስማት እንደ ኮምጣጤ የሚመራቸው ግለኞች፣ የስኬት ደንቃራዎች ናቸው።
የአሉታ ድምፃቸው  ለግንበታ ሳይሆን ፣ ለማውደም ያነጣጠረ ስለሆነ፣ ሰሚውን የሚያንጽ ምንም የእወቀትና የጥበብ ቃል የለውም፡፡ ከራሳቸው ጋር ሰላም የሌላቸው፣የራሳቸውን የግል ኑሮ በውጤታማነት የመምራት አቅም ያጡ፣ቤታቸው፣ትዳራቸው፣የተፋታባቸው፣ በእኩይ ስነ ምግባራቸው ቤተሰብ ወዳጅ ያራቃቸው ስለሆኑ፣ለሀገር አመራር የበቃ ሰናይ ስነ ምግባር አላቸው ብሎ ማሰብ፣ በመሪነት ወንበር ድንገት ተቀምጠው ለሚያወርዱት ውርጅብኝ ተስማምቶ መፈረም ነው፡፡
ቤቱን በቅጡ ያላስተዳደረ ሰው፣ የህዝብ አለቃ ሲሆን፣ተለውጦ የመልካም አስተዳደር ሰብዕና ይጎናጸፋል ተስፋ ማድረግ፣ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ ለዚህ ነው አንድ ሰው “እኔ” ብሎ እራሱን ሳያስተዋውቅ፣ ይህ ሰው ከቤተሰቡ፣ከወዳጆቹ፣ ከስራ ባልደረቦቹ ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመስል ነበር? ብሎ መጠየቅ የሚያስፈልገው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች አንዱ ጋር የሚሆኑት፣ሌላው ጋር የሆኑትንት፣ ስለሆነ ነው፡፡
ቆም ብለው እራሳቸውን የማያዩ፣ የሚሰነዘርላቸውን ገንቢ ሀሳብ ተቀብለው የማያስተካሉ፣ ህክምናም የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ታክመው ችግራቸውን  ያልቀረፉ ሰዎች፣ያለምን ስነ ልቦናዊ እገዛ ነገ ጠዋት ሲነሱ   ሌላ ሰዎች ሆነው ይለወጣሉ ብሉ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ በመለኮታዊ ታምር ይሁን ራስን በግል  ሆነ በጋራ በማረቅ ያልተቃና ጠማማነት፣ ነገ ቀና ሆኖ ቀን ይለውጠዋል፤ ማለት የሚያከስር ተስፋ ነው፡፡
ስለዚህ እነዚህ በሌላ ወገን ስኬት የሚቃጠሉ፣ሌላውን በመክሰስ ራሳቸውን ነፃ የሚያደርጉ የሚመስላቸው ሰዎች፣አሉታዊ ሂስ መስጠታቸውን መቼም ስለማያቆሙ፣ማን መሆናቸውን አጥርቶ ማወቅ፣ሁልጊዜ ከሚወረውሩት ፍላፃ እራስንና የተያዘን መልካም ሀሳብ ለመጋረድ ይጠቅማል፡፡ ስለ እንደነዚህ ዓይነት እኩይ ሰብዕናዎች ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ፣ የሰላም ሰዎች አለመሆናቸውን ነው፡፡ ሆን ብለው በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና፣ በብሔረሰብና መካከል ጠብና ግጭት የሚጭሩ የሰላም ጠሮች ናቸው፡፡
ህዝብ ውጥረት ውስጥ ሲወድቅ፣የእነሱን እኩይ ስነ ምግባር ልብ ስለማይል፣ሁልጊዜ አለመረጋጋትን በመዝራት፣ራሳቸውን በዚያ ግርግር የሚደብቁ፣ በዜጋ ግራ መጋባት የሚስቁ የሚሳለቁ ከንቱ ሰዎች ናቸው፡፡ ራሳቸው የጫሩትን ጠብ፣ዞር ብለው ደግሞ ካልዳኘን ብለው የሚቀርቡ ጉበኛ ፈራጆች፣ሌባ ፖሊሶችም ናቸው፡፡ በወገን ግጭት ምክንያት በከንቱ የሚጠፋ የሰው ሕይወት፣ ጊዜ፣ የሀገር ሀብትና፣ንብረት የማይገዳቸው፤ ነገር ግን በግጭቱ ምክንያት የሚከፈትላቸውን መልካም አጋጣሚ ለዘረፋቸው የሚጠቀሙ ምንኞች ናቸው፡፡
እነዚህ ግለሰቦች ወይንም መሪዎች የሰላም መፍትሔ የላቸውም ኖሯቸውም አያውቅም የግጭቱ ዘመን እንዲራዘም እሳቱ ላይ ጋዝ የሚያርከፈክፉ አደጋ ጣዮችም ናቸው፡፡ የሰላም ምክርን ማሳጣት ብቻ ሳይሆን፣ ምንም ዓይነት የሰላም ማመቻመች አይመቻቸውም፡፡ ለእርቅ የሚደረገውን ሀሳብ ሁሉ ውድቅ የሚያደርጉ ከመሆናቸው የተነሳ፣ ባላዋቂ ሰዎች ውስጥ እየተደበቁ የራሳቸውን እኩይ ሃሳብ በማራመድ የሳር ውስጥ እባብ በመሆን ይታወቃሉ፡፡ ለሰላም ሲባል ሊከፈል የሚገባውን ዋጋ መክፈል የማይፈልጉ የውጥረትና ግጭት  ዘመን እንዲረዝም የሚሹ፣ የረባ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃ የሌለውን  አላዋቂ ዜጋ እየደለሉ፣ በጀርባ የሚፈናጠጡ ተጣባቂና ተለጣፊ ህዋሳት ናቸው፡፡
እነዚህ ግለሰቦች እያወቁ ከሚረጩት መርዝ ህዝብም ሆነ መንግስት ሊጠነቀቅ ይገባል። ሂስ ሰጪ ሁሉ ገንቢ እንዳልሆነ መገንዘብ ከመፈራረስ ያተርፋል፡፡ መልካም መሪዎች ግን ለበጎ ምክር  ብድግ ብለው የሚሰለፉ፣ በእሺ ባዮች ሳይሆኑ፣ ከቀና ልብና ለቀና የነገ ተስፋ ሲሉ፣ እውነቱን በፍቅር በሚናገሩ ሰዎች የተከበቡ ናቸው፡፡ መሪዎች ጉድለታቸውን በዜጋቸው ብቃት በመሙላት፣ ስልጣናቸውን በማከፋፈል የተሻለ እይታ ባላቸው ሰዎች ሊከበቡ እንጂ በምሁራንና የተሻለ ያውቃሉ በሚባሉ ዜጋዎች ምክንያት ስጋት ውስጥ ሊገቡ አይገባቸውም፡፡

Read 13432 times