Saturday, 22 May 2021 12:33

መልእክቶቹን’ የሚልካቸው ማነው?

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)


           እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አንድዬ! አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡– ማነው እሱ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– እኔ ነኝ አንድዬ!
አንድዬ፡– አንተ ማነህ?                                             
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አንድዬ፣ እኔ ነኝ! እኔ ምስኪኑ ሀበሻ ነኝ!
አንድዬ፡– ታዲያ ምንድነው እንዲህ የሚያስጮህህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– ምን መሰለህ አንድዬ…
አንድዬ፡– የሚመስለኝን እኔ እነግርሀለሁ። የራሳችሁን የምድሩን በጩኸት የምትገለባብጡት አልበቃ ብሏችሁ ጭራሽ የእኔንም ቤት በጩኸት ብዛት ተማክራችሁ የላኩህ ነው የሚመስለኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አንድዬ፣ እንደሱ አይደለም፡፡ እንደሱ አይደለም፡፡ ነገሩን በተሳሳተ መንገድ ነው የተረጎምከው፡፡
አንድዬ፡– ምን ላድርግ፣ አንተ በመጣህ ቁጥር በትነህብኝ የምትሄደው ነገር አለ መሰለኝ እኔኑ ግራ እየገባኝ፡፡ ግዴለም፣ ቃላቶችህ ቢጋቡብኝ እንደምንም አስተካክለዋለሁ፡፡ ችግሩ አስተሳሰባችሁ የተጋባብኝ እንደሆነ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አንድዬ፣ እንዴት እንዲህ ታ….
አንድዬ፡– እንዴት እንዲህ አስባለሁ? ይልቅ ከዚህ አልፌ ባለማሰቤ አመስግነኝ።  አሁን እንዲህ ጣራዬን ልታወርደው እስከትደርስ ድረስ ያስጮኸህ ምን ልትለኝ ፈልገህ ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– ላማክርህ ነዋ!
አንድዬ፡– ምንድነው የማማክርህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡–ያው…
አንድዬ፡– ቆየኝማ፣ ዘለዓለም እናንተን ሳማክር መኖር አለብኝ እንዴ! ነው ወይስ እድሜ ልክ ኮንትራት አስፈርማችሁኛል?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አዎ! አዎ አለብህ! አንድዬ፣ ማማከር አለብህ፡፡
አንድዬ፡– ረጋ በል፣ አትጩህ እንጂ! አንተ ስትጮህ እኮ ስንቱ ሰላማዊ ሰው እንደሚሸበር አታውቅም?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– ይሸበር አንድዬ! ይሸበር! ዘለዓለም እኛ እየተሸበርን ሌላው የሰላም እንቅልፉን የሚለጥጥበት ምከንያት የለም! ይሄን ያህል የዓለሙ ሁሉ ሀጢአት መጋዘን የእኛ ቤት ነው እንዴ!
አንድዬ፡– እሱንማ ለእኔም ብትነግሩኝ ደስ ይለኛል፡፡  ዛሬ ግን ምንም ነገርህ አላማረኝም፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አይደለም አንድዬ! አ…
አንድዬ፡– ቆይማ ረጋ በል፣ እሺ? ረጋ በል። ምን ላድርግ እኔው ወርጄ ልለማመጣችሁ እንጂ! እግረ መንገዴን እንደው ልቤ እንዲያርፍ  አንድ ነገር ልጠይቅህ፣ ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– ጠይቀኝ፣ አንድዬ…
አንድዬ፡– መቼም እዛ ታች ምኑንም ምናምኑንም መነጣጠቅ ለምዶባችኋል፣ እኔን ከመንበሬ ለማንሳት መክራችሁ ውሳኔ ላይ ደረሳችሁ እንዴ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አንድዬ፣ እንደሱ አትበል! እኛ እንዴት እንደዛ እናስባለን?
አንድዬ፡– የምድሩን ጨረሳችኋ! ይኸው ስልጣን ያለውንም፣ ገንዘብ ያለውንም ስልጣንና ገንዘብ የሌለውንም፣ ወንበሩንም ምኑንም ሁሉ ስትነጣጠቁ ከረማችሁ። መሬቱንም እንደፈለጋችሁ ሆ እያላችሁ እየገመሳችሁ ስትነጣጠቁ ከረማችሁ፡፡ የምድሩ ሲያልቅባችሁ  እኔ እንጂ ሌላ ምን ቀራችሁ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አንድዬ፣ ዛሬ ምንም ብትቆጣ አልቀበልህም፡፡ እኔን ልትሰማኝ…
አንድዬ፡– እሺ፣ እሺ የምትለኝን ሁሉ እሰማኻለሁ፣ መጀመሪያ ግን መልካም ፈቃድህ ሆኖ ድምጽህን ትቀንስልኛለህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– ይቅርታ አንድዬ፣ ግን ዛሬ ረጋ ብዬ መናገር ያቅተኛል፡፡
አንድዬ፡– መረጋጋት እኮ ለአንተም ጥሩ ነው፡፡ አለበለዛ ልብህ ጧ ያለች እንደሁ ዘመዶችህ በእኔ ሊያሳብቡ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አንድዬ፣ እርጋታ ብለን እኮ ነው ለዚህ የበቃነው! እርጋታ ብለን እኮ ነው እላያችን ላይ ይሄ ሁሉ አረም የበቀለው።  አንድዬ እየበቀለብን ያለው የአረም ብዛትና አይነት እኮ… ምን ብዬ ልንገርህ!
አንድዬ፡– እኮ ይሄን ሁሉ አረም እኔ ልኬባችሁ ነው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡– ተው አንድዬ እንደእሱ አታስብ…
አንድዬ፡– ነገርኩህ እኮ፣ በመጣህ ቁጥር ምን እየበተንክብኝ እንደምትሄድ አላውቅም። እሱ መሆን አለበት የሚያስቀባጥረኝ፡፡ እሺ ምን ልትለኝ ነው የፈለግኸው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– እንደዚህ ስንሆን፣ ማንም ከየትም እየተሰባሰበ ሲጫወትብን፣ አናታችን ላይ ሲጨፍርብን ዝም ብለህ የምታየው እኛ ከማን የባሰ አስቀየምንህና ነው! እዚህ ዓለም ላይ ከእኛ የባሰ ሀጢአተኛ በሞላበት ምን በወጣን ነው መጫወቻ የምንሆነው!
አንድዬ፡– ማነው መጫወቻ ያደረጋችሁ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– ማን ያላደረገን አለ፣ አንድዬ! ማን መጫወቻ ያላደረገን አለ! ከእኛው ጉዶች እስከ ምድረ ፈረንጅ ኳስ ሊያደርገን እየሞከረ ነው፡፡
አንድዬ፡– እኮ እኔ እዚህ ውስጥ ምን ቤት ነኝ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አንድዬ፣ አንተ ካልተከላከልከን ማን ይከላከልልናል?
አንድዬ፡– ራሳችሁን መከላከል ነዋ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አንድዬ፣ ስንቱን ተከላክለን እንችላለን! ሀገር አትለው፣ መንደር አትለው…ብቻ ከዚህም ከዛም እየተሰባሰበ  ትከሻውን ያሳየናል፡፡
አንድዬ፡– እናንተ ትከሻ የላችሁም እንዴ! የፈጠርኩላችሁ መስሎኝ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡– የሳሳ አስመሰልነዋ አንድዬ፣ ለጉርብትና ብለን፣ አብረን ለመኖር ብለን የሳሳ አስመሰልነዋ! ጉድ ልንገርህ ሱዳን ከአቅሟ፣ ሱዳን እንኳን ከአቅሟ ገብታ መሬታችንን ይዛለች፡፡ እና… ከዚህ የበለጠ መጫወቻ መሆን አለ!
አንድዬ፡– ለሱዳን እናንተ አንሳችሁ ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አንድዬ፣ ማነስ አይደለም፡፡ እኛማ ድንገት መርቅነው ከሆነ ሲለቃቸው በራሳቸው ይወጣሉ ብለን ነው። ይኸው ጭራሽ ተንሰራፍተው ቁጭ አሉ። ብቻ አንድዬ ስንቱን ልናገረው፡፡ ደግሞ፣ ደግሞ…
አንድዬ፡– ደግሞ ምን…
ምስኪኑ ሀበሻ፡– ደግሞ አንተ በዚህ ላይ ታስፈራራናለህ፡፡
አንድዬ፡– እኔ! ደግሞ ወደ እኔ ዞራችሁ? ምን ብዬ ነው ያስፈራራኋችሁ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– በመላእክተኞች ነዋ!
አንድዬ፡– ቆይ ቆይ እስቲ በደንብ አስረዳኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡– “ምን አይታችሁ፣ ገና ታልቃላችሁ ብላችሁ ንገሩ; ተብለናል እያሉን ነው፡፡ እውነተኛውን ከሀሰተኛው መለየት አቃተን እኮ!
አንድዬ፡– ሳላውቅ ልኬያቸው ይሆን እንዴ! ልቀልድ እንጂ ምን ላድርግ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡– እኛ እኮ ግራ ስለገባን ነው፡፡ እውነተኛውን ከሀሰተኛው መለየት አቃተን፡፡
አንድዬ፡– እውነተኛውን ምን?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– እውነተኛውን ከአንተ መልዕክት የደረሰው…
አንድዬ፡– ቆይ በቃ በቃ፣ እሱን እዛው እንደ ፍጥርጥራችሁ፡፡ እንዲህ አይነት ነገር በራሳችሁ ቋንቋ አይመቸኝም፡፡ ስለ እንደዚህ አይነት ፍሬከርስኪ ነገሮች ከዚህ በላይ መስማት አልፈልግም፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አንድዬ አትቆጣ። እኛም እኮ ግራ ቢገባን ነው! የሚነግሩን ሁሉ “ታልቃላችሁ፣ ትበላላላችሁ” ነው፡፡ አንድዬ ስለ እኛ  ደግ ደጉን የምንሰማው... ደግሞ…
አንድዬ፡– እኮ እኔው ነኝ “ታልቃላችሁ፣ ትበላላላችሁ” እያልኩ መልእክት የምልከው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አንድዬ፣ እነሱ ናቸው እንዲህ...
አንድዬ፡– በቃህ አልኩህ እኮ! ለመዘባረቅ ከሆነ ደግመህ እንዳትመጣብኝ! ለአሁኑ ደህና ግባ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡– አሜን፣ አንድዬ!
እናማ ምን መሰላችሁ... ጥያቄው “ታልቃላችሁ፣ ትበላላላችሁ የሚሉትን መልእክቶች የሚልካቸው አንድዬ ካልሆነ እነማን ናቸው?” የሚል ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1664 times