Print this page
Saturday, 22 May 2021 12:29

የልጆች ሥነልቦና እና ኮሮና

Written by  ብርሃኑ በላቸው አሰፋ
Rate this item
(1 Vote)

      በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት ፈንድ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ባወጣው መረጃ መሰረት፤ በመላው ዓለም ኮቪድ19 ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ተማሪዎች ላይ ተፅዕኖውን አሳርፏል። ከነዚህም ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት ልጆች ናቸው፡፡
 ጥናቱ እንደሚያመለክተው፤ ልጆች ሙሉ ለሙሉ አልያም በከፊል በቤት ውስጥ ቢያንስ ለዘጠኝ ወራት መቀመጣቸው  ከፍተኛ ለሆነ ሥነልቦናዊ ቀውስ ያጋልጣቸዋል። ዩኒሴፍ በዚህ ጥናቱ፤ በመላው አለም ኮሮናን ተከትሎ፣ ከሰባት ልጆች መካከል አንዱ ለአእምሮ ጤና መታወክ እንደሚጋለጥ  ጠቁሟል፡፡
 የአለም ጤና ድርጅት ባደረገው ሌላ ጥናት ደግሞ በመላው አለም ከ10-12 % የሚጠጉ ልጆች፣ ለአእምሮ ህመም የተጋለጡ ናቸው። ጥናቱ  እንደሚጠቁመው፤ እንደ ኮሮና መሰል ወረርሽኝ በሚከሰትበት ወቅት ልጆች ችግሩን የመቋቋም አቅማቸው ይለያያል፡፡ አንዳንድ ልጆች ከሌሎች  በተሻለ ችግሩን የመጋፈጥ አቅም ይኖራቸዋል፡፡  ይሁንና አንዳንድ ልጆች ደግሞ ወረርሽኙ በሥነ ልቦናቸውና ስሜቶቻቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል፡፡
ኮቪድ 19ን ተከትሎ የሚስተዋለው ሥነልቦናዊ ጫና የተለያዩ መገለጫዎች አሉት፡፡ በዋናነት ከሚታዩት ምልክቶች መካከል ድበታ፣ ጭንቀት፣ ትኩረት ማጣት፣ ቁጣ፣ ፍርሃት፣ ፀፀት፣ መነጫነጭና ተስፋ ቢስነት ይጠቀሳሉ፡፡
እነዚህ ስሜቶች ደግሞ አካላዊ መገለጫዎች ይኖራቸዋል፡፡ ለአብነትም የጨጓራ ህመም፣ ራስ ምታት፣ የምግብ ፍላጎት እጦት ይገኙበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ  ኮቪድ 19 በልጆች ማህበራዊ  መስተጋብራቸው ላይ ተፅኖ ማሳረፉ አልቀረም ፡፡ በዋናነትም የልጆች የእለት ተእለት ልማዳቸው መገታት አልያም መዘበራረቅ፣  ምቾትና ደህንነት እንዳይሰማቸው ያደርጋቸዋል፡፡ በመገናኛ ብዙኃንና በማህበራዊ ትስስር የሚሰራጩ  ተከታታይ የሞትና የህሙማን  ዘገባዎች ልጆችን ለፍርሃትና  ጭንቀት ያጋልጣቸዋል።  
ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ታዲያ በዚህ ፈታኝ ወቅት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በልጆች  ላይ የሚስተዋለውን እንግዳ ባህሪና ልምምድ በንቃት ሊከታተሉ ይገባል፡፡  ወረርሽኙ በልጆች ሥነልቦና ላይ የሚያደርሰውን ስብራት ለመጠገን በተለይ የወላጆችና አሳዳጊዎች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
የመጀመሪያው የወላጆች ሃላፊነት በኮቪድ 19 ዙርያ ግልፅ የሆነ ውይይት ማድረግን ይመለከታል፡፡ ውይይቱ ልጆች ስለ ወረርሽኙ ያላቸውን አመለካከትና የሚፈጥርባቸውን ስሜት እንዲገልፁ ምቹ ከባቢ ይፈጥራል። ሌላው ልጆች ለብቻቸው ከአቅማቸው በላይ የሆነውን አልያም የሚያብሰለስሉትን እንዲተነፍሱ እድል ይሰጣል፡፡ በዚህ ወቅት ከወላጆች የሚሰሙት የአብሮነት ማረጋገጫ ቃላት የሥነ ልቦና ብርታትን ያጎናፅፋቸዋል። ልጆች የውስጥ ስሜታቸው እውቅና ተሰጥቶት በወላጆቻቸው መደመጣቸው ብቻ  የሥነልቦና ቁስላቸውን የመፈወስ አቅም አለው፡፡
ወረርሽኙን ተከትሎ ልጆች በፍርሃትና ግራ መጋባት ውስጥ ሊገቡ ስለሚችሉ ወላጆች ይህንን በመረዳት ገንቢ ምክርና የማረጋጋት ስራ እንዲሰሩ ይጠበቃል፡፡ ወላጆች ኮቪድ 19ን በተመለከተ የሚሰጡት ማንኛውም መረጃ እድሜያቸውን ያገናዘበ መሆኑን ሊያረጋግጡ ይገባል፡፡ ሌላው ልጆች እድሜያቸውን ያገናዘበ የመገናኛ የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም እንዲኖራቸው ወላጆች ክትትል እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡
በቤት ውስጥ ከልጆች ጋር በቂ ጊዜን ማሳለፍ ለአብነትም፡- ስዕል መሳል፣ መፃህፍት ማንበብ፣ እድሜያቸውን የሚመጥን የጋራ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገኙበታል፡፡ ይህም  ስነልቦናቸውን ከማበርታት በተጨማሪ በጨዋታ ውስጥ አካላዊ ጥንካሬና የፈጠራ ክህሎታቸውን ያዳብራል፡፡ በኮሮና ወቅትም ቢሆን የህይወትን በጎ ገፅታ በማጉላት የልጆችን ተስፋ ማነቃቃት ይመከራል፡፡
 ሠላማችሁ ይብዛ!!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው  በHolistic Child Development (M.A)
የመጀመሪያ አመት ተማሪ ነው፡፡

Read 3351 times