Monday, 24 May 2021 00:00

የአመቱ የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች ይፋ ተደረጉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የቻይናው የኢንዱስትሪና የንግድ ባንክ በ1ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል

             ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት የ2021 የፈረንጆች አመት የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎችን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በተቀመጡት አራት መስፈርቶች ድምር ውጤት በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የአመቱ የአለማችን ግዙፍ ኩባንያ የቻይናው የኢንዱስትሪና የንግድ ባንክ አይሲቢሲ ሆኗል፡፡
ኩባንያው በአመቱ 190.5 ቢ ዶላር ሽያጭ፣ 45.8 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ፣ 4.9 ትሪሊዮን ዶላር አጠቃላይ ሃብት እና 249.5 ቢሊዮን ዶላር የገበያ ዋጋ በማስመዝገብ በድምር ውጤት በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ነው ፎርብስ ያስታወቀው፡፡
የአሜሪካዎቹ ኩባንያዎች ጄፒሞርጋን ቼዝ እና ቤክሻየር ሃታዌይ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን የያዙ የአመቱ የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ የቻይና ኮንስትራክሽን ባንክ አራተኛ፣ የሳዑዲው የነዳጅ ኩባንያ አራምኮ ደግሞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
የአሜሪካው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል፣ ባንክ ኦፍ አሜሪካ፣ የቻይናው ፒንግ አን ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ የቻይና የግብርና ባንክና የአሜሪካው አማዞን እንደ ቅደም ተከተላቸው ከስድስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን ፎርብስ አስታውቋል፡፡
በአለማችን የሚገኙ ኩባንያዎችን አጠቃላይ ሃብት፣ የገበያ ዋጋ፣ ሽያጭና ትርፍ በመገምገም በየአመቱ ደረጃ የሚሰጠው ፎርብስ መጽሄት ለ19ኛ ጊዜ ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ 2000 ኩባንያዎችን ያካተተ ሲሆን፣ ኩባንያዎቹ በድምሩ በአመቱ 39.8 ትሪሊዮን ገቢ አግኝተዋል፡፡
ኩባንያዎቹ በአመቱ ያስመዘገቡት ትርፍ ካለፈው አመት በ24 በመቶ በመቀነስ 2.5 ትሪሊዮን መድረሱን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የገበያ ዋጋቸው 79.8 ትሪሊዮን ዶላር፣ አጠቃላይ ሃብታቸው ደግሞ 223 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ መጽሄት የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ በየዘርፉ በቀዳሚነት ከተቀመጡት መካከልም፣ በአየር መንገድ ዘርፍ ዴልታ ኤርላይንስ፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ አፕል፣ በሪልስቴት ዘርፍ ብሩክፊልድ አሴት ማኔጅመንት፣ በባንክ ዘርፍ  ቻይናው የኢንዱስትሪና የንግድ ባንክ፣ በመድህኒትና ፋርማሲ ዘርፍ የአሜሪካው ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን፣ በትራንስፖርት ዘርፍ ፌዴክስ እንዲሁም በኢንሹራንስ ዘርፍ የቻይናው ፒንግ አን ይገኙበታል፡፡


Read 2682 times