Thursday, 27 May 2021 00:00

ክርስቲያኖ ሮናልዶ በማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ብዛት 1ኛ ደረጃን ይዟል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ኢንስታግራምና ዩቲዩብን ጨምሮ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተከታይ ያፈሩና ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ የአለማችን ዝነኞችን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው ቪዡዋል ካፒታል ድረገጽ፤ ፖርቹጋላዊውን የእግር ኳስ ተጫዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአንደኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል፡፡
ሮናልዶ ፌስቡክንና ትዊተርን ጨምሮ እስከ ሚያዝያ ወር መጨረሻ በድምሩ 517 ሚሊዮን ተከታዮችን ማፍራቱን የጠቆመው ድረገጹ፣ አብዛኞቹን ተከታዮቹን ያፈራው ከኢንስታግራም ገጹ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ታዋቂዎቹ የአለማችን ኮከብ ድምጻውያን ጀስቲን ቢበር በ455 ሚሊዮን፣ አሪያና ግራንዴ በ429 ሚሊዮን፣ ሴሊና ጎሜዝ በ425 ሚሊዮን እና ቴለር ስዊፍት በ31 ሚሊዮን ተከታዮች ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ዋይኔ ጆንሰን በ342 ሚሊዮን፣ ኬቲ ፔሪ በ338 ሚሊዮን፣ ካይሌ ጄነር በ333 ሚሊዮን፣ ሪሃና በ332 ሚሊዮን እና ኪም ካርዲሺያን በ319 ሚሊዮን የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ከስድስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም መረጃው ይጠቁማል፡፡
ድረገጹ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተከታይ ያፈሩ ወይም ተጽዕኖ ፈጣሪ ብሎ ከዘረዘራቸው 50 የአለማችን ዝነኞችና ታዋቂ ሰዎች መካከል በኪነጥበቡ ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ መካከልም 67 በመቶ የሚሆኑት ብዙ ተከታይ ያፈሩት በኢንስታግራም ገጻቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡
ከኪነጥበቡ ውጭ በማህበራዊ ሚዲያው ተጽዕኖ ፈጣሪ ከተባሉ ሰዎች መካከልም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማና የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንራ ሞዲ የሚገኙበት ሲሆን ሞዲ በድምሩ 175 ሚሊዮን ያህል ተከታዮችን ማፍራታቸውን ድረገጹ ጠቁሟል፡፡


Read 4774 times