Monday, 24 May 2021 00:00

የያዕቆብ የግርድፍ መረጃ ጣጣ ወይስ የጋዜጣ ፍቅር?

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(1 Vote)

    ባለፈው ሳምንት የአዲስ አድማስ ዕትም.. የደራሲ ያዕቆብ ብርሃኑን ህብረተሰብ አምድ ላይ “ህዝብን ማን ይሰራዋል?” በሚል ርዕስ የፃፈውን ምጥን-ሀተታ አነበብኩት። ፀሃፊው በሳታቸው ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የራሴን ምልከታ ለማከልና-ለማስተካከል ምጥን ምላሽ ቢጤ አዘጋጀሁ፡፡ በርግጥ ያዕቆብ በሰበሰበው ግርድፍ - መረጃዎች ላይ ተንተርሶ ግዙፍ ርዕሰ-ጉዳይ ለማንሳት መድፈሩ በራሱ ክሽፈት ቢሆንም፣ ስህተቱን ነቅሰን ከመስመር የወጡ ሀሳቦቹን እንዳንተቸው ለጋዜጣ ያለውን ፍቅር እየነገረ በፍቅር ያለዝበናል፡፡
ህዝብን ማን ይሰራዋል ይለናል፤ ያዕቆብ በፅሁፉ መግቢያ ላይ ቀብድ በማስያዝ ሲያንደረድረን፤አዎ ታላቅ ርዕስ እንደሆነ እርግጥ ነው..እርሱም “ሀገርን የሚያህል ግዙፍ ጥያቄ” ሲል ያረጋግጥልናል፡፡ ከዚህ በኋላ ለተነሳበት ርዕሰ-ጉዳይ የፅሁፉ ዝርዝር ይዘት ከመነሻ እስከ መዳረሻ እርስ-በርስ የሚጣረስን የጋዜጣን ኃያልነት አጉልቶ ነባር የፖለቲካ ጋዜጠኞችን የሚያንኳስስ፣ እጅ-እግር የሌለው ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡ ያዕቆብ እነዚህ ፖለቲካዊ ርዕዮተ አለማቸውን እየጠቀሰ የሚዘልፋቸውን በስም አይጠቅስም..በጅምላ ፈርጆ ይዘልፋቸዋል፡፡ እንዲህ ሲል.. “በህይወትና በፖለቲካ አረዳዳቸው መቆርቆዝ እንጂ እድገት አይታይባቸውም!” ሲል በደፈናው ያጠለሻቸዋል፡፡ በምን አግባብ እንደሆነ በምክንያት አስደግፎ ቢያስረግጥልን ጥሩ  ነበር፡፡ ህዝብ ከጋዜጣ ይሰራል ያለን ያዕቆብ፤ ሀሳቡን አክብረን ለመቀበል ለጥሞና የሚሆን በቂ ፋታ ሳይሰጠን አምደኞችን ለመተቸት መፍጠኑ አንድም ለትዝብት ሁለትም በፖለቲካ አረዳዳቸው የምናከብራቸውን፣ ከፃፉት የተማርንባቸውን ባለ-ውለታዎቻችንን ክብር ያለ-መስጠት ንፉግነት ነው፡፡
ግርድፍ መረጃ ዘለላ-ሀቅ ሊኖረው ይችላል። የተሟላ ስዕል መስጠት ግን አይችልም፡፡ ይሄን ይዞ ያለ-ተጨባጭ መተንተንም ሆነ መተርጎም ከማጠየቅ መቅደም የለበትም፡፡ ጋዜጣ ለሀገር ግንባታ ካለው አስተዋጽኦ ጎን-ለጎን ተያይዞ ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው ከአመታት በፊት በዚሁ ጋዜጣ ላይ አለማየሁ ገላጋይ ጽፎ ያነበብኩት አንድ መጣጥፉ ነች፤.. “ጋዜጣን በፀፀት” ትሰኛለች፡፡ ..በጊዜው ልቤን የነካ፣ስሜቴን ያሳዘነ.. ጋዜጣ ላይ ለፃፈ ብቻ ሳይሆን ለመፃፍ የሚያስብ ተስፋ አስቆራጭ እውነታን ያዘለ ጥናታዊ-መጣጥፉ ነው። አለማየሁ በዚህ መጣጥፍ የሀገራችንን የጋዜጣ አምደኛ.. ጊዜ፣ እውቀት አቅም አሟጦ፤ ነገር ግን የጋዜጣ ህልውናና ፍፃሜ ገና ጀምበር ሳታዘቀዝቅ መረሳት መሆኑን በተዋበ ቋንቋ እሚነግር.. ቀዝቃዛ ሀዘን ውስጥ የሚከት የፀፀት ጅራፍ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ.. ይሄን ለአመታት ውስጤ የቀረ የአለማየሁ ፅሁፍ “ደቦ” በሚል ርዕስ እንዳለ ጌታ ባዘጋጀው የነባርና የአዳዲስ ደራሲያን ስራዎች የተካተቱበት ስብስብ ውስጥ ተካቶ በድጋሚ ማንበቤ እንዳስደሰተኝ ሳልሸሽግ ተናግሬ ማለፍ እፈልጋለሁ፡፡)
ያዕቆብ የአለማየሁን ፅሁፍ አላነበበውም ለማለት የሚያስችል ግምት የለኝም፡፡ በጋዜጣ ዙሪያ በቂ ተሞክሮና ንባብ ሳያንሰው ለምን በግርድፍ መረጃ ላይ ተንተርሶ ሚዛኑን የሳተ ፅሁፍ ሊያዘጋጅ እንደቻለ ግን ግልጽ አይደለም፡፡
ባለኝ የግል ንባቤ በአንድ-ወቅት ታይተው ከጠፉ በጨቋኝ የአገዛዝ መዳፍ ከህትመት ከተገፈተሩ አያሌ ጋዜጦች መካከል “የኛ ፕሬስ” ጋዜጣ ላይ በአምደኝነት ብዕሩን ሲያሟሽ ጀምሮ የማውቀው ወጣት ፀሐፊ ሆኖ ሳለ ነበር፡፡ ከፅሑፎቹ የዘወትር ታዳሚዎች መካከል አንዱ ነበርኩ። በተለይ በማህበራዊና ኪነ-ጥበባዊ ጉዳዮች ላይ አድምቶ እሚያሰፍራቸው ትዝብቶቹ ልቦናዬን ቆንጥጠው የመያዝ አቅም ነበራቸው፡፡.. “የማዕበል ጥንስስ”፣ "ሳልስቱ ጣኦታት" ..በመጽሐፍ አስጠርዞ ለንባብ ጀባ ያለን እምብዛም ሳያረፋፍድ ነበር፡፡ ሁለቱንም መጽሐፎቹን አንብቤ ያከበርኩት ትጉህ ወጣት ነው.. የግል ትጋቱ ላያስመሰግነው የሚችልበት በቂ ምክንያት አለ ብዬ አላምንም፡፡ በተለይ “ብኩን ነፍሳት” ወይም “ሰለስቱ ጣኦታት” የጀርመናዊው የኖቤል አሸናፊ ትንታግ ብዕረኛ ሄርማን ካርል ሄስ.. ”ናርሲስ ኤንድ ጎልድመንድ” በጎ መንፈስ ያረፈበት፣ በቂውን-ያህል እንደ ልብ ያልተነበበለት ግሩም ሙከራ ነው። ጀርመን በተደጋጋሚ የኖቤል ሽልማትን ተፈታትነው የነቀነቁ አግበስብሰው ያፈሱ ትንታግ ብዕረኞች የታደለች አውራ ሀገር ነች፡፡ ..ፍራንዝ ካፍካ፣ ወልፍ ጋንግ ጎተ፣ ቶማስማን፣ ፓትሪክ ሰስኪንድ..ሌሎችም፤…የሄስ ልጨኛ ስራ "ናርሲስ ኤንድ ጎልድመንድ".. “..ዕድል-ፈንታ” በሚል ውርስ ትርጉም ወደ አማርኛ ተመልሷል። ..የስነ-ጽሁፋቸው በጎ አሻራ በያዕቆብና መሰሎቹ የሀገራችን ወጣቶች የጥበብ ስራ ላይ በተጽእኖነት አልፎ አልፎም ቢሆን ብቅ ብሎ መታየቱ አልቀረም፡፡
ዛሬ ብዕሬን ለማንሳት ምክንያት የሆነኝ የህዝብ አሰራር ትርክት ቢሆንም.. ካላጋነንኩ በስተቀር ያዕቆብ በጠቅላላ ከፃፋቸው ፅሁፎቹ በቁጥር ቢሰላ ሰባ በመቶውን አንብቤአቸዋለሁ ለማለት እደፍራለሁ፡፡ ..እንኳን ፅሁፎቹ ህይወቱም  የ"ጥበብ ናሙና” ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህንን ለማወቅ ብዙ-ጊዜ መጣጥፎቹንና  የሰራቸውን የመፅሐፍ ዳሰሳዎችን ማጤን በቂ ነው፡፡ በስነ-ጽሁፍ የመነነ የከተማ - ባህታዊ እንደ-ልብ ማግኘት ዘበት ነው፡፡ ለዚያውም በዚህ አፍሮ-ጋዳ ዘመን! ማህበራዊ - ትስስር ገጽ እያለ! መገናኛ ብዙሃን እንደ-ጉድ በፈሉበት ጠፍ-ዘመን ላይ! የስነ-ልቦና ባለሙያው ዶክተር እዮብ ማሞ “ትኩረት” በሚል ርዕስ በፃፉት መጽሐፋቸው፤ “…አንድ አለም-አቀፍ ተነባቢነት ያለውን ጋዜጣ አንብበን የምናገኛቸው መረጃዎች ብዛት..ከመቶ አመታት በፊት አንድ ሰው በአንድ አመት ከሚያገኛቸው መረጃዎች በእጥፍ ይበዛል..”ሲሉ ፅፈው ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡
የጋዜጣ-ፍቅር
ጋዜጣ የመረጃና-የእውቀት ትሩፋቱ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚዳረስ ፀጋ አለው። የጋዜጣ ፋይዳ ለሚሰራበት ህዝብ፣ ለሚቀረጽበት ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን የአለማችን ስመ-ጥር ደራሲያን ዘመን-አይሽሬ ስራዎቻቸውን እሚያረቁት፣ የሀሳብ ጎርፍ እሚያጥለቀልቃቸው.. ሳምንታዊ ጋዜጣና መጽሄቶችን እያገላበጡ እንደነበር ታሪክ በተደጋጋሚ የዘገበውና ያወሳው ጉዳይ ነው፡፡ ያዕቆብ ለጋዜጣ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ የአሜሪካዊውን ደራሲ ረቻርድ ክሉገርን እና ሉዊስ ቡኔልን.. እንደ-መከዳ መንተራስ አልነበረበትም! ፍቅሩ የሁላችንም ነውና እኛም እንጋራዋለን፡፡
እውነት ለመናገር በመውጫው ለጋዜጣ ያለውን ፍቅር የገለፀበት መንገድ እኔም ያለፍኩበት ህይወት ነውና ልቤን ነክቶታል፣ ትዝታዬን ቀስቅሶታል..እንዲህ ሲል ፍቅሩን ተገላግሎታል፤ “ስደትን አምርሬ የምጠላው እኔ፤The Atlantic የተሰኘውን መጽሄቷን በየወቅቱ ለማንበብ ብቻ አሜሪካ ድረስ በእግሬ እንኳን ብሄድ ቅር አይለኝም፡፡”
ያዕቆብ ስለ ስደት አስከፊነት አይደለም ሊነግረን የፈለገው፡፡ ሥለ-ስደት በይበልጥ ለመረዳት በአሁኑ-ወቅት በስፋት እየተነበበ ያለው.. የዮርዳኖስ አልማዝ መንገደኛ ቅጽ ሁለት እላፊን ማንበብ ጠቃሚ ቁም-ነገር ያስጨብጣል..እኔም እያጋመስኩት ያለሁት ማለፍያ የስደት-ሰነድ ነው፡፡ ይሁንና ያዕቆብ አሜሪካ ድረስ በእግርም ቢሆን ተጉዞ ዘ አትላንቲክን ሳያመልጠው ቢያነብ ደስታው እንደሆነ ምኞቱ ሆድ ያባባል፡፡ ለጋዜጣና መጽሄት ፍቅር ሲባል የተከፈለ መስዋዕትነት ሊኖር ቢችልም ተፅፎ የታተመ እስካሁን በንባቤ አላጋጠመኝም፡፡
በአንድ ወቅት ከሩቅ-ምስራቅ ባይሆንም ከክፍለ-ሀገር ወደ መዲናይቱ ሸገር እዚህ በስም የማልጠቅሳቸው አድማስን ጨምሮ ተወዳጅና ተናፋቂ ጋዜጣና መጽሄቶችን ለማንበብ ስንል እኔና ጥቂት መሰሎቼ የተጓዝንባቸው ጊዜያት የጉዞ ታሪካችን ሳይሆን የጋዜጣና የመጽሄት ትዝታችን ነበር።


Read 450 times