Print this page
Monday, 24 May 2021 00:00

ኢትዮጵያ ከህንድ የኮረና ቀውስ ምን ትማራለች?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      (የኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስ ክለብ1 ስራ አስኪያጅ፣ ዶ/ር ሀይሉ ጌታቸው)

            የኮሮና ቫይረስ መጀመሪያ በቻይና ውሃ ታህሳስ 21 ቀን 2012 ለአለም ከተገለጸበት ጊዜ አንስቶ በብዙ ደረጃዎች አልፏል፡፡ ቻይና ስለ ቫይረሱ ሁኔታ ለአለም ሳይንቲስቶች በገለጸችበት ወቅት ጊዜ፣ የአብዛኞቻችን ግንዛቤ ግራ የመጋባትና በሽታው ምናልባትም እንደ ወፍ ጉንፋን ሊሆን ይችላል በሚል ግምት፣ በሽታውን አቅልሎ የማየት ዝንባሌ ነበረን፡፡ ቻይና የውሃን ከተማ ወይም ግዛት በዘጋችበት ወቅት የተጋነነ እርምጃ ነበር የመሰለን፡፡ በሽታው በኢጣሊያና በስፔን ደርሶ ብዙ ዜጐች ሲያልቁ፣ አለምን ክፉኛ አስደንግጧል፡፡ በኢጣሊያ ሰሜናዊ ክፍል ያውም የኮሮና ቤተ ክርስቲያን አካባቢ (ሎባርዲ) ያሳየ ሲሆን ያስከተለው እልቂት፤ የነበረውም የሐኪሞች ተስፋ መቁረጥ እጅግ አስደንጋጭ ነበረ፡፡ ኢጣሊያ ካደጉት አገሮች ተርታ የምትሰለፍ አገር ብትሆንም ቅሉ ለበሽታው መንበርከኳ አለምን አሸብሯል። በተመሳሳይ መልኩ፤ ከስፔን የሚወጡ  አስደንጋጭ ነበሩ፡፡
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በጣም አደጉ ከሚባሉት አገሮች አሜሪካንና እንግሊዝም ደርሶ  ብዙ ህዝብ ጨርሷል፡፡ እስከ አሁን ባለው መረጃ፤ ከአሜሪካ ስድስት መቶ ሺ፤ እንግሊዝ መቶ ሰላሳ ሺ ሞት ተመዝግቧል፡፡ በሽታው በብራዚልና በደቡብ አፍሪካ ባህሪውን ቀይሮ ተከስቷል፡፡ የብራዚሉ ወረርሽኝ የፕሬዚዳንት ጀር ባሳዩት የኮሮና ቫይረስን ተጽእኖ የማሳነስ አዝማሚያ  ዋጋ አስከፍሏል። ቫይረሱ  አራት መቶ አርባ ሺ ብራዚላውያንን ጨርሷል፡፡ አሁን በቅርቡ ክፉኛ ደግሞ በሽታው የተለየ ፈጣን የስርጭት ባህሪ፣ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሺ ህንዳውያን የበሽታዉ ሰለባ ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ክለብ በሰራው ምርምር መሰረት፣ አሁን ቫይረሱ ያለበትን ሁኔታ  ከሶስት አቅጣጫዎች ((1) የኮሮና ቫይረስ ክትባት፣(2) የቫይረሱ በቤት ውስጥና ከቤት ውጪ ያለው የተለያየ ስርጭት እና (3) የኮሮና ቫይረስ በህንድ አገር ባልተጠበቀ ሁኔታ
እንዴት ሊሰራጭ እንደቻለና ኢትዮጵያ ከዚህ ምን መማር እንዳለባት) ቢታዩ ጠቃሚ ነው ብሎ ያምናል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ክትባት
የኮረና ቫይረስን ከመከላከያ መንገዶች ውስጥ ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ፣ የፊት ጭምብል ማድረግ፣ እጅን በሳሙና መታጠብ፣ ሳኒታይዘር መጠቀም ቤት ውስጥ መቀመጥ እና ሌሎችም በመንግስት የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች ይጠቀሳሉ፡፡ ሌላው የመከላከያ መንገድ ክትባት ነው፡፡ ክትባትን በተመለከተ ለማዳበርና ለማሳደግ ጊዜ የፈጀ ቢሆንም፣ የአለም ጤና ድርጅት፣ ለአሜሪካ መንግስት፣ ለአውሮፓ ህብረት፣ ለራሺያ መንግስት እንዲሁም ለቻይና እና ህንድ እውቅና ሰጥቷቸው በርካታ የክትባት መድሃኒቶችን ለአገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ ተችሏል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ክትባት  ትኩረት ስለተሰጠው ክትባት ለመስራት በአማካይ ከሚፈለገው 18 ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ክትባቱ ተዘጋጅቶ ለህዝብ ቀርቧል፡፡ እንደ አሜሪካና አውሮፓ ህብረት ያሉት አገራት በብዛት ዜጎቻቸውን ክትባቱን እንዲያገኙ አድርገዋል። (ለምሳሌ፡- እስራኤል በተሳካ ሁኔታ ዜጎቿን ከትባለች) የክትባቱ ስርጭት በመላው አለም ሲታይ ፍትሐዊ ያልሆነ ወገንተኝነት ያመዘነበት እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ አፍሪካን ጨምሮ ባላደጉት አገሮች ግን የክትባቱ ስርጭት ብዙም ተስፋ ያለው አይመስልም። የኮቪድ -19 ክትባት ስርጭት በመላው አለም ፍትሐዊ ካልሆነ አሁን የሚታየው የኮሮና ቫይረስ ባህሪውን እየቀያየረ፣ የሰውን ልጅ እያጠቃ እንደሚቀጥል ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም የመከላከያ መንገዶቹ እና አብዛኛውን ህዝብ የመከተቡ አጀንዳ ካልተሳካ በስተቀር እንደ አውሮፓው የጭለማ ዘመን (500-1000 ዓ.ም) ውጤቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት አዳጋች አይደለም፡፡  በዚህ ጉዳይ ላይ የሠው ልጅ በህብረት ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የክትባቱ ስርጭት እንዲዳረስ መሰለፍና መታገል አለበት፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ዜጎቿን ለመከተብ የአቅሟን እየጣረች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቢሆንም ጥረቷ ዜጎች ላይ እየደረሰ ካለው ጉዳት አንጻር በቂ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ከወዳጅ አገሮች፣ ከለጋሽ መንግስታት፣ ከአለም ጤና ድርጅት እንዲሁም ከዜጎቿ አስፈላጊውን ትብብር በመፍጠርና በማቀናጀት የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለህዝቧ የማቅረብ አቅም ልታዳብር ይገባታል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በቤት ውስጥና ከቤት ውጭ ያለው የተለያየ ስርጭት
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በአመዛኙ ከህዝብ አላስፈላጊ መሰባሰብ ጋር መያያዙ ይታወቃል። የህዝብ መሰባሰብ ግዴታ የሆነባቸው የስራ መስኮች ለምሳሌ እንደ ት/ቤት፣ የህክምና ተቋማት፣ የሀይማኖት ድርጅቶች፣ የማደሪያ ስፍራዎች ወዘተ… አሉ፡፡ ይህን በተመለከተ የአለም ጤና ድርጅትና የአሜሪካው ሲዲሲ ያወጡት መመሪያ አለ፡፡ ይህንን መመሪያ በትክክል ለመተግበር የኢኮኖሚ አቅምና የማህበረሰብ እድገት ወሳኝ ነው፡፡  እነብራዚል፣ ደቡብ አፍሪካና ህንድ መመሪያውን ችላ በማለታቸው ነው ለከፋ ችግር የተጋለጡ ኢትዮጵያም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ለከፋ ችግር መጋለጧ አይቀርም።
የኮሮና ቫይረስ ክትባት በአለም ደረጃ እየተሰራጨ ቢሆንም፤ አሳሳቢው ነገር ክትባት የወሰደው ሰው በሽታውን የመከላከል አቅም በቤት ውስጥ እና ከቤት ውጪ ባለው ስርጭት በአለም ሳይንቲስቶች መግባባት አልተደረሰበትም፡፡ በተወሰነ ቦታ ላይ ምሳሌ መኖሪያ ቤት፣ የት/ቤት ክፍሎች፣ የህዝብ መጓጓዣ ላይ ስርጭቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችልና፤ በተቃራኒው ከቤት ውጪ (ንጹህ አየር ባለበት ቦታ ላይ) ያለው ስርጭት ደካማ መሆኑን ብዙ ሊቃውንቶች መስክረዋል፡፡ የተከተቡት ሰዎች በቤት ውስጥና ከቤት ውጪ በበሽታው የመያዝም ይሁን በሽታውን የመከላከል ሁኔታ በበሽታው ጠቢባን መስማማት ላይ ስላልተደረሰ ሀገራት ፖሊሲ ለማውጣት ተቸግረዋል፡፡
በሀገራችንም ይህንን አሳሳቢ ሁኔታ በመረዳት በት/ቤቶችና በመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚታየው ጥሩ አዝማሚያ፤ በመኖሪያ ቤቶች፣ በመጠጥ ቤቶች፣ በመዝናኛ ስፍራዎች ተግባራዊ እንዲሆን መንግስት የተጠና ፖሊሲ አውጥቶ ለህዝብ ማስታወቅ አለበት፡፡ በዚህም ላይ ነገሩ የሚመለከታቸው የግል ድርጅቶች (እንደ ኮሮና ቫይረስ ክለብ አይነቶች) የምክር ሀሳብ በመስጠት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።
የኮሮና ቫይረስ በህንድ አገር ባልተጠበቀ ሁኔታ እንዴት ሊሰራጭ እንደቻለ እና ኢትዮጵያ ከዛ ምን መማር እንዳለባት
ህንድ ከሌሎች ሀገሮች በተሻለ ሁኔታ ኮሮና ቫይረስን መከላከልና መቆጣጠር እንደምትችል ስትገልፅ ቆይታለች። ዜጎቿም በእኛ አገር በሽታው አይሰራጭም ብለው ነበር፡፡ ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብአቶችን እያመረተች ለአውሮፓ አገሮች ጭምር የምትልክ አገር መሆኗ እውነት ሆኖም በቸልተኝነትና በጥንቃቄ ጉድለት ከአሜሪካና ብራዚል በባሰ ሁኔታ በሽታው በህዝብ መካከል ተሰራጭቶ የከፋ እልቂት አስከትሏል። ህንድ ውስጥ የተከሰተው ስርጭት የአለም ጤና ድርጅት በገለጸው መሰረት፣ የኮሮና ቫይረስ ባህሪውን የቀየረ በጣም አደገኛ፤ ከአሁን በፊት ከታዩት አራት (የቻይና፣ የእንግሊዝ፣ የደቡብ አፍሪካና የብራዚል) የኮሮና ቫይረስ ባህሪያት በተለየ ሁኔታ በአንድ ጊዜ ስርጭት ሶስት ባህሪያትን ያሳየ እንደሆነ ተረጋግጧል። ይህ ሁኔታ ለህንድ መንግስትና ህዝብ ብቻ ሳይሆን የአለም ህዝብ እንቅስቃሴን፣ የአለም አቀፍ የኢኮኖሚ ልውውጥን አደጋ ውስጥ የከተተ፤ በአገራት መካከል አለመተማመንን የፈጠረ ክስተት ሆኗል፡፡  ህንድ ከገባችበት ማጥ እንድትወጣም የዓለም አገራት ትብብርና ድጋፋቸውን አድርገዋል። ህንዶች ይህንን የኮሮና ቫይረስ ቀውስ ተምረውበት ሌላ ባህሪይ ያለው የኮሮና ቫይረስ እንዳይፈጠር ሳይንቲስቶቿ በትብብር መትጋት ይገባቸዋል።
ሁላችንም “ጤና ለሰው ልጅ ሁሉ” ብለን መቆም አለብን፡፡ በአለም ላይ በተለይ በአሜሪካ፣ ብራዚልና ህንድ የተከሰተው አስከፊ፣ አስደንጋጭና፣ ከአቅም በላይ የሆነ ወረርሽኝ ለኢትዮጵያ ጥሩ የማንቂያ ደውል ሊሆናት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ትምህርት ወስዳ ህዝብን ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ የመስጠት አቅም ማጎልበት አለባት፡፡ የህክምና ባለሙያ በብዛት በወረርሽኝ ህክምና ላይ ማሰልጠን ይኖርባታል። የሀይማኖት ተቋማትም በወረርሽኝ ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ የግል ድርጅቶችም ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስ ክለብ ያሉት ህብረተሰቡን የማነቃቃትና የማደራጀት ከፍተኛ ድርሻ ሊወስዱ ይገባል። ትምህርት ሚኒስቴር በሚያካሂዳቸው ስልጠናዎች ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ በተላላፊ በሽታ ላይ በሚሰጠው ትምህርት እንደ ኮሮና ቫይረስ ባሉ አስከፊ በሽታዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ማስተማርና የት/ቤት ክለቦችን አቋቁሞ ተከታታይ ስልጠና መስጠት አለበት፡፡
በመጨረሻም እኛ ኢትዮጵያውያን ከህንዶች አስከፊና አሳዛኝ የኮቪድ-19 ቀውስ  ተምረን ግዴለሽነትን በማስወገድ ለህይወታችን ዋጋ መስጠት ይገባናል።
***
(የኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስ ክለብ (Ethiopian Corona Virus Club(ECVC)) ወረርሸኝ ከመከሰቱ በፊት፣ በተከሰተበት ወቅትና ከተከሰተም በኋላ ለህዝብ መረጃ ለመስጠት የተቋቋመ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነዉ፡፡ Phone: 09 88 23 96 61/ 09 11 44 90 18; email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )


Read 4146 times
Administrator

Latest from Administrator