Wednesday, 26 May 2021 00:00

አካባቢያዊ ዲፕሎማሲ፤ ቀጠናዊ ትብብር እና ዘላቂ ልማት

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(1 Vote)

  አካባቢያዊ  ዲፕሎማሲ (Environmental diplomacy)፣ ክ1970ዎቹ ጀምሮ እየበለጸገ የመጣ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ዘርፍ ነው። ይህ ዘርፍ፣ በተለይም በሰው ሰራሽ ጋዞች ምክንያት ከፀሐይ ወደ መሬት የሚመጣውን ጎጂ ጨረር የማጣራት አገልግሎት የሚሰጠው የከባቢ አየር ሽፋን (Ozone layer) እየሳሳ ከመሄዱና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በተካሄዱ ዓለም አቀፍ ድርድሮች ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ሊዳብር ችሏል። አካባቢያዊ ዲፕሎማሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባገኙ መሰረታዊ መርሆች ላይ የተመሰረተ ነው። ከነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው፣ ሁሉም ሃገሮች ለሰው ልጆች የጋራ ጥቅም የተሰጡ የተፈጥሮ ሃብቶችን (Global commons) የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት አለባቸው የሚል ነው። ሁለተኛው፣ በአንድ ሃገር የሚከሰት የአካባቢ ብክለት (pollution) እና መራቆት (degradation) በሌላ አካባቢ ለሚከሰት የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት  አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ያስገነዝባል። ይህ ሁኔታ በተለይ፤ በድንበር ተወስነው በማይገቱት የአየርና የውሃ ብክለት ላይ ጎልቶ የሚታይ ነው። በሶስተኛ ደረጃ፣ ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ ደህነንት (wellbeing) አስፈላጊ የሆኑ የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ዓለም አቀፋዊ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን የሚያስገነዝበው መርህ ነው። በእነዚህ ላይ በመመርኮዝ፣ ክ1970ዎቹ ጀምሮ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ በአካባቢ ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የትበብር ማዕቀፎች (frameworks)፣ ስምምነቶች (treaties) እና ህጎች ጸድቀው በስራ ላይ ውለዋል።
ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ግጭቶች ለዘመናት ከሰው ልጆች ጋር የኖሩ ከባቢያዊ ሁነቶች ናቸው። እንዲህ አይነት ግጭቶች በተለይ መሰረታዊ የዕለት ተዕለት ኑሮአቸው ከተፈጥሮ ሃብት ጋር በጥብቅ የተሳሰረና ከእጅ ወደ አፍ  (subsistence) የሆነ ኑሮ በሚገፉ ማህበረሰቦች መካከል ጎልቶ ይታያል። ባለፉት ዓስርተ ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ የተከሰቱት አብዛኞቹ የእርስ በአርስ ግጭቶች ከበስተጀርባቸው የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ጥያቄ እንዳለበት በርካታ ጥናቶች ያሳያሉ። ይህ እንዳለ ሆኖ፣ በፈጣን ሁኔታ እያደገ ከሚሄደው የህዝብ ብዛት የተነሳ፣ እነኚህ ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ከባቢያዊ (local) ግጭቶች በሃገሮች መካከል ሊፈጠሩ ወደሚችሉ ግጭቶች ሊያድጉ ይችላሉ የሚል ከፍተኛ ስጋት አለ። ከእነዚህ በዋነኛ የስጋት ምንጭነት ከሚጠቀሱ የተፈጥሮ ሃብቶች መካከል አንዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ የመጣው የውሃ እጥረት (fresh water scarcity) ነው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015፣ ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሃብት ፓነል (International Resource Panel) ባወጣው ሪፖርት መሰረት፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2030 ከ3.5 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ የዓለም ህዝቦች መካከለኛና ከፍተኛ የውሃ እጥረት በሚያጋጥማቸው ሃገሮች ውስጥ የሚኖሩ ይሆናሉ። ይህንን ችግር ለመወጣት፣ የውኃ አጠቃቀምን በየደረጃው ከማሻሻል ባሻገር በሃገሮች መካከል ትብብርን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት አግኝቷል።  በመሆኑም፣ ከ1990ዎቹ ጀምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የውኃ አጠቃቀም ድንጋጌዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪነት ሊጸድቁ ችለዋል። እነኚህ ድንጋጌዎች በሶስት አበይት መርሆች ላይ የተመረኮዙ ሲሆኑ፣ እነርሱም የፍትሃዊ ተጠቃሚነት (equitable utilization)፤ በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት አለማድረስ (no significant harm) እና ትብብርን (cooperation) የማጠናከር መርሆች ናቸው።
ተደጋግሞ እንደተገለጸው፣ ኢትዮጵያ ባላት ልዩ ምህዳራዊ ስብጥር የተነሳ በአፍሪካ ውስጥ ሁለተኛዋ የውሃ ማማ ተብላ ትጠቀሳለች። በሌላ በኩል፣ አብዛኛዎቹ ተፋሰሶቻችን ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ ወንዞች የሚጠናቀቁ በመሆናቸው ከውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሃገሪቱ ለበርካታ ፈተናዎች እንድትጋለጥ አድርጓታል። አንዲህ አይነቱ ፈተና ከህዳሴ ግድብ ቀደም ብሎም ከሌሎች ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ተከስቷል። ለምሳሌም ያህል፣ በኦሞ ተፋሰስ ውስጥ ኢትዮጵያ የኃይል ማመንጫዎች መገንባት በጀመረችበት ወቅት፣ የግድቦቹ መገንባት በኬንያ ውስጥ ለሚገኘው የቱርካና ሃይቅ ውሃ የሚመግበውን ፍሰት ያቃውሰዋል በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቶ ነበር። በወቅቱ፣ በበርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አማካኝነት ‘የቱርካናን ሃይቅ እናድን’ በሚል መፈክር ስር የጊቤ አንድ ሁለት እና ሶስት ግንባታን ለማስቆም እንቅስቃሴ ተደርጓል። ይህ ሁኔታም በተለያየ ወቅት ለኬንያ ፓርላማ በአጀንዳነት ከመቅረቡም በላይ፣ በአንድ ወቅት  ለተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም ጉባዔ በአጀንዳነት እንዲቀርብ ግፊት ተደርጎ ነበር። ይህንን ጥያቄ በአግባቡ ለማስተናገድ በቅድሚያ የግድቦቹ መሰራት በሃይቁ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በሳይንሳዊ መንገድ ማረጋገጥና ይህን ካወቁም በኋላ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ምን መደረግ አለበት የሚለውን በሁለቱም ሃገሮች ተሳትፎ መመልከቱ አስፈላጊ ነበር። በዚህ መሰረት ገለልተኛ በሆነ የምርምር ተቋም የተካሄደው ቀዳሚ ጥናት በግድቦቹ መሰራት የሚከሰተው የፍሰት መለዋዋጥ ባለፉት መቶ ዓመታት በተለዋዋጭ የአየር ሁኔታዎች ከተከሰተው መለዋወጥ የተለየ አለመሆኑን በማረጋገጡ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ አጀንዳ መሆኑ ቀርቶ ሃገሮቹ የጋራ ተጠቃሚነታቸውን በሚያጠናክሩ ትብብሮች ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ ተችሏል።   
የዘመናችን ፈተና ከሆነው የዓለማችን ከባቢ አየር ለውጥ ጋር ተያይዞ የተካሄዱ ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፣ የዝናብ ስርጭቱ ተለዋዋጭነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀጠና በሚመጡት ዓመታት ከወትሮው ያልተናነሰ፣ በአንዳንድ አካባቢም ከወትሮው የጨመረ ዝናብ ያገኛል። ይህ ለሃገሪቱ መልካም ዜና የመሆኑን ያህል በሌሎች ቀጠናዎች ሊከሰት ከሚችለው የዝናብ እጥረት ጋር በተያያዘ ተጨማሪ የዲፕሎማሲ ፈተና ሊደቅንባት እንደሚችል ይገመታል። እነኚህን ፈተናዎች በውጤታማነት ለመሻገር፣ በማናቸውም ተፋሰስ ውስጥ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎቻችንን በወቅቱ ባለው የሳይንስ እና የምህንድስና ዕውቀት ላይ የተመረኮዙ ዝርዝር ቴክኒካዊ ስራዎች ከመስራት ጎን ለጎን ጊዜውን የሚመጥን የአካባቢ ዲፕሎማሲ ስራ መስራት እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህንን ጉዳይ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ካጋጠሙ ተግዳሮቶች ጋር አያይዘን ብንመለከት፣ በናይል ተፋሰስ ተነሳሽነት (Nile Basin Initiative) አማካኝነት ለዓመታት የተሰራው ቴክኒካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሥራ፣ የግብጽን መንግስት ፈርዖናዊ አሰተሳሰብ በማዳከሙ ሂደትና ለህዳሴው ግድብም ከፅንሰ ሃሳብ ወደ ተግባር መሸጋገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይታመናል። በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደትም ውስጥ፣ የግድቡን ቴክኒካዊ አስተማማኝነት ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት በአብዛኛው የተሳካ በመሆኑ በዚህ ሥራ ላይ የተሳተፉ ወገኖች ሊመሰገኑ ይገባል። ይህ ጥረት፣ የኢትዮጵያን ፍትሃዊ አጠቃቀም ባስከበረና በታችኛው ተፋሰስ ሃገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት አለማድረሱን ባረጋገጠ መልኩ ሊቀጥል ይገባል።
ከዚህ በተጨማሪ ግን፣ ወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ መሰል ፈተናዎችን ለመቀነስና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ።  ከሁሉም ቀዳሚው፣ የትኛውንም ወንዞቻችንን ለማልማት በምንነሳበት ጊዜ፣ ተናጠላዊ (stand-alone) ፕሮጀክቶችን፣ ተፋሰስ-ተኮር (Basin-oriented) በሆኑ ስልታዊ የልማት ዕቅዶች ማእቀፍ ውስጥ እንዲታቀዱና እንዲተገበሩ ማድረግ ነው። የተፋሰስ-ተኮር አካሄድ፣ በተለያዩ መሰል ፕሮጄክቶች መካከል ሊኖር የሚገባውን ተደጋጋፊነት ከማጠናከሩም ባሻገር በልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች መሃል ሊኖር የሚችለውንም መተሳሰር በማሳለጥ ሃገራዊ ልማቱን ለማፋጠን ያግዛል። በተጨማሪም፣ ተፋሰስ-ተኮር ልማት ለከባቢ አየር ለውጥ የማይበገር (climate-resilient) ኢኮኖሚ ለመገንባትም ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ከሁሉም በላይ፣ እንደ ኢትዮጵያ ላለ በርካታ ወንዞቿ ድንበር ተሻጋሪ ለሆኑባት ሃገር፣ ተፋሰስ-ተኮር ልማት የወንዞቻችን መዳረሻ ከሆኑት ጎረቤት ሃገሮች ጋር ፍትሃዊ የሆነ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ቀጠናዊ ትብብር ለማጠናከር ሁነኛ መሰረት ይጥላል። በዚህ ረገድ፣ በናይል ተፋሰስ ተነሳሽነት ውስጥ ኢትዮጵያ የነበራት ቁልፍ ድርሻ እንደ ምሳሌ የሚወሰድ በመሆኑ ይህንኑ በሌሎችም ድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሶች መድገምና የዚህ ጥረት ውጤት የሆነውን የናይል ተፋሰስ ሁሉን አቀፍ የትብብር ማዕቀፍ ተግባራዊ እንዲሆን መጣር በወንዞቻችን ዙሪያ ሊኖር የሚችለውን ቀጣይ ዲፕሎማሲያዊ ፈተናዎች ለመወጣት እንደሚያግዝ ይታመናል። ከፖለቲካውም አኳያ፣ አብዛኞቹ ተፋሰሶች ካንድ በላይ ክልሎችን የሚሸፍኑ በመሆናቸው በክልሎች መካከል ሊኖር የሚገባውን የልማት ትብብርም ለማጠናከር ያግዛል።  
በሁለተኛ ደረጃ፣ የሃገራችንን ፍትሃዊ የተጠቃሚነት መብት ማስከበርንና በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ ዓለም አቀፍ ኃላፊነታችንን በተቀናጀ መልኩ ማራመድ ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ አስተያየት የሚሰጡ አንዳንድ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና የመንግስት ባለስልጣናት ሃገሪቱ ያሏትን ወንዞች ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ መጠየቅ እንደማያስፈልጋት ሲናገሩ ይደመጣል።  ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነቱ አነጋገር የግብፅና ሱዳንን የታሪካዊ ባለቤትነት ክርክር ትርጉም የለሽነት ለማሳየት የተባሉ እንደሚሆኑ ቢገመትም፣ በዙሪያችን የሚገኙ እና በወንዞቻችን ተጠቃሚ የሆኑ መልካም ጎረቤቶቻችንን ሊያስደነግጡም፣ ሊያስኮርፉም እንደሚችሉ መረዳት ይኖርብናል። በእንዲህ አይነት አስተሳሰብና አካሄድ ለመጓዝ መሞከርም፣ በተፈጥሮ የተሰጡን ፀጋዎች የግጭቶች መነሻ እየሆኑ፣ ወደ እርግማንነት ሊቀየሩ የሚችሉበት ሁኔታ ውስጥ ሊከተን እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ የመንግስት ባለስልጣናትና ዲፕሎማቶች በወንዞቻችን ስለመጠቀም መብት በሚናገሩበት ወቅት ሁሉ ፍትሃዊ አጠቃቀምን በሌሎች ላይ ጉዳት ካለማድረስ እና በትብብር ከመልማት ጋር አያይዘው ቢናገሩ በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ፈተናዎችን ለመቀነስ ይረዳል። በዚህ ረገድ፣ አትዮጵያ ከግድቦቿ የምታመነጨውን ኤሌክትሪክ በምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት (East African Power Pool) ትብብር መሰረት ለጎረቤት ሃገሮች ለማዳረስ የምታደርገው ጥረት ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ለቀጠናዊ ትብብሩ እንደማሳያ ማቅረብ ይቻላል።
በመጨረሻም፣ በቅርቡ ከሚካሄደው ምርጫ ጋር በተያያዘ በአንድ ሚዲያ፣ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ለመከታተል ችያለሁ። በዚህ ክርክር ወቅት፣ ሁሉም ፓርቲዎች ጥቅል የሆኑ ሃገራዊ ጥቅምን በማስከበርና ዓለም አቀፍ ደንጋጌዎችን መሰረት ያደረገ መልካም ጉርብትናን በማጠናከር ዙሪያ ጠቃሚ ሃሳቦችን ሲያነሱ ተደምጠዋል። ከዚህ በላይ ከተዘረዘረው አኳያ ግን፣ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ልዩ ስጋት ሆኖ ሊመጣ የሚችለው የአካባቢ ዲፕሎማሲ ፈተናዎች በአግባቡ አለመነሳቱ ያሳስባል። ይህንን ክፍተት ለመሙላት፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርትን የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎችም ሆኑ የዲፕሎማቶች ማሰልጠኛ ተቋማት በአካባቢ ዲፕሎማሲ መስክ የተጠናከረ ስልጠና መስጠት ይኖርባቸዋል። ለሥልጣን የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ የአካባቢ ዲፕሎማሲን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎቻቸው አንደኛው ምሰሶ ቢያደርጉ ሃገራዊና ቀጠናዊ የአመራር ብቃታቸውን በማጎልበት ለመጪው ዘመን መንግሥታዊ ፈተናዎች የሚኖራቸውን ዝግጁነት ያጠናክረዋል። ይህም፣ ኢትዮጵያን ለቀጠናው የስጋት ምንጭ ከመሆን ይልቅ ግንባር ቀደም የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም ተምሳሌት ሊያደርጋት ይችላል።     
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው  ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ የአፍሪካ ሳይንስ አካዳሚም አባል ናቸው።


Read 5826 times