Saturday, 22 May 2021 12:38

“ከአመጿ ጀርባ”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

     “ከአመጿ ጀርባ” የሚል ነው - መጽሐፉ። እውነተኛ ታሪክ ነው? ልብወለድ ድርሰት ነው? እርግጡን መናገር ያስቸግራል። መጽሐፉ፣ አዲስ ነው - በኤደን የተፃፈ፣ ወይም የተደረሰ።  ሽፋኑም ላይ፣ ገለጥ ሲደረግም፣ “ልብወለድ” ወይም “እውነተኛ ታሪክ” የሚል ታፔላ አልተለጠፈለትም። “አልነግራችሁም። አንብባችሁ ድረሱበት!” ለማለት ይሁን አይሁን አይታወቅም። በእርግጥ፣ ከድርሰቱ ወይም ከታሪኩ በፊት፣.... ስለመጽሐፉ ይዘት የሚናገር፣ መግቢያ ጽሑፍ አለ - አንድ ገፅ። እዚሁ መግቢያ ላይ፣ ስለ “ገፀባሕርያት” ትነግረናለች - ደራሲዋ። ልብወለድ ታሪክ ቢሆን ነው።
ግን ደግሞ፣ በመጽሐፉ ውስጥ፣ በእውነተኛ ስማቸው ለተጠቀሱና ለተተረኩ ሰዎች፣ መልዕክት ታስተላልፋለች። እውነተኛ ታሪክ ቢሆን ነው።
ልብወለድ ድርሰት ወይስ እውነተኛ ታሪክ?  ወይስ የሁለቱ ቅልቅል - አንዱ በሌላው ውስጥ ሰርጎ ገብ? ቁርጡን፣ ከደራሲዋ እስክንጠይቅ ድረስ፣... ከመጽሐፏ የመጀመሪያ ገፆች፣... ጥቂት ጥቂት እናስነብባችሁ - ልብወለድ ታሪክ እንደሆነ በመተማመን ወይም  ከልብ በእጅጉ ተስፋ በማድረግ።

              የአመፅ ዋዜማ።
ሁሉም ነገር ዋዜማ አለው፤ እውነቴን ነው።
...ህይወት፣ አንድ ሁነት ከመዝራቱ በፊት፣ ብዙ ሂደቶችን አልፎ፣ በርካታ የመግቢያ ደውል አስምቶ ነው። ሳይረገዝና ሳይማጥ የሚወለድ፣ ምንም የሕይወት ክስተት የለም። ነገሩ የማስተዋል ጉዳይ ነው።
የዛሬ አስራ ሁለት ዓመት ገደማ መሆኑ ነው፤ ... ግን፣ ልክ እንደትላንት ነው የማስታውሰው። በጊዜው፣ በጣም እወደው ከነበረው፣ ከድሮ ፍቅረኛዬ ጋር የተገናኘንበትን ቀን ልናከብር፣ ቀጠሮ ነበረን።
ከዚህ ቀን በፊት... ለጥቂት ወራት ምን ሳስብ እንደነበር፣ በአጭሩ...
የሕይወቴን ብኩንነትና እርባና ቢስነት፣ ከመቼውም በላይ የተረዳሁበት ጊዜ ነበር። ከሶስቱ ቁልፍ የሕይወቴ ማእዘኖች ውስጥ፣ ሁለቱ (ቤተሰቦቼና ስራዬ)፣ ፍሬ እና ደስታ አልባ ነበሩ። የእነሱ ሸክም ደግሞ፣ ሶስተኛውንና ጤነኛውን ጎኔን፣ ፍቅሬን እየገደለው ነበር።
ቤተሰቦቼን መሸከምና ማስታመም የታከትኩበት፤ የስራ ቦታ አለቃዬን ማከምና ማስተማር በቃኝ ያልኩበት፤ እራሴንም ጭምር ማደንዘዝ እና ማደነዝ የታከትኩበት ጊዜ ነበር። እነዚህ ሁለት ክፉኛ የታተሙ የሕይወቴ ጎኖች፣ ሦስተኛውና የምሳሳለት ፍቅሬ ላይ መጣል “ይብቃ” ያልኩበት፣ ታሪክ ቀያሪ ወቅት ነበር።
ሁለቱ የሕይወቴ ጎኖች ምንም ማብራሪያ አይሹም። ብዙ ሸክም እና ሕመም ይዘዋል። በተለይም ከቤተሰቦቼ ጋር የተያያዘው ጎኔ። እንደው ጎኔ ልበል እንጂ፣ የትኛው ጎኔ፣ የትኛው አናቴ ወይም እንጀቴ እንደሆነ መለየት ከባድ ነው።
አንደኛው የሕይወቴ ማእዘን፤ ፍቅሬ።
ስለ ስሱ ጎኔ ላውራ፣ ስለ የድሮ ፍቅረኛዬ። ሄኖክ ይባላል። እስከዛሬ ድረስ ሳስበው፣ ፈገግታው ልቤን ያበራዋል።
ወጣቶች ነበርን። ከ”ዩንቨርስቲ” ተመርቀን፣ ጥቂት ዓመታት መስራታችን ነበር። ፍቅራችን ወሰን አልነበረውም። ከተማው ውስጥ የነበርነው ከዋክብት፣ እኛ ብቻ ነበርን።
ስንገናኝ፣ ከተማችን ብቻ ሳትሆን ምድርም ትሞቃለች፤ ትደምቃለች። ሌሎችም ፍቅረኞች ሲዋደዱ ይሰማናል።
እኛ ስንስቅ፣ ግማሽ ጨረቃ ትሞላች። ሰዎች ሐዘናቸውን ይረሳሉ። ያለ ምክንያት ይፈነጥዛሉ። ይደሰታሉ። ፍቅራችን ከእኛ በላይ ነበር። የእኛም አልነበረም። ፍቅር ከነበረበት ጥልቀት ውስጥ ገብተን ስለቀመስነውና፣ ጠጥተነው ስለሰከርን፣ የእኛ መስሎን በፍቅር ወይን ልባችን ታወረ። ሰከርን።
ከስካራችን እና ከፍቅራችን ጀርባ ግን፣ ሁሌም አንድ ነገር ይታወቀኝ ነበር... የጨላለሙት ሁለቱ የሕይወት ማእዘኖቼ፣ ፍቅሬን እንዳፈኑት።
ሁለቱን ሸክሞቼን የማራግፈው፣ ውዴ ላይ እንደሆነ አውቃለሁ። ሸክሜ፣ ከእኔ አልፎ እሱንም እንደከበደው፣ ባይናገረውም ገብቶኛል። ምድርን የሚያሞቀው ፍቅራችንን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲያቀዘቅዘው ይታወቀኛል። ይሁን እንጂ፣ ሸክሜን ማውረድ፣ ወይም ውዴን ብቻ መምረጥ፣ ቀላል አልነበረም። ያው... እስኪሆን ድረስ ማለት ነው።
ፍቅራችን ወሰን አልነበረውም። በአንድ ሳንባ፣... ማለቴ በአንድ የሰው ሳንባ፤ የምንተነፍስ ነበር የምንመስለው። ግን ከቀን ወደ ቀን፣ የእኔ የህይወት ሸክም እጅግ እንደከበደው ገባኝ።
እንዴት ሁል ጊዜ ንትርክ እና ብሶት እያወራሁ፣ ቀናችንን ላበላሸው?
የለየላቸው ወመኔ ወንድሞቼንና ተስፋ የቆረጠው አባቴን፣ መጦር፣ መንከባከብ፣ መልሶም ማስተዳደር ደከመኝ። በዚያም ላይ፣ የሚያሳዩኝ ንቀትና ማንቋሸሽ፣ ታከተኝ። እንዴት ልበለው?
የአለቃዬን ጆሮ የሚወጋ ድምጽና ጭቅጭቅ መስማትና ትንኮሳዎቹን ማስተናገድ ሰለቸኝ። እያንዳንዷን ጉዳይ፣ ለአለቃዬ መልሼ እንደ ልጅ ማብራራት ታከተኝ። አቅሜን የሚመጥን ስራ እና ደሞዝ ናፈቁኝ። እንዴት ልበለው? ይሔንንስ፤ በየጊዜው እንዴት ደጋግሜ ልንገረው?
ህመሜ፣ ከእኔ አልፎ፣ ለውዴ መትረፉ ግልጽ ነበር። የፊቱ የፈገግታ ብርሃን፣ የልቡን የፍቅር እሳት እንዳደበዘዘው ታወቀኝ። ፈራሁ። ፈርቼ፣ በማላውቀው ጥልቀት ፈራሁ። ከእኛ ህይወት እልፎ ተርፎ ምድርን ያበራ ፍቅራችንን እንደማጣው ገባኝ። ሸክሜ፣ ስስ ጫንቃውን ክፉኛ እንደተጫነው ታወቀኝ።
ውዴ፣ እንደ እኔ የተወሳሰበ እና ሸክሙ የበዛ ህይወት ያለው አይመስለኝም። ጤነኛ ቤተሰብ እና ጤነኛ ስራ አለው። “ጤነኛ” የሚለው ቃል እራሱ፣ አሁን እንዲያግባባን እንጂ፣ ትርጉሙ ብዙ ነው።
...ፍቅራችን፣ በነበርንበት አካሄድ፣ ይሞታል እንጂ ህይወት አይዘራም ብዬ አምኛለሁ። ያንን ማየት፣ ለእኔ የሞት ሞት ነበር። በህይወቴ የነበረኝን ብቸኛ ተስፋ ላለማጣት የነበረኝ ሌላ ብቸኛ አማራጭ፤ እኔው እራሴ ቀድሜ መልቀቅ ነበር፤ ሳልነጠቅ መስጠት።
ውዴ ግን፣ ከአኳኋኔ ገብቶታል። የአፍቃሪ ቀልብ አይስትም። ከሶስት ወር ምጥ በኋላ፤ ሶስተኛ ዓመት ሊሞላን አካባቢ፤ እውነቱን እንደምነግረው አወቅኩ። እኔ ቀኑን አልመረጥኩም፤ ቀኑ ነው የመረጠን።
አንደኛው የሕይወት ማእዘን፤ ስንበት።
ሐሙስ ነበር ቀኑ። ከሰዓት በኋላ፣ ከቢሮ ፍቃድ ጠይቄ፣ እውዴ ቤት ሄድኩ። ምኔ እንደሄደም አላውቅም። ብቻ የተወሰነ ነገሬ ሄዷል። ቤቱን በአበባ፣ በጥቃቅን ጣፋጭ ነገሮችና በፍቅር ሞልቶታል። ሦስተኛ ዓመታችንን ልናከብር መሆኑ ነው።
ውዴ እና እኔ... በብዙ ነገርም እንመሳሰላለን። እጅ ለእጅ ተቆላልፈን፣ በፍቅር ሰረገላ፣ ቸርቸር ጎዳናን ቁልቁል እየከነፍን ስንወርድ... ዙረታችን ይገርመኛል። ፒያሳን እንደ ታቦት እንዞራታለን። ክሪያሶዝ እየተሻማን እንበላል። ቶሞካ ማኪያቶ እንጠጣለን። ምንም ከማንገዛቸው ትልቅ የልብስና የወርቅ መደብሮች፣ በአይናችን እንቀላውጣለን። ከየአዟሪው ማስቲካ እንገዛለን፤ ስናኝክ እንውላለን።
ትንሽ ኪሳችን ሞላ ካለ፤ ድሃብ ምሳ እንበላና፣ ሳንቲም ከተረፈን ሲኒማ አምፒየር እንገባለን። ...ጊዜው ካልመሸ መላቀቅ ስለሚከብደን፤ የጫማችን ተረከዝ እስኪጣመም ድረስ ፒያሳ ለፒያሳ እንዞራለን። አሁን አሁን ሳስበው፣ ፒያሣ ላይ የሚያጣብቅ አንዳች አባዜ ነበረብን።
እናም ውዴ የዚያን ሀሙስ... ጠብ እርግፍ ብሎ፣ እንደ አዲስ እንግዳ አስተናገደኝ። ምን እየሆንኩ እንደነበር በቅጡ አላስታውስም። ብቻ የሆነ ሰዓት ላይ እንደምንም ብዬ....
“ማ... (ለምን ሙሉውን “ማር” ብዬ እንደማልጠራው አላውቅም)፤ አንድ ምነግርህ ነገር አለኝ” አልኩት። አይኖቹን ሙሉ ለማየት እየተሳቀቅኩ።
“እኔም የምነግርሽ ከባድ ጉዳይ አለኝ፤ ማን ይቅደም?” አለኝ፣ ፀጉሬን በለስላሳ እጆቹ እየደባበሰኝ።
ዝም አልኩ። ዝምታዬ፣ በጣም ጮክ ያለ ነበር። ብዙ ድምፁ ነበረው። ሰምቶኛል። ግብቶታል። ማመን ስላልቻለ ጠየቀኝ።
“የኔ ማር አንቺ ቅደሚ፤ ምንድንነው የምትነግሪኝ?”፤... ፍርሀትና ልመና ድምጹ ውስጥ ነበር።
“ልቤ አብዝቶ ስለሚወድህ፣ እዚህ ላይ ይብቃን። እኔ ጣጣዬ ብዙ ነው። አንተ በቻልከው ሁሉ አክመኸኛል። የማያገግም የቤተሰቦቼን ህመም አብረኸኝ ታመሃል። የስራ ቦታ ሸክሜንና ብሶቴን ተቀብለኻል። አንተንም፣ ፍቅራችንም፣ ከዚህ በላይ መግደል አልፈልግም። እዚህ ላይ ይብቃን” አልኩና...
“ኡ፣ኡ... ፍፍፍፍ”... አልኩ። እንደወለድኩ ያህል ተሰማኝ። ለእርሱ ደግሞ፣ ሲሸሸው የከረመው መራራ እውነት ነበር። በተቀመጠበት ፈዞ ቀረ። ሁለታችን፣ የተለያየ መደንዘዝ ውስጥ ገብተን ስለነበር፣ ከዚያ በኋላ የነበረውን ነገር ብዙ አላስታውስም።
* * *
ዓርብ ጠዋት እንደምንም እየተጎተትኩ ቢሮ ገባሁ። ይቅርታ አሁንም፤ እኔ ልግባ፣ ወይንም ቀፎው ሰውነቴ ይግባ፣ እርግጠኛ አይደለሁም። ብቻ ሰውነቴ፣ እንደ ድንጋይ ከብዶኝ አረፈድኩ።
ወደ አራት ሰዓት አካባቢ፣ ስልኬ ጠራ። የውዴ አከራይ ነበረች። የምትለው ነገር፣ በግልጽ አይሰማም። ለቅሶና ጮኸቷ ውስጥ ግን፣ መርዶዬ ገባኝ። በቅፅበት ዙሪያዬ ሲጨልምብኝ ትዝ ይለኛል። ከእዛ በኋላ የሆነውን አላስታውስም።
* * *
ዓርብ ከሰዓት፣ ከዚህኛው ምድር አልነበረኩም። ምናልባትም፣ አራተኛው ወይንም አምስተኛው ሰማይ ላይ ነበርኩ። ይሄ እንግዲህ፣ የእኔ ግምት ነው። እዚህ ምድር ላይ እንዳልተገናኘን አውቃለሁ። ምናልባት፣ እኔ ግማሽ መንገድ ሄጄ፤ ውዴም ግማሽ መንገድ ወርዶ፣ ሊያበረታታኝ እና አይዞሽ ሊለኝ ይሆናል የተገኛኘነው። እኔ ምን አውቃለሁ? ለሁሉም፣... ከውዴ ጋር የመጨረሻ ስንብት አደረግን።
የነበርንበት ቦታ፣ ብዙም የሚያላቅስ አልነበረም። አብረን ለረጅም ሰዓት የተቀመጥን ይመስለኛል። ምንም ምናወራው ነገር አልነበረንም። አፍም አልነበረንም። ድምጽም አልነበረንም። በዝምታችን ውስጥ ግን፣ በቃላት የማይገለጽ፣ ጥልቅ አንድነትና የሚሞቅ ፍቅር ነበር። ፈገግታው ምድርን ያሞቃል። በመለያየት ጥልቀት ውስጥ ያለን አንድነት፣ ያየው ብቻ ያውቀዋል። የመለያየት ጥጉ ጋ ስትደርሺ ብቻ ነው፣ መለያየት የሚባለው ሀሳብ የውሸት እንደሆነ የምትረጂው። ያኔ የህይወትን አንድነት እና ሙሉነት ትረጂያለሽ። የእኔ፣ የእሱ፣ የእሷ፣ የእነርሱ የሚባል ነገር እንደሌለ ይገባሻል። እርግጥ ነው፣ ይሔ የሚገባው ለጥቂት እብዶች ብቻ ነው። ከዛማ ውዴን፤ ለስራ ጉዳይ እንደሚሸኝ ፍቅረኛ ሸኘሁት። በናፍቆት እና በስስት።
* * *
ቅዳሜ ጠዋት፣ ሆስፒታል አልጋ ላይ ነቃሁ። ለመስማትም ለማልቀስም እቅም አልነበረኝም። ከጥቂት ደቂቃ ንቃትና ህመም በኋላ፣ እንደገና ወደ ጥልቅ እንቅልፍ ገባሁ።
ለምንድን ነው መልካም ሰዎች የማይበረክቱት? ለምንስ በየጓዳችንና በየአደባባዩ፣ “ኧረ ይሄን ሰው ንቀልልኝ!” የሚባሉ ጨካኝ ሰዎች፣ እንደ ማቱሳላ ዘልዛላ እድሜ የሚሰጣቸው? ምክንያቱ አልገባኝም።
ማታ ላይ ወደ ለቅሶ ቤት ሄድኩኝ። የገባኝ ቢመስለኝም ብዙ ያልገባኝ ነገር ነበር። ብዙውን አላስታውስም። ማን ምን እንዳለ አላውቅም። ስወጣ ግን፣ አከራዬ ጠጋ ብላ አቀፈችኝና እያለቀሰች፣...
“አፈር ልብላ ልጄ፤ አንድ ፍሬ ልጅ!... ምን ሰይጣን ሹክ አለብኝ?” ብላ፣ አንዲት ብጣሽ ወረቀት ሰጠችኝ፤ ...አንጀት የሚበጣጥስ ነገር የያዘች።
* * *
ውዴ፤ ህይወት፣ ለብዙዎቻችን ቀላል ጓደኛ አይደለችም። አብረን ስንሆን ግን፣ የማልችለው ነገር አልነበረም። ያንቺም የኔም፣ ትልልቅ ፈተና፣ ተራ ነበር። ፍቅራችን ያሸንፈው ነበር። ፍቅራችን ስትወስጂብኝ ግን፣ ሁሉም ነገር ይከብዳል። ካንቺ በፊት፤ ብቻዬን ኖሬዋለሁ፤ አውቀዋለሁ፤ አልችለውም።
የእኔ የህይወት ፈተና፣ ካንቺ በጣም ቢብስ እንጂ፣ አያንስም። በሸክም ላይ ሸክም ለመጨመር፣ ዝርዝር ውስጥ አልገባም። ህይወቴ፣ ጣእምና ትርጉም ያላት፣ ካንቺ ጋር ስሆን ነበር። እኔ ልጠይቅሽ የተዘጋጀሁት አብረን እንድንኖር ነበር። አንቺ ደግሞ...
ከባድ ልዩነት ነው። ግን እረዳሻለሁ። ፍቅር ይረዳል። ህይወት በብዙ መልኩ ፈትናኝ እዚህ ደርሻለሁ። አሁን ግን ይብቃኝ። ደክሞኛል። ለመሄዴ፣ ራስሽን ምክንያት ለማድረግ አትሞክሪ። ከራሴ ውጪ ማንም ተጠያቂ አይደለም። ይልቅ፣ እያንዳንዷን ቀን ኑሪባት። ሳቂባት። ጀግና እንደሆንሽ አሳያት። መኖርን፣ እንደኔ አትፍሪ። ታሸንፊዋለሽ። ማንም ደስታሽን እንዲወስድ አትፍቀጂ።...



Read 2418 times