Saturday, 22 May 2021 15:18

ዚፖራ

Written by  ከጃእርስዎ ሞትባይኖር ኪሩብዔል
Rate this item
(7 votes)

      ዚፖራ ነው ስሜ የምትል ልጃገረድ በፈረንጆች ገና ሰሞን ተተዋወቅሁኝ። ከተቀመጥኩበት ሥፍራ ድረስ ሰተት ብላ መጥታ “አንዴ ላነጋግርህ እችል ይሆን?” ስትል ቀለስለስ ብላ ጠየቀችኝ።
ምጥን ሰው መሆን የጀመርኩበት ወቅት ስለነበር በአግባብ ከሚያጋጥሙኝ ሴቶች በስተቀር የዓለም ሥራ ፌዝና ጨዋታ የሚሹትን በዘዴ አቅርቤ፣ ርቄ ስሜታቸውም እንዳይጎዳ ሰብዓዊ ምግባርም ባልጎደለው ዘዴ እሸኛቸዋለሁ።
ሃያ አንደኛው ክፍለ-ዘመን አውሮፓ፣ ቅዱስ ከእርኩስ አልለይ በአለበት ዓለም፣ ለወዳጅነት በፍቅር፣ በጓደኝነት ሽፋን የሚመጣውን ጣጣ እምናየው፣ በዦሮ ነጋ ጠባ የምንሰማው ነው። እኔም ታዲያ አጉል ድፍረቴ ከብዙ ጣጣና መከራ ከቶ ያወጣኝ ሰው በመሆኔ አንድ ነቁጣ አድርጌ ከዚህ ላይ ይበቃ ይሻላል፤ የወላድ መኅፀን ስንቱ ፍሬ ያፈራልና፤ ቆንጆ በቀረበችኝ ቁጥር ሁሉ አብሬ ስላፋ ሕይወት መላ-ቅጡን ማጥፋት ጀመረች። የዋዛ ፈዛዛ መዳራት ከንቱነቱ የሚለይለት የሚከሰተው ሲለያዩ አንዲት ትዝታ እንኳን አለመተው፣ አለማስቀረቱ ነው። እና በዚህ ወቅት ነው ዚፖራ ካልታወቀ አቅጣጫ ድንገት የነፈሰችው።
“ኢትዮጵያዊ አይሁድ ነህ አይደል?”
“አዎ ነኝ፤ እንዴታ።”
“ጣሊያን ሃገራችሁን ቅኝ ለማድረግ የአደረገው ሙከራ ላይ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ወረቀት እየጻፍኩኝ ነው።  በተቻለ መጠን ሁሉ የታሪኩን ምዕራፍ ያውቃሉ ከተባሉት የእዚህ ኮሌጅ ምሁራን ጋራ ተወያይቻለሁ። ከአንተ ጋራ እንድወያይ የጠቆመኝ መምህሬ ነው። ትምክህተኛ ሕዝቦች ናቸው፤ ግን ከቀናሽ አልፎ አልፎ ትሁት ግለሰቦችም ሊያጋጥሙሽ ይችላሉ ብሎኛል። አንተ ከየትኛው ምድብ ነህ?”
የአመጣጧ መንደርደር ሲገርመኝ ይባሱን ይሄን አከለችበት። የትምህርቱ ጉዳይ መምዘዟ ምክንያት እንደሆነ የሐበሻ አንጎሌ ጠረጠረ። አጠገቤ ከሚገኘው ወንበር እንድታርፍ ጋበዝኋት። መንፈሷ የተረጋጋ ያህል እየተዝናናች የላላውን ፀጉር ማሲያዣ በጥርሶቿ ሰንጥቃ አሰፋችውና መልሳ አሰረችው። አቀማመጧንም አመቻቸች።
“ትምክህተኛ ናችሁ በሚል ጥቁሻ የጀመርሽኝ እንዴት ነው-- እንዴት ብዬ ልረዳሽ እችላለሁ?”
“እኔ አይደለሁም ያልኩት መምህሬ ነው።; የአንጠለጠለችው ጉትቻ የሂንዱ ሴት አማልዕክት አንደኛዋ መሆኗን አስተዋልሁኝ። በግራ ጣቶቿ እየአሻሽቻቸው “ታዲያ ምንድነው ስለ ጣልያን ዘመን ልታወያየኝ የምትችለው?”
የአነጋገሯ ድፍረትና ቃና ጠብ የፈለገች ሴት መሆኗን ያሳውጃል። ማን እንደላከብኝ ነው የአልተረዳሁት። “እዚህ ኮሌጅ ምመጣው ስለ ሀገሬ በብዛት መጽሐፍት ስለሚገኙ ለማንበብ ይሁን እንጂ ተማሪም አስተማሪም አይደለሁም። ለምን  ወደ እኔ እንደጠቆሙሽ አልተረዳኝም። ደግሞም በብዛት የተጠበቡ እጅግ ታሪክ የሚያውቁ ሊቃውንት አሉልሽ። እኔ እንደው ጊዜ ማሳለፊያና ህይወት እንዳይሰለቸኝ ያህል ጨዋታ ማበርከቻ ተረክ መጽሔት የራዲዮ ማቅረብ ነው ስራዬ; ስላት ዕንቁላል የመሰሉ ዓይኖቿን ጉልጉል አድርጋ ተመለከተችኝ። ምንዥላት እንዥላቶቼን ሁሉ እኔ ውስጥ ዘልቃ እምታይ መሰለኝ።
ሃሳቤን ለማዳመጥ ፈልጋ ዓይኖቼን እየነዳደፈች “ምሳ ብጋብዝህና በሰፊው ብንወያይስ ምን ይመስልሃል?”
እንዲህ በመሰለ ድፍረት የመጣ ነገር መለየት አለበት ብዬ ቦርሳዬን አንግቤ ብድግ አልኩ። ተያይዘን ከግቢው ስንወጣ አንዳች ቃል አልተነፈሰችም። ጠልፎ በኪሴዋ አጣድፋ ዴቨን የተሰኘ ከከተማ  ወጣ ያለ መንደር አደረሰችኝ። እስከ አሁን አንዳች ሳትተነፍስ ልክ እንደወረድን ከእግር እስከ ራሴ ረቂቅ በሆነ አስተያየት ትመረምረኛለች። ማስቲካ አውጥታ ጋበዘችኝ። በምስጋና ተቀበልኩኝ።
“የቀረፋውን ቃና እወደዋለሁ” አለች። “ይሄ ግን የተለየ ነው። ሲውዲን ሃገር በቅርቡ የተፈለሰፈ ነው። ውጤቱን ትንስ ቆይተህ ታየዋለህ። የአሳደገችኝ አክስቴ ነች የላከችልኝ። ቻይና ሰባት ዓመት አጥንታ ተመልሳ የባህላዊ ወጌሻ መድሃኒት ማደራጃ ማዕከል ከፍታ አውሮፓ ውስጥ ዝነኛ ሆናለች” አለች።
ከባቡር ጣቢያ እጅግም ሳይርቅ ከቤት ዕቃው ጠረን በምግብ ሽታ ብዙ ዘመን ሽንኩርት የተቁላላበት የት እንደሆነ የሚነግር አዳራሽ ገባን። አሳላፊዎቹ በፈገግታ ተቀብለው ወደ ጥግ መቀመጫ ሰጡን። ገና አረፍ እንደአልን የማስቲካው ቃና ሆዴ ውስጥ ተሰማኝ። ድምፅ ማጉተምተም ነገር። የልጅቱ ቅጥ እጅግ ከዕድሜዋ አካሏ የበለጠ በመሆኑ ጉጉቴን አባሰው። ምግባችን ቀርቦ ጨዋታው ቀጠለ።
“ዚፖራ ነው ስሜ” አለች ፍርጥም ብላ።
“አዎን በመጀመሪያ ስንገናኝ እኮ አስተዋወቅሽኝ፤ ሰምቻለሁ።”
ምግብ ቤቱን በሥጋት እየገላመጠች “ነግሬሃለሁ እንዴ?” ስትል በድንጋጤ ድምፅ ጮኸች። መሃረብ አውጥታ አፍንጫዋን አባበሰች።
“እንዴት ዘነጋሽው? እሩቅ ጊዜ እንኳን አይደለም" ብል እንደገና ዙሪያውን ቃኘችና በዝግታ “እሱስ አዎን።” ድንገት መረበሿ አሳሰበኝ። ምናልባት አንድ ሃሳብ ተሰንቅሮባት ይሆናል በሚል ጨዋታችንን ለማዝናናት ስለየቤቱ የቆዩ የወግ ዕቃዎች አስተያየት ስጀምር፤
“የአንተንም ነግረኸኛል አይደል?” ትንፋሿ እጅግ ይቃሽባል። “አዎን ይመስለኛል። ቆየኝ አንዴ እ...” ብላ ከአጠገቤ ተስፈትልካ ወደ ጓዳ ገባች።
ለጥቂት ጊዜ ጠብቄ ብትዘገይብኝ አሳላፊውን ጠርቼ “አብራኝ የነበረች አንዲት ሴት ወደ መጸዳጃ ክፍል ከገባች ቆየችብኝ። ለቤቱ እንግዳ ነኝ። አንድ ጊዜ ደህንነቷን ብታረጋግጥልኝ እባክህ የኔ ወንድም; ስል በትህትና ጠየቅኩኝ።
ሄደና ተመልሶ መጣ። “ደህና ነች። የአይን ብሌን መነጽሯ ጠፍቶባት ነው። መጣሁኝ ብላለች” አለኝ።
ተነስቼ ልወጣ ትንሽ ሲቀረኝ በዝግታ መጥታ ተቀመጠች፡፡
"ምነው ምን ገጠመሽ?"
“ምንም”
“እንዴት ምንም? ሰውዬው የብሌን መነጽሯ ጠፍቶባት ነው አለኝ እኮ?”
“በር መቆርቆሩን ሲበዛብኝ ጊዜ ለመመለሻ ያህል የሰጠሁት መልስ ነው። ደህና ነኝ። አንተ ግን ማን ነህ?”
“እንዴት ማን ነህ?”
በመስኮቱ ወደ ውጪ እየተመለከተች፤ “የት ተገናኝተን ነው የመጣነው? ምን ፍለጋ?”
ይህንን ስትል የገጿ ደም ጓጉሎ ፊቷ እንደአባበጠ አስተዋልኩኝ። የቀድሞዋ ሙናዋ ወዴት ገብታ ይህቺ  የሌሊት ወፍ የዞረችባት ሴት ከየት እንደተከሰተች መገመት አዳገተኝ። ቅንጣት ታህል ቀልድ አነጋገር እንደሌለበት በደንብ ስለገባኝ በጥንቃቄ ቃላቶቼን እየቆጠርኩኝ፤ "ምነው ዚፖራ ምን ገጠመሽ ከመጸዳጃው ቤት? ይሄን ያህል መንገድ አብረን ተጉዘን መጥተን ልረዳሽ ብዬ ጉዳዬን ገድፌ በቁም ነገር አብሬሽ ወጥቼ ምነው? ለምን እንደዚህ ታረጊኛለሽ?"
ፊቷን፣ ቅንድቧን እየዳሰሰች “ምነው ምን አደረግኩህ? የት ነው ተገናኘነው ብዬ ንፁህና ሰላማዊ ጥያቄ ነው ያቀረብኩት” እየአለች አስተናጋጆች እንዳይሰሙ ትሸማቀቅ ጀመር።
ቀልድና ቁምነገርን የሚለየው የድምፅ ቅላፄዋ እንኳን አንዳች ነገር አላመለክትም አለኝ። ውጥን - ጨራሽ የሆነው አንጎሌ ይለይለት፤ ግፋ፤ በርታ ሲል፤ ልቤ ደግሞ በበኩሏ ተጠንቀቅ እያለች ትነዝር ያዘች። ከመጸዳጃው ክፍል የተጠናወታት መጋኛ ይበርድላት እንደሆነ ብዬ በዝምታ ተጠባበቅሁኝ።
ትምባሆ አውጥታ ለኮሰችና በነበልባል የክብሪቷን ስንጥር እስከ ቁንጢት አከሰለቻት። ገጿ ግን የሆነ ደባ ሴራ ላይ እንደሆነ ጽፏል።
ዘለግ ያለው አስተናጋጅ የአልታዘዘውን ጠርሙስ ነጭ ወይን ከመሃል ጠረጴዛው ሾመና ሄደ። ዙሪያዬ በክበበ-ነገር እንደታጠረ ግልጽ ሆነልኝ። የነገሩ ዓይነት ምንድነው? በፅዋ የተቀዳልኝን ወይን በስሱ ሳብ እያደረግሁኝ የነገር ፍላፃ እሚወረወርባትን አቅጣጫ ስጠባበቅ፤
“ለምንድነው ፂምህን የምታሳድገው?; አለች።
“የሩሲያ ንግሥ ካትሪንን የመሰለ የፂም ግብር የሚያስከፍል መንግሥት ስለሌለ ነዋ የኔ እህት።”
“የእውነት ፀሐፊ ነህ?” ስትል በለዘበ ድምፅ ጠየቀች።
“የእኔ ስራ ባዶ ሉክ ስለሚያሳዝነኝ መክተብ ነው። ሰዎች ግን የደራሲነት ሞያ ነው ብለው ሰይመውልኛል” ብል እሷ ግን ጠረጴዛው ላይ ዘመም፣ ጋደም እያለች ከልቧ ተንከተከተች። የወይኑ ውጤት ነው ብዬ እንዳልል ግማሽ ብርጭቆ ያህል እንኳን አላጎደጎደም። ከስሜታቸው ጋራ ቅልልቦሽ መጫወት የሚያረካቸው ሴቶች እንዳሉ ስለማውቅ አልገረመኝም።
የምግብ ቤቱ ደንበኞች ቀስ በቀስ አዳራሹን እየለቀቁ ሄደው፣ ከአስተናጋጁ ጋር እኛን ደምሮ ስድስት ያህል ሰዎች በፋኖስና ደብዛዛ አምፖል ብርሃን ተከበን እንገኛለን።
ቦርሳዋን አንግባ ብድግ ስትል አስተናጋጆቹ ሁሉ ከእየቆሙበት በፈገግታ ሸኟት። የሒሳብ ክፍያውን ለመረዳዳት ከኪሴ ቦርሳዬ ጋር ስግደረደር መዳፌን ጨበጥ አድርጋ “አይዞህ አትቸገር፤ የአጎቴ ንብረት ነው። በወር አንድ ቀን ሁለት እንግዳ እንድጋብዝ ተፈቅዶልኛል” አለች።
በነፋሻው ጭር ባለ መንገድ በዝግታ እየተራመድን የትምህርቷን አካሄድና ዕድገት ስታወራኝ፤ ቀደም ብላ ከምግብ ቤቱ የሆነችውን ሁኔታ ሳስታውስ አንዳንዴ እንዲሁ ስርዓት መላ-ቅጥ የሚጠፋባቸው ፍጥረቶች እንዳሉ ሁሉ፣ ይቺም አንደኛዋ ትሆን ይሆናል ብዬ የሠጋ አንጎሌን አረጋጋሁት።
“ለምንድነው የሃገራችሁ ሰዎች ሁልጊዜ ሩጫ አንደኛ የሚወጡት? እስቲ ንገረኝ እባክህ?”
“ለብቻ የሚሰራ ነገር ስለሆነ ነው ብለው አንድ አባታችን ነግረውኛል” ስላት አፏን ይዛ እየሳቀች ፈንጠር ብላ ወደፊት ቀደመች። “ምነው ይህን ያህል የሚያስቅ ነገር ምን ተገኘ?”
ሳቋ ሲበርድላት በመሃረብ ዓይኖቿን እየጠራረገች፤ “ኡህ... የባሕል ነገር እንደው ይገርማል” አለች።
እንግሊዞች ሕንድ በጋ እያሉ የሚጠሩት እንደ ገበሬ አብዶ ዝናብ ድንገት ከተፍ የሚለው የመፀው ወራት ፀሐይ የህብረት ጨረሯን ሁሉ-ነገር ላይ አንጸባርቃ፣ ዓመት በገጠመ ሁሉ ለምልመው፣ አብበው፣ ረግፈው፣ ጠውልገው ወደ ዳርቻ የሚረግፉትን ቅጠላ -ቅጠል እማይሰለች ምክር ትመክራቸው ይመስል በዝግታ በንፋስ መጥረጊያ ሲገፉ ታስተውላለች። ከጥቂት ጋሻ መሬት ርቀት የህንፃ ሰናዖር መሰል  የሎንዶን ከተማ ሁከትና  ትርምስ ሰማይ ምድሩ ላይ ይደረንቅ ይመስል፣ ከእዚህ  ገጠር ሕይወት አሸልባ ዳር ዳሩን ትሄዳለች።
“ወዴት ነው በተመስጦ ሄድክ ጥለኸኝ?” አለች።
“አይዞሽ አይዞሽ። አብሬሽ ነኝ እዚሁ። የመጣንበትን ዋና ጉዳይ ረስተን በገጠር ሽውታና ፀጥታ መዋጣችን እየታሰበኝ ነው” አልኳት።
“ስቀልድህ ነው እባክህ። የማጠናውም ታሪክ የለኝም።  እኔ ለራሴ ወደ የልብስ ስፌት ለመሰማራት እያመነታሁ ነው። ከጓደኞቼ ጋር ተወራርጄ ነው የአነጋገርኩህ። ፈፅሞ መቅረብና  ማነጋገር አዳጋች ነው ይህን ሰውዬ፤ ብለው ሲሉ እኔን የሚሳነኝ  ነገር የለም፤ እንወራረድ ብዬ ብልሃቴን ለማስመስከር ያደረግኩት ነው። እንደማትቀየመኝ ተስፋ አደርጋለሁ” አለችና በይቅርታ  ስሜት  መዳፌን ጨበጥ አደረገች።
ከመንገድ ዳርቻ ካለ አግዳሚ ወንበር አረፍ አልኩኝ። አሁንም በቅብጠት አነጋገር፤ “ይሄንን ያህል ስሜትህን ይጎዳሃል ብዬ አላሰብኩም ነበር።”
“አይ ለጉዳት እሚያደርስ ነገር እንኳን አልተፈጠረም። እንደው አንቺና የባልንጀሮችሽ የውርርድ ቁሳቁስ መሆኔ አስገረመኝ እንጂ።”
“አትገረም፤ አትገረም። ልትገረምም አይገባም። እንደውም ይኸውልህ በእዚሁ አጋጣሚ በቅርብ ለመተዋወቅ ቻልን። ፀሐፊ ስለሆንክ ደግሞ ብትፅፈኝ ጥሩ ባሕሪይ ሳይወጣኝ አይቀርም። ጓደኞችህ ለፅሑፍ አመቺ ተፈጥሮ አለሽ እያሉ ይሳለቁብኛል። አንተ ደግሞ በባለሙያ ዓይን ስትገምተኝ ምን እመስልሃለሁ?”
የጣሊያን ወረራ ታሪክ ምርምሩ ሳይጀመር አብቅቶለት፣ ወደ የጽሑፍ ባህሪነት በጥቂት ሰዓት ውስጥ መለወጡ ድንቅ ሆነብኝ። በዚህም ነገሩ ቢበቃ ተመኘሁ። “ፃፈኝ ብላ የምትቀርብ ሁላ እኮ የስነ-ጽሑፍ ዋጋ አላት ማለት አይደለም” ስል በትህትና አስረዳሁ።
“አይ እኔን  እኮ አይደለም፤ እኔን ሳይሆን የሚያጋጥሙኝን  ነገሮች ብትጽፋቸው ብዬ ነው። ብዙ ትንግርት በየቀኑ ይገጥመኛል እኮ። ለምሳሌ ትላንትና ጠዋት ከዕንቅልፌ እንደተነሳሁ ድንገት ፍፁም ደስታ መላ ሰውነቴን ወረረኝ። ምክንያቴን ብፈልግ፣ ብፈልግ ፣ ባወጣ ፣ ባወርድ ፣ ጓደኞቼ ጋር ብደውል አንዳች ነገር፣ ይህ ነው የተባለ ሰበብ አላገኘሁለትም። ከመኝታ ክፍሌ ገብቼ ሳለቅስ እናቴ ሰምታ መጣችና አጠገቤ ቁጭ ብላ ታስተዛዝነኝ ጀመር። ነፍሴን ይበልጡን አቅለሸለሻት። ደስታዬ በውኔ እናቴን ሲያሳዝን ምን ብዬ ላብራራላት፡፡ #አይዞሽ ሴት ልጅ ከእናቷ የምትሸሽገው አንዳች ነገር ስለሌለ ንገሪኝ የኔ ጥንቸል” እያለች ታግባባኝ ጀመር። ግልብጥብጥ ያለ ሁኔታ ውስጥ እንደገባሁ ተገንዝቤ “በደስታ ነው የማለቅሰው” ለማለት የሚደፍር አንደበት ስለአልነበረኝ፣ የሷንም ስሜት ማባከን እንዳይሆን ብዬ መላ ፈጠርኩና “ቀድሞ ከጦር ሜዳ የተሰዋ ወንድማችንን ሃቢብን አስታውሼ ነው” ብዬ አልኩ። ደለልኋት። አፅናንታ ሳስማኝ በፈንታዋ ልታለቅስ ወደ መኝታ ክፍሏ ሄደች። ይሄንን ታዲያ ምን ትለዋለህ? ምን ይባላል?”
በእውነቱ የነገረችኝ ነገር ለሐሳብና አስተያየት የተቸገረ ሁኔታ ነበር። መንስኤው የአልታወቀ ደስታ ካለ፣ እንደዚሁም ደግሞ ካለአንዳች ምክንያት ማዘንም ሊመጣ ነው ማለት ነው?
"ሌላስ ምን አስደናቂ ነገር ገጥሞሻል?”
እንደ ማመንታት እያለች፤ “እ... አንድ አንዱን እንኳን በግልፅ ለመናገር ከእዚህ የቀረበ ይበልጡን ብንተዋወቅ እመርጣለሁ። የሚያሳፍር ጉዳይ ሆኖ ሳይሆን ማንኛቸውም ሰው በንፁህ ይረዳዋል ብሎ ለመገመት ያዳግታልና ብዬ ነው።”
የአነጋገሯ ውበትና የቃል አጣጣሏ በውል ያለየለት ኅቡዕ ዕምቅ ተሰጥኦ እንደአላት አስታወቀኝ። “አሁን ለምሳሌ እሩቅ ሳንሄድ ቅድም ከነበርንበት ምግብ ቤት ጥዬህ ወደ መጸዳጃ ቤት ገብቼ የዘገየሁብህ ለምን መስሎሃል? ደስታው ድንገት መጣብኝ እና እኮ ነው። ሰው ላይ ይጋባና ምን ያመጣ ይሆን ብዬ እሰጋለሁ።”
“መቼ ነው የጀመረሽ ይሄ የትፍስህት ምች?" አልኩ
“ዓመት ሊሞላው ነው። አንዲት እጅግ የምወዳት የነፍስ ጓደኛዬ አንድ ቀን መስክ ላይ ጋደም ብለን ስጨዋወት ደስታዬ መጣና እሷንም ሰበቃት። በደስታ አልቅሳ፤ አልቅሳ ከአጠገቤ ጠፋች። ከዚያን ዕለት አንስቶ ዓኗን አይቼ አላውቅም። ወላጆቿን  በስልክ ባነጋግራቸው ለዕረፍት ኢቢዛ የተባለች ሃገር መሄዳችን ነው ይዘናት ብለው አመሰገኑኝ።”
“ወደእነሱም ተዛምቶ ደስታው ማለት?”
“መሆኑ ነዋ” አለችና ከጎኗ አንዲት አደይ አበባ ቀንጥሳ በለምለም ጣቶቿ መሃከል ትጫወትባት ጀመር።
“እኔንጃ? ጊዜም ሁኔታም አይወስነውም። እንዲሁ ብቻ ዋጥ ውስድ ሲያደርገኝ ከእዚህ ገነት መንፈስ ከምወጣ መሞትን ያስመኛል።”
“ኃይማኖተኛ ሴት ነሽ?”
“ቤተሰቦቼ በተለይ አባቴ ሰንበት ከምኩራብ አይቀርም። እኔ ግን እግዚአብሔርን እየፈለግኩ ነኝ። ሴት አያቴ ተኝተን መነሳታችን የፈጣሪ መኖሩን ማረጋገጫ ነው፤ ብዙ አትልፊ፤ አትመራመሪ፤ ትለኝ ነበር። ምነው ለምን ጠየቅከኝ?”
“አይ ምናልባት የእምነትሽ ትሩፋት እንደሆነ ብዬ ነው?”
“እኔ እንኳን ኃይማኖት ለአጠብቅ የወደድኳቸውን ወንዶች እንኳን ማሰቡ ነው ናላዬን የሚያዞረው። የምን ትሩፋት አመጣህ? ይኸው ይኸው ተመልከት አመለጠህ። ሁለት  ቢራቢሮዎች ሲደባደቡ? እንዴት ያስደንቃል መሰለህ ልፊያቸው? በጣም! ጠብም ልፊያም ይመስላል።”
ይሄንን ስታወራ ድንገት ከዕድሜዋ ቀንሳ ትንስዬ ልጃገረድ መሰለችኝ። አደይ አበባዋን ከዦሮዋ ስር ሰክታ እንደ እንዝርት ሾረችና “ያምርብኛል? በል ንገረኝ እስቲ; አለች።
"ከለበስሽው ሹራብ ቀለም ጋር በጥሩ ይጣቀሳል” ስላት በደስታ ፍንድቅ አለች።    
“ሌላ የሚጋጥመኝ ነገር ምን መሰለህ? ማስታወስ።”
“አንዴት ማለት ማስታወስ?”
“ማስታወስ ነዋ በቃ። በሁለት ዓመቴ የተገዛልኝ የእግር ሹራብ እንዴት ድመቷ እንደቀደደችብኝ ድንገት ይታወሰኛል። ወይም ደግሞ ዳቦ ጋጋሪ፤ ጋሪ እሚገፋው አንድ ቀን ጉንጬን ቆንጥጦ #አንቺ አሻንጉሊት; ያለኝ በሦስት ዓመት እድሜዬ ከሰላሳ አንድ ዓመት በፊት መሆኑ ነው፤ ድንገት ይታወሰኛል።”
“ወላጆችሽ ምን  ይላሉ ይሄን ስትነግሪያቸው?”
“አልነግራቸውም። አንድ አንዱን ብቻ ነው እንደ ቀልድ የማጫውታቸው እንጂ አልነግራቸውም። አያቴ... ሴት አያቴ አለች አላልኩህም? የነርቭ ብዛት የማያመጣው ነገር የለም። በዚሁ ላይ  ታክሎ ደግሞ ትምህርት አስጠልቶ ልብስ ሰፊነት አስመልክቶሻል፤ እንደምንም ብለሽ ለባል ብትበቂ አምላኬን አመሰግነዋለሁ። እናትሽ እንደሆነ ተስፋ ቆርጣ ቁጭ ብላለች ትለኛለች።”
“የምታስታውሺውን ትፅፊዋለሽ?”
“ለእዚህ እኮ ነው አንተን የፈለግኩህ። ብትፈልግ ደግሞ ለብዙ ወራት ተከታትዬ ነው የአገኘሁህ። ከጓደኞቼ ጋራ ተወራርጄ አይደለም” አለች።
ፍላጎቷንና ሐሳቧን በረገድ ለማስቀመጥ እንደማይሞከር ተገንዝቤ ማዳመጡን ብቻ በደንብ እንዳዳምጥ ወሰንኩኝ።
“መፃፍ እችላለሁ፤ ግን ሐሳቤ እጄን እየቀደመው ገፁ በቃላት ጎርፍ ይደፈርስብኝና ቀዳድጄ እጥለዋለሁ። አንተ ግን ብትፅፈው ሳያምር አይቀርም። አይመስልህም? ስለ ኢትዮጵያ ቋንቋ ጥቂት ነገር ሰምቻለሁ። ስለዚህ በተለየ ፊደል እንዲጻፍ ፈልጌ ነው። በመጀመሪያ በሂንዱ ዳቦናጋሪ ፊደል ታስቦኝ ነበር። እና ፀሐፊ ሳፈላልግ አንድ ቀን  የነገርኩህ ደራሽ ደስታዬ ጋደም ብዬ መጣብኝና በመሃሉ ዴር ሱልጣን የተሰኘ የኢየሩሳሌም ገዳማችሁ ውስጥ አንድ ካህን ችቦ አብርተው፣ በነበልባሉ ጨለማው ላይ የእናንተን ፊደልና እብራይስጥን ቀላቅለው ሲጽፉ ታየኝ። ይሄ ግልፅ ምልክት ነው፤ ከወዴትም ተላከ ከወዴትም ባይረዳኝም  መልዕክቱን ተቀብያለሁ። እና አንተን መፈለግ ጀመርኩኝ።”
ይሄ ደራሽ ትፍስህት መጥቶ እንዴት ምን እንደሚያደርጋት  በአየሁ ብዬ ጓጓሁ። ፊቷን ዞር ገጥ በአደረገች ቁጥር የምጣላት እየመሰለኝ ልቤ ጋል፣ ንዝት ትላለች።
የእንግሊዝ ገጠር ምሽት ችኩል ነውና ሳናውቀው ድንግዝግዝ አለብን። ወደ ሎንዶን በባቡር ተሳፍረን ስንገሰግስ ሁለታችንም በየራሳችን ውጥን ተጠምደን አብረን መሆናችን ተዘነጋን። ስንሰነባበት፣ “መቼ ነግቶ ደውዬልህ ተገናኝተን? ኡ! እንዴት ቸኩያለሁ መሰለህ። ጽሑፍህ ገና ድሮ ታትሞ አየሁት፤ ብታምነኝም ባታምነኝም። ነገ ሌላ ቀጠሮ እንዳታበጅ። ሙሉ እምነቴ ነው አደራህን?” ብላ እጆቿን እያውለበለበች ወደ እየቤቱ የሚጣደፈው ምልዓተ- ሕዝብ ግርግር መሃል እንደ ውሃ ጠብ ብላ ተሰወረች።
እንኳን በማግስቱ፣ በሰልስቱ፣ በሳምንቱ፣ በወሩ ከነድምጿ ጠፋች።
ከኮሌጅ ግቢ ብንጠራወዝ፣ ብዞር መሰል ሴቶች እንኳን ከዓይኔ አልገባ አሉ። የደስታዋ ቅፅበት ተበራክቶ ለሰው አላብቃቃ ብሏት ይሆናል ብዬ ከጓደኞቼ ጋራ ቀላልጄ ልረሳ ስታገል፤ የሰፈራችን የዋናና ስፖርት ማኅበር ህንፃ በራፍ ላይ ሶስት ልጃገረዶች ቆመው እየተጠቃቀሱ ይንሾካሾካሉ። ትኩረታቸው ወደ እኔ ላይ እንደሆነ ገብቶኛል።
አንደኛዋ ጣደፍ እያለች መጥታ “አቶ ጸሐፊው እንደ ምንድነህ? እኛ የዚፖራ ጓደኞች ነን። ስለአንተ ትነግረን ነበር ብዙ።  ለጽሑፍህ ይረዳህ ይሆናል እነሆ” ብላ የጋዜጣ ቅዳጅ ሰጠችኝ፡፡
“አስደናቂ እረፍት” በሚል ርዕስ ስር የሚከተለውን  ያትታል። “ዚፖራ ቤንዚጋ የምትሰኘው ሴት በደስታ ብዛት ሕይወቷ ማለፉን ለጥቂት ሳምንታት ሲረዷት የቆዩት የህክምና ባለሙያዎች አስታወቁ። የዚፖራ አሟሟት በየጊዜው የሚጠልፋት የደስታ ምች ባለፈው ሳምንት  ለረዥም ሰዓት ጸንቶ ስለቆየባት የልቧ ምት ከአቅም በላይ ሆኖባት እንደሆነ ሐኪሞቹ ዘግበዋል። ዚፖራ ወደ ሕይወቷ ማለፊያ አቅራቢያ ቀልድና ጨዋታ ከማብዛቷም በላይ ልቤን ወስዳችሁ ማዳምጡሰው ከተሰኘው የታዋቂያን የስም ቅርጽ ትዕይንት ቤት እንድታስቀምጡ ተናዝዣለሁ ማለቷን አልሸሸጉም።”
19...................ሎንዶን
("ከደመና በላይ" ከተሰኘው የደራሲው መድበል የተወሰደ)Read 1938 times