Saturday, 29 May 2021 11:26

ቦርዱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ከ98 ሚ. ብር በላይ አከፋፈለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    ብልፅግና ከ23 ሚ. ብር በላይ፣ ኢዜማ ከ11 ሚ.ብር በላይ ይሰጣቸዋል
                        
                 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በምርጫው ለሚወዳደሩ 51 የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በአጠቃላይ 98 ሚሊዮን 624 ሺ 174 ብር ባዘጋጀው መስፈርት መሰረት አከፋፍሏል።
ቦርዱ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩል ለእያንዳንዳቸው 483 ሺ 451 ብር ያከፋፈለ ሲሆን ቀሪውን ገንዘብ ፓርቲዎቹ ባቀረቡት ብዛት፣ በሴት እጩ፣ በአካል ጉዳተኛ እጩና በሴት ስራ አስፈፃሚዎች ብዛት ማከፋፈሉ ታውቋል።
233 እጩዎችን ያቀረበው በፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) በእኩል ካገኘው 483 ሺህ 451 ብር በተጨማሪ ባቀረባቸው እጩዎች ደግሞ 615 ሺህ 937 ብር ተሰጥቶታል።
ቦርዱ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአንድ እጩ 2ሺህ 649 ብር እንዲሁም በአንድ ሴት እጩ 9 ሺህ 982 ብር፣ በአንድ የአካል ጉዳተኛ እጩ 155 ሺህ 722 ብር ሰጥቷል፡፡ ለምርጫው በጠቅላላ 510 እጩዎች ያቀረበው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፤ 2 ሚሊዮን 302 ሺህ 802 ብር አግኝቷል። 605 ጠቅላላ እጩዎችን ያቀረበው እናት ፓርቲ በበኩሉ፤ 3 ሚሊዮን 539 ሺህ 695 ብር የተሰጠው ሲሆን በቀጣይ ዙር ቀሪው ደግሞ 3 ሚሊዮን 56 ሺህ 244 ብር ይሰጠዋል ተብሏል።
578 እጩዎች በማቅረብ የሚወዳደረው ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፤ 4 ሚሊዮን 565 ሺህ 882 ብር የተሰጠው ሲሆን በቀጣይ ዙር 4 ሚሊዮን 82 ሺህ 430 ብር ይሰጠዋል።
በአጠቃላይ 1540 እጩዎችን ያቀረበው የኢትዮጵያውያን ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) 11 ሚሊዮን 337 ሺህ 470 ብር የተሰጠው ሲሆን 2799 እጩዎችን ያቀረበው ብልፅግና ደግሞ 23 ሚሊዮን 182 ሺ 953 ብር የሚሰጠው ይሆናል።
በሁለተኛው ዙር ኢዜማ 10 ሚሊዮን 854 ሺህ ብር የሚሰጠው ሲሆን ብልፅግና ደግሞ 22 ሚሊዮን  699 ሺህ ብር ይሰጠዋል።
ምርጫ ቦርድ በመጀመሪያ ዙር 98 ሚሊዮን 624 ሺህ 174 ብር፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ 77 ሚሊዮን 835 ሺህ 740 ብር ለፓርቲዎች ለማከፋፈል መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሏል።


Read 11384 times