Saturday, 29 May 2021 11:25

“በካርዳችሁ የፈለጋችሁትን ምረጡ”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከፍተኛ አመራሮች በጉራጌ ዞን በሚገኙ የምርጫ ወረዳዎች ከግንቦት 13 - ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሲያደርጉ የነበረው የምርጫ ቅስቀሳ በወልቂቴ ከተማ በተደረገ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
በወልቂጤ ከተማ በተደረገው ዝግጅት ላይ የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፤ መራጮች በተለያየ መንገድ የሚደረግባቸውን ማስፈራራትና ጫና በመቋቋም ምንም ዓይነት ግጭት ውስጥ ሳይገቡ ሰኔ 14 በካርዳቸው የፍላጎታቸውን እንዲመርጡ አሳስበዋል። የገዢው ፓርቲ ሰዎች ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት የተለያየ ሙከራ እያደረጉ እንደሆነ የጠቀሱት የኢዜማ መሪ ፤«የምርጫ ዕለት ለማን ድምጻችሁን እንደሰጣችሁ ከራሳችሁ እና ከፈጣሪያችሁ ውጪ ማንም አያውቅም። በሚያደርጉትና በሚያወሩት ሳትረበሹ የልባችሁን ምረጡ!» ብለዋል።  ምርጫው በሰላም ተካሂዶ ማኅበረሰቡ የሰጠው ድምፅ በንፅህና ከተቆጠረ ማንም ያሸንፍ ማን ሁላችንም እናሸንፋለን ያሉት መሪው፤ ለዚህም ከምርጫው ጋር በተያያዘ ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት በሙሉ የየበኩላቸውን ኃላፊነት በከፍተኛ አትኩሮት እንዲወጡ የአደራ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የኢዜማ ከፍተኛ አመራሮች ባለፉት 5 ቀናት በጉራጌ ዞን በሚገኙት ቡዒ፣ ኬላ፣ ቡታ ጅራ፣ አገና፣ ሐዋሪያት፣ አረቅጥ፣ ቋንጤ፣ ጉንችሬ፣ ድንቁላ፣ እምድብር እና ወልቂቴ ከተሞች የተሳካ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ተጠቁሟል።
የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የምርጫ ቅስቀሳ ዝግጅቶቹ ላይ ፀሐይና ዝናብ ሳይበግራቸው ረጅም ርቀት ጭምር እየተጓዙ ለተሳተፉ ነዋሪዎች እንዲሁም ቅስቀሳዎቹ የተሳኩ እንዲሆኑ ላደረጉት የየአካባቢው የኢዜማ መዋቅሮች አባላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


Read 11628 times