Print this page
Saturday, 29 May 2021 11:34

“ማዕቀቡ ሊያስተሳስረን እንጂ ሊያስደነግጠን አይገባም”

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(8 votes)

  • አሜሪካ ማዕቀብ ከመጣል ይልቅ ከኢትዮጵያ ጎን ልትቆምና ልታግዛት ይገባል - ሴናተር ጂም ኢንሆፍ
     • ከፈረንጅ ጋር ከመካሰሳችን በፊት የራሳችንን ችግር እንፍታ- ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና
     • ማዕቀቡ ኢትዮጵያውያንን ሊያስተሳስር እንጂ ሊያስደነግጥ አይገባም- የፖለቲካ ምሁር
               
             አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ከመጣል ይልቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አንድነቷን የጠበቀች የተረጋጋችና ሰላማዊ አገር ለመገንባት እያደረጉ ያሉትን ጥረት ማገዝና  ከጎናቸው ልትቆም እንደሚገባት የአሜሪካ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተር ተናገሩ።
የኦክላሆማ ሴናተሩ ጂም ሄናኦፍ ከትላንት በስቲያ ለህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር፤ አሜሪካ አሁን እያከናወነች ያለው ተግባር ተገቢ አለመሆኑንና ኢትዮጵያን በተለያዩ ማዕቀቦችና ጫናዎች ከማስጨነቅ ይልቅ “ምን እናግዛችሁ” በማለት፣ አገሪቱ የጀመረችውን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ልታግዝ ይገባል ብለዋል።
ሴናተሩ በንግግራቸው “አንድ ወሳኝ ነገር ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ወዳጅ ለሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ መናገር እፈልጋለሁ፤ ወንድሜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ከጎንህ ነኝ፤ የታሪኩን ሥረ ነገር የምናውቅ የገጠማችሁን ችግር የምንገነዘብ  ሁላችን ከጎናችሁ አብረናችሁ እንቆማለን” ብለዋል። አያይዘውም፤ አሜሪካ ሁለቱን ወገኖች ለማደራደር እየሄደችበት ያለው መንገድ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመው፤ “ሁለቱን ቡድኖች በእኩል ዓይን መመልከት አይገባም፤ እኩል አይደሉም። አንደኛው የተመረጠና አገር እያስተዳደረ ያለ መንግስት ነው፤ ሌላው ስልጣኔን ተነጠቅሁ ብሎ ያኮረፈ ቡድን ነው። እነዚህን ቡድኖች በአንድ አይን መመልከቱ አግባብ አይደለም” ብለዋል።
የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ባለስልጣናት፣ ላይ የጣለው የቪዛ ማዕቀብ እንዲሁም  የምጣኔ ሀብትና የደህንነት ድጋፍ ዕቀባ ማድረጓ ተገቢ አይደለም ያሉት የፖለቲካ ምሁራን በበኩላቸው፤ ሁኔታው አገሪቱ የውጪ ፖሊሲዋን በአግባቡ መፈተሽና መመርመር እንዳለባት አመላካች ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የራሷ ሉአላዊ ግዛት ያላትና የራሷን ብሔራዊ አንድነት ጠብቃ የኖረች አገር ናት ያሉት የፖለቲካ ምሁሩ ዶ/ር ተስፋዬ ባዩ፤ ማንም አካል እንደ ልቡ የሚያዛትና እንዲህ ካላደረግሽ ይህን አልሰጥሽም እያለ የሚያስፈራራት አገር አይደለችም ብለዋል። አሜሪካ በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎች ስታሳድር መቆየቷ የሚዘነጋ አይደለም ያሉት ምሁሩ፤ በእነዚህ ጫናዎችና እጅ ጥምዘዛዎች ሳትበገር የራሷንና የህዝቧን ጥቅም ለማስከበር የሚችል ጠንካራ መንግስት የሚያስፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች ብለዋል።
በተለይም ከለውጡ መምጣት ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች በሚነሱ የእርስ በርስ ግጭቶችና መተራመሶች ጊዜ ሁሉ ዜጎቿ በአገራቸው ጉዳይ ላይ አንድ ሆነው መፅናታቸው የተለመደ ጉዳይ ነው ያሉት ምሁሩ፤ ይህንንም ወደ ኋላ ያሉ ታሪኮቿን በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።
 “አሁንም በአሜሪካ የተጣለብን ማዕቀብ የሷን ፈለግ በሚከተሉና በሷ በሚታዘዙ ሌሎች አገራትም ሊቀጥል እንደሚችል በማመን ራሳችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል፤ ማዕቀቡ ኢትዮጵያውያንን ሊያስተሳስር እንጂ ሊበታትን እንደማይችል ማሳየት ግገባናል” ሲሉ ተናግረዋል ምሁሩ። መንግስት ከምንጊዜውም በላይ በፅናት የሚቆምበት፣ ዜጎቹ እምነት የሚጥሉበት መሆኑንም ማረጋገጥ ይገባዋል  ዶ/ር ተስፋዬ ባዩ፡፡
የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት በሰጠው ምላሽ፤ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችው የቪዛ ገደቦችና ተያያዥ ውሳኔዎች የሁለቱን አገራት የቆየ ወዳጅነት የሚጎዳ መሆኑንና ኢትዮጵያም ከአሜሪካ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት መልሳ ለመፈተሽ እንደምትገደድ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ አዲስ ፖለቲካዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀውን ብሔራዊ ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀች ባለችበት በዚህ ወቅት ይህ ውሳኔ መውጣቱ የሚያስተላልፈው መጥፎ መልዕክት አለ ያለው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ በዚህ የምርጫ ወቅት ከአሜሪካ መንግስት ትጠብቅ የነበረው ድጋፍና እርዳታ ነበር ብሏል።
አሜሪካ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከተፈረጀው ህውሐት እኩል የኢትዮጵያን መንግስት መመልከቷ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ጉዳይ ነው ያለው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የህውሃት ቡድን እንዲያንሰራራ የሚደረገውን ማንኛውንም አይነት ሙከራ በፍፁም አንፈቅድም ብሏል።
የእናት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ ጌትነት ወርቁ በአሜሪካ የተጣለው ማዕቀብ በተመለከተ ሲማገሩ፤ ስህተቱ አሁን ባለው ሁኔታ የተዛባ መረጃ ሲያስተላልፉ የነበሩትን እንደነ አምነስቲ ያሉ የመረጃ ምንጮችን መጠቀሙ ነው ይላሉ። ሌላው በግልጽ የሚታየው ነገር የአሜሪካ ውሳኔ ህውሐትን ከመቃብር ውስጥ እፍ ብሎ ለማውጣት የሚታገል ዓይነት መምሰሉ ነው ብለዋል-ዋና ፀሀፊው፡፡
ህውሐት ለአድማጭ የሚቀፍ ወንጀል በመከላከያው ላይ ፈጽሞና መከላከያውን ራቁቱን አዋርዶ እያለ ይህ በበቂ ሁኔታ አለመገለፁ።  ውሳኔው የተጻፈው በቅን መንፈስ ነው ለማለት አያስደፍርም” ብለዋል አቶ ጌትነት።
የኢኮኖሚ ማዕቀቡ  የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ያመለከቱት የፓርቲው ዋና ፀሐፊ፤ “የነቀዘ ስንዴ ነው የሚቀርብን እያሉ መሳለቁ ከዕውቀት ማነስና  ፖለቲካን ካለመረዳት የሚመነጭ ብዬ አምናለሁ” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
“ማዕቀቡ የሚጎዳው አራት ኪሎ ያሉትን  ሳይሆን ድሃውን ማህበረሰብ ነው። በየጊዜው እየጨመረ የሚሄደውን የዋጋ ንረት ህብረተሰቡ መቋቋም እንዳይችል ያደርገዋል።” ብለዋል ዋና ፀሀፊው አቶ ጌትነት ወርቁ፤
የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ የአሜሪካ  መንግስት የጣለውን ማዕቀብ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ ማእቀቡ የኢትዮጵያ መንግስት የደረሰበትን የዲፕሎማሲ ክስረት አመላካች ነው ብለዋል። የውስጥ ችግሮቻችን በአግባቡ መያዝና መፍታት ባለመቻላችን ምክንያት የደረሰብን ችግር ነው ሲሉም ገልፀውታል።
“የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት 3 ዓመታት ችግሮችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ በጉልበት ለመፍታት ሲሞክር ቆይቷል። ይህ ደግሞ ይህንን ክስረት አድርሷል” ብለዋል- ፕሮፌሰሩ። በአሜሪካ ኬክ ያደጉ ሁሉ ማዕቀቡን አስመልክተው ሲናገሩ የሰለጠነ ቃል እንኳን አይጠቀሙም ያሉት የኦፌኮ ሊቀመንበሩ፤ አልሻባብን እንደማስፈራሪያ መጠቀሙ የሚያስገርም ጉዳይ ነው፤ አልሻባብ በይበልጥ ማንን እንደሚጎዳ እንኳን አያውቁም ብለዋል። የተከፋፈለ ህዝብ ይዘን በእልህ ችግሮችን ለመግፋት መሞከር ምኞት ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ ቄሱም ሼኩም  ያቃተውን ችግራችንን በሌሎች ለማላከክ መሞከሩ አግባብ አይደለም። ከፈረንጅ ጋር ከመካሰስ የራሳችንን ችግር መፍታትና ወደ መደራደር ልንሄድ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

Read 12753 times