Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 10:42

“መለስ ሰው አክባሪና ትሁት ናቸው” ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ዜና እረፍት የተሰማዎትን ቢገልፁልን…

በግሌ ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶኛል፤ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ፀጉር ድረስ የሚሰማ ዓይነት ስሜት፡፡ እንደ ቤተሰብና እንደ ወንድም እቆጥራቸው ነበር፡፡ ደብዳቤ ስጽፍላቸው እንኳን “ውድ ወንድሜ” እየተባባልን ነው የምንነጋገረው፡፡  እጅግ ሰውን የሚያከብሩ ናቸው፡፡ የደረሰብኝን ሃዘን መግለጽ ያቅተኛል፤ ቃላትም የለኝም፡፡ ትልቅ ድንጋጤ ነው፤ ማመን ያቅታል (እንባ) ምግብ መብላት ሁሉ ነው ያቃተኝ፤ ፆሜን ነው የዋልኩኝ፡፡

ከጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ጋር ትውውቃችሁ የት እና እንዴት ነው?

እርሳቸውን የማውቃቸው በትግል ሜዳ እያሉ ነው፡፡ በ1989 በፈረንጆች አቆጣጠር  ነበር፡፡  በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ጦርነትና ረሃብ የተከሰተበት ወቅት ነበር፡፡ ያኔ አሜሪካ ነበርኩ፡፡ እናም ጥቂቶች ኢትዮጵያውያን እየተነጋገርን ነበር፡፡ ምን እናድርግ ብለን እንቅስቃሴ ጀመርን፡፡ የኢትዮጵያ ችግር በዛን ወቅት ውሃና ድርቆሽ አልነበረም፡፡ ጦርነት በሚፈጠርበት ጊዜ ገበሬው የዘራውን ሳያጭድ ይሸሻል፡፡ ዋና ችግራችን የነበረው ብዙ ጉልበታችንን፣ ሃብታችንን፣ ንብረታችንን ያወዳደመው ጦርነት ነበር፡፡ ጦርነቱ በወቅቱ በሁለት ወገን ጐድተናል፡፡ የሰው ሃይልና፣ ምጣኔ ሃብታችን እየባከነ ስለነበረ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተወሰንን ሰዎች በአንድ ቀን ተሰባስበን፣ ራት በልተን ቃል ኪዳን ገባን፡፡ የፖለቲካ መሪዎችን ቀርበንና ለምነናቸው ጦርነት እንዲቆምና ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲፈጠር በሽምግልና ስም ውል ገባን፡፡ ማታውኑ ደብዳቤ ፃፍን፡፡

“መላው እህቶቻችን ወንድሞቻችን ጦርነት ላይ የምትገኙት፤ ሃገራችን ታሪኳ የታወቀና የተከበረች ናት፡፡  ሃገር በጦርነት እየተጐዳ ነው፡፡ እኛ ሽማግሌዎች እናንተን በአንድ ቦታ ሰብስበን ውይይት አድርገን፣ የሰላም ውል እንድትገቡ፣ የሽግግር መንግስትም ይቋቋም” የሚል ነበር ደብዳቤው፡፡ በመጀመሪያ መልስ የሰጡን ክቡር መለስ ናቸው፡፡

ይህ የሰላም ውል ለአቶ መለስ እንዴት ደረሳቸው?

እሳቸው በዛን ወቅት ሱዳን አካባቢ ነበሩ፡፡ በዛን ጊዜ አብዛኞቹ የትግል መሪዎች የነበሩት ሱዳን አካባቢ ነው፡፡ ሁሉም መልስ ሰጡን፤ ደርግ ግን መልስ አልሰጠንም ነበር፡፡ ምላሻቸውም “እኛ ደስተኞች ነን፤ በሰላም ውሉ ላይ እንሳተፋለን” የሚል ነበር፡፡ ይህ የሚያስገነዝበውም ጠ/ሚ መለስ ለሰላም ይቸኩሉ ነበር ማለት ነው፡፡ እነማናችሁ እናንተ ብለው አልናቁንም፡፡ ከዛም ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ተገናኘን፤ የሰላም ውሉ እንደተጀመረ ወደ ፊት ለመቀጠል ተስፋ ሠጡን፤ ለንደን የተደረገ የሽግግር መንግስት ውል ይቅር ተባለ፡፡ ከዛም ሁኔታው ፈራርሶ፣ በኋላም ደርግ ለቀቀ፡፡ ስዊዘርላንድ ያቀድነውን የሰላም ውል ውይይት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲደረግ አስበን፣ ወደ 35ሺ ዶላር ይዘን መጥተን እዚሁ በአፍሪካ ህብረት ተደረገ፡፡ የሰላም ኮሚቴዎች መጥተን ተካፈልን፡፡ አንድ ሳምንት ተቀምጠን ተወያይተናል፤ ስብሰባው እንዳለቀ የሽግግር መንግስት ተቋቋመ፡፡

በዛን ወቅት አቶ ኢሳያስም ነበሩ፡፡ እሳቸውም በወቅቱ ሽምግልናን ያከብሩ ነበር፡፡ ከዛም ፈቃድ ሰጥተውን “በኢትዮጵያ ሰላምና እድገት ማህበር” የሚል ቢሮ ከፈትን፡፡ ለወደፊቱም ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ለመስራት አቶ መለስ ፍላጐታቸውን አሳዩን፡፡

ኦነግ በወቅቱ የሽግግር መንግስት ሲቋቋም አስራ አንድ ቦታ ነበር የነበራቸው፡፡ በምንም ምክንያት እንደሆነ ጠለቅ ብዬ አላውቅም፡፡ በወቅቱ ከመንግስት ተለየ፡፡ እነሱ ሲወጡ እንደገና ግጭት ተፈጠረ፡፡ ዋሽንግተን የኦነግን ተወካይ አግኝተን ውይይት ካደረግን በኋላ በርካቶች እስር ቤት ገቡ፡፡ በዛን ወቅት ለክቡር አቶ መለስ፤ በድሮ ጊዜ እስረኛም ይፈታል፤ ሰው ይቅር ይባላል፤ አዲስ አመትን ምክንያት አድርገው እስረኞቹ ቢለቀቁ መልካም ነው ብለን ፃፍንላቸው፡፡ ክቡር አቶ መለስን አግኝተን ስናነጋግራቸው ስለ እስረኞች፤ የኤርትራን ጉዳይንም በተመለከተ መፍትሔው ምንድነው አልን፡፡ የኤርትራ ሽማግሌዎችና የኢትዮጵያ ሽማግሌዎች ብለን በአንዱ ቡድን ኢትዮጵያ፣ ከዛም ኤርትራ ሄድን፡፡ አቶ መለስ ውጤትና ሰላም ፈላጊ ነበሩ፡፡ ምክር ተቀባይ ነበሩ፡፡ ይሁን ያልናቸውን ተቀብለው ሂደቱን ያሳውቁናል፤ እንደዚህ እናድርግ እንደዚህ ይሁን ይላሉ፡፡ ከትግል ሜዳ ጊዜ ጀምሮ የኦነግ፣ የኤርትራ፣ በቅርብም የቅንጅት ጉዳይ በተነሳ ጊዜ መልካም ምላሽን በመስጠት አክብረውናል፡፡

በቅንጅት ጉዳይ ላይ ስትሰሩ ከጠ/ሚ ጋር ትገናኙ ነበር?

አዎ፡፡ በጣም፡፡ እንደውም በወቅቱ እኔ አዲስ አበባ አልነበርኩም፤ ወሬውን ስሰማ ከአሜሪካ ሮጥ ብዬ መጣሁ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩን ስናናግራቸው “እባካችሁ ምከሩ፤ አዲስ አበባን አሸንፈዋል፤ ፓርላማ እንዲገቡ ምከሯቸው፤ በመንግስትም ቦታ ይኑራቸው” የሚል ንግግር ነበረን፡፡

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን፣ ዶ/ር ያዕቆብን፣ ኢንጂነር ሃይሉ ሻወልን አነጋገርኳቸው፤ እነሱም ደስ ብሏቸው ነበር፡፡ ከዛ ወደ አሜሪካ ተመለስኩ፡፡ ክቡር ጠ/ሚ ደብዳቤ ፃፉልኝ፡፡ እንደተነጋገርነው “ፓርላማ ገብተው ቦታቸውን እንዲይዙ፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር ቦታቸውን እንዲወስዱ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ማስተዳደር እንቀጥላለን ምክራችሁ ይቀጥል” ብለው ፃፉልኝ፡፡

እኔም በወቅቱ አዲስ አበባ ደውዬ ከሽማግሌዎች ጋር ተነጋገርኩ፡፡ በድጋሚ ጠ/ሚ ነገሩ የመካረሩን ሁኔታ አይተው ደብዳቤ ላኩልኝ፡፡

“ይፍጠኑ! አሁን በቅርቡ ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል፤ ይሄ ከሆነ ደግሞ ግጭት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ፓርላማ ገብተው ስራቸውን እንዲሰሩ፤ ነገሩ እንዳይባባስ” ብለው ደብዳቤ ላኩልኝ፡፡

ደውዬ ስለ ሁኔታው ከዶ/ር በየነ ጋር ተነጋገርኩ፤ አደራ አደራ አልኳቸው፡፡ …ወደ አዲስ አበባ መጣሁ ግጭት ተነስቶ በርካታ ሰው አልቆ ጠበቀኝ፡፡

በቅንጅት ፓርቲ ውስጥ የነበሩ አመራሮች ወደታሰሩበት ሄጄ አገኘኋቸውና አወራኋቸው፡፡ ጠ/ሚ ጋርም በሁኔታው እየተነጋገርን ነበር፡፡ ወደ እርሳቸው ጋር ሄጄ መፍትሔው ምንድን ነው አልኳቸው “ይሄ ነገር ለአገራችን የማይበጅ ነገር ነው፤ “ከውጪ የሚመጡ ሰዎች በዚህ ጉዳይ አያገባቸውም፡፡ በእናንተ በአገር ሽማግሌዎች ማለቅ የሚገባው ጉዳይ ነው” አሉን፡፡ እንደእሳቸው ፍላጐት ቢሆን ኖሮ ግን ነገሩ እንደዛ አይባባስም ነበር፡፡ እሳቸው ልባቸው ክፍት ነበር፡፡

ቅንጅቶቹ ፍ/ቤት ተጠርተው ጉዳዩ በዳኛ እጅ ሲገባ እኔ ሮጥ ብዬ መጥቼ አናገርኳቸው፡፡ “አሁንማ ከእኔ እጅ ወጥቷል፤ ጉዳዩ ፍ/ቤት ደርሷል፡፡ የፍ/ቤት ጉዳይ ሲያልቅ ወደ እኔ ይመለሳል፤ እስከዛ ድረስ ምንም ነገር ማድረግ አልችልም” አሉ፡፡ ፍ/ቤት ባይደርስ ኖሮ በጣም ጥሩ ውጤት እናገኝ ነበር፤ በክቡርነታቸው፡፡

ሌላ ቀደም ብሎ በየዓመቱ እስረኞች ይፈቱ ብለን ተነስተን ነበር፡፡ በኤርትራ ጦርነት በዛ በኩል ሽማግሌዎች ጥሩ ንግግር ነበረን፤ በኋላ ግን አልጄሪያ ገባበት፤ በኤርትራ በኩልም ቢሆን በእኛ በኩል እንዲያልቅ ነበር የፈለጉት፡፡ ሌሎች የቀሩ እስረኞችም ነበሩ፡፡

ከዛም በኋላ የወ/ሪት ብርቱካን ጉዳይ ነበር፡፡ ህጉ አስቸጋሪም ቢሆን በመንግሥት በኩል በሩ ተከፈተ፡፡

ከዛ በኋላ ከጠ/ሚ መለስ ጋር የነበራችሁ ውይይቶች፣ ምን ይመስላሉ? ቃል የገቡት ነገር ነበረ?

በቅርብ እንከታተል የነበረውን የኦጋዴን፣ የኤርትራ፣ የኦብነግና ሌሎች ግጭቶችን በተመለከተ በእርሳቸው በኩል አንድም ጊዜ በሩ አልተዘጋብንም፤ ሰላም እንዲሰፍን፤ የራቀውን ለማቀራረብ በራቸው ክፍት ነበር፡፡ በደብዳቤም በግልም በመገናኘት እርሳቸው ጋር አንድም የቀረ ነገር የለም፡፡

የብዙ ነገር ጉዳዮች በሮች ሰፋ ሰፋ እያሉና እየተከፈቱ ሄደው ነበር፡፡ በኦጋዴንም፣ በኦሮሞም፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችም በኩል በርካታ ውይይቶችን አድርገን መንገድ ከፍተውልን ነበር፡፡ በአቶ ክቡር መለስም የተጀመሩ ነገሮች እንዲቀጥሉ ወደ ሰላም እንድንሄድ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያድግ ነው፡፡ መንፈሳቸው ከእኛው ጋር ነው፡፡ የአገር ሽማግሌዎች ያመጡትን ህዳሴ የሚል ቃል ተቀብለውን እስከዛሬም እየተጠቀሙበት የኢትዮጵያ ህዳሴ እንዲጠናከር በርትተው ሲሰሩ ነበር፡፡

የኢትዮጵያን መፃኢ ሁኔታ እንደ ሀገር ሽማግሌዎች እንዴት ይገልፁታል?

ጠ/ሚ የጀመሩትን ነገር እስከ መጨረሻው ማስቀጠልና ማስኬድ ነው ፍላጐታችን፡፡  እሳቸው ብዙ ነገር ላይ አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ እሳቸው የጀመሯቸውን ቀጣይ ነገሮችን እንዲቀጥል የሚቋቋመው አዲስ መንግስት ማለትም የአቶ መለስ ደቀመዝሙሮችም የጀመሩት ስራ ከፍፃሜ እንዲደርስ ማድረግ አለባቸው፡፡ የአባይ ግድብ፣ የመንገድ ሥራ የባቡር፣ ትምህርትን ማስፋፋት … ከልብ ቆርጦ መነሳት ያስፈልጋል፡፡ እንደ እኛ ግን ዋናው ነገር የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ ተቃዋሚዎች ተቃቅፈው አንድ እንዲሆኑ ነው፡፡ ክቡር አቶ መለስም ምኞታቸው ይሄው ነበር፡፡ ሁልጊዜ ስንነጋገር አንድ ቀን እንቅፋት ፈጥረውብን አያውቅም፡፡ ንግግሮች ጊዜ ከመውሰዳቸው በስተቀር፡፡ ኢትዮጵያ ለመላው አፍሪካ ምሳሌ ናት፡፡ ክቡር አቶ መለስም የሰሩት ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ ለመላው አፍሪካ ነው፡፡ ሌሎች አፍሪካ አገሮችም እኮ ኢትዮጵያ እናታችን ይላሉ፡፡ የደቡብ አፍሪካው ኢምቤኪ “ኢትዮጵያ እናታችን እኮ ናት” እያሉ ያወሩኝ ነበር፡፡

አሜሪካን አገር ለመጀመሪያ ጊዜ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካን ስተዲስ የተመረጥኩ እኔ ነበርኩ፡፡ ጥቁር አሜሪካኖች ነበሩ፡፡ We are Ethiopian people ይሉኝ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳም የገነነች፣ የተከበረች ናት፡፡ ጠ/ሚ ይህን ተረድተው በታሪክ እንድናቆያት ነው አላማቸው፡፡

ግዚያችንን በመጣላት፣ በመከራከር ወደ ጥፋት እንዳንሄድ፣ ይህችኑ ኢትዮጵያ እንድናቆያት ነው ራዕያቸው፡፡ ብዙ አፍሪካ እኮ እንደመሪ የሚከተሏቸው ናቸው፡፡

በዓለም ላይ ብዙ መሪዎችን አውቃለሁ፤ ብዙዎቹ ትዕቢተኞች ናቸው ይኩራራሉ፡፡ በአቶ መለስ ግን ይህን አይቼ አላውቅም፤ ቅን፣ ሰው አክባሪ ትሁት ናቸው፡፡ ቤተሰቦቻቸውም ሁሉ እንደተራው ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ ሰው ራሱን ለዘላለም የሚኖር ይመስለዋል፡፡ ትዕቢት ነው፤ ራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ከሰው እበልጣለሁ ይላል፡፡ በሚገርም ሁኔታ እሳቸው ትሁትና ቅኖች ናቸው፡፡ ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋር ቅርበቱ አለኝ፡፡ በጣም ስብር ያሉ የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸው፡፡

እኔ እንደውም ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁበት ምክንያት በየዓመቱ በአዲስ አመት የተለመደ በዓል አለ፡፡ እስረኞች ይፈታሉ፡፡ ግንቦት 7፣ ጋዜጠኞች፣ ሙስሊም ወንድሞቻችን አሉ እንዴት አድርገን እነሱን እናወጣለን በሚል ንግግር ስለነበረን በእርሱ ላይ ለመወያየት ነበር፡፡ በአጋጣሚ ይህ ተፈጠረ፡፡ ክቡርነታቸው ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይተን ነበር፤ እሳቸው ተስፋ ሰጥተውኝ ነበር፡፡ ለዚሁ ነበር እሳቸውን ለማየት ጓጉቼ የነበረው፡፡ የሆነ ሆኖ የተጀመሩትን ነገሮች እንቀጥላለን፡፡

እርሳቸውን እንደወንድም ነው የምቀርባቸው፤ ስንፃፃፍም ወንድሜ ሆይ ብዬ ነው የምጽፈው፡፡ ጠ/ሚ መለስን አያውቋቸውም፤ የሚያስገርመኝ እኛ በር ለማስከፈት እየሞከርን ነው፡፡ ዝም ብለው የሚናገሩ ከአፋቸው ክፉ ነገር የሚወጣ፣ በሩቁ ተቀምጠው የሚናገሩት ያሳዝነኛል፡፡ ለኢትዮጵያም ጥሩ አይደለም፤ ባህላችንም አይደለም፡፡ በውጭ የሚኖሩትንም ስሜት እንረዳለን፡፡ እኛ ሽማግሌዎች ለዛም ነው ገብተን የምንናገር፤ የተሰራውን መዝሙር ለመዘመር አይደለም፡፡

እነሱም ቁስል ኖሮባቸው ይሆናል ያንን ቁስሉን አከብራለሁ፡፡ ቁስሉን በክብር ማከም እንጂ ጠርጐ መወርወር አይደለም፡፡

አደራ ነው የምላቸው ወንድሞቼን፤ ስለሀገራችሁ ስትቆረቆሩ የክብር መቆርቆር ይሁን፤ መጥፎ ምሳሌ አንሁን፡፡

 

 

Read 1909 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 10:48