Saturday, 29 May 2021 11:44

ከአንድ በላይ እርግዝና

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

    ከአንድ ልጅ በላይ እርግዝና ሲከሰት በተለያዩ ምክንያቶች አስደሳች ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶች በተለያዩ ጊዜያት እርጉዝ ከመሆንና ሁልጊዜ እንደ አዲስ ልጅን ከማሳደግ ለመገላገል ይረዳል ይላሉ፡፡ ከአንድ ልጅ በላይ በመረገዙ የሚደነቁና የሚደሰቱ የመኖራቸውን ያህል በዚያው ልክ በግዴታ እንጂ በጸጋ የማይቀበሉም ይኖራሉ፡፡ እነዚህም ከኢኮኖሚ፤ ህጻናቱን በመንከባከቡ ረገድ የሚያግዝ የሰው ኃይል እጥረት የመሳሰለውን በምክንያትነት ያቀርባሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ መንትዮቹ ከተረገዙ እና በሰላም ለመወለድ ከበቁ በተቻለው መጠን ወላጆች መስዋእትነትን ከፍለው የሚያሳድጉ መሆኑ እሙን ነው፡፡
መንትያ የሚለው አባባል በአማርኛው የተለመደ መሆኑ እንጂ በእንግሊዝኛው (multiple birth) ይባላል፡፡ ይህም መንትያ የሚለው አባባል ምናልባትም ሁለት ለማለት ሲሆን የእንግሊዝኛው አባባል ግን ከአንድ በላይ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ከአንድ በላይ የሆነው እርግዝና ግን እስከሰባት ሊደርስ የሚችል ሲሆን ስያሜዎቹም እንደሚከተለው ተገልጾአል፡፡ ምንጫችን https://www.beaumont.org ነው፡፡
twins – ሁለት ልጅ
triplets – ሶስት ልጅ
quadruplets – አራት ልጅ
quintuplets – አምስት ልጅ
sextuplets – ስድስት ልጅ
septuplets – ሰባት ልጅ
ለመሆኑ ከአንድ በላይ የሆነ ልጅ መውለድ ለምን ያጋጥማል?
ከአንድ ቁጥር በላይ እርግዝና እንዲከሰት የሚያደርጉ ምክንያቶች በርካቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚጠቀሱት ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ከአንድ ቁጥር በላይ ልጅ መውለድ ከቤተሰብ በውርስ ሊገኝ ይችላል፡፡
አንዲት ሴት እድሜዋ ከ30 አመት በላይ ሆና ልጅ ብታረግዝ ከአንድ ቁጥር በላይ ሊሆን የሚችልበት እድል ይኖራል፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ አንድ እና ከዚያ በላይ የወለደች እናት በተለይም ከአንድ በላይ የወለደች ከሆነች በቀጣይም ከአንድ ልጅ በላይ የማርገዝ እድል ሊኖራት ይችላል፡፡
ከአንድ ልጅ በላይ ልጅን ማርገዝ በዘር የሚለያይ ይሆናል፡፡ ለምሳሌም አፍሪካን አሜሪካን የሆኑ ሴቶች ከሌሎች ዝርያዎች ይበልጥ ሁለት ልጅ የመውለድ እድል አላቸው፡፡ በእስያ ያሉ ሀገራት ሁለት ልጆችን የመውለድ እድላቸው አነስተኛ ሲሆን የራሽያ ግዛት በሆነችው ካውካሰስ (Caucasian) ዝርያ የሆኑ ሴትች ደግሞ ሶስትና ከዚያ በላይ የሆኑ ልጆችን በአንድ ጊዜ ይወልዳሉ፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ ከአንድ ቁጥር በላይ ልጅ ለመውለድ ምክንያት የሚሆኑት ከላይ የተጠቀሱት ተፈጥሮአዊ ምክንያቶች ብቻ ሳይሆኑ ከስነተዋልዶ ጤና ቴክኖሎጂ እና ሕክምና አገልግሎት ጋር በተያያዘም ሊከሰት እንደሚችል መረጃው ይጠቁማል፡፡
እንቁላልን ቀስቃሽ መድሀኒቶች፤-
በዚህ የህክምና እርዳታ ምክንያት ሴትየዋ ብዙ እንቁላሎችን እንድታመርት እድል የሚፈጥርላት ሲሆን ምናልባትም ከአንድ በላይ እርግዝና እንዲከሰት እና ከአንድ በላይ ልጅ የመውለድ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
እንቁላልን ለማነቃቃት ድጋፍ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች፤-
In vitro fertilization (IVF) በሚል የሚታወቀው ልጅን በላቦራቶሪ እንዲፈጠር አድርጎ ከተፈጠረ በሁዋላም ወደ ማህጸን በማስገባት ልጅ እንዲወለድ እድሉ በሚፈጠርበት ወቅት በሚሰጠው የተለያየ የህክምና እርዳታ የተነሳ ከአንድ በላይ እንቁላል ለእርግዝና እንዲዘጋጅ ሊያደርግ ስለሚችል ከአንድ ቁጥር በላይ ልጅ እንዲረገዝ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
ከአንድ ልጅ በላይ እርግዝና እንዴት ይከሰታል?
ከአንድ በላይ ልጅ የሚረገዘው በግንኙነት ወቅት ከአንድ እንቁላል በላይ የሚሰበር ከሆነ እና እነዚህ እንቁላሎች ወደማህጸን ገብተው ሲያድጉ ነው። ይህ (fraternal) ወንድማዊ ወይንም እህታዊ በሚለው የሚገለጽ የመንትያ አይነት ሲሆን ወንዶች ወይንም ሴቶች አለዚያም ከሁለቱም አይነት ልጆች እንዲወለዱ የሚያስችል ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተወለዱ እህትና ወንድም መልካቸው ሙሉ በሙሉ አንድ አይነት  የማይመስል ሲሆን በዚህ አወላለድ ግን ተመሳሳይ እና አንድ አይነት ልጆች ደወለዳሉ። እነዚህ ልጆች የየራሳቸው እንግዴ ልጅ እና የሽርት ውሀ ከረጢት ይኖራቸዋል፡፡
አንዳንድ ጊዜ አንድ እንቁላል ብቻ ለእርግዝና ይዘጋጅና ነገር ግን በሂደት እንቁላሉ ሁለት ወይንም ከዚያ በላይ በሆነ ቁጥር በመከፈል ጽንስ እንዲቋጠር የሚያስችል ሲሆን ይህ አይነቱ መንትያ (identical) የሚባል ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የሚወለዱት መንትያዎች ወንድ ወይንም ሴት ብቻ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ልጆች በጣም ከመመሳሰላቸው የተነሳ አንዱን ከአንዱ ለመለየት በሚያስቸግር ሁኔታ ወላጆቻ ቸውን ጭምር ሊያደናግሩ ይችላሉ፡፡ (identical) በሚል የሚታወቁት መንትያ ልጆች የየራሳቸው እንግዴ ልጅ እና የሽርት ውሀ ከረጢት የሚኖራቸው ሲሆን በአብዛኛው ግን አንድ የእንግዴ ልጅን ሊጋሩ ይችላሉ፡፡
ከአንድ ልጅ በላይ በሚረገዝ ጊዜ እራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በተለየ ሁኔታ መደረግ ያለባቸውን እና መወሰድ የሚገባውን ጥንቃቄ ምንጊዜም ከሐኪም ወይንም አዋላጅ ነርሶች ማግኘት ይቻላል፡፡ በእነሱም ክትትልና ምክር መሰረት የሚከተሉትን መተግበር ይጠቅማል፡፡
ስለ አጠቃላይ የሰውነት ጤንነት፤ ስለእርግዝናው ሁኔታ እና በህክምናው ዘርፍ ያለውን ታሪክ ጠንቅቆ ማወቅ፤
ምን ያህል ልጆች እንደተጸነሱ ማወቅ፤
ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ የሚሰጥ የተለየ የህክምና ክትትል፤ የምክር አገልግሎት፤ የሚወሰድ መድሀኒት የመሳሰሉት ነገሮች ቢኖሩ በትእግስት ሐኪም የሚሰጠውን ትእዛዝ ማክበር፤
የእርግዝናውን ሁኔታ እና የጊዜ መጨመር ወይንም የመውለጃ ጊዜ መቃረብን መከታተል፤
የሚፈልጉትን ነገር ወይንም ምርጫንና አስተያየትን በግልጽ ለሐኪም እና ለሚቀርቡ ቤተሰቦች መግለጽ፤ የመሳሰሉትን መተግበር ጤናማ ልጆችን ለመውለድ ያግዛል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች በተጨማሪም አስፈላጊ የሆኑ ጠቃሚ ሀሳቦች እንደሚከተለው ተጠቅሰዋል፡፡
እናቶች ሁለት ወይንም ከዚያ በላይ ጽንስ ከያዙ ተtጨማሪ ካሎሪ እና ፕሮቲን፤አይረን እንዲሁም ሌሎች ንጥረ ነገሮችን ቀደም ሲል ይመገቡ ከነበረው በተጨማሪ ማግኘት አለባቸው፡፡ ክብደትን ማስተካከልንም አብሮ መከታተል ያስፈልጋል፡፡
ከአንድ ልጅ በላይ የጸነሱ እናቶች ከተለመደው በላይ ለእርግዝና ክትትል ወደሐኪማቸው መቅረብ አለባቸው፡፡ ምናልባትም ከእርግዝናው ጋር በተያያዘም ይሁን ወይንም በሌላ ምክንያት የሚደርስ የጤና መጉዋደል ወይንም እርግዝናውን በተመለከተ የሚኖሩ ችግሮች ቢኖሩ አስቀድሞ መፍትሔ ለመስጠት ያግዛል፡፡  
ለተሻለ ሕክምና አገልግሎት ወደሚሰጥባቸው ጤና ተቋማት መተላለፍ፤
እረፍት ማድረግ (አንዳንድ ጊዜ ሆስፒታል ተኝቶ የመውለጃ ጊዜን መጠባበቅ)
ስለ ጽንሱም ሆነ እናትየው ያልተቋረጠ የህክምና ክትትል ማድረግ ….ወዘተ የመሳሰሉት አስፈላጊ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
በአጠቃላይም ከአንድ በላይ ጽንስ በሚረገዝበት ወቅት የደም ግፊት የመሳሰሉት ሕመሞች ሊከሰቱ የሚችሉ ሲሆን በአብዛኛውም የመወለጃ ጊዜው ከ37/ ሳምንት በላይ ላይቆይ እና የመወለጃ ጊዜውን ላይጠብቅ ይችላል https://www.beaumont.org እንደገለጸው፡፡  


Read 12247 times