Saturday, 29 May 2021 11:48

ለአፄዎቹ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

    ‹‹ስፖርት ለኢትዮጵያ ሕብረት›› በሚለው ዘመቻ 1 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል
                በመጀመርያው ገቢ ማሰባሰብ ከ162 ሚሊዮን ብር በላይ ተገኝቷል፡፡

             የ2013 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ፋሲል ከነማ መላውን የኢትዮጵያ ባስተሳሰረ ታሪካዊ ምሽት  መነጋገርያ ሆኗል፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በሸራተን አዲስ ሆቴል  ክልቡ የመጀመርያውን የገቢ ማሰባሰብ ያካሄደ ሲሆን ከ162 ሚሊዮን ብር በላይ ለማግኘት ችሏል፡፡ ‹‹ስፖርት ለኢትዮጵያ ሕብረት›› በሚል መርህ አፄዎቹን ለማጠናከር በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ላይ ኦሮሚያ ክልል 25 ሚሊየን፣ አማራ ክልል 20 ሚሊየን፣ ሲዳማ ክልል 5 ሚሊየን፣ ሱማሌ ክልል 5 ሚሊየን፣ ደቡብ ክልል 4 ሚሊየን ብር ለመስጠት ቃል የገቡ ሲሆን፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ 2 ሚሊዮን ብር፤ ሼህ ሙሐመድ አሊ አላሙዲንና አቶ ወርቁ አይተነው እያንዳንዳቸው 10 ሚሊየን፣ አቶ በላይነህ ክንዴ 5 ሚሊየን፣ የግራንድ ሆቴል ባለቤት ወይዘሮ ትልቅ ሰው ገዳሙ አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ሚድሮክ ኢትዮጵያ 5 ሚሊየን ብር፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 5 መቶ ሺህ ብር እንዲሁም ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉና ሙዚቀኛዋ አምሳል ምትኬ እያንዳንዳቸው 50 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የእግር ኳስ ክለቡ በገቢ ማሰባሰቢያ እቅዱ እስከ 1 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ያቀደ ሲሆን በቀጣይ አርብ ግንቦት 20 በባህርዳር ግንቦት 21 በጎንደር ከተሞች ከፍተኛ አቀባበል  እንደሚደረግለት ፤ የንጉስ እራት እንደተዘጋጀ እና  በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ለደጋፊዎች ኮንሰርት እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የ2013 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ላይ አፄዎቹ የሻምፒዮንነት ዋንጫ ሲሸለሙ በ23 ጨዋታዎች 53 ነጥቦች አስመዝግበዋል፡፡ የሊጉ ሻምፒዮን በመሆናቸው የ1 ሚሊዮን ብር ሽልማት ከማግኘታቸው በላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ የተሰራ ቁመቱ 80 ሴንቲ ሜትርና ክብደቱ ከ 15-20 ኪሎ የሆነ  ልዩ ዋንጫቸውን በሸራተን ሆቴል በሚዘጋጀው የኮከብ ተጫዋቾችና ግብ አስቆጣሪዎች ሽልማት ላይ እንደሚረከቡ ታውቋል። በ2013 ቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ላይ ኢትዮጵያ  ቡና በ40 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ  በመያዝ በቀጣይ የውድድር ዘመን ላይ በኮንፌደሬሽን ካፕ መሳተፉን ሲያረጋግጥ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ37፤ ሰበታ ከነማ በ36 እንዲሁም ሃድያ ሆሳና በ35 ነጥብ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ አከታትለው ወስደዋል፡፡ ወልቂጤ ከነማ፤ ጅማ አባጅፋር እና አዳማ ከነማ ከቤትኪንግ ፕሪሚዬር የወረዱ ክለቦች ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር እንዲሁም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የዓመቱ ኮከብ ተጨዋችነት ክብር ደርቦ ያሸነፈው የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር በ29 ጎሎች የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ሲሆን በውድድሩ ታሪክ በአንድ ውድድር ዘመን ከፍተኛውን የጎን ብዛት ያስመዘገበ ተጨዋች ሆኖ አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቧል፡፡
ፋሲል ከነማ በዋናነት በጎንደር ከተማ አስተዳደር እየተደገፈ የመጣ ክለብ ሲሆን በየውድድር ዘመኑ ከጠቅላላ የከተማው በጀቱ 5% እየተመደበለት ሲወዳደር ቀይቷል። “ስፖርት ለኢትዮጵያ ህብረት’’ በሚል መሪ ቃል በጀመረው የገቢ ማሰባሰቢያ  ክለቡ ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው ማድረግ  እና መላው ኢትዮጵያዊያን የሚሰለጥኑበት የእግር ኳስ አካዳሚ ጎንደር ላይ መመስረት ዋና አላማዎቹ  አድርጓቸዋል፡፡ ክለቡን በሚያሳድግ አቅጣጫ ቦርዱን በማዋቀር እንደሚሰራ፤ ከስፖንሰር ጋር በተያያዘ ጠንካራ ስራዎችን እንደሚያከናውን፣ 100 ሺ ቋሚ የተመዘገቡ ደጋፊዎችን በአባልነት ይዞ እንደሚቀጥልና በአጭር ጊዜ እቅድ ያለውን ስታዲየም በማደስ በቀጣይ ዋናውን ስታዲየም ለመስራት እንደሚንቀሳቀስም ይጠበቃል፡፡
.በጎንደር ከተማ ተቀማጭ የሆነው ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ከተመሰረተ 52 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡  በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ተሳታፊነቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተጠናከረ የመጣ  ቢሆንም፣  በተለይ ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት ከዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ተርታ መሠለፍ የቻለ እና እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት መሆኑም ልዩ ያደርገዋል፡፡ለበርካታ የውድድር ዘመን በሁለተኛ ዲቪዚዮን ሲወዳደር ከቆየ በኃላ ፕሪሚዬር ሊጉን ለመጀመርያ ጊዜ የተቀላቀለው ከ13 ዓመታት በፊት ነው፡፡ በመጀመርያው የሊግ ተሳትፎው የመውረድ እጣ ገጥሞታል፡፡ ከዚያም በኋላ ወደ ሊጉ መመለስ የቻለው ከ8 የውድድር ዘመናት በኋላ የከፍተኛ ሊግን አሸንፎ ነበር፡፡
ክለቡ በሚቀጥለው ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ይሆናል፡፡  በአህጉራዊ ደረጃ ያለው ልምድ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በኮንፌደሬሽን ካፕ ቢወዳደርም በመጀመርያ ዙር ማጣርያ ተሳትፎው ተወስኗል፡፡


Read 479 times