Saturday, 29 May 2021 11:58

የኬሮድ ሩጫ ዓለም አቀፍ እውቅናውን በቶሎ ሊያገኝ ይችላል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   ከሳምንት በፊት በወልቂጤ ከተማ በተካሄደው ኬሮድ 15ኪ ሜ የጎዳና ላይ በዞኑ ለሚደረገው የስፖርት እንቅስቃሴ ከፍተኛ መነቃቃት ለመፍጠር ተችሏል። የዞኑ አስተዳደርና  የከተማው ነዋሪዎች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የማሰልጠኛ ማዕከል እንዲገነባላቸው በይፋ ጠይቀዋል። በመጀመርያው የኬሮድ 15 ኪ ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ  ላይ 107 የክለብ አትሌቶችና  አሰልጣኞቻቸው፤ 163 በግልና በማናጀር የሚሰለጥኑ አትሌቶች ተሳትፈውበታል። ውድድሩ በተስማሚ አየር ንብረት እና የመሮጫ ጎዳና ላይ መካሄዱን በርካታ አትሌቶች ያደነቁት ሲሆን ከ10,000 በላይ የከተማው ነዋሪዎች 15 ኪሎሜትሩን ለመሮጥ በመሞከርና በተመልካችነት ልዩ ድባብ ፈጥረዋል፡፡
በውድድሩ ላይ በርካታ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ባለድርሻ አካላት መጋበዛቸውም የጎዳና ለካይ ሩጫውን አጀማመር ያማረ አድርጎታል፡፡  የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን  ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር  ውድድሩን እስከፍፃሜው ፕሮግራም በመታደም የመነቃቂያ ንግግር ለከተማው ነዋሪ እና ለተወዳዳሪ አትሌቶች ያሰለፉ ሲሆን ሻለቃ ሀይሌ ገ/ስላሴ በስፍራው ተገኝቶ ውድድሩን አስጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌደረሽን ፕሬዝዳንት ደራርቱ ቱሉ፤ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገዛኸኝ አበራ እና የፌደረሽኑ  ዋና ፀሀፌ አቶ ቢልልኝ መቆያ ለአሸናፊዎች የክብር ሽልማት ያበረከቱ ሲሆን በአትሌቲክስ ፌደረሽኑ የተሳትፎና የውድድር፤ የስፖርት ፋሲሊቲ ማህበራትና የአትሌቶች አገልግሎት የስልጠና ጥናትና ምርምር ዲያሬክተሮች የበኩላቸውን ድጋፍ በመስጠት ተሳትፈውበታል፡፡ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ቢኒያም ምሩፅ ሽልማት ያበረከተ ሲሆን  ከሙሉ የስራ አስፈፃሚው አባላት ጋር በወልቂጤ በመገኘት ለጎዳና ላይ ሩጫው ልዩ ማበረታቻ አድርገዋል፡፡ የጉራጌ ዞን  አስተዳደር ሃላፊዎች፤  የወልቂጤ ዮንቨርሲቲ ፕሬደዛንት፤ የንብ ባንክ ፕሬደዛንት ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ውድድሩን ሽልማት በመስጠት እና በመታደም ልዩ ሞገስ አጎናፅፈውታል፡፡
ኬሮድ ሩጫ ከዞኑ በተገኙ አትሌቶችን በማቋቋም ለመጀመርያ ጊዜ ሊያካሂድ በበቃው ውድድሩ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ላይ በስፖርቱ ያለፉ እና የሚገኙ ባለሙያዎች በጋራ ከሰሩ የሚፈጠረውን ውጤት ያመለክታል፡፡ውድድሩ የተካሄደው በጣም በሚያምር የአየር ሁኔታ ውስጥ ሲሆን በወንዶችም ሆነ በሴቶች ምድብ በአትሌቶች መካከል ጠንካራ ፉክክር የታየበት ነበር። የኬሮድ አትሌቲክስ ልማት ማህበር ፕሬዝዳንት የቀድሞ አሠትሌት እና አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ውድድሩ በሚቀጥለው አመት ከውጭ ምርጥ አትሌቶችን በማሳተፍ፤ ዝግጅቱን ዘመናዊ በማድረግ ከአሁን በተሻለ መልኩ እንደሚያዘጋጁ ተናግሯል።
የመሮጫው ጎዳና ልኬት በዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫ ማህበር AIMS  ኢትዮጵያዊ ባለሙያ መረጋገጡ ይታወቃል። በአትሌቲከስ ውስጥ ያለፉ፤ አሁን የዓለም ምርጥ አትሌት የሆኑ እና ወደ ማናጀርነት አሰልጣኝነት የገቡ ባለሙያዎች በኬሮድ አትሌቲክስ ማህበር መሰባሰባቸው የጎዳና ላይ ሩጫው በአጭር ጊዜ ውስጥም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የሚያገኝበት እድል ሊፈጠር ይችላል፡፡ የጎዳና ላይ ሩጫዎችን በማዘጋጀት ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና በማግኘት ፈርቀዳጅ እና የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር ሙሉ አባል እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ኤአይኤምኤስ AIMS ከዓለም አትሌቲክስ ማህበር ጋር ተባብሮ የሚሰራ ሲሆን የጎዳና ላይ ሩጫዎችን  በብስክሌት የሚለካበት አሰራር ብቸኛው እና ትክክለኛው የኮርስ መለኪያ  እንደሆነ ይገለፃል፡፡ የልኬቱ ውጤት የAIMS አባልነት መሠረታዊ መስፈርት ሲሆን በዓለም ዙርያ የሚገኙ ሯጮች የመሮጫ ጎዳናውን ትክክለኛነት በማረጋገጥ  በልብሙሉነት እንዲሳተፉ እና ወደ ትልቅ ውድድር የሚሐጋገሩበትን ህጋዊ ሰዓት ለማስመዝገብ ያስችላቸዋል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫዎችን ከዋና ውድድሮቹ ተርታ የሚያሰልፍ ሲሆን በሶስት የተለያዩ የውድድር መደቦች ማራቶን፣ ግማሽ ማራቶን እና ሌሎች የጎደና ላይ ሩጫዎች ብሎ ይከፋፍላቸዋል።  ባለፉት 10 ዓመታትም ለጎዳና ላይ ሩጫዎቹ የወርቅ፤ የብርና የነሐስ ደረጃዎች  በመስጠት ከ88 በላይ ውድድሮችን በልዩ እውቅና ዘርዝሯቸዋል፡፡ ለጎዳና ላይ ሩጫዎች የፕላቲኒየም ደረጃ መሰጠት የተጀመረው ከ1 የውድድር ዘመን በፊት ሲሆን፤ ዘንድሮ ደግሞ የፕላቲኒዬም እና የወርቅ ደረጃ ያላቸው የጎዳና ላይ ሩጫዎች  የኤሊት ተብለው ተጨማሪ እድገት ወስደዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበር ለጎዳና ላይ ሩጫዎች የሚሰጣቸውን ደረጃዎች በየአመቱ እየገመገመ እንደሚሸልማቸውም ታውቋል፡፡  የውድድር አዘጋጆች ይህን ዕውቅና ለማግኘት ለማህበሩ ማመልከት ያለባቸው ሲሆን እና ውድድራቸው በርካታ መመዘኛዎችን ማሟላት ይኖርበታል፡፡ ደረጃ የሚሰጥባቸው መስፈርቶች የሚለያዩ ሲሆን በተለይ የፕላቲኒዬም እና የወርቅ ደረጃዎችን  መለያዎች በጣም ጥብቅ መስፈርቶች መያዛቸው ነው፡፡ ከአምስት በላይ የውጭ አትሌቶችን ማሳተፍ፤ የውድድሩ ኮርስ ለተሽከርካሪዎች ትራፊክ ዝግ መሆን፤ ለውጤት መመዝገቢያ ሙሉ የኤሌክትሮኒክስ ጊዜን መጠቀም፤ ውድድር ሥነ-ምህዳራዊ ጉዳትን ለመቀነስ በሚያስችል መንገድ መደራጀቱ ከመመዘኛዎቹ ይገኙበታል፡፡   

Read 492 times