Saturday, 29 May 2021 12:21

“ከንጋት ጀርባ” መፅሐፍ ሰኞ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 በደራሲና ተዋናይት ኤልሳቤት አሉበል የተሰናዳውና የራሷን የስደት ታሪክ የሚተርከው “ከንጋት ጀርባ” መፅሐፍ ሰኞ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር ይመረቃል።
መፅሐፉ በዋናነት ደራሲዋ ተዋናይ ኤልሳቤት ከትውልድ ቀየዋ ተነስታ በከባዱ የሊቢያና ሰሃራ በረሃ አቆራርጣ በስደት በርካታ መከራዎችን አሳልፋ እንዴት አሜሪካ እንደገባችና ከህልሟ ጋር እንደተገናኘች የሚተርክ ሲሆን፣ ኤልሳቤት አሜሪካ ከገባች በኋላ የፊልም ትምህርቷን ተከታትላ ምርጥ ተዋናይትና የካስቲንግ ዳይሬክተር ለመሆን መብቃቷንም በመፅሐፉ ተርካለች። “የሀበሻ ፊልም ማህበር” መስራች የሆችው የመፅሐፉ ደራሲና ባለታሪኳ ኤልሳቤት ይህንኑ ታሪኳን “Behind the sunrise” በሚል ርዕስ ፅፋ ለንባብ ያበቃች ሲሆን ይህንኑ መፅሐፍ “ከንጋት ጀርባ” በሚል ወደ አማርኛ መልሳ የሀገሯ ሰዎች ከታሪኳ እንዲማሩ ለማድረግ የቻለች ሲሆን መፅሀፉን ለማስመረቅም ወደ ሀገሯ መግባቷን የምረቃ ስነ-ስርዓቱ አዘጋጅ ምስክር ጌታነው ሚዲያና ፕሮሞሽን ገልጿል። በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ገዛኸኝ ፀጋው (ዶ/ር)፣ የሙዚቃ ባለሙያ ሰርፀ ፍሬ ስብሃት፣ የፍልስፍና ምሁር ዮናስ ዘውዴ፣ ሙሃዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረትና ወዳጄነህ መሃረነ (ዶ/ር) ልዩ ንግግርና ስለመጽሐፉ አስተያየት ይሰጣሉ ተብሏል። አርቲስት ዓለማየሁ ታደሰና አርቲስት ደሳለኝ ሀይሉ ከመፅሀፉ የተመረጡ ታሪኮችን የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ወግ በዕፀገነት ከበደ፣ ግጥም ደግሞ በበላይ በቀለ ወያ እንደሚቀረብና ሻሎም ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ቡድን መርሃ ግብሩን እንደሚያደምቅ አስተባባሪው ጋዜጠኛ ምስክር ጌታነው  ገልጿል። በ406 ገፅ የተቀነበበው መፅሐፉ በ280 ብር ለገበያ ቀርቧል።


Read 11534 times