Sunday, 30 May 2021 00:00

በእስር ላይ የሚገኙት የማሊ ፕሬዚዳንትና ጠ/ሚኒስትር ስልጣን ለቀቁ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ባለፈው ነሃሴ ወር በማሊ የተደረገውን መፈንቅለ መንግስት በመራው ኮሎኔል አስሚ ጎይታ ባለፈው ሰኞ በቁጥጥር ስር የዋሉትና በእስር ላይ የሚገኙት የአገሪቱ የሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንት ባህ ንዳው እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሙክታር ኳኔ ባለፈው ረቡዕ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው አመት በአገሪቱ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት የመሩትና በሽግግር መንግስቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲሰሩ የቆዩት ኮሎኔል አስሚ ጎይታ፣ ባለፈው ሰኞ የአገሪቱን ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር የተጣለባቸውን መንግስታዊ ሃላፊነት በአግባቡ አልተወጡም፣ ያልተገባ ሹም ሽር አድርገዋል በሚል ማሰሩን የዘገበው ቢቢሲ፤ ኮሎኔሉ ስልጣኑን በመረከብ በቀጣዪ አመት ሊካሄድ ቀን የተቆረጠለት ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ እንደሚካሄድ መግለጹንና ይህን ተከትሎም በእስር ላይ የሚገኙት ባለስልጣናቱ ባለፈው ረቡዕ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን በይፋ ማስታወቃቸውን አመልክቷል፡፡
ከማሊ ዋና ከተማ ባማኮ አቅራቢያ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ማስታወቃቸውን ተከትሎ፣ ከእስር እንዲለቀቁ ከወታደራዊው ሃይል ጋር ድርድር እየተደረገ እንደሚገኝም አልጀዚራ ዘግቧል።
ኮሎኔሉ ባለፈው አመት በመሩት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ኬታን ከሥልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ በአገሪቱ የ18 ወራት የሽግግር ምክር ቤት መቋቋሙን ያስታወሰው ዘገባው፣ ኮሎኔሉ ግን ዳግም መፈንቅለ መንግስት በሚባል መልኩ ፕሬዝዳንቱንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማሰሩ አገሪቱን ወደከፋ ሁኔታ ሊያመራት ይችላል መባሉን አመልክቷል፡፡
የአፍሪካ ህብረት፣ ኢኮዋስ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና አውሮፓ ህብረትን ጨምሮ አለማቀፍ ተቋማት ኮሌኔሉ ከሰሞኑ ያሰራቸውን ፕሬዝዳንቱንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአፋጣኝ እንዲፈታ ጥሪ ቢያቀርቡም ምንም ተስፋ ሰጪ ምላሽ ሳይገኝ መቆየቱንም አመልክቷል፡፡



Read 2675 times