Print this page
Sunday, 30 May 2021 00:00

ለጀማሪዎች እድል የሚሰጠው `ቴስት ኦፍ አዲስ` በግዮን ሆቴል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የግዮን ሆቴሉ ሰፊ መናፈሻ በበርካታ ካፌዎች ሬስቶራንቶችና የምግብ አዘጋጆች ተሞልቷል። እዚህም እዚያም በረድፍ ተሰድረው ከተተከሉት ውብ ድንኳኖች የሚወጣው የምግብ አምሮትን የሚቀሰቅሰውና አፍንጫን የሚፈታተነው የተለያዩ ምግቦች ሽታ ስፍራውን አውዶታል። ከወዲያ በተንጣለለው የሙዚቃ መድረክ ላይ እየነጠረ ስፍራውን ያደመቀው የዲጄ ሙዚቃ የመዝናናትና የመነቃቃት  ስሜትን ይፈጥራል። ስፍራው ደስ ይላል። ዋሊያ ቢራ ከብሉ ሚዲያ ጋር በመተባበር ላለፋት 6 ዓመታት “ቴስት ኦፍ አዲስ”ን ሲያዘጋጅ ቆይቷል። በአመት ሁለትና ሶስት ጊዜ የሚዘጋጀውን ይህንን ፕሮግራም በርካቶች በጉጉት ይጠብቁታል። ዓለም በሯንም ደጇንም ዘግታ እንድትከርም ባስገደዳት የኮሮና ወረርሽኝ ጦስ ሣቢያ ተቋርጦ የነበረው ይህ 22ኛው ዙር “የቴስት ኦፍ አዲስ” (የሞግብና የመዝናኛ ፕሮግራም) በብዙ ወጣቶች ዘንድ ተናፍቆ ሠንብቷል።
የ”ቴስት ኦፍ አዲስ” ዝግጅት ታዳሚዎች የሆኑት ኤርምያስ ዘውዱና ጓደኞቹ የነገሩኝም ይህንኑ ነበር። “ራሣችንን ፈታ የምናደርግበት በመድረክ ሙዚቃዎች የምንዝናናበት ፕሮግራም ነው። በተለይ እንዲህ የመዝናኛ ዝግጅቶች በሌሉበትና በተለያዩ ጉዳዮች ተጨናንቀን በሰነበትንበት ጊዜ ራስን ለማዝናናት የሚያስችሉ ፕሮግራሞች መጀመራቸው ደስ የሚል ነገር ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ በቀላሉ እድል ለማግኘት የማይችሉ ግን አስገራሚ አቅም ያላቸው ጀማሪዎች ስራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ እድል መስጠቱ ጥሩ ነገር ነው” ሲሉ አውግተውኛል።
የዋሊያ ቢራ ሲኒየር ብራንድ ማናጀር ፋይዳ ዘውዱ እንደነገሩኝ፤ የፕሮግራሙ አላማ ጀማሪ የሙዚቃ ባለሙያዎች ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት አዳዲስ ሬስቶራንቶችና የምግብ አዘጋጆች ራሣቸውንና የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ለተገልጋዩ በስፋት ለማስተዋወቅ እድል የሚያገኙበት፣ ዋሊያ ቢራ ከደንበኞቹ ጋር በስፋት የሚገናኝበት እድልን የሚያመቻችና በተለይ ለወጣቶች መልካም የመዝናኛ አጋጣሚን የፈጠረ ፕሮግራም ነው። ዋልያ ቢራም ዘንድሮም ይዞ የቀረበው በአዲስ መልክና ጣዕም አዲስ ዝግጅት እንደሆነም ገልጸዋል።
ራሣቸውን ለማውጣት እድል ያላገኙ አዳዲስና አቅም ያላቸው የሙዚቃ ባለሙያዎችን እድል በመስጠት ሰፋ ያለ ተመልካች አግኝተው እንዲበረታቱ በማድረጉ ረገድም ዝግጅቱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተነግሯል።
ግንቦት 14 እና 15  ቀን 2013  ዓ.ም በተዋበው የግዮኑ መናፈሻ ውስጥ የተካሄደው የ”ቴስት ኦፍ አዲስ” የምግብና መጠጥ ፌስቲቫል ላይ የሆድን ብቻ ሣይሆን የአዕምሮን ረሃብ የሚያስታግሱ የተለያዩ ዝግጅቶችም ተካሂደዋል።
ፕሮግራሙ የኮቪድ 19 በሽታ መከላከያ መመሪያዎችን በጠበቀ መልኩ የተከናወነ ሲሆን በዚህም መሠረት ከመደበኛው ጊዜ 1/4ኛውን የፕሮግራም ታዳሚ ብቻ ማስተናገዱንም አዘጋጆቹ ተናግረዋል።

Read 947 times
Administrator

Latest from Administrator