Print this page
Monday, 31 May 2021 00:00

አስፋው የምሩ (ጋሽዬ)፦ የአገር ባለውለታና የታላቅነት ተምሳሌት

Written by 
Rate this item
(23 votes)

   በ1958 ዓ.ም ትምህርት ቤቱን በድንገት የጎበኙት ቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ከዚህ በታች የሰፈረውን መልዕክት አስፍረዋል፦ ክጽሁፉ በኋላ በቃላቸው             ትምህርት ቤቱንም “አሠረ ሐዋርያት ትምህርት ቤት” ብለነዋል አሉ።


           እንደ መንደርደሪያ
ባለፈው ጽሁፍ ጋሽዬ በሕዝብ ዘንድ ብዙ አለመታወቁን፣ በተማሪዎቹና በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ግን ከፍተኛ ተወዳጅነትና ከበሬታ እንደነበረው፣ በንጉሡ ዘመን “በቀዳማዊ ኃይለሥላሤ የሽልማት ድርጅት” በትምህርት ዘርፍ የሚሰጠውን ከፍተኛ ሸልማት በ1962 ዓ.ም  ማግኘቱንና በዓለም አቀፍ ደረጃም “የዓለም ሕጻናት ጀግና” ተብሎ መሽለሙን፤ ተያይዞም “የዓለም ሎሬት” የሚል ማዕረግ እንደተሰጠውና እሱ ግን “ጋሼ” እየተባለ መጠራቱን እንደሚወድ እንዲሁም ለኖቤል ተሸላሚነት እጩ ተወዳዳሪ እንዲሆን የቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበል መቅረቱን አንስተን ነበር።
ጋሽዬን እንዲህ ስሙ በፍቅር እንዲጠራና “የድሆች አባት” ያሰኙት፤ የወላጅ አልባ ሕጻናትና የጎዳና ተዳዳሪዎች ተቆርቋሪነቱ፣ የወጣቶች የቀለም አባትነቱ፣ የእናቶችና የልጃገረዶች አለኝታነቱ፣ በድንገተኛ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ቀድሞ ደራሽ መሆኑና የአካባቢው ተንከባካቢና በአጠቃላይ  “የአንድ ብዙ" መሆኑ ነው፡፡ ይህንን አገልግሎት ያለምንም ቋሚ በጀት፣ ዕርዳታ ከዚህም ከዚያም እየለመነ፣ ያለማቋረጥ ላለፉት 60 ዓመታት ማከናወኑም ተጠቅሷል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በ1950ዎቹ መጀመሪያ በዛፍ ጥላ ሥር በተጀመረ የማስተማር ተግባር ቁጥራቸው ከሁለት መቶ ሃምሳ ሺ በላይ የሆኑ ወጣቶች የትምህርት እድል ማግኘታቸውም ተጠቅሷል።
የዚህ ጽሑፍ ዋና መልእክት ደግሞ በተለምዶ አነጋገር “ታዋቂ ያልሆኑ  ሰዎች” ለአገርና ለወገን የሚጠቅም እጅግ በጣም ታላቅ አኩሪ ተግባር ማከናወን እንደሚችሉ አስፋው የምሩን (ጋሽዬን) በተምሳሌነት አቅርቦ ማሳየት ነው፡፡ በሌላ መልኩ፤ የጽሑፉ የሃሳብ ማጠንጠኛ ደግሞ “It always seems impossible until it is done“  “አንድ ነገር በተግባር እስከ አልተተገበረ ድረስ የማይቻል / የማይሆን ነገር ይመስላል” የሚባልውን ነገር ጋሽዬን እንደ ምሳሌ በመውሰድ ምን ማለት እንደሆነ ማሳየት ነው፡፡
ለምሳሌ፦
ኢትዮጵያና ጣሊያን ጦርነት ሲገጥሙ፣ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ተብሎ አልተጠበቀም ነበር፤ ሆኖም ግን ክብር ለአድዋ ጀግኖቻችን ይሁንና በአፄ ምኒልክ መሪነት ዓለምን ባስገረመ ሁኔታ ኢትዮጵያ አሸነፈች። የማራቶን ሩጫን (42ኪ.ሜ) በባዶ እግር ሮጦ  ሪከርድ በመስበር ጭምር ማሸነፍ ይቻላል ተብሎ አይገመትም ነበር፡፡ ነገር ግን ጀግናው አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ፤ሪከርድ በመስበር ጭምር ዓለምን ጉድ አሰኘ፡፡
አንድ ራሱ ጎዳና ተዳዳሪ በነበረ ወጣት በዛፍ ጥላ ሥር የተጀመረ ትምህርት ቤት፣ ያለ ምንም ቋሚ በጀት፣ ያለማቋረጥ ከ60 ዓመታት በላይ በመዝለቅ፣ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የተቸገሩ ወጣቶችን ያስተምራል ተብሎ አይጠበቅም፤ ነገር ግን ይህ ተግባር  በአስፋው የምሩ ተከናወነ።
እንደዚህ የመሰሉ በተለየ አኳኋን የሚከናወኑ አስደናቂ ሥራዎች፣ የተለየ አስተሳሰብና አተገባበርን ያመላክታሉ፡፡ ተግባሩን የሚፈጽሙትም ሰዎች “የተለዩ ሰዎች (Extra ordinary Men)” ይባላሉ፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ሰዎችንና ተግባራችውን ቀረብ ብሎ ማየት የስኬታቸውን መንገድ ለመከተል ይረዳል።
በግሌ ጋሼ በአገር ውስጥ የሚገባውን ያህል ዕውቅና አግኝቷል ብዬ አላምንም። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ግን ለጋሼ እውቅና ማስገኘት ሳይሆን፣ ከእሱ ስራዎች ምን እንማራለን የሚለው ጉዳይ ላይ ማተኮር ነው፡፡  በመሆኑም ጋሼ ሕይወቱን / ራሱን ለማሸነፍ የሄደበትን ጎዳና፤ ያጋጠሙትን የሕይወት ውጣ ውረዶች የተቋቋመበትን መንገድ፣ የአንድ ብዙነቱንና ፋና ወጊነቱን ሲያከናውን የተከተላቸውን የሕይወት መርሆዎችን ከሕይወት ጉዞው ጋር እያያያዙ በወፍ በረር ዕይታ መቃኘት ነው፡፡
የጽሁፉ አቅራቢ ጋሼን ከ20 ዓመታት በፊት በተፈጠረ የሥራ ግንኙነት አውቀዋለሁ፡፡ ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ ግን የጋሼን ሁኔታ በቅርብ በመከታተል የሕይወቱን መንገድ ለመረዳት ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ የጋሼና የትምህርት ቤቱ ታሪክ አንድ ዓይነትና የተያያዙ ናቸው። ምንም እንኳን በግል ባህሪው ስለ እሱ ምንም ነገር እንዲታወቅ ባይፈልግም፤ ጋሼን ከትምህርት ቤቱ ለይቶ ማየት አይቻልም። ትምህርት ቤቱ የተጓዘበት መንገድ ስለ ጋሼ ብዙ ነገር ያስረዳል። ትምህርት ቤቱን ራሱ መሠረተ፣ እዛው  ኖረ፣ እዛው አስተማረ ፣እዛው ሕይወቱን መሰረተ፣ እዛው አለፈ። ሁሉም ነገር እዛው በዛው ተከወነ። ስለ ጋሼ ጠጋ ብሎ ላስተዋለው ምናባዊ እይታው (imagination) ከፍ ያለ መሆኑን ከንግግሮቹና ክጽሁፎቹ መገንዘብ ይቻላል።
ስለዚህ የትምህርት ቤቱን ታሪክ ማወቅና መረዳት የጋሼን የሕይወት ታሪክ እንደማወቅ ይቆጠራል፡፡ የትምህርት ቤቱ ታሪክ ደግሞ በመጻህፍት ቤቱ ውስጥ በአግባቡ ተሰንዶ ይገኛል፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ምንጮች  ከቤተ-መፃህፍቱ የተገኙት ሰነዶች ናቸው። ሰነዶቹ በትምህርት ቤቱ ስለተከናወኑ ተግባሮች፣ የማኅበረሰብ ድጋፎችና የተለያዩ ነገሮች ዝርዝር መረጃ ይሰጣሉ፡፡
ታዳጊው አስፋው
አስፋው ገና የ9 ዓመት ታዳጊ እያለ በኪሱ 0.50 ሳንቲም ብቻ ይዞ ነጋዴዎችን ተከትሎ ወደ አዲሽ አበባ ዘለቀ። ቄሱ አባቱ ዲያቆን እንዲሆንላቸው ይፈልጉ ስለነበር፣ ቀደም ሲል ከእኩዮቹ ጋር ወደ አዲስ አበባ አምጥተዋቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ለታዳጊው አስፋው ወደ አዲስ አበባ ከነጋዴዎቹ ጋር ያደረገው ጉዞ ለሁለተኛ ጊዜ ነበር፡፡ የመኖሪያ መንደሩ ከአዲስ አበባ 120 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው በቀድሞ አጠራር ሽዋ ክፍለ ሃገር ልዩ ስሙ ቡልጋ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን፤ አዲስ አበባ የማረፊያ አድራሻው ደግሞ ቀድሞ ድቁና የተማረበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡
አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላ ግን ሁሉም ነገር እንደገመተውና እንደጠበቀው ሳይሆን ቀርቶ ራሱን የጎዳና ተዳዳሪ ሆኖ አገኘው፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ በተፈጠረው መልካም አጋጣሚ ከጎዳና ተዳዳሪነት ወደ ቤት አገልጋይነት ተሸጋገረ፡፡ እያገለገለ በትርፍ ጊዜው እንዲማር በመጠየቁና ስለተፈቀደለት ”ካቴድራል” እየተባለ የሚጠራው ትምህርት ቤት ገባ፡፡ የትምህርት ውጤቱም የብሩኅ አእምሮ ባለቤት መሆኑን የሚያሳይ ነበር። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በአጭር ጊዜ ከማጠናቀቁም በላይ፣ የ8ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤቱ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ በጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት የነፃ የትምህርት እድል አገኘ። ለምዝገባ ሲሄድ ቦታ እንደሌለ ተነገረው፡፡ የሰማውን ማመን አቃተው፡፡ በእሱ ምትክ ከሱ ያነሰ  ውጤት ያመጣ ከፍሎ እንዲማር እንደተመደበ ተረዳ፡፡ ያጋጠመው መልካም እድል በመሰናከሉ ቅር ቢሰኝም፤ ትምህርቱን ለመቀጠል ባደረበት ፅኑ ፍላጎት ተገፍቶ ከብቶች በተጫኑበት መኪና ውስጥ ተደብቆ በመሳፈር ወደ ጂቡቲ ጉዞ ጀመረ፡፡ ኬላ (ፍተሻ ጣቢያ) ላይ በከብቶች መካከል ቁልጭ፡ ቁልጭ ሲል ተገኘ፡፡ የኬላው ጠባቂዎችም በሁኔታው በመገረም ለጥቂት ጊዜያት ካሰሩት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ላኩት፡፡
ወጣቱ አስፋው አዲስ አበባ እንደ ደረሰ፣ በቀጥታ እንደገና ወደ ዊንጌት ትምህርት ቤት በመሄድ ጉዳዩን ለዋናው ዳይሬክተር በዝርዝር አስረዳቸው። አሳቸውም በሰሙት ነገር ማዘናቸውን ከገለጡለት በኋላ፣ በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን “የነጻ ተማሪ” አድርገው እንደሚቀበሉት፣ ነገሩ ባይሆን እንኳን ራሳቸው እየከፈሉ እንደሚያስተምሩት ቃል ገቡለት፡፡ ይህም ሌላኛው መልካም አጋጣሚና የሕይወት መስመሩ የተቀየረበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ነበር በ1950ዎቹ መጀመሪያ ዊንጌት ትምህርት ቤት የገባው።
ወጣቱ አስፋው
አስፋው ሁሉጊዜም አካባቢውን መቃኘት የሚወድ በመሆኑ አንድ ለየት ያለ ነገር በትምህርት ቤቱ አካባቢ አስተዋለ። እሱ ከሚማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ ከተማሪዎች የሚተርፈው ምግብ ሲቃጠልና ጉድጓድ ውስጥ ሲቀበር ተመለከተ። በሌላ አቅጣጫ ደግሞ በአካባቢው ከሚገኝ ቤተ ክርስቲያን አያሌ ችግረኞች ምግብ ሲለምኑ አስተዋለ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ያሳለፈው አጠቃላይ የጎዳና ሕይወቱ ትዝ አለው፡፡ በቀጥታ ወደ ትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ ሄዶ ሃሳቡን ገለጠላቸው። ፈቀዱለት፡፡ ከዚያን ቀን በኋላ ትርፍራፊውን ምግብ እየሰበሰበ ለተቸገሩ ልጆች በትምህርት ቤቱ አጥር ላይ እየተንጠለጠለ ማደል ጀመረ፡፡ ይህም ኣላረካውም፡፡ ሌላ ጥያቁ ኃላፊውን ጠየቀ።  በሃሳቡ በመገረም አሁንም ፈቀዱለት። የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ከተመገቡ በኋላ ችግረኞች በግቢ ውስጥ የተለየ ቦታ ተዘጋጅቶላቸው የሚመገቡበትን ሁኔታ ነበር ያስፈቀደው፡፡ ችግረኞች መታወቂያ ተዘጋጅቶላቸው በሥርዓት ይመገቡ ጀመር።
የምግብ ችግራቸው የተቃለለላችውና በወጣቱ ድርጊት ልባቸው የተነካው ”ትርፍራፊ በሊታዎች”፣ በትርፍ ጊዜው እንዲያስተምራቸው ጠየቁት፡፡ ያልጠበቀው ጥያቄ ነበር። ከትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር ከተመካከረ በኋላ በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ በዛፍ ጥላ ሥር የሚሰጠው ትምህርት የተጀመረው በዚህ መልክ ነበር፡፡ አስፋው ይህንን ሁሉ ተግባር ሲያከናውን ራሱ ገና የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ዘመኑም 1951 ዓ.ም ነበር፡፡

ወጣቱ አስፋው በ1950 ዎቹ መጀመርያ በዛፍ ጥላ ሥር ሲያስተምር “የእንቁራሪቷና የአንበሳው ታሪክ”
ምግባቸው የተማሪዎች ትርፍራፊ፣ መማሪያቸው የዛፍ ጥላ ሥር፣ አዳራቸው የቤተ ክርስቲያን ታዛዎችና ”የትላልቅ ሰዎች መቃብር” የሆኑ ወጣቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ፡፡ አስፋው ከቤተ ክርስቲያኑ ሌላ አማራጭ እንዲፈልግ ተነገረው። ቢያወጣ ቢያወርድ ጠብ የሚል ሃሳብ አላገኘም፡፡ ከብዙ ማሰላሰል በኋላ አንድ ሃሳብ መጣለት።  አንድ ቀን የመጣለትን ሃሳብ ለጓደኞቹ አካፈላቸው። ሁሉም በመገረም ዓይናቸውን አፍጥጠው ተመለከቱት። ጤንነቱን ተጠራጠሩ፡፡ በመጨረሻም አንበሳውን አክላለሁ ብላ ተነፋፍታ ስለሞተችው እንቁራሪት ተረቱለት። አቅሙን አለማወቁን መጠቆማቸው ነበር። በሌላ አባባል "አወቅሽ አወቅሽ ሲሏት...” የሚለውን መተረታቸው ነበር። የጓደኞቹን ተረት ወደ ጎን ትቶ ደብዳቤውን ጽፎ ላከ፡፡ለብዙ ጊዜ መልስ ሳያገኝ ቀረ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን የደብዳቤው ምላሽ ደረሰው። ያየውን፣ ያነበበውን ማመን አቃተው። ዓይኑን እየጠራረገ ደጋግሞ አነበበው። ደብዳቤው እንዲህ የሚል መልእክት ይዟል፦
“…በአካባቢው ባዶ የመንግሥት ቦታ ካለ ይሰጠው ይላል”
ደብዳቤውን ይዞ ላይ ታች ቢልም ሰሚ አላገኘም፡፡ ያሰበውን ሳይፈጽም የማያርፈው ወጣት አንድ ሃሳብ መጣለት፡፡ አሁን ማንንም ማማከር አልፈለገም። አጋጣሚውን መጠበቅ ብቻ ያዘ፡፡ ጊዜው መድረሱን ሲረዳ፣ ተማሪዎቹን አሰልፎ ዋናው መንገድ ላይ ተገኘ። መኪናው ከዊንጌት ትምህርት ቤት ቀስ ብሎ እየወጣ ነበር፡፡ የእሱ ተማሪዎች እየጮኹ ይዘምራሉ። መኪናው ቀስ ብሎ እየሄደ ነው፡፡ መኪናው አጠገቡ እንደ ደረሰ አስፋው በድንገት ጎማው ሥር ተወርውሮ ወደቀ፡፡ ሹፌሩ በፍጥነት መኪናውን አቆመ። አስፋው ግን ብድግ ብሎ አቤቱታውን በከፍተኛ ድምጽ ማሰማቱን ቀጠለ፡፡ መኪናው ውስጥ ክኋላ አንድ ግርማ ሞገስ የተላበሱ ሰው ተቀምጠዋል፡፡ የወጣቱን ጩኽትና ተማሪዎቹን ሲመለከቱ አንድ ነገር ትዝ አላቸው። ”ከአንድ ወጣት ተማሪ የተፃፈላቸው ደብዳቤ”። ንጉሡ መሬት እንዲሰጠው የሚለውን ትዛዛቸውን አጽንተው በማዘጋጃ  ቤት በኩል በአስችኳይ እንዲፈጸም ድጋሚ ትዛዝ ሰጡ፡፡ ከቤተ ክርስትያን አካባቢ የነበረው ግፊትም ጋብ አለ።
በአካባቢው ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ በርግጥ በጊዜው እንደዚህ ዓይነት ተግባር መፈጸም የተለመደ የአቤቱታ አቀራረብ ዘዴ ነው። ይህኛውን ለየት የሚያደርገው ግን በወቅቱ “የታኅሳስ ግርግር” የሚባለው መንግሥትን የመገልበጥ ሙከራ ተደርጎ የክሸነፈበት ወቅት በመሆኑ፣ የንጉሡ የክቡር ዘበኛ ጠባቂዎች ጥንቃቄና ጥርጣሬ ከፍተኛ መሆኑ ነበር፡፡ ስለዚህ በዚህ ወቅት ይህንን ተግባር መፈጸም አስደንጋጭም አደገኛም ነበር፡፡ ነገር ግን ወጣቱ አስፋው ከልቡ ጋር የመከረውን አደረገ፡፡
ለሌላ አንድ ዓመት ከተንከራተተ በኋላ ማዘጋጃ ቤቱ የዊንጌት ትምህርት ቤትን አጥር ይዞ፣ የጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን አዋስኖ ስፋቱ 300 ካ/ሜ የሆነ ቦታ ሰጠው። ይህ ወቅት አስፋው ላይ ከፍተኛ  ጫና ፈጥሮበት ነበር፡፡ የራሱን ትምህርት መማር፣ ልጆችን ማስተማርና የቦታውን/ የመሬቱን ጉዳይ ማዘጋጃ ቤት እየተመላለሱ መከታተል፡፡ በእውነትም በጣም አስቸጋሪ ወቅት ነበር፡፡
“አስፋው ትምህርት
ቤቱንም ጓደኞቹንም አስደነገጠ”
ወጣቱ አስፋው የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ፡፡ በወቅቱ ለዊንጌት ተማሪዎች ሁለት ምርጫ አላቸው፡፡ የኮሌጅ (ዩኒቨርስቲ) ትምህርታቸውን መቀጠል ወይም ሥራ መቀጠር። ጉደኛው አስፋው ሁለቱንም አልፈልግም በማለት ትምህርት ቤቱንም ጓደኞቹንም አስደነገጠ። ምርጫው  ትምህርትን በማስፋፋት መኃይምነትንና ድህነትን መታገል እንዲሁም በተቻለው አቅም ሁሉ ማኅበረሰቡን ማገልገል መሆኑን አስታወቀ።
“ጋሽዬና ትምህርት ቤቱ”
ለትምህርት ቤቱ ማሠሪያ የሚሆነውን ገንዘብ በተለያየ መንገድ (ከተማሪዎች ትርዒት፣ ከዊንጌት ትምህርት ቤት መምህራን መዋጮ ወዘተ) ከሰበሰበ በኋላ፣ በተሰጠው ቦታ ላይ ከተማሪዎቹ ጋር በመሆን ራሱ ጭቃ አቡክቶ፣ አጠና ተሽክሞ፣ ወጪ ወራጅ አቁሞ፣ ማገር ማግሮ፣ ቆርቆሮ መትቶ ለራሱ መኖሪያ የሚሆን አነስተኛ ቤት በአንዱ ጥግ፣ ለተማሪዎቹ ፣ማደሪያና መማሪያ የሚሆኑ ክፍሎች በሌላው ጥግ አሠራ፡፡
በጋሼና በትምህርት ቤቱ መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ የግል ሕይወቱም ሆነ የትምህርት ቤቱ ዋና ዓላማ ”ትምህርትንና ማኅበራዊ አገልግሎትን በተቻለ አቅም ለተቸገሩ ወገኖች ማዳረስ” የሚል ነው። ይህንን ዓላማ ለማሳካት የወጣትነት፣ የጎልማሳነት እንዲሁም የአዛውንትነትን ዕድሜውን ሁሉ ገብሯል፡፡
ትምህርት ቤቱ የማስተማር አገልግሎቱንና የማኅበረሰብ ድጋፎችን አጣምሮ ስለሚሰራ አደረጃጀቱ ለየት ያለ ነው፡፡ ትምህርት ቤት ብቻ ነው እንዳይባል በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ወላጅ አልባ ሕፃናት በትምህርት ቤቱ ውስጥ እየኖሩ ይማሩ ነበር፡፡ የወጣቶችና የሕፃናት ማሳደጊያ እንዲሁም የማኅበረሰብ ድጋፍ የሚደረግበት ተቋም ነው እንዳይባል ከአካባቢው ወደ ትምህርት ቤቱ እየመጡ የሚማሩ ችግረኛ ተማሪዎች ቁጥር ከወላጅ አልባ ሕፃናቱ ቁጥር በብዙ እጥፍ ይበልጣል።
የዚህ ዓይነት አደረጃጀት ትምህርት ቤቱን በትምህርት ሚኒስቴር መዝግቦና ቋሚ በጀት መድቦ ለማስተዳደር አስቸጋሪ አድርጓታል። በሌላ በኩል ሁኔታው ለጋሼ ትምህርት ቤቱን በራሱ መንገድ እንዲያካሂድ ዕድል ፈጥሮለታል፡፡ ለጋሼ ዋናው ችግር የሆነበት የበጀት ችግርንና የአስተዳደር ነፃነትን አቻችሎ መጓዝ ነበር፡፡
“ንጉሡና ብሔራዊ ሎተሪ...”
በአንድ ወቅት አስፋው የዕለት ገቢ ሳይኖረው ይህንን ትምህርት ቤት እንዴት እንደሚያስተዳድረው ተጠይቆ ሲመልስ፦”...ትምህርት ቤቱ ሥራውን የሚያካሂደው በየፊናው በሚመጣው ዕርዳታ በመሆኑ፣ ማንኛውንም የሚደረግልኝን ዕርዳታ እቀበላለሁ፡፡ ለማኝ የሰጡትን መቀበል እንጂ ማማረጥ የእሱ ፋንታ አይደለም ”ብሎ ነበር፡፡ ጋሼ ትምህርት ቤቱ የሚያጋጥመውን የገንዘብ ችግር ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፦
“...በተደጋጋሚ ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ባጋጠመኝ ጊዜ ፍፁም ከማልጠብቀው አቅጣጫ ዕርዳታ ይደርሰኝ ነበር፡፡ በተለይ ግን ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ያገኘነው 5000 ብር እና ብሔራዊ ሎተሪ ያደረገልን የ6500 ብር ዕርዳታ፣ ከዊንጌት ትምህርት ቤት ወዳጆቼ ያገኘሁት 2000 ብር ድጋፍ የእኔንም የትምህርት ቤቱንም ተስፋ  ያለመለሙ ነበሩ፡፡;
“ቅድሚያ ትምህርትን ማዳረስ”
አስፋው የመደበኛ ትምህርቱን ለማስፋፋት የተከተለው መንገድ “Education is more important than the building.” “ትቅድሚያ ለትምህርት” የሚል ነበር። በ1955 ዓ.ም አካባቢ አስፋው ይህንን ሁኔታ ሲያብራራ፤ ”የትምህርት ሚኒስቴርን መመሪያ ተከትዬ ክፍሎቹን ብሠራ ኖሮ የሚኖሩኝ ተማሪዎች ቁጥር 400 ብቻ ይሆን ነበር፡፡ እኔ ግን 2500 ተማሪዎች አሉኝ። ከእነዚህ ውስጥ 380 ያህሉ ትምህርት ቤቱ ውስጥ እየኖሩ የሚማሩ ወላጅ አልባ ወጣቶች ናቸው” ይላል፡፡
ትምህርት ቤቱ ከትምህርት ሚኒስቴር በ1955 ዓ.ም ዕውቅና ቢያገኝም፣ በሚከተለው የተለየ አደረጃጀት ምክንያት ሙሉ የበጀት ድጋፍ አያገኝም ነበር፡፡ መደበኛ በጀት ስላልነበረውም የረዥም ጊዜ ዕቅድ አልነበረውም፡፡
“ድንገተኛው ጉብኝት”
ትምህርት ቤቱ በ1955 ዓ.ም ዕውቅና ካገኘ በኋላ የተማሪዎች ጥያቄ እየበዛ ትምህርት ቤቱም በተቻለው መጠን እየተስፋፋ ነበር። መጋቢት 21 ቀን 1958 ዓ.ም በትምህርት በቱ የተለየ ነገር ተከሰተ። ንጉሡ ትምህርት ቤቱን ለመጎብኘት በድንገት ተገኙ። ከጉብኝታቸው በኋላም ይህንን አስተያየት በወረቀት ላይ አሰፈሩ፦
“በዚህ ተማሪ ቤት በጠቅላላው ደስ ብሎናል፡፡ አስተማሪዎችና ተማሪዎች በርቱ፤ ላገር ጠቃሚ ትሆናላችሁ እግዚአብሔር ይርዳችሁ።” ብለው ከጻፉ በኋላ በቃላቸው ትምህርት ቤቱንም “አሠረ ሐዋርያት ትምህርት ቤት” ብለነዋል አሉ።

“የተለየ ወጣት”
አስፋው በእነዚህ ተግባሮቹ ማለትም ከገጠር ወደ ከተማ የመጣበት ሁኔታ፣ ለንጉሡ በጻፈው ደብዳቤና አቤቱታ አቀራረብ፣ በመጨረሻም ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ በወሰነው ውሳኔና ትምህርት ቤቱንና መኖርያውን የሠራበት መንገድ ሲታይ፦
ወጣቱ አስፋው ውስጡን የሚያዳምጥ፣ የሕይወቱን ጥሪ የሚከተል፣ በመጀመሪያ ራሱን አሸንፎ በመቀጠል ደግሞ ሌሎችን ለመርዳት የተነሳው ገና በለጋ ዕድሜው፣ ገና በጠዋቱ በመሆኑ የተለየ አስተሳሰብ ያለው፣ የተለየ ድርጊት የሚፈጽም በአጠቃላይ የተለየ ሰው (Extra Ordinary person) መሆኑን በተደጋጋሚ ክፈጸማቸው ተግባሮቹ መረዳት ይቻላል።


Read 10168 times
Administrator

Latest from Administrator