Print this page
Saturday, 29 May 2021 14:14

የ‘ኩኩ መለኮቴ’ ነገር...

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

     "ኮሚክ እኮ ነው፡፡ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ከእለታት አንድ ቀን… አለ አይደል… “በቃ በሞባይል ድምጽ ሳይቆራረጥ ማውራት ላንችል ነው!” ሲባል መልሱ ምን ሊሆን ይችላል መሰላችሁ፣ “ምን እናድርግ! የአጼዎቹ ስርአት ጥሎብን የሄደ ችግር ነው፡፡”
              
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በመኪና አሽከርካሪዎች ባህሪይ ከአፍሪካም፣ ከዓለምም ስንተኛ እንደሆንን ይጣራልን፡፡ ግራ ገባና...የከተማችን ባለመኪኖች፣ ያውም የሆሊዉድ ሰዎችን አይነት ሊመስሉ ምንም የማይቀራቸውን መኪና እየነዱ የሚያሳዩት ባህሪይ...አለ አይደል... “ጧት ቁርስ ሆት ዶግ፣ እንቁላል ቁጭ ቁጭና ብላክ ሌብል፣ ቀን ምሳ ቢፍ ስቴክና ብሉ ሌብል፣ ማታ እራት ቺክን ሮስትና ጎልድ ሌብል የሆነ ‘ዳየት’ በአፍንጫችን ይውጣ!” ብንል አይፈረድብንም፡፡ (“በቃ ነፍስ ካላቸው ምግቦች እነኚህን ብቻ ነው  የማውቀው ለምትሉና ‘አኒማል ፕሮጀክት’ ስልችት ላላችሁ እስቲ “ቁርሴን እርጥብ ነው የበላሁት፣ እርጥብ ምን እንደሆነ ንገሩኝ፣” ብላችሁስ!  
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... አብዛኞቹ የአዲስ አበባ አሽከርካሪዎች ‘እየነዱ’ ነው ‘እያበረሩ’ የሚባሉት! የሆነ ሰው መጥቶ... “እመንም፣ አትምንም አራቱም ጎማዎች ከመሬት ለቅቀው ለአንድ አስር ሜትር ያህል በአየር ላይ የሚበር መኪና ቦሌ መንገድ አየሁ፣” ቢለኝ በችኮላ “የጠጣኸው ጠጅ ሙሉ ለሙሉ በግራዋ ብቻ ነው የተጠመቀው?” ከማለቴ በፊት “ምናልባትም አይቶ እንደሆንስ!” ልል እንደምችል ለማስመዝገብ ያህል ነው፡፡ ተቸገርን እኮ! የምር አንዳንዶቹ መኪኖች አጠገባችን ሳይደርሱ እንኳን ‘ሽው’ ብለው ሲያልፉ የሚፈጥሩት ነፋስ “እንዳሞራ ክንፍ አውጥቼ ልብረራ...” ሊያሰኙን ምንም አይቀራቸው፡፡
እኔ የምለው... የባህሪይ ነገር ካነሳን የሆነ የከተማችን ክፍል ነው፣ መአት መኪኖች ተጠጋግተው ቆመዋል፡፡ የምር እኮ... “አነኚህ መሀል፣ መሀል ያሉት እንዴት ብለው ነው የሚወጡት!” የሚያሰኝ ነው፡፡ (መኪኖች መንገድ ዳር ምናምን ሲቆሙ በመሀላቸው ሊኖር ስለሚገባው እርቀት የሆነ ህግ ምናምን ነገር የለም እንዴ! )
እናላችሁ...የሆነች እንደ ዘመናዊዎቹ ከሩቅ የምትጣራ ባትሆንም ከማን አንሼ አይነት መኪና ውስጥ ሞተር አጥፍቶ የተቀመጠ ሰው አለ፡፡ በሞባይል እያወራ ነበር፡፡ ከእሱ ፊት የነበረው መኪና ባለቤት  ይገባና አስነስቶ ሲያንቀሳቅስ ሸርተት ብሎ ኋላ የነበረውን ይገጨዋል፡፡ ከዛ ገጪው ራሱ አንበሳ ሆኖ ይወጣላችሁና በሰላም መኪና ውስጥ የነበረው ሰውዬ ላይ ይጮህበታል፡፡
“ለምንድነው መኪናህን ወደ ኋላ የማታደርግልኝ! መኪናዬን ያደረግኸው ይታይሀል!” የሚገርም እኮ ነው፡፡ የ‘ምኒታ ተቆጢታ’ የሚሉት ነገር አይነት ነው፡፡ ታዲያላችሁ...በእርጋታ ተቀምጦ የነበረው ሰውዬ ተፈናጥሮ ሲወጣ...አለ አይደል... “አንዳንድ ሰው በጣም ሲናደድ ክብደቱ በምን ያህል ኪሎ ነው የሚጨምረው?” ያሰኛል፡፡ አልተናገረ፣ እልጮኸ...ብቻ ሰውየውን ተጠግቶ አፈጠጠበት፡፡ የተፈጥሮ ተአምር የሚባለውን ነገር ይሄኔ ነው የምታደንቁት፡፡ በሦስት ስከንድ ውስጥ ከአንበስነት ወደ‘ሚያውነት’ መውረድ ይቻላል! (ቂ...ቂ...ቂ...) ደግነቱ ወዲያው እግር የጣለው አይነት ትራፊክ ከች አለ፡፡
በቀደሙት ዘመናት እንደ ጨዋታ አይነትም የምትባል ነገር ነበረች...
ኩኩ መለኮቴ
እሷ በበላችው በእኔ ላከከችው፡፡
ኋላ የነበረው ሰውዬ እኮ መኪናውን ላንቀሳቅስ ቢል እንኳን መፈናፈኛ አልነበረውም፡፡ እናላችሁ የፊተኛው ሰውዬ በስነስርአቱ መኪናውን ማንቀሳቀስ ስላቃተው ሀገር ሰላም ብሎ የነበረው ሰውዬ ላይ ማሳበብ አለበት! ግን ምን መሰላችሁ...የሆነ ባህል ሊሆን ምንም የቀረው የማይመስል ነገር ነው... በሁሉም ነገር ላይ ሌላ ጣት የምንቀስርበት መፈለግ፡፡
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል...በምኑም በምናምኑም ‘ሰበብ’ ፍለጋ... ‘ናሽናል አይዴንቲቲ’ ነገር ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡ በፊት ጊዜ የብሄራዊ ቡድናችን ሌላ ሀገር ሄዶ ሦስትም፣ ምናምንም ጠጥቶ መምጣት ለምዶበት ነበር፡፡ (አንድ ጊዜ የአልሲሲ ሀገር ተጫዋቾች ስምንት ነው ምናምን ነገር አጠጥተውን ነበር፡፡ (አይ... ‘ድፍረቱ’ ዛሬ የተጀመረ አይደለም ለማለት ያህል ነው፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...) ታዲያ...ቡድናችን በተሸነፈ ቁጥር ሁልጊዜ የሚሳበበው በምን ነበር መሰላችሁ...በአየሩ፡፡ “አየሩ ከብዶን ነው፣” ይባል ነበር፡፡  
በቦተሊካው የሆነች አሁን፣ አሁን ከመሰልቸቷ የተነሳ ለ‘ጆክነት’ እንኳን የማትመች ሰበብ አለች፡፡ ቦተሊከኛውም፣ አክቲቪስቱም፣ ተንታኙም፣ አንዳንድ የከተማችን ነዋሪዎችም--- ሁላችንም   በ‘ትናንት’ ላይ ማሳበብ ይቀናናል፡፡
ኩኩ መለኮቴ
እሷ በበላችው በእኔ ላከከችው፡፡
“ይሄ ነገር እንዴት ነው እንዲህ ሊሆን የቻለው?”
“ያለፉት ስርአቶች ጥለውብን የሄዱት ነው፡፡” 
ኮሚክ እኮ ነው፡፡ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ከእለታት አንድ ቀን… አለ አይደል… “በቃ በሞባይል ድምጽ ሳይቆራረጥ ማውራት ላንችል ነው!” ሲባል መልሱ ምን ሊሆን ይችላል መሰላችሁ፣ “ምን እናድርግ! የአጼዎቹ ስርአት ጥሎብን የሄደ ችግር ነው።”
እንበል እሱዬው አንድ ሰሞን ከመወፈሩ የተነሳ … “ከብት ከነነፍሱ የዋጠ ነው የሚመስለው!” የሚለውን አፋችን ላይ ‘ድንገት የሚመጣውን’ (ቂ…ቂ…ቂ…) አባባል ትተን “አጅሬው እኮ ራሱ  እንትኑን ሊመስል (በ‘ጨዋ’ አነጋገር) ምንም አልቀረውም!” ስንለው ቆይተን ሊሆን ይችላል፡፡ ታዲያላችሁ... ሁልጊዜ ‘ቦምቦሊኖ ጉንጭ’ መሆን የለምና (‘ቦምቦሊኖ ጉንጭ’ ያውም በዚህ ዘመን!) ነገርዬው ሁሉ እርግፍ ይላል፡፡ እናላችሁ... እሱ ወይ ‘ሲፑ’ን አብዝቶ ወይም ዳየቱን በግራምና በኪሎ ግራም ከሚለካ ‘ሶሊድ ፉድ’ ከጠርሙስ ወደሚቀዳና በሊትር ወደሚለካ ‘ሊክዊድ ፉድ’ ለውጦ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይ ደግሞ በ‘ኦቨርታይም’ ሥራ ሰበብ እያመሻሸ የሆነ ጂም ውስጥ እንደ ልብ የማይገኝ (ቂ...ቂ...ቂ...) ‘የአካል ብቃት እንቅስቃሴ’ ለጤና ከሚገባው በላይ አብዝቶ ይሆናል፡፡ እናላችሁ… መቼም አንዳንድ ወዳጅ አይቶ ዝም አይልምና ይጠይቃል...
“ስማ አንተ ሰውዬ፣ በጣም እኮ ነው የቀነስከው፡፡ ምን ሆነህ ነው? በቀን ሰባቴ የምትበላው ሰውዬ በቀን አንዴ ወረድክ እንዴ!”
“ምን ታካብዳለህ! አሁን ያን ያህል ቀንሼ ነው!”
“ቀንሼ ነው ወይ! ስማ  አምስት ጉንጭ የነበረህ ሰውዬ እኮ፣ አሁን  በጉንጮችህ ቦታ ውሀቸው የደረቀ ኩሬዎች ብቻ ናቸው ያሉት!”
“በአንተ ቤት ነገር ማሳመርህ ነው፡፡”
“እውነቴን ነው፣ ምን ሆነህ ነው?”
“እኔ ምን ላድርግ ከሰባት ቀን አምስቱን ቁርስ ምን እንደምበላ ታውቃለህ? ንገረኛ፣ ታውቃለህ?”
“አላውቅም፡፡”
“ድርቆሽ ፍርፍር! ታምናለህ፣ ድርቆሽ ፍርፍር ለቁርስ!”
“እና እሱ ምን ቸግር አለው?”
“ምን ችግር አለው! በሳምንት ለተከታታይ አምስት ቀን ሞክረውና ታውቀዋለህ፡፡ ሙሉ ቀን እኮ አንጀትህ አይቀርህ፣ ጨጓራህ አይቀርህ፣ ሲፍቅህ ነው የሚውለው፡፡ የምን ድርቆሽ…የብርጭቆ ወረቀት በለው፡፡ ሴትየዋ አመንምና፣ አመንምና ልታሰናብተኝ ነው መሰለኝ!”
“እኔ የምለው… ድርቆሹን የምትበላው ተፈርፍሮ ነው ወይስ ደረቁን ነው የምትቅመው?”
ኩኩ መለኮቴ
እሷ በበላችው በእኔ ላከከችው፡፡
እና ምን ለማለት ነው…የራሳችንን ነገሮች ለመሸፈን ስንል የማናመጣው የምክንያት አይነት አይኖርም ለማለት ነው፡፡
“ስማ ያቺ ባለሆቴሏ ጓደኛችን ጉድ ሆነች እኮ!”
“አስተካክለው፣ ገርልፍሬንዴ በል፡፡”
“አልኩ፡፡”
“ምን ሆነች?”
“ከሰረች፣ ሙልጭ ነው ያለችው፡፡”
“ለነገሩ እኮ እሷም ቢሆን ከሚገባው በላይ ጠገብ ብላ ነበር፡፡ ሠራተኛ ሁሉ እየለቀቀ አልነበረም እንዴ!”
“ማነው እንደሱ ያለህ?”
“ማንም ይበለኝ፣ እንደውም ደንበኞችን ሁሉ ማንጓጠጥ ጀምራ ነበር ሲባል ነው የሰማሁት፡፡”
“ዝም በላቸው... ጓደኞቿ ናቸው ያስጠመጠሙባት፡፡"
ኩኩ መለኮቴ
እሷ በበላችው በእኔ ላከከችው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1785 times