Saturday, 29 May 2021 14:29

የካህሊል አማልክት ‹‹Beloved prophet››

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(4 votes)

  የካህሊል ጅብራን ነፍስ ሁሉንም በመፈለግና ሁሉንም በማጣት ቅዝምዝም መሀል ተሰንቅራ የጠፋች የቅጽበት ብልጭታ ትመስላለች፡፡ በማይረካ ጥማትና በማያባራ ሽሽት መካከል ተወጥራ ሲነካኳት ስቃይን የምትዘምር አንዲት ፍሬ የክራር ክር፡፡ ሕይወቱን የምታተርፍለትን አንዲት የጉበት ቀዶ ጥገና ማድረግን ችላ ብሎ ሞትን በጨበጣ የታገለ…  
ካህሊል ጅብራን የአባቱን ሕልፈት ተከትሎ በ1895 እ.ኤ.አ ከእህቱና እናቱ ጋር በስደት አሜሪካ ገባ፡፡ በዚያ ወቅት ራሱን እንኳን በቅጡ መግለፅ የማይችል አይናፋር ልጅ ነበረ፡፡ ድንገት ግን የ21 ዓመት ልጅ እያለ በአስር ዓመታት የምትበልጠውን ሜሪ ሐስከልን ተዋወቀ፡፡ ሜሪ ካህሊልን ዘግቶ ከተቀመጠባት ጠባብ የጭለማ ክፍሉ ጎትታ አውጥታ ከዓለም ጋራ አስተዋወቀችው፡፡ ፓሪስ ድረስ ልካ ስነ-ስዕል አስተማረችው። እርሱም በምላሹ እንደ ጣዖት አመለካት። የነፍስ ጓደኛው አደረጋት፡፡ የሴቶች ሁሉ መስፈሪያ ትልቋ ሔዋን እንደሆነች በነፍሱ ዘመረላት፡፡ እስከ መጨረሻው ብቸኛ አርታኢውም እሷው ነበረች፡፡
የሜሪና የካህሊል ጓደኝንት ብዙ ጊዜ ተፈትኖ እየታደሰ የቀጠለ፣ ከምናውቃቸው ጉድኝቶች የተለየና ሊገልፁት የሚያስቸግር ይመስላል፡፡ ሜሪ ሐስከል ሲበዛ ደግ ሴት ነበረች፡፡ ከካህሊል በፊትም ቢሆን ለራሷ የሚላስ ሳይኖራት እየቆጠበች የምታስተምራቸው የግሪክ ታዳጊዎች ነበሯት፡፡ ይኸው መልካምነቷ ከአፈር ላይ አንስታ በዓለም ላይ ከዊሊያም ሼክስፒርና ላኦ ትዙ ቀጥሎ በሦስተኝነት በሰፊው የተነበበውን ደራሲ እንድትፈጥር አስችሏታል፡፡
ለ27 ዓመታት ይህን ሁሉ ስታደርግ ከካህሊል የምትጠብቀው ብቸኛ ነገር ቢኖር ለሚያገኛቸው ሰዎች ሁሉ የምወዳት ፍቅረኛዬ ናት ብሎ እንዲያስተዋውቃት ብቻ… በግል ማስታወሻ ደብተርዋ ላይ አስፍራው እንደተገኘችው በዓለም ላይ ለእርሷ ካህሊል ጅብራንን ከመውደድ የሚበልጥ ምንም ነገር አልነበረም፡፡
በአንጻሩ ያለ ሜሪ ሐስከል ካህሊል ከትንኝ ያነሰ፣ ከላባ የቀለለ ለቁምነገር የማይጠራ ሰው በሆነ ነበር፡፡ ትልቁ ካህሊል ከሜሪ ጋር  አለመተዋወቅ ቀርቶ ከእርሷ ጋር የነበረው ጓደኝነት በሆነ ምክኒያት ተቋርጦ ቢሆን ኖሮ በተወዳጁ ፋንታ ዕድገቱ የቀነጨረውን ነብይ የማየት ዕድላችን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነኝ ይመስለኛል። ሜሪ ሐስከል ግን ባደረገችው ነገር ለአፍታም ሳትኩራራ አንዲት ሴት በእህትነት፣ በእናትነት፣ በፍቅረኝነት፣ በጓደኝነት፣ በሰውነት ልትሰጠው የምትችለውን ፍቅር ሁሉ ቅንጣት ታህል ሳትሸራርፍ እየለገሰች፣ በሐምራዊ የንቃት ክንፎች እየበረረ እልፍ መሻገሮችን እንዲያስስ አስችላዋለች፡፡ በ1914 እ.ኤ.አ ክረምት በጻፈላት ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡-
“The day will come when I shall be able to say, ‘I became an artist through Mary Haskell… You have the great gift of understanding, beloved Mary. You are a life-giver, Mary. You are like the Great Spirit, who befriends man not only to share his life, but to add to it. My knowing you is the greatest thing in my days and nights, a miracle quite outside the natural order of things.››
ሜሪ፣ ካህሊል በኪናዊ ምጥቀቱ ከፍ ባለበትም ይሁን በሞራል በተሽመደመደባቸው ጊዜያት ሁሉ ያለማመንታት ከጎኑ ነበረች፡፡ ይህንን ደብዳቤዋን ተመልከቱ፡-
‹‹I don’t even want you to be a poet or painter: I want you to be whatever you are led or impelled to become… Your work is not only books and pictures. They are but bits of it. Your work is you, not less than you, not parts of you… These days when you “cannot work” are accomplishing it, are of it, like the days when you “can work.” There is no division. It is all one. Your living is all of it; anything less is part of it. — Your silence will be read with your writings some day, your darkness will be part of the Light.››
ካህሊል ለትዳር የጠየቃት ብቸኛዋ ሴት ሜሪ ሐስከል ነበረች፡፡ ባይሳካም ቅሉ… ምናልባት ያለመሳካቱ ምክንያት ካህሊል ትዳርን አጥብቆ የማይፈልግ ሰው በመሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹አብሮነታችሁ የመሰናዘሪያ ቦታ አይንፈጋችሁ፡፡ በአንድነት ቁሙ ነገር ግን መተዛዘል እስቲሆን ድረስ አትደራረቡ። የቤተ መቅደስ አዕማድ ሲቆሙ ራቅ ራቅ ብለው ነው፡፡›› ይላልና፡፡
እስኪ ይሄኛውንም ካህሊል ለሜሪ የጻፈላትን ደብዳቤ ተመልከቱ፡-
‹‹I wish I could tell you, beloved Mary, what your letters mean to me. They create a soul in my soul. I read them as messages from life. Somehow they always come when I need them most, and they always bring that element which makes us desire more days and more nights and more life. Whenever my heart is bare and quivering, I feel the terrible need of someone to tell me that there is a tomorrow for all bare and quivering hearts and you always do it, Mary.››
ተፅዕኗቸው ከሜሪ ጋር ለንጽጽር የሚቀርብ ባይሆንም ሌሎች በርካታ ሴቶች በካህሊል ሕይወት ነበሩ፡፡ እርሱም ስለ ሴቶች እንዲህ ብሏል፡- ‹‹የዓይኔን መስኮትና የመንፈሴን በሮች የሚከፍቱት ሴቶች ናቸው፡፡ እናቴ፣ እህቴና ጓደኛዬ የምላቸው ሴቶች ድጋፍ ባያደርጉልኝ ኖሮ፣ ዛሬ እኔም የዓለምን ጸጥታና እርጋታ በማንኮራፋት ድምጽ ከሚረብሹት ሰዎች መካከል ተጋድሜ ሳንጎላጅ እገኝ ነበር፡፡››  
አዎ የካህሊል አማልክት ሴቶች ናቸው፡፡ እህቱ፣ እናቱ፣ ሜሪ ሐስክል፣ ሜሪ ዚያዴ… ሌሎችም፡፡  የሁለቱ ጓደኛሞች ደብዳቤዎች የተጠናቀሩበትን የዚህን መጽሐፍ (Beloved prophet) አርትኦት የሰራችው Virginia Hilu ለዚህ መጽሐፍ መግቢያ በጻፈች መጣጥፍ እህቱ ማሪያና እና ሜሪ ሐስክል በካህሊል ዙሪያ ያደሩት የነበረውን የሕይወት ድር በተመለከተ ስትጽፍ፡- ‹‹both women had simple tastes, a purity of heart, and a common Goal: to help Gibran, to enable him to develop his fullest in whatever area he choose. They were united in their belief in his greatness.›› ብላለች፡፡
 ራሱ ካህሊል ጅብራን በየካቲት 12 1908 እ.ኤ.አ ለጓደኛው አሜን ጉሬብ ቦስተን ስለመገኘቱ ምክንያት ሲጽፍ፡- ‹‹and now since you have heared my story you will know that my stay in Boston is neither due to my love for this city, nor to my dislike for new York. My being here is due to the presence of a she-angle who is ushering me towards a splendid future and paving for me the path to intellectual and financial success.››
ሜሪ ሐስከል ትቀጥላለች፡፡ እ.ኤ.አ የካቲት 6 1912 ከቦስተን በጻፈችለት ደብዳቤዋ ላይ እንዲህ ትላለች፡- ‹‹ God lends me his heart to love you with. I asked for it when I found my own was too small, and it really holds you, and leaves you room to grow. I do long to see your beautiful new picture.››
እውነትም የካህሊል አማልክት ሴቶች ነበሩ፡፡ ያ አስደናቂው የስነ ተረት ሊቅ ጆሴፍ ካምቤል ‹‹ሴቷ ሕይወት ራሷ ነች፡፡ ወንዱ ደግሞ አገልጋዩዋ…›› ይላል፡፡ በካህሊል በኩል የሆነው ግን ግርምቢጥ ሆነ… የመላው ስነ ተፈጥሮን ውል የነጥብ ያህል አሳንሶ የተሸከመ አንስታይ መዳዳት፣ በካህሊል በኩል ዓለምን በሙሉ ለማዳረስ ለሚተናነቅ ተባዕታይ ምኞት፣ ጉምዠት፣ የኑባሬ ሀቲት ፍለጋ መቃተት የምልዓት ክንውን ማሸርገድን፣ ማበርን መረጠ፡፡ (ግድየላችሁም ይህችን ሀቲት ቢያንስ አንድ ሣምንት ብናሳድራት አጎምርተን ልንመለስባት እንችላለን፡፡ ይሄው የማይታጠፍ ቃሌን ሰጠሁ፡፡)       
ካህሊል ግን  አሁንም ከፍታው ቀጥሏል። ሜሪም አስከ ዘለዓለም አብራው ከፍ የምትል ይመስላል፡፡ መጻሕፍቱ በሁሉም የዓለም ማዕዘናት በስፋት ይነበባሉ፤ ይተረጎማሉ፡፡ እንደ ጥናቶች ጥቁምታ ከሆነ፤ አሁን በሚነበብበት ፍጥነት ከቀጠለ ካህሊል ከሃያ ወይም ሠላሳ ዓመታት በኋላ በሰፊው በመነበብ ሼክስፒርንም ሆነ ላኦትዙን የሚያስከነዳበት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡
ካህሊል ስለ ሜሪና ልጅነቱን ስላደመቀችልት ሀገሩ ሊባኖስ ዘምሮ አይጠግብም፡፡ በስደት በኖረባት አሜሪካ ያፈራውን አብዛኛውን ነገር ለሀገሩ ተናዞላታል፡፡ እንዲህ ይላል፡- ‹‹የእኔዋ ሊባኖስ በማለዳ ክንፎቻቸውን የሚያማቱ የእርግብ መንጋዎችን ትመስላለች፡፡››
ለእኔም ሀገሬ ኢትዮጵያ ሊባኖስ ትመስለኛለች፡፡ ራቅ ራቅ ብለው የበቀሉ ዋርካና ዝግባዎች ባይኖሯትም፣ እንደ ሊባኖስ መሰሎቻቸው ሁሉ ‹ለሕይወት› ዝግ በሆኑ ሴቶቿ ሀገሬ ሊባኖስን ትመስላለች። ውድቅት ላይ በሹክሹክታ ብቻ በሚሰማ የምስጋና ዜማ አንቀላፍታ፣ ንጋት በምህላ ድምጾች የምትነቃ… ሀገሬ
ካህሊል ግን እንደ ፈጠረው ገጸባህሪ አልሙስጠፋ ጻድቅ ብቻ አልነበረም፡፡ ግለ ታሪኩን ያጠኑ ሰዎች ግብዝ (hypocrite)፣ የለየለት ቀጣፊ እንደነበርም መስክረዋል። ለሜሪ ሐስክል በተደጋጋሚ ከኢየሱስ ጋር እንደሚገናኝ፣ ራሱንም እኔ ኢየሱስ ነኝ ብሏታል ይባላል፡፡ አንድ ሁለት ደብዳቤዎቹም ላይ ይህን መሰል ነገር አንብቤያለሁ፡፡ ግን ቢያንስ ለዛሬ ይህን ስለመሳሰሉ ነገሮች ባናወራስ?
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ፍራንክሊን ሩዝቤልት ባለቤት Eleanor Roosevelt አንድ የሚገርም አባባል አላት። ‹‹ውብ ፊቶች የተፈጥሮ ድንገቴ ክስተቶች ሲሆኑ፤ ውብ ነፍስ ግን የሕይወት ዘመን የጥበብ ስራ ነች!›› የምትል፡፡ በዚህ ላይ እውነተኛ ጓደኝነት ሲታከልበትማ አስቡት… ካህሊል አዕላፋት የሚረዳቸው አጥተው ወደ ውስጥ እያነፈረቁ በተሸኙበት ዓለም ለነፍሱ የቀረበች ሜሪ ሐስከልን በማግኘቱ ለዕድለኝነቱ መግለጫ ቃላት አይገኝለትም፡፡
ግን ግን ስንቶቻችን ነን ውብ ጓደኝነታችንን በምስር የለወጥን?
ታላቅ ሰው የመፍጠር ዕድላችንን እንደ አንዳች ንቀን መወነጃጀልን የመረጥን?
ምናልባት ሁላችንም!  


Read 1653 times