Saturday, 29 May 2021 14:32

ከሞት ጋር ጨዋታ!

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(2 votes)

   ከስራ መመለሴ ነው፡፡ ሰውነቴ ዝሏል። የምግብ ፍላጎት ቢኖረኝም፤ ፍሪጅ ከፍቶ መመገብ ጣዕረ-ሞት መስሎ ታየኝ፡፡ እናም ተውኩት፡፡
አይኔን ጨፈንኩ፡፡ ወደ ኋላዬ የበለጠ ... ለጠጥ በማለት የመዝናናት ስሜት ለመፍጠር ሞከርኩ፡፡ በእርግጥም የቤቴ ድባብ በፀጥታ የተሞላ በመሆኑ ነፃነት ተሰምቶኛል፡፡ የወንበሩ መርገብ ጀርባ ቢያጥፍም፤ የአየሩ መቀዝቀዝና ነፋሻማ መሆን መንፈስ ያድሳል፡፡
አዎ...ደስታን፣ ነፃነትን ፈለግኋት፡፡
ዕራቴን ማዘጋጀት ቢኖርብኝም፤ ለዛሬ ... ውስጤን ማዳመጥ ቀጠልኩ። በትዝታና በቁጭት መርከብ ላይ መሳፈሬ የገባኝ ዘግይቶ ነው፡፡ ማሰብ...ማሰብ... አሁንም ... አሁንም... ወደ ውስጥ ...ድግግሞሹ ሰመመን ፈጠረብኝ፡፡
ዘላለም ከሚመስል የፀጥታ ማዕበል በኋላ፤
“ሠለሞን... ሠለሞን...!” እያለ  የሚጠራኝን ድምፅ ፍለጋ ተሽከረከርኩ፡፡
ያየሁትን ማመን ከበደኝ። መንጋ ነው፤ የሙት መንፈስ፡፡
የለበሱት ማቅ ነው፡፡ ሰውነታቸው ከስጋ አልተገነባም፡፡ አጥንትም የለውም። ጨርቅ ብቻ፡፡ የሚውረገረግ ጨርቅ  ብቻ ...ጨርቅ፤ ጨርቅ ብቻ ...እኩል የሚራመዱ፣ በህብር የሚውረገረጉ፡፡
“አሁን ከአሁን ተሰበሩ” እያልኩ አቅሜ ያልቅ፣ ትኩረቴ ይሰረቅ ነበር። ማንን ተከትለው እንደሚነጉዱ ፣ ወደዬት እንደሚሄዱ ለመረዳት ጣርኩ፡፡ ለጊዜው የሚታየኝ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን የመንጋውን መጨረሻ (ብዛት) ለማወቅ ያደረኩት ጥረት አልተሳካም፤ ምድር ሙሉ ተወራለች፡፡ ጠጠር መጣያ የለም፡፡
መገረሜ  «እግዚኦ!” በሚል ቃል ተተካ፤ አፌን በመዳፌ አፍኜ፡፡
ሰገዱልኝ፡፡ ድርጊታቸው አስደነቀኝ፡፡ የሰሙኝ መሰለኝ፡፡
“ለምን እኔ ላይ ታፈጣላችሁ?” ድንገት አመለጠኝ፡፡
“ጊዜህ ደርሷል፤ ተዘጋጅ” አለ፤ ከመካከላቸው ጥቁር በጥቁር የለበሰ መልከ መልካም፡፡
“አንተ ማነህ? “አልኩት፤ ጣቶቼን ቀስሬ፡፡
በቅፅበት ጣቶቼ ሲሟሽሹ፤ ሲፈራርሱና ወደ አመድነት ሲቀየሩ ታየኝ፡፡ የህመም ስሜት ፈለኩ፤ የለም፡፡ የራሴ ሰውነት ስለመሆኑ ተጠራጠርኩ፡፡
ወደ ብናኝነት የተቀየረውን ጣቴን ስመለከተው የተወሰኑ የሙት መንፈሶች አየር ላይ ሲቃሙ፤ ሲንሳፈፉ በንቀት ገረመምኳቸው፡፡ በድጋሚ የተወሰነው የመዳፌ ክፍል ተቆርሶ ሲወድቅ እንደ መብረቅ መሬት  ሰንጥቆ ገባ፡፡ መንፈሶቹ በቅፅበት ከቆሙበት ቦታ ወደ መሬት ሠርገው ሲገቡ ተመለከትኩ፡፡
እኔም እርምጃዬን ቀጠልኩ፡፡
“ወዴ’ት ትሔዳለህ?”  አለ፤  ተመልሶ መምጣቱን ተረዳሁ፡፡
አፈጠጥኩበት፡፡
“ልሸኝህ?” አለኝ፤ ዝም አልኩት፡፡
ጀርባው ላይ እንድፈናጠጥ ጋበዘኝ። አደረግሁት፡፡ ይለሰልሳል፡፡ ወደ መሬት ማህፀን ሰረግን፤ ከበውት የነበሩት የሙት መንፈሶች ወደ ብናኝነት ተቀየሩ፡፡
በቅፅበት የእኔን ተክለ ሠውነት ተባዝቶ ተመለከትኩት፡፡ የመሬት ማህፀን ጥልቀትና ስፋት አማለለኝ፡፡
“የበሉኝ ፣የተዋደቁት ለዚህ ነው...” አልኩኝ። ናቅኋቸው፡፡ በድርጊታቸው ተዝናናሁ፡፡
“ከዚህ ጥፉ! “ጮህኩኝ!...ጮህኩኝ! የራሴን ምስል አባረርኩት፡፡
ሁሉም ቀስ በቀስ ወደ ምድር ማህፀን ሠረጉ፡፡ ግን ይህ ሁሉ ምስል ለሞት ምኑ ነው?
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1539 times