Saturday, 29 May 2021 14:34

ሀገሬ ዋርካ ናት!!!

Written by 
Rate this item
(16 votes)

ገና በጥዋቱ ~ ለስሟ መጠሪያ
አቢሲንያ ብሎ ~ ሲሰጣት መለያ
አንዳች ዕምቅ ሚስጥር ~ ለኛ ያልተገለጠ
ፈጣሪም አድልቶ ~ ከአርያም ሰጠ
ከግዮን ከወንዙ ~ ከዳሎል ዝቅታ
ከኤርታሌ ረመጥ ~ከዳሽን ከፍታ
አክሱም አናቱ ላይ~ ከላሊበላ ስር
ሀገሬ ተገምዷል ~ በወፍራም የደም ክር
በዚህ የጭንቅ ወቅት~ ምጧ እንዲህ ሲጠና
አዋላጅ ፈልጉ ~ ሳይጠናባት ገና
ለምን ካላችሁኝ
ከራስጌም ከግርጌም ~ ቢታጣ እንኳ ትራስ
ይጋረዳል እንጂ ~ ይፈናቀላል ወይ~ ያልጠነከረ አራስ
አደራ!
አደራ!
አንቺ ብቻ ታገሽ
አንገት እንዳትደፊ ~ ከቶ እንዳትይ ዘንበል~ መጠንከር ነው ደጉ
በጨርቅ ተከልለሽ~ እስኪሰዋ ድረስ ~ የመስዋት በጉ
ቢያድለን ኑሮማ ~ ሀገር ጨርቃችን ናት~ ሁሉን ተሸካሚ
የውስጣችን ጉድፍ~ ሸፍና ያስቀረች ~ ዛሬም አስታማሚ
አዎ ሀገር ጨርቃችን ናት
እንደ እፉኝት ልጆች~ ገመናዋን ሸፋኝ ~ማብቀል የተሳናት
የመጣው የሄደው ~ ቆርጦ ዕጣ ሊጣጣል ~ ሰርክ የሚመኝላት
ሀገር ጨርቃችን ናት
ግና!
ሰንደቋን ጨርቅ ነው ~ ብለው ሲያሟርቱ ~ እነ ግፍ አይፈሩ
አክሱም ለወላይታው ~ምን ያደርግለታል ~ ብለው ሲፎክሩ
ጉደኛ ናትና
ቀብረናታል ሲሉ ~ ቀብራቸው አረፈች~ ይቅለለው አፈሩ
እስኪ ይጠየቅ ጴጥሮስ ~ ያነ ሀዋርያ
የሀምሌ አቦ ስብሃት ~ የክርስቶስ ባሪያ
ያነ ቅዱሱ ጳውሎስ~ በሚያልፍበት መንገድ~ እግሩ በረገጠው
በጨርቅ ጥላ አልነበር~ ድዊ ሚፈወሰው
ይሄው ዛሬ ደግሞ
ከደመቀው በላይ ~ እጅጉን ደምቆልን ~ ተነቅሎልን ሳንካ
ዕድል በለስ ቀንቶን ~ ገዱ ለኛ ሆነ ~ ብርሃኑም ፈካ
ዳሩ ምን ያደርጋል
ሁሉም ደርሶ ተንታኝ ~ ሁሉም ተናጋሪ ~ በሆነበት ዓለም
በሩ ገርበብ ሲል ~ ያለፈውን አዋጅ ~ ማያካክስ የለም
ተንፍሱም እያሉ ~ ብዕር ቢሰጧቸው
እንደምን ይፃፉ ~ ቃታ እየታያቸው
ይልቅ
አለም አድናቆቱን ~ ይቸርሀል ነገ
በመደመር ስሌት ~ መቀነሱም አብሮ~ እኩል ስላደገ
ግና እንደዛሬው~ እንዲህ ሀገር ሲታወክ
የሰራዊት ብዛት ~ ሀገር አያፀናም ~ ቢልም ቅዱስ ቃሉ
ዘመን ተገልብጦ ~አመሉ የበዛውን~ ሰራዊት ይላሉ
ምንም እንኳን
ቅርንጫፏ ወድቆ
ቅጠሏም ረግፎ~ስሯ እንዲህ ቢደርቅም
ሀገሬ ዋርካ ናት
መቸም መቸም ቢሆን
በግፈኞች መጋዝ አትገነደስም፡፡

Read 3021 times