Print this page
Saturday, 05 June 2021 12:32

በትግራይ ክልል ተፈፀመ ከተባለ ወንጀል ጋር በተያያዘ በ53 የሰራዊቱ አባላት ላይ ክስ ተመሰረተ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

 “የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ መውጣት ጀምረዋል

             በትግራይ ክልል ባለፉት ሰባት ወራት ተፈፀመ ከተባለ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያልተመጣጠነ ሃይል በመጠቀምና በፆታዊ ጥቃት በተጠረጠሩበት 53 የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊ አባላት ላይ ክስ መመስረቱን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ አስታወቀ፡፡ ከእነዚህ ክስ የሰራዊቱ አባላት ውስጥ 25ቱ የተከሰሱት በወሲባዊ ጥቃት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬተሪያት ቢለኔ ስዩምና የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ከትናንት በስቲያ በትግራይ ክልል ውስጥ ስለተከሰተውና አሁን ላለው ሁኔታ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በዚሁ መግለጫቸው፤ በትግራይ ክልል ለሚገኙ የሰብአዊ እርዳታ የሚሹ ዜጎች እርዳታውን የማቅረቡ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው፤ መንግስት ከእርዳታ ሰጪ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በ93 ወረዳዎች እርዳታ እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል 14ቱ ወረዳዎች በመንግስት የተሸፈኑ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡ በክልሉ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ያሳዩት አቋም፣ “የኢትዮጵያን ክብር” ያልጠበቀና በአንዲት ሉአላዊት አገር ላይ የማይደረግ ጣልቃ ገብነት ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ ተፈፀሙ ስተባለው የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ዐቃቤ ህግ ምርመራ መጀመሩን የገለፁት የፌደራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፤ በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር  ዘመቻው ተግባራዊ በሚደረግበት ወቅት በዜጎች ላይ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎች መፈፀማቸውንና ከዚሁ ወንጀል ጋር በተያያዘም 53 የሠራዊቱ አባላት በህግ ቁጥጥር ስር ወስደው ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ የሚወጡበትን ጊዜና ሁኔታ አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ  የጠ/ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬተሪያት ቢልነኔ ስዩም፣ ሂደቱ ተጀምሯል፡፡ “የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ መውጣቱን ጉዳይ አስመልክቶ የመከላከያ ሚኒስቴር ሪፖርት አቅርቧል” ብለዋል፡፡


Read 13713 times