Saturday, 05 June 2021 14:05

"ህልምህን ካላከበርከው፤ ትገፈተራለህ!!"

Written by  ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(6 votes)

    "-ሰው በክህሎት እየዳበረ ፣ በዕውቀት እየጎለመሰ የሚሄድ ፍጡር ነው፡፡ ማህበራዊ ሰንሰለቶች ለተለያዩ ስርዓቶች መፈጠር ምክንያት ናቸው፡፡ ፈትሻቸው፡፡ እርምጃህ ወቅቱን የዋጀ ይሁን፡፡ ስኬት ከወቅት ጋር የተሳለጠ መስተጋብር ውጤት ነው፡፡ ጊዜው የፈጠራቸውን ዓውዶች ተረድቶ ተመጣጣኝ ምላሽ መስጠት ያሸልማል፡፡--"
                          
               ለውጥን ገና ማህፀን ውስጥ ሆነን ተለማምደነዋል፤ ተለውጠናልም፡፡ እድገት ሁሉ ለውጥ ሲሆን ለውጥ ሁሉ ግን እድገት አይደለም፡፡ ብርቱ ህይወት የመስዋዕትነት ተምሳሌት ልትሆን የምትችልበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡
አጥብቀን የምንሻው የትኛውም አይነት ውጤት ሂደት ነው፡፡ ሂደት ደግሞ መንገዱ ነው፡፡ የመንገዱ፤ መዳረሻ “ስኬት” የሚመስለው የትየለሌ ነው፡፡ ግን እኮ ስኬት ሁሌም የምንኖረው እንጂ ነገ የምደርስበት ወይም ያጣነው ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ስኬት ሁሌም ከውስጣችን ያለ እንጂ ከውጭ የምንፈልገው ወይም የሚሰጠን አይደለምና፡፡ ጉዞህን ከለየህበት ቅፅበት ጀምሮ የምትኖረው ነው፤ ስኬት። የማያቋርጥ ውጤታማነትና የገደብ የለሽ ደስታ ምንጩም ይህ ይመስለኛል፡፡
ከውጭ የሚሰጠን ነገር በረከት ወይም ስጦታ እንጂ ስኬት አይደለም፡፡ ስጦታ፤ እያደረግነው ላለው ስራ ከሆነ፣ ምክንያቱ የውስጣችን ማንነት ሽልማት ሆኖ በጉዟችን ውስጥ እንደ አንድ ፌርማታ ልናየው እንችላለን፡፡
ስኬት  የማይረግብ እሾት (መሻት) ዘላቂ ሽልማት ነው፡፡ ውስጥን ፈንቅሎ የሚወጣ የሚንቀለቀል ጥሬ ጉልበት ነው፡፡ እመነኝ፣ እሾትህ ከችሎታህ በላይ ከሆነ ተዓምር ትሰራለህ፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ሰዋዊ ችሎታዎች በትምህርት ወይም በልምምድ የሚገኙ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው፤ “እሹ ታገኙማላችሁ፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል” የሚባለው፡፡ ስለዚህም መሻትህን ጠብቀው። ጉጉትህን አክመው፡፡ በምናብህ የጠራ ምስል ተመልከት፡፡ መንገድህን ተረዳው፡፡ የተገደቡና ያልተገደቡ ተፈጥሯዊ ማንነቶችህን አጥናቸው፡፡ የሀይልህ ብርታት የሚወሰነው በነኚህ ማንነቶችህ ላይ ነው። ማስተዋልና ትግስት ተላብሰህ ከፀናህ ህልምህ ሁሉ እውን ይሆናል፡፡ ብቻ መንገድህን በአእምሮህ ተመልከተው። የአእምሮህን ጓዳ ጎድጓዳ ፈትሸው፤ መርምረው፤ የነፃነትህም ሆነ የህይወት ግብህ ሚዛን መፍለቂያ፤ የደህንነትህ ምሰሶ፤ አንድም ሁለትም ነውና፡፡
የጠራ ህልም፤ በግልፅ ቋንቋ ሚዛን ጠብቆ ወረቀት ላይ ይሰፍራል፡፡ የህይወት ፍሬም ልንለው እንችላለን፡፡ ስታስበው የምትሔድበትን ሳትገነዘብ ስኬት መናፈቅ ሰማይን በጣቶችህ ለመዳሰስ እንደመሞከር አይሆንብህም?...
ሰው በክህሎት እየዳበረ፣ በዕውቀት እየጎለመሰ የሚሄድ ፍጡር ነው፡፡ ማህበራዊ ሰንሰለቶች ለተለያዩ ስርዓቶች መፈጠር ምክንያት ናቸው፡፡ ፈትሻቸው፡፡ እርምጃህ ወቅቱን የዋጀ ይሁን፡፡ ስኬት ከወቅት ጋር የተሳለጠ መስተጋብር ውጤት ነው። ጊዜው የፈጠራቸውን ዓውዶች ተረድቶ ተመጣጣኝ ምላሽ መስጠት ያሸልማል፡፡ የራስን አቅም መመዘኛም ይሆናል፡፡ ለዚህም መሰለኝ ኤርሚያስ አመልጋ፤ “ ካላታገለኝና ካልፈተነኝ፣ልኬ አይደለም!...” የሚለው (የማይሰበረው ኤርሚያስ አመልጋ፣ 178፣ አንተነህ ይግዛው እንደፃፈው)፡፡
ስለሆነም ስኬት ማለት ምኞት ብቻ አይደለም፤ ለሚሻውና ልቦናውን በጌትነት ላጠመቀው፣ ዓውዱን ላወደው ፣የማግኛውን ዘዴ ለቀየሰውና በመጨረሻም ያቀደውን ለተከታተለውና ላስፈፀመው ነው “እምነት ክብረት ዓለም” ሚሊዮኑን የምታስታቅፈው። ይህም የምትሰራውን ለይተህ ከማወቅ ይጀምራል፡፡ “ያለ ስራ የለም እንጀራ “ እንዲሉ አበው፤ አንድ ሰው ሊያሳካ የሚፈልገውን ጉዳይ ሲከውን ስኬት እንለዋለን፡፡ ስለሆነም ህይወት እንደ ምግብ ቤት ነው፡፡ መክፈል እስከቻልን ድረስ የፈለግነውን እናገኛለን፡፡ ዋናው ጉዳይ “ግባችንን ከተረዳን በኋላ የምከፍለው ዋጋ ምን ድረስ መሆን አለበት” የሚለው ላይ የሚኖረን አቋም ነው፡፡
ስኬት ውስጣዊ ነው፤ በውስጣችን አድጎ ህይወታችንን ወደ ምንፈልገው አቅጣጫ የሚመራ ሂደት፡፡ መለወጥ እችላለሁ፤ ማድረግ እችላለሁ የሚል እልህ የተላበሰ ከራስ ጋር የሚደረግ ትንቅንቅ ነው፡፡ ወደ ምድር ስንመጣ (ከእናታችን ማህፀን ስንወጣ) አልቅሰን፤ ከምድር ስንሄድ ደግሞ በፀፀትና በቁጭት መሆን የለበትም፡፡ ይህ ሁኔታ የሚስተካከለው በስኬት ነው፡፡ ስለሆነም በምድር ስንኖር የሚገባንን ወስደን፣ በሚገባን ልክ መጥነን ኖረን፣ የተገለገልናትን ምድርና ዓለም በስፋት አገልግለን፤ ከተጠቀምነው በላይ አትርፈን ትውልድን አገልግለን... ፀፀትን አስወግደን በሰላም ማለፍ (መሰናበት) ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል ገጣሚው ከበደ ሚካኤል ፤
“ፅድቅና ኩነኔ ቢኖሩም ባይኖሩም፤
ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም፡፡”
በማለት የተቀኙት፡፡ (The major key to your better future is you!.)
ስኬት ማለት ህይወትን በቁምነገር መቀበል ነው፡፡ የራስን እድል በራስ መወሠንም ጭምር ነው፡፡ ስኬታማነታችንን በራሳችን መወሰን እንችላለን ስንል  ሰዋዊ ፀጋዎችን ተጠቅመን ነው፡፡ ከነዚህ ፀጋዎች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚጫወቱት ምናብ (imagination) እና አመክኒዮ (Reason) ናቸው፡፡ እንግዲህ የነፃነት ምንጩ እነዚህ ፀጋዎች ይመስሉኛል፡፡ ነፃነት ምንድን ነው? ከተባለ ደግሞ “የበለጠ ተወዳዳሪ መሆን” ማለት ነው ፤እያንዳንዱ ሰው ውስጡ ያለውን ጥበብ ለራሱና ለሌሎች ሊተርፍ በሚችል መልኩ ለማድረስ መጣር ማለት ነው፡፡”ታላላቅ ሰዎች እራሳቸውን ይፈጥራሉ” የሚለው ብሂል የበለጠ ገላጭ  ይመስለኛል፡፡
መሻትህ ለውስጥህ እውነት ነፀብራቅ ነው፡፡ የጌትነትህ ምንጩ ማንነትህን በተገቢው ዓውድ መሾምህ ላይ ነው፡፡ ይህ ጌትነትህ ደግሞ የማይታየው ረዳትህ ነው፡፡ ብልጫ የምናሳይባቸው ነገሮች ምንጭ ይህ ስውሩ ሀይላችን ነው፡፡ ስለሆነም ለአንተ ብቻ የሚታይህ የጠራ መንገድ፤ ለኑሮህ መቃናት ቁልፍ ነው፡፡ ጨብጠው፡፡ “ሰው ማለት ለማይታየው ህልሙ አሽከር ነው” የሚባለው፤ ለዚህ ነው፡፡ ስለሆነም ስውር ረዳት ይኑርህ፡፡ የስኬት የመጀመሪያው ነገር የማይታይ ረዳት ማግኘት ነው፤ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የሚታየው ነገር ሁሉ የመጣው ከማይታየው ነገር ነው፡፡ ስለሆነም ህልምህን ቅረፅ፡፡ እመነው፡፡ ተግብረው። ለመሰናክሎች እጅ አትስጥ፤ “እምነት የለሽ ነው፣ መንገዱ ሲጨግግ፣ ጉዞውን የሚያቋርጠው” ፡፡ የህልምህ ሾፌር አንተው ነህ፡፡ ፌርማታዎችህ ፤ ምርጫዎችህ ናቸው። መዳረሻህ የፃፍከው አንተነትህ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 668 times Last modified on Tuesday, 15 June 2021 19:57